Saturday 22 August 2020

በድጋሚ ፖስት የተደረገ

እርሱ ኪዳነ ምሕረታችን ነው

በ2000 ዓመተ ምሕረት ኪዳነ ምሕረት የተሰኘና ይህ ስም የተሰጠው ለማይገባው አካል ነው የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ቡክሊት ማሳተም ጀመረን፡፡ በዚህ ቡክሊት በእግዚአብሔር ፈቃድ እስከ አሁን ድረስ የቀጠለና የተለያዩ መልእክቶችን በ25 እትሞች በማዘጋጀት በነጻ ለማዳረስ ተችሏል፡፡ ባለ ሃያ ገጽ ሆኖ የሚወጣው ኪዳነ ምሕረት (ቊጥር 21 ብቻ 32 ገጽ ይዞ ታትሟል) በአንዳንድ አገልጋይ ነን ባዮች ለሚሰራጩት የስሕተት ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽ በመስጠት ብዙ ሰዎችን የማንቃት ሥራ ሠርቷል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ግን ይህ ስም ለፍጡር እንጂ ለጌታችን አይገባም የሚሉት ሰዎች ተቃውሟቸውንና ጥያቄዎቻቸውን በተደጋጋሚ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ጥያቄዎቻቸውንና ተቃውሟቸውን ሲያቀርቡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ፍለጋ ብዙ ደክመዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ለተቃውሞ እንዲረዷቸው የተማጸኗቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባትና የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመልከት ጥረት ተደርጓል፡፡
በቅድሚያ የተነሣው ጥያቄ መዝሙረ ዳዊት 88÷3 ላይ ‹‹ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ›› በሚል የተቀመጠውን ምንባብ መሠረት በማድረግ ነው (ይህን ጥቅስ መነሻ በማድረግ ኢየሱስ ኪዳነ ምሕረት ሊባል አይገባውም ለማለት ተዘጋጅቶ ለነበረው የስሕተት መልእክት መልስ የተሰጠበትና ‹‹ስሙን ለማን ሰጡት?›› የሚለውን ጽሑፍ በኪዳነ ምሕረት ቊጥር 8 ላይ ይመልከቱ)፡፡
ሰዎቹ ይህን ጥቅስ ለማይገባው አካል የሚሰጡት ጥቅሱን ከሙሉ ምዕራፉ ፈልቅቀውና ለብቻው ቆርጠው በመውሰድ ነው (ለኑፋቄ ትምህርታቸው እንዲረዳቸው በተዘጋጀውና በ2000 በታተመው ሰማንያ አሐዱ ውስጥ ‹‹ከመረጥሁት›› የሚለውን ‹‹ከመረጥኋቸው›› በሚል ያሰፈሩት ቢሆንም በግርጌ ማስታወሻ ላይ ግን በዕብራይስጥ ወይም በበኩረ ጽሑፉ ላይ ‹‹ከመረጥሁት›› እንደሚል አስቀምጠውታል፡፡ ይህ ደግሞ አውቆ አጥፊነታቸውን ግልጽ ያደርጋል)፡፡ ሰዎቹ ‹‹ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ›› በሚል ክፍሉን ቆንጽለው እንደ ወሰዱ ማሳያ የሚሆነው ‹‹ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ›› ከሚለው ጋር አብሮ ያለውንና ‹‹ለባርያዬም ለዳዊት ማልሁ›› በሚል የሰፈረውን ክፍል ቆርጠው መጣላቸውን ስንመለከት ነው፡፡
ምዕራፉ እግዚአብሔር ለዳዊት የገባውን ኪዳን መሠረት በማድረግ የቀረበ ትምህርት ነው፡፡ ይህንንም ለመረዳት መናፍቃኑ ቆርጠው ሊጠቀሙበት ከሚወድዱት በተጨማሪ፥ ጎላ ጎላ ያሉትንና ቀጣዮቹን ‹‹ዘርህን ለዘላለም አዘጋጃለሁ፥ ዙፋንህንም ለልጅ ልጅ እመሠርታለሁ›› በሚል በቊጥር 4 ላይ የሰፈረውን፣ ‹‹ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት›› በሚል ቊጥር 20 ላይ የሰፈረውን፣ ‹‹ዘሩንም ለዓለምና ለዘላለም፥ ዙፋኑንም እንደ ሰማይ ዘመን አደርጋለሁ›› ተብሎ ቊጥር 29 ላይ የተጻፈውን፣ ‹‹ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ›› የሚለውን ቊጥር 35 ላይ የተጻፈውን መመልከት ሲቻል ነው፡፡ ሰዎቹ እነዚህን ሁሉ ወደ ጎን በማለት አንድን ቊጥር ብቻ ለይተው በማውጣት ለዛውም የቊጥሩን ሙሉ ክፍል ሳይወስዱ ለተሳሳተ መልእክታቸው የሙጭኝ ማለታቸው መጽሐፍ ቅዱሱን የሚፈልጉት ለትምህርታቸው ድጋፍ እንዲሆናቸው እንጂ ሊታዘዙት አለመሆኑን ያሳያል፡፡
ይህ እግዚአብሔር ለዳዊት የገባው ኪዳን በ2ኛ ነገሥት 7÷8-16 ባለው ክፍል ላይ ‹‹አሁንም ዳዊትን ባሪያዬን እንዲህ በለው፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ መንጋውን ስትከተል በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ፤ በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆቹ ስም ታላቅ ስም አደርግልሃለሁ። ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፥ እተክለውማለሁ፤ በስፍራውም ይቀመጣል፥ ከዚያም በኋላ አይናወጥም፤ እንደ ቀድሞው ዘመንና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፈራጆች እንዳስነሣሁበት ጊዜ ግፈኞች ተመልሰው አያስጨንቁትም፤ ከጠላቶችህም አሳርፍሃለሁ። እግዚአብሔርም ደግሞ፦ ቤት እሠራልሃለሁ ብሎ ይነግርሃል። ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ ከአባቶችህም ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ፥ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፥ መንግሥቱንም አጸናለሁ። እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፤ የመንግሥቱንም ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ። እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ክፉ ነገርም ቢያደርግ፥ ሰው በሚቀጣበት በትርና በሰው ልጆች መቀጫ እገሥጸዋለሁ፤ ከፊቴም ከጣልሁት ከሳኦል እንዳራቅሁ ምሕረቴን ከእርሱ አላርቅም። ቤትህና መንግሥትህም በፊቴ ለዘላለም ይጠነክራል፥ ዙፋንህም ለዘላለም ይጸናል›› በሚለው ተገልጦ ይገኛል፡፡
ቀደም ሲል እንደተባለው በመዝሙረ ዳዊት ላይ የሰፈረው የይዝራኤላዊው የኤታን ትምህርት እግዚአብሔር ለዳዊት የገባውን ኪዳን ማድነቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለዳዊት የገባው ኪዳን ዙፋንህን ለዘላለም አጸናሉ የሚለው ነበር፡፡ ይህ እንዲሆን ግን ዳዊትም ሆነ ከዳዊት በኋላ የሚነግሡት የዳዊት ልጆች ከዚህ ኪዳን ውጪ በሆነ መንገድ መሄድ አይኖርባቸውም፡፡ የዳዊት ልጅ የሆነው ሰሎሞን እግዚአብሔርን በመበደሉ ምክንያት ምንም እንኳ መንግሥቱ ለሁለት የተከፈለ ቢሆንም እግዚአብሔር የገባው ኪዳን (‹‹ዙፋንህ ለዘላለም ይጸናል›› የሚለው) በክርስቶስ የጸና መሆኑን የሚከተሉትን ጥቅሶች በመመልከት መረዳት ይቻላል ‹‹እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል›› ‹‹ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው›› (ሉቃስ 1÷32፤ ዕብራውያን 1÷8)
ምንም እንኳን መናፍቃኑ ጥቅሱን ለሌሎች ለመስጠት ቢቋምጡም የጥቅሱ መልእክት ከፍጡር ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከጌታችን ጋር የተያያዘ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ኪዳነ ምሕረታችን ክርስቶስ ነው የምንለው፡፡
‹‹ለድኅነታችን በተሰቀለው በአንድያ ልጅህ በኢየሱስ በባሕርይህ ምክር ደስ ተሰኝተህበት ቃል ኪዳንህን ሁሉ በእርሱ አድርገሃል›› (መጽሐፈ ቅዳሴ (1984) ገጽ 65)፡፡

@gedlatnadersanat
@gedlatnadersanat

No comments:

Post a Comment