Monday 10 August 2020

ያዳነን እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ነው እንጂ አማላጅ ወይም መልአክ አይደለም
(ክፍል ፪)
ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ የነቢዩን ኢሳይያስን ቃል ሲተረጉም [ምዕራፍ ፷፫]“ወኢሳይያስኒ ነቢይ ይቤ አኮ ውእቱ መተንብል ወኢመልአክ አላ ለሊሁ እግዚእ ዘመጽአ ወአድኀነነ ወኢያድኅነነ በደመ ነኪር ወኢበሞተ ብእሲ አላ በደሙ ባሕቲቱ ወአኮ ውእቱ ዘካልእ ወበእንተዝ ነገረ ጠቢብ ጳውሎስ ህልወ ዘከመ ይደሉ - ነቢይ ኢሳይያስ ሰው ኾኖ ያዳነን እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ነው እንጂ አማላጅ ወይም መልአክ አይደለም፤ በባዕድ ደም በዕሩቅ ብእሲ ሞት አላዳነንም፤ ራሱ በደሙ አዳነን እንጂ የሌላ ደም አይደለም፤ ስለዚህም ጠቢብ ጳውሎስ [ዕብ ፪፥፱-፲።] እውነቱን በሚገባ ተናገረ” ሃይ አበ ዘቄርሎስ ፸፯ ክፍል ፵፮፥፲፫።
በክፍል ፩ ጦማር ለጌታችን ሊነገሩ የማይገቡ ጥዩፍ ቃላትን ከእነ አመክንዮአቸው ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በጦማሩ መርዘም ምክንያት የተማረራችሁ አንዳንዶች ወዳጆች ምናለ ለሦስት ጊዜ የሚኾነውን አንድ ላይ አደረግህብን የሚል አቤቱታ በውስጥ የመልእክት ሳጥን አሰምታችሁኛል፡፡ መርዘሙ ጠፍቶኝ አልነበረም፤ ሀሳቡ እየተቆራረጠ አዲስ ገብ የሚኾኑ ሰዎች ግራ እየተጋቡ እንደኾነ ስለተረዳሁ እንጂ፡፡ በተለይም በእጅ ስልኮቻችሁ ለምታነብቡ ሰዎች ረጃጅም ጽሑፍ እንዴት እንደሚያደክማችሁ ይሰማኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ያሉት በአጭር በአጭር ለማቅረብ ሳይመቹ አይቀሩም፡፡ አስኪ የተቻለኝን አደርጋለሁ፡፡ ደግሞም አትርሱ እንደምታውቁት በእኛ ቤት ስስት የለም፡፡ ባይኾንልኝ ደግሞ እናንተው ቻል አድርጉት፡፡ ቁም ነገር ነውና በቀላሉም አትመልከቱት፡፡ በተለይም የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፡፡ ጉዳዩን እየተመላለስሁ የምቃኘው የሃይማኖት ጉዳይ ቢኾንብኝ እና ከጥቂቶች በስተቀር ሌሎች ብቅ ባይሉ እንጂ መነዛነዝ ፈልጌም አይደለም፡፡
አሁን ወደ ቀጣዩ ክፍል እናመራለን . . . በቅድሚያ መላኩ ባወቀ የተባለው ሰው ያበላሸውን ብልሽት ከማየታችን በፊት በዕብ ፭ ላይ ያለውን የመልእክቱን ቁመና እንመለከታለን ከዚያ በኋላ እርሱ ያበላሸውን እየጠቀስን ከሙሉ መልሱ ጋር እንመለስበታለን፡፡
ዕብ ፭፥፯ በትርጓሜ ጳውሎስ መነሻነት
ጥሬው ንባብ እንዲህ ይላል፡- “እርሱም ሥጋን ለብሶ በዚህ ዓለም በነበረበት ጊዜ ፣ በታላቅ ጩኸት እና ዕንባ ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤ ጽድቁንም ሰማው”ትርጓሜያችን ደግሞ እንዲህ ይላል፡፡ “ወአመ ሀሎ በመዋዕለ ሥጋሁ፡፡ ይኸውም ሊታወቅ ሰው ኾኖ የሰውነት ሥራ በሠራበት ወራት፤ ጸሎተ ወስኢለ አብዐ ጸሎትን እንደላም ስኢልን እንደበግ አድርጎ አቀረበ፡፡ በዐቢይ ገዓር ወአንብዕ - በፍጹም ኀዘን በብዙ ዕንባ አቀረበ፡፡ የልቡና ነውና ግዳጅ ይፈጽማልና አንድ ጊዜ ነውና በዓቢይ ገዐር ወአንብዕ አለ፡፡ ኀበ ዘይክል አድኅኖቶ እሞት አለ፡፡ ወሰምዖ ጽድቆ - ቁርጥ ልመናውን ሰማው፡፡”
ሰፋ አድርገን እንየው፡፡ በኦሪቱ መሥዋዕት ኾኖ ከሚቀርቡት እንሳሳት መካከል የላም እና የበግ መሥዋዕት ይገኝበታልና ጸሎትን እንደ ላም፣ ስኢልን (ልመናን ምልጃን) እንደ በግ አድርጎ አቀረበ ይላል፡፡ ጸሎትና ልመና ብቻ ሳይኾን ራሱን ዐቢይ መሥዋዕት አድርጎ ስላቀረበ የጌታችንን ሊቀ ካሕናትነት (ሊቀ ካሕናት ይጸልያል ይለምናልና) ለማጠየቅ እንዲህ አለ፡፡ የኦሪቱ ሊቀ ካሕናት ላምና በግ ያቀርብ ስለነበረ ያንን አስቀርቶ ሐዲስ መሥዋዕት ራሱን አቀረበልን ለማለት ሊቃውንቱ ያራቀቁት ትርጉም ነው፡፡ እነዚያ በጉን ያቀርቡ ነበር ጌታችን ግን ራሱ በጉን ኾኖ ራሱን ለመሠዋት አቀረበ፡፡ ለሞት ያቀረቡት ሌሎች ይኹኑ እንጂ ሠዊ አልኾኑም፡፡ እነዚያ ገዳዮች እንጂ መሥዋዕት አቅራቢዎች አይደሉምና፡፡ በክፍል አንድ ላይ ምልጃ የሚለው ቃል የግድ አማላጅ በሚለው ዘርፍ ብቻ ሳይኾን ልመና ጸሎት ተብሎም እንደሚተረጎም ዐይተናል፡፡ ስለዚህ ግእዙ ስኢል ያለው አማርኛው ምልጃ ያለውን ሲኾን ጌታችን በጌቴ ሴማኒ ሳለ ያቀረበውን ጸሎት ወይም ልመናውን እንደኾነ ልብ እንበል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ኦሪቱ ሊቀ ካሕናት ሲናገር “ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል” ይላል፡፡ ዕብ ፭፥፫። ሐዋርያው በዚህ ቃል የኦሪቱ ሊቀ ካሕናት ኹለት ዓይነት መሥዋዕት እንደሚያቀርብ ያስረዳል፡፡ በመጀመሪያ እርሱ ራሱ በደል ያለበት ነውና ስለ ገዛ ኃጢአቱ መሥዋዕት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ስለራሱ መሥዋዕትን ካቀረበ በኋላ ስለ ሕዝቡ የሚያቀርበውን መሥዋዕት ያስከትላል፡፡ ይህንንም ከሚከተለው የኦሪት ቃል መረዳት ይቻላል፡፡
አስቀድሞ ስለራሱ መሥዋዕት እንደሚያቀርብ ሲናገር፡-
“ሙሴም አሮንን፦ ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኃጢአትህን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፥ ለራስህና ለሕዝቡም አስተስርይ፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዘ የሕዝቡን ቍርባን አቅርብ አስተስርይላቸውም አለው። አሮንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ስለ ራሱ ኃጢአት መሥዋዕት የኾነውን እምቦሳ አረደ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ከኃጢአቱ መሥዋዕት ስቡንና ኵላሊቶቹን፥ የጕበቱንም መረብ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ። ሥጋውንና ቁርበቱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አረደ፤ የአሮንም ልጆች ደሙን አመጡለት፥ እርሱም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ረጨው። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በየብልቱ፥ ራሱንም አመጡለት፤ እርሱም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው።” ይላል፡፡ ዘሌ ፱፥፯-፲፫። ራሱ ሳይነጻ ስለሌላው መሥዋዕት ሊያቀርብም ሊያሳርግም አይችልምና፡፡
ስለራሱ መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ ስለ ሕዝቡ ደግሞ ሌላ መሥዋዕት እንደሚያቀርብ ሐዋርያው ሲገልጥ እንዲህ ይላል፡-
የሕዝቡንም ቍርባን አቀረበ፤ ስለ ሕዝቡ ለኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን ፍየል ወስዶ አረደው፥ ስለ ኃጢአትም እንደ ፊተኛው ሠዋው። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አቀረበ፥ እንደ ሥርዓቱም አደረገው። የእህሉንም ቍርባን አቀረበ፥ ከእርሱም እፍኝ ሙሉ ወስዶ በጥዋት ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። . . . ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ገቡ፤ ወጡም፥ ሕዝቡንም ባረኩ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ። እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፥ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ስቡንም በላ፤ ሕዝቡም ሁሉ ዐይተው እልል አሉ፥ በግምባራቸውም ወደቁ።” ዘሌ ፱፥፲፭-፳፬።ይህ መሥዋዕት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚቀርብ ሲኾን ሊቀ ካሕናቱም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚገባው በዚያው ቀን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ “አሮንም በዓመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተሥረያ ያደርጋል፤ በዓመት አንድ ጊዜ ለልጅ ልጃችሁ ማስተሥረያ በሚኾን በኃጢአት መሥዋዕት ደም ማስተሥረያ ያደርግበታል” እንዲል፡፡ ዘጸ ፴፥፲።
ሌላኛው ዓይነት ደግሞ ዕለት ዕለት የሚቀርብ ሲኾን በየቀኑ አንድ ዓመት የኾነው ጠቦት ይሠዋል፡፡ “በቀን በቀን ዘወትር ኹለት የዓመት ጠቦቶች ታቀርባለህ” እንዲል፡፡ ዘጸ ፳፱፥፴፰። አንዱን በጠዋት ሌላውን በሠርክ ይሠውታል፡፡ እንደዚሁም የእህል፣ የመብራት፣ የዘይት፣ የዕጣን መሥዋዕትም ይቀርብ ነበረ፡፡ በመቀጠልም ቅዱስ ጳውሎስ የኦሪቱ ሊቀ ካሕናት በእግዚአብሔር ተመርጦና ተሾሞ ለአገልግሎት እንደሚሰየም ሲያመለከት “እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም።” ይላል፡፡ ዕብ ፭፥፬። እስከዚህ ያለው የኦሪቱ ሊቀ ካሕናትን ገጽታ ያመለክታል፡፡ ወደ ሐዲስ ኪዳኑ ሊቀ ካሕናት ለመምጣት የብሉይ ኪዳኑን ማሳየት አስፈለገው፡፡
ልዩነቱ ይታወቅ ዘንድ ይህ መኾኑ ሠናይ ነው፡፡ ወዲያውም ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካሕንነት መናገር ይጀምራል፡፡ “እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካሕናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን፦ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፤ እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ፦ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘለዓለም ካሕን ነህ ይላል” እንዲል፡፡ ዕብ ፭፥፭-፮። “ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካሕናት ሊሆን ራሱን አላከበረም“ ሲል እንደ አሮን የሚሾመው አስፈለገው ማለቱ አይደለም፡፡ አሮንን እግዚአብሔር ሾሞታል ኢየሱስ ክርስቶስን ግን ማን ይሾመዋል? ታዲያ “ራሱን አላከበረም” ሲል ሐዋርያው ተሾመ ማለቱ ካልኾነ ምን ማለት ሊኾን ይችላል? የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡
ለምሳሌ ጌታችን በወንጌል “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም” ሲል የማደርገውን ሁሉ በባሕርይ አባቴ ልብነት አስቤ በባሕርይ ሕይወቴ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት ሕያው ኾኜ እነርሱም በእኔ ቃልነት ኾነው በፈቃድ በሥምረት አንድ ኾነን ማንኛውንም ነገር እንሠራለን ሲል እንጂ ራሱን ከመለኮታዊ ሥልጣኑ ዝቅ ማድረጉ ወይም መለየቱ አይደለም፡፡ በአባቴ በአብ በሕይወቴ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ በእኔ ፈቃድ እንጂ (ይህቺውም ፈቃድ አንድ ናት) ከእነርሱ ተለይቼ የምሠራው ሥራ የለም ሲለን እንዲህ ተናገረ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ “ራሱን አላከበረም” ብሎ ሐዋርያው ሊነግረን የፈለገው ሊቀ ካሕንነቱ በራሱ በወልድ፣ በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ በባሕርይ አባቱ በአብ ፈቃድ የኾነ እንጂ ከኹለቱ ተለይቶ ለብቻው ያደረገው አይደለም ሲለን ነው፡፡ የብቻው ወይም በተለየ የግሉ ፈቃድ አይደለም ለማለት የተጠቀመው አገላለጥ እንደኾነ እናስተውል፡፡
ይህንንም ሲያጠናክር ቀዳማዊ እና ደኃራዊ ልደቱን አስተባብሮ “አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጂሃለሁ” ማለቱን ያመጣል፡፡ ወልድየ አንተ (አንተ ልጄ ነህ) ብሎ ቀዳማዊ ልደቱን፣ ዮም ወለድኩከ (ዛሬ ወልጄሃለሁ) ብሎ ደኃራዊ ልደቱን ነገረን፡፡ ይህ ልደት የባሕርይ ልደት ነው፡፡ ይህንን ባሕርያዊ ልደት ከነገረን በኋላ “አንተ ካሕኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጼዴቅ” ያለውን ይጠቅሳል፡፡ ካሕንነትህ የባሕርይ ልደት በመወለድህ ነው ብሎ ነቅዐ ሢመቱን (የሹመቱን ምንጭ) ዐሳየን፡፡ ልደቱ መቅደም መቀዳደም እንደሌለበት ሁሉ ሢመቱም እንዲያ ነው፡፡ በሰጪ እና በተቀባይ መካከል ያለ ሥርዓተ ሢመት ሳይኾን በህልውና በመገናዘብ ያለ ሹመት ነው፡፡
የካሕኑ መልከ ጼዴቅ ክሕነት መጠቀሱም ስለ ዕብራውያን ነው፡፡ እነርሱ (ዕብራውያን) የታላቁን ካሕን የመልከ ጼዴቅን ትውልደ ነገዱን ሀገረ ሙላዱን አያውቁትም፡፡ ስለዚህ ክሕነቱን ከእገሌ አገኘው ለማለት አልተቻላቸውም፡፡ እግዚአብሔር ወልድም ክሕነቱን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ተቀበለ አይባልም የባሕርይ ገንዘቡ ነውና፡፡ ነቢየ ልዑል ኢሳይያስ “አለቅነትም በጫንቃው ላይ ነው” እንዲል ሥልጣን ሁሉ ሹመት ሁሉ ኃይል ሁሉ የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ኢሳ ፱፥፮። ስለ ፈቃድ አንድነት ተሾመ ቢባልም በደረቁ ሿሚ ሸላሚ ያለው እንዳይመስለን፡፡ ካሕኑ መልከ ጼዴቅ ምሳሌነቱ አንዱ በዚህ ነውና፡፡የብሉይ ኪዳኑ ሊቀ ካሕን እንደተመደበው ከእህል እስከ ጠቦት ያሉትን የመሥዋዕት ዓይነቶች ያቀርባል፡፡ ጌታችን ግን ራሱን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ሲል እንደተናገረው፡፡ ዮሐ ፩፥፳፱።
የብሉይ ኪዳኑ ሊቀ ካሕናት ራሱ መሥዋዕት ከማቅረቡ በፊት ለራሱ መሥዋዕት ያሻዋል፡፡ ከዕዳ ከበደል ነጻ አይደለምና፡፡ የሐዲስ ኪዳኑ መሥዋዕት ጌታችን ግን ነውር የሌለበት ንጹሐ ባሕርይ ነው፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ” ሲል እንደተናገረው፡፡ ፩ጴጥ ፩፥፲፱። ደግሞም ቅዱስ ጳውሎስ “ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካሕናት ይገባልና” እንዲል፡፡ ዕብ ፯፥፳፮።
የኦሪቱ ሊቀ ካሕናት የራሱንም የሕዝቡንም ኃጢአት ለማስተሥረይ በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ መግባት ይጠበቅበታል፡፡ ጌታችን ግን አንድን መሥዋዕት እርሱም ራሱን (ሥጋውን እና ደሙን) አንድ ጊዜ ለዘለዓለሙ አቀረበ፡፡ “ሊቀ ካሕናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም” እንዲል፡፡ ዕብ ፱፥፳፭። ደግሞም በሌላ ስፍራ “በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል። ሊቀ ካሕናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሟል፤ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘለዓለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ” በማለት እንደተናገረ፡፡ ዕብ ፲፥፲-፲፪።
የብሉይ ኪዳኑን ሊቀ ካህናት ቅዱስ ጳውሎስ “ቆሟል” ሲለው ጌታችንን ግን “ተቀመጠ” ይለዋል፡፡ መቆም አገልግሎትን ከፍ ዝቅ ማለትን ሲያመለክት መቀመጥ ግን ሥልጣንን፣ ዕሪናን (መተካከልን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር)፣ ከእንግዲህ ምንም ዓይነት የልመናም ይሁን የሊቀ ካሕንነት ሥራ የማይሠራ መኾኑን፣ ሥራውን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወይም ጨርሶ በኃይሉ መንበር መቀመጡን ያጠይቃል (ያስረዳል)፡፡ ግን የሐዲስ ኪዳን ካሕናት በመቅደስ የሚሠውት ሥጋውና ደሙ ዛሬም ትኩስ በዕለተ ዐርብ በቀራንዮ እንደታረደው በግ ኾኖ ይቀርባል፡፡ እኛም ሥልጣን በተሰጠው ካሕን ሲባረክ ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት፣ ወይኑ ተለውጦ ደመ መለኮት ኾነ ብለን አምነን ሳንጠራጠር እንቀበለዋለን፡፡

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ እኛ በሠንጠረዥ ውስጥ ያስረዳነውን እርሱ እንዲህ ብሎ ይገልጠዋል፡፡ “ወዝውእቱ ዘለብሰ አርአያ ገብር ወነድየ ከመ ንብዐል ንሕነ በንዴተ ዚአሁ ዝንቱ ዘተዐገሠ ሕማመነ ወፆረ ደዌነ ወነሥአ ጌጋየነ ወሦዐ ርእሶ በእንቲአነ መሥዋዕተ ንጹሐ ውእቱ ካሕን ዘለዓለም፡፡ ወውእቱ በግዐ መሥዋዕት ወውእቱ ካሕን ሠዋዒ ወውእቱ ተወካፌ መሥዋዕት ምስለ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ - የተገዥ ባሕርይን የተዋሐደ በእርሱ ትሕትና እኛ እንከብር ዘንድ የተዋረደ እርሱ ነው፤ ሕማማችንን የታገሰ ደዌያችንን የተሸከመ በደላችንን የተቀበለ ፤ ስለእኛ ራሱን የማያልፍ የማይለወጥ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበ የማይሻር የማይለወጥ ካሕን ነው፡፡ የሚሠዋ [መሥዋዕት ኾኖ የቀረበ] በግ እርሱ ነው፣ የሚሠዋ [መሥዋዕት አቅራቢ] ካሕን እርሱ ነው፣ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው። ” ሃይ አበ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ፴፮ ክፍል ፬፥፳፭-፳፮። ሊቁ በደላችንን የተቀበለ ሲል ስለእኛ በደለኛ የተባለ በእኛ ተገብቶ ማለትም ስለእኛ ፋንታ ራሱን አቅርቦ እርሱ ግን ያለ በደሉ መከራ መቀበሉን ያመለክታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የተናገሩትን
በተለይም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እና የተዋሕዶው መዶሻ ቅዱስ ቄርሎስ ስለ ጌታችን ሊቀ ካሕንነት በተለይም ከዕብ ፭፥፯ ጋር የተዛመዱትን በቀጣዩ ክፍል እንመለከታለን፡፡
(ይቀጥላል . . .)

No comments:

Post a Comment