Thursday 3 October 2019

የመልዕክት ርዕስ ፦ ሰዎች ለእግዚአብሔር መዝሙር ወይም ምሥጋና ሊያሰሙ የፈለጉበት ምክንያቶቻቸው ምንድናቸው ? ---- የመልዕክት ርዕስ ፦ ሰዎች ለእግዚአብሔር መዝሙር ወይም ምሥጋና ሊያሰሙ የፈለጉበት ምክንያቶቻቸው ምንድናቸው ? ከዚህ በመቀጠል እነዚህን ስምንት ነጥቦች የርዕሳችን መንደርደርያና የትምህርቱም ዋና ዋና ሃሳቦች ስለሆኑ በማስተዋል ተመልከቷቸው 1ኛ ) ከዳዊት ምክንያቶች ጥቂቶቹ ፦——— እግዚአብሔር ሰማ ማረኝም እግዚአብሔር ረዳቴ ሆነኝ ክብሬ ትዘምርልህ ዘንድ ዝምም እንዳትል ልቅሶዬን ለደስታ ለወጥህልኝ ማቄን ቀድደህ ደስታንም አስታጠቅኸኝ አቤቱ አምላኬ ለዘላለም አመሰግንሃለሁ - - - - - ( መዝሙር 29 ( 30 ) ፥ 10 - 12 ) 2ኛ ) ዳዊት በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ብቻ ዘምሮ ሊቀር ውሳኔ ያደረገ ነበረ መዝሙር 62 ( 63 ) ፥ 1 _ 11 ፤ መዝሙር 104 ፥ 33 ፤ መዝሙር 146 ፥ 2 3ኛ ) ሰዎች መዝሙርን ለእግዚአብሔር ሊያሰሙ የፈለጉበት ምክንያቶቻቸው ሲበላሽ መዝሙራቸውም ሆነ በአጠቃላይ መዝሙራቸውን ያቀረቡበት መንገዳቸውም ሁሉ አብሮ ይበላሻል ለእግዚአብሔር ዘመናዊ በሆኑ በሳክስፎንና በኦርጋን ስለዘመርን እግዚአብሔርን ዘመናዊ አናደርገውም ፣ በባሕላዊ መሣርያዎች በክራር በመሰንቆና በዋሽንት ስለዘመርን ደግሞ እግዚአብሔርን ጥንታዊ አናሰኘውም :: ይሄ እግዚአብሔር በክራርና በዋሽንት ስለስለተዘመረለት ኋላ ቀር አይደለም ፣ በሳክስፎንና በጊታር ስለዘመርንለት ደግሞ ዘመነኛ አይሆንም :: እርሱ ዘመን የማይቆጠርለት ዘመንም የማይወስነው አልፋና ኦሜጋ ነው ራዕይ 1 ፥ 8 ፤ መዝሙር 102 ፥ 12 ፣ 26 _ 27 ፤ ዕብራውያን 13 ፥ 8 :: ከዚህ የተነሳ የሰዎች መዝሙራቸው ሳይሆን መዝሙራቸውን ያቀረቡበትን መንገዳቸውንም ሆነ ምክንያቶቻቸውን በማስተዋል ልናይላቸው ይገባል ፣ ሊያስተካከሉ በተገባቸው ሁኔታ ደግሞ እንዲያስተካክሉ ልንረዳቸው ያስፈልጋል :: 4ኛ ) ምክንያቶቻቸው የተበላሹባቸው እሥራኤል ዘምረው የዘፈኑ ነበሩ ስለዚህ ዘፍነን ከሆነ ወደ መዘመር ያምጣን እንጂ ዘምሮ ከመዝፈን ግን እግዚአብሔር ይጠብቀን ዘጸአት 15 ፥ 19 _ 21 ፤ ዘጸአት 32 ፥ 15 _ 35 ፤ የማቴዎስ ወንጌል 26 ፥ 30 5ኛ ) የምንዘምርበት መንገድ በተለያዩ ምክንያቶች ሊበላሹ ይችላሉ ፣ የሚዘምሩበት ምክንያት ከተበላሹባቸው ሰዎች መካከል አንደኛው የጠፋው ልጅ ታላቅ ወንድም ነው ፣ ሌላዎቹ ደግሞ በሆሳዕና ዕለት የሕጻናቱን ምስጋና የተቃወሙ ፈሪሳውያኑ ናቸው :: የሉቃስ ወንጌል 15 ፥ 25 _ 32 ፤ የሉቃስ ወንጌል 19 ፥ 27 _ 40 6ኛ ) የምንዘምርበት ምክንያቶቻችን እንዳይበላሹብን የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን ? ልንል ፣ ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ስንልም ባለንበት በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በውሳኔ ልንቆም ይገባል መዝሙር 136 ( 137 ) ፥ 1 _ 5 7ኛ ) ያ ካልሆነ ግን የሕይወት ብልሽት ይገጥመናል ፣ ሰዎችም ይዘባበቱብናል ( መሣፍንት 16 ፥ 23 -25 ) 8ኛ ) የመዘመር ምክንያቶቹ ያልተበላሸበት ዳዊት ልቤ ጽኑ ነው እቀኛለሁ እንዳለ ለሚስቱም ለሜልኮል ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ዘፍኛለሁ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእሥራኤል ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ ሲልም እንደተናገረ እኛም ከሃሳባቸው ጋር ባለመስማማታችን ምክንያት ለናቁን የዘመናችን ሜልኮሎች ሁሉ እንዲህ ልንል ይገባል ከዚያም መልስ በሰነዘሩት ሃሳባቸውም ሳይቀር ላለመሸነፍ ልባችንን በዚያው መንገድ ልናጸናው ያስፈልጋል መዝሙር ( 108 ) ፥ 1 _ 13 ፤ 2ኛ ሳሙኤል 6 ፥ 21 ወይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment