Sunday 6 October 2019







ሰላምን እንድንከተላት የተወለደልን ክርስቶስ ወይስ ጊዮርጊስ ?


የጥንትዋ ሐዋርያዊቷ ኦርቶዶክሳዊት ወንጌል ሰባኪዋ ሳትሆን የአሁንዋ ወይንም የዛሬዋ ኦርቶዶክስ እንዲህ ትለናለች 



ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ ጊዮርጊስ ተወልደ ነዋ 





ትርጉም ጊዮርጊስ እነሆ ተወልዷልና አሁንም ሰላምን እንከተላት ( የጥር 2 ዚቅ ) 


በዚሁ በኦርቶዶክስ መጽሐፍ ውስጥ ይህንን ሃሳብ የሚያፈርስ ቃል እንዲህ ሲል ተጽፎአል 



ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ መድኃኒነ ተወልደ ነዋ 


መድኃኒታችን እነሆ ተወልዷልና አሁንም ሰላምን እንከተላት ( የልደት ሰላም ምልጣን )

ወድ ወገኖቼ ሆይ ለዳኝነት መጽሐፍቅዱሳችንን ሳንገልጥ በዚህች ቤተክርስቲያን ውስጥ ሁለት የማይገናኙ ሃሳቦች እናገናኛችሁ ወይም እናስታርቃችሁ ብንላቸው እንኳ አንዱ በሌላው ከመሸነፍና ከመዋጥ ውጪ ሌላ መታረቅያ መንገድ የማናገኝላቸውን  ሃሳቦችን አግኝተናል :: ታድያ እነዚህ ሃሳቦች ለማናችንም የተሰወሩ ስላልሆኑ ለማመሳከርያ ስንል እንኳ መጽሐፍቅዱሳችንን መግለጥ ባንፈልግም  በመወለዱ ሰላምን ያመጣው ክርስቶስ መሆኑ ለመጥቀስ   ጌታ በተወለደበት ሌሊት መላዕክቱ ያሰሙት የሰላም መዝሙር ሳይጠቀስ አይታለፍም ( የሉቃስ ወንጌል  2 : 10 ) :: እንደገናም በዚህ ጉዳይ   መጽሐፍቅዱስን ያላነበበ ማንንም ሰው ብንጠይቀው እንኳ መድኃኒት ሊሆነው የተወለደለት ኢየሱስ መሆኑን ስለሚያውቅ ምርጫው አድርጎ መከተል የሚፈልገው  ኢየሱስን ነው :: ስለሆነም መድኃኒታችን እነሆ ተወልዷልና አሁንም ሰላምን እንከተላት ሲል በትክክለኛ ምርጫው ኢየሱስን ሊከተል ይወስናል  እንጂ ጊዮርጊስን መድኃኒት አድርጎ በመቀበል  ጊዮርጊስን ለመድኃኒትነት መርጦ ጊዮርጊስ እነሆ ተወልዷልና አሁንም ሰላምን እንከተላት በማለት ጊዮርጊስን የመከተል ምርጫው አያደርግም:: ቤተክርስቲያኒቱ ግን ትምህርቷን እንደ ቃሉ ባለማድረግ በዚሁ የተረት መጽሐፏ ሕዝቡን በመንታ መንገድ ላይ  አቁማው ትገኛለች :: መድኃኒት የሚያስፈልገውን ጊዮርጊስ የተባለውንም ፍጡር መድኃኒት ከሆነው ከኢየሱስ ጋራ በእኩል ደረጃ አስቀምጣ ሰዉ መድኃኒቱና ምርጫውም አድርጎ ኢየሱስን እንዳይከተል ይእዜኒ ለሰላም ንትልዋ ጊዮርጊስ ተወልደ ነዋ ጊዮርጊስ እነሆ ተወልዷልና አሁንም ሰላምን እንከተላት ስትል ሰዎች መድኃኒት የሆነውን ኢየሱስን ከመከተል ይልቅ ጊዮርጊስን መድኃኒቴ ብሎና መድኃኒቱ አድርጎ እንዲከተል ስታበረታታ ትገኛለች :: ስለዚህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆይ እውነትን ከስሕተት ትለይ ዘንድ እነዚህ ሃሳቦች ቀርበውልሃል በመሆኑም ኢየሱስን ተከትለህ መዳን ሲገባህ ከዚህ ይልቅ ጊዮርጊስ ተወልዶልኛልና ሰላምን ልከተላት ብትል በራስህ  ላይ የፈረድክ ራስህ ነህና ምርጫው የአንተ ነው :: እንደገናም የተወለደልኝ ኢየሱስ ነውና ሰላምን ልከተላት ብትል አሁንም ምርጫው የአንተው የራስህ ነው :: ለዛሬ ጽሑፌን በዚሁ አበቃሁ ተባረኩ:: 


እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና ( ኤፌሶን 2: 14 - 18 )


ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤ የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው። ( 1ኛ ጴጥሮስ 3 : 10 - 12 )

አባ ዮናስ ጌታነህ 

No comments:

Post a Comment