Saturday 22 August 2020

ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር የማይስማማው መጽሐፍ

በፌስ ቡክ ገጼ ላይ መድሎተ ጽድቅን በተመለከተ መጻፍ ከመጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ የግለ ሰብ መጽሐፍ መሆኑን ዘንግተውት ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ግልጽ ባይሆንልኝም አንድ የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ የተነካ እንደሆነ በማስመሰል ብዙና ብዙ የጻፉ ሰዎችን አስተያየት አይቻለሁ፡፡

በዚህ ምክንያት እስኪ ይህን በተመለከተ አስተያየታችሁን ስጡኝ ለማለት ይህቺን ጽፌአለሁ፡፡ መድሎተ ጽድቅ በሁለት ትምህርቶቹ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር አይስማማም፡፡ ሁለቱን ካቀረብኩ በኋላ ከጓደኛውም ጋር መግባባት አለመቻሉን ደግሞ አሳያችኋለሁ፡፡ ሁሉንም እንካቸሁ፤

በገጽ 121 ላይ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ደጋግ አባቶች ‹‹… ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ በአዳም በደል ምክንያት የተዘጋችውን ገነት እስኪከፍታት ድረስ ከሲኦል መውጣትና ወደ ገነት መግባት አልቻሉም ነበር›› የሚል ነገር ያስነብባል፡፡ ይህን ሐሳቡን በገጽ 343 እና 345 ባሰፈረው ንባብ ውስጥ ከነአብረሃም፣ ይስሓቅና ያዕቆብ ቀድሞ ገነት የገባው ከጌታ ጎን የተሰቀለው ወንበዴ ነው በሚል ያጸናዋል፡፡ ይህ ሐሳቡ ግን ‹‹መላእክትም የጣሉአቸው ሰዎች እያዩ ተቀበሏቸው፤ ነፍሳቸውንም አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብም ወደ አሉበት፤ ደስታ ወደሚገኝበት ወደ ገነት ወሰዷቸው›› ከሚለው ከመቃብያን መጽሐፍ ጋር ተስማሚ አይደለም (1ኛ መቃብያን 3÷38)፡፡ በእርሱ እምነት መሠረት ደጋግ አባቶች (እነ አብርሃም) ገነት የገቡት ከጌታ ሞት በኋላ ሲሆን መቃብያን ደግሞ ከጌታ ሞት በፊት ገነት አሉ እያለ ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛቸው ናቸው የተሳሳቱት?

ለ) በሁለተኛ ደረጃ የማነሣው ነገር በገጽ 486 ላይ በገዳማት በመቀበር መዳን አለ ብላ ቤተ ክርስቲያን አስተምራ አታወቀም ያለውን ነው፡፡ በገድለ ተክለ ሃይማኖት ምዕራፍ 61 ቊጥር 32 ላይ ያለውንና የተክለ ሃይማኖት መቃብር ‹‹… የኃጢአታችን ቤዛ…›› መባሉን ምን አስተያየት ይሰጥበት ይሆን?
መድሎተ ጽድቅ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር ብቻ አይደለም ከጓደኛውም ጋር አይስማማም፡፡ ይህንንም በገጽ 195 ላይ ‹‹ስለዚህም ይላል ቅዱስ ጳውሎስ ‹ከእነርሱም (ከእስራኤላውያን) አንዳንዶቹ ጌታን እንደተፈታተኑት በእባቦችም እንደጠፉ ጌታን አንፈታተን›› የሚለውን ጥቅስ በቀጥታ የሚያገናኘው በዘኁልቊ 21 ጋር ቢሆንም የእሱ ጓደኛ ግን ይህን የሚቀበል አይመስልም፡፡ ‹‹በ1ኛ ቆሮንቶስ 10÷9 ‹ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦችም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን› የሚለው ቃል ከዮዲት 8÷24 የተገኘ ቃል ነው›› በማለት ሐሳቡን አስፈሯል (ዳንኤል ክብረት (ዲያቆን)፣ ኦርቶዶክስ መልስ አላት (ዐዲስ አበባ፣ 2000) ገጽ 55)፡፡

ስለዚህ መደሎተ ጽድቅ ለተሀድሶዎች መልስ እሰጣለሁ ብሎ ከመነሣቱ በፊት ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት እና ከወዳጆቹ ጋር መስማማት አይኖርበትም ትላላችሁ?

@gedlatnadersanat

No comments:

Post a Comment