Saturday 10 March 2018

ለተወዳጁ ወንድማችን ዶክተር ወዳጄነህ የተሰጠ መጽሐፍቅዱሳዊ መልስና የማስገንዘብያ ቃልለተወዳጁ ወንድማችን ዶክተር ወዳጄነህ የተሰጠ መጽሐፍቅዱሳዊ መልስና የማስገንዘብያ ቃል የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሰላም ለእናንተ ይሁን በዶክተር ወዳጄነህ መሐረነና የኤክሶዶስ ቲቪ ፕሮግራም አዘጋጅ በሆነችው እህታችን ቤተልሔም ታፈሰ መካከል በተደረገው ውይይት የቀረቡትን ሃሳቦች ተመልክተን ትክክል የሆነውን ትክክል ናቸው በማለትና አገልግሎታቸውንም ጭምር በመደገፍ ፣ በማበረታታት የተናገርን ሲሆን ትክክል ያልሆነውን ሃሳባቸውን ደግሞ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት እርምት እንዲያደርጉ ተገቢውን መልስ ሰጥተንበታል በተለይም በዚህ ጉዳይ ላይ ይበልጥ እንድንነሳሳና መልስ እንድንሰጥበት ካደረጉን ነገሮች አንዱ የወንጌል ተቃዋሚዎችና አሳዳጆች ከሆኑት መካከል አብዛኞቹ የኦርቶዶክስ ዓበይት በዓላትንና አጽዋማትን እንደ መነሻ አድርገው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኢየሱስን አታውቅም ማለት በደል ነው ብለው የተናገሩትን የዶክተር ወዳጄነህን ንግጝር እና የማብራርያ ሃሳብ ምክንያት በማድረግ << ታላቅ ምስክርነት ፓስተር ዶክተር ወዳጄነህ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ሳያውቋት ለወጡትና ለሆዳቸው ብለው ለሚሰድቧት ትልቅ ትምህርት ነው >> ሲሉ ለተናገሩት ተቃዋሚዎቻችን መልስ ለመስጠት ስንል እኛም የዶክተር ወዳጄነህን የውይይት ሃሳቦች ማንሳትና እንደ እግዚአብሔር ቃል የሆነውን መልስ መስጠት ግድ ብሎናል እንደገናም ሁሉም ሰው እንዲሰማው እና እውነቱንም እንዲያውቅ ይህንን በቪዲዮ የቀረበ ምላሽ አዘጋጅተን ለቀናል ታድያ አገልጋይ ዶክተር ወዳጄ ነህ ከዚህ በፊት በነበረው አገልግሎታቸው በአብያተክርስቲያናት ዙርያ በተከፈተላቸው በር ሁሉ ታማኝ በመሆን ያስተላለፉትና የሰጡት ትምህርት በብዙዎች ዘንድ አስደሳችና ተወዳጅነትን ያተረፈላቸው መሆኑን ብዙዎች የሚመሠክሩትና እኛም የምናውቀው ጉዳይ ቢሆንም አሁን ላይ ለተደረገላቸው ቃለ ምልልስ ግን የተሳሳተ አስተያየትና እንደ እግዚአብሔር ቃል ያልሆነ መልስ የሰጡ በመሆናቸው በሰማነው መልስ እራሳቸው ዶክተር ወዳጄነህን ሳይቀር ወደኋላ የተመለሱ ያክል ቆጥረን ከተቃዋሚ ጎራ የምንመድባቸው አድርጐናል ይሁን እንጂ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመን እኛም ለዶክተሩ የምንሰጠው ትልቅ ምክር የአንድን ቤተ እምነት ዶክትሪንና የእምነት አስተምህሮ አንስቶ በአደባባይ ሊያውም በሶሻል ሚድያ እንዲህ ነው ሲሉ ከማውራትና ከመናገር በፊት የዛን ቤተ እምነት አስተምህሮ ከመነሻው አስቀድሞ በማወቅና አሁን ላይ ያለውንም ሁኔታ ደግሞ እንደሚገባ በመረዳት ከጅማሬ እስከ ፍጻሜው ያለውን እውነትና ስሕተቱንም ጭምር ጠንቅቆ በማወቅ ከመረጃ ጋራ መናገር በእጅጉ ያስፈልጋል እንላለን አለበለዚያ ግን ጉዳዩን አለማንሳቱም ሆነ አለመነካካቱ ይመረጣል የሚል ምክር ነው የምንሰጠው ይሁን እንጅ ይህንኑ ጉዳይ በአስተያየትና በምክር የምናልፈው ሳይሆን የዶክተሩንም የአደባባይ ይቅርታ እንፈልጋለን ለምን ቢባል ዶክተሩ ወደ ኦርቶዶክስ የተመለስኩኝ ትክክለኛ ኦርቶዶክስ በመሆኔ ነው ይህንን የተናገርኩት ቢሉ ኦርቶዶክስ ነኝ ያሉ በመሆናቸው በእኛ በኩል ከሃሳባቸው እንዲመለሱ ትምህርት ከምንሰጣቸውና ከምንጸልይላቸው ውጪ ሌላ ምንም ልንላቸው አንችልም ነበር ነገር ግን ዶክተሩ እኔ ኦርቶዶክስ ነኝ አላሉም ኦርቶዶክስን ግን ከሥር መሠረቷ አብጠርጥረው የሚያውቋት ይመስል ተሃድሶ ፣ ማኅበረቅዱሳን እያላችሁ መዘላለፉ ቢቀርና ይቅርታ መጠያየቅ ብታደርጉ ሲሉ ሊመክሩን ወደዱ ይህ ብቻ አይደለም ጠባብ በሆነ ነገር ውስጥ ገብቶና አንድ ኦርቶዶክስ ይዞ ጴንጤ ማድረግ አግባብነት የሌለው እንደሆነ አያይዘው ሃሳባቸውን አክለዋል ይሁን እንጂ የእኛ አገልግሎት ግን እንደርሱ አይደለም በሐዋርያዊት ኦርቶዶክስ በውስጥዋ ተወልደን ያደግንና መጻሕፍቶችዋ ሳይቀር የሚሉትን የተረዳን በመሆኑ ኦርቶዶክስን ወደ ጥንተ መሠረትዋ ለመመለስ እግዚአብሔር ያስነሳን ሰዎች ነን ኦርቶዶክስን ጴንጤ ልናደርግ የተነሣን ግን አይደለንም እርሳቸውም ይህንን አነሳሳችንን ከዚህ በፊት በነበረን መተዋወቅና ቅርርብ ውስጥ ጠንቅቀው ያውቁታል ከዚህ ሌላም በዚህ አገልግሎት ከእኛ ጋር ባይሰለፉም የአገልግሎታችን አጋዥ እንደነበሩ ላስታውሳቸው እወዳለሁ ታድያ ይሄ ሁሉ ነገር እያለ ዛሬ ይህን ማለቱ ለምን ይሆን ? ብያለሁ እንደገናም የተሃድሶና የማኅበረቅዱሳንን ግጭት ዶክተሩ ቀለል አድርገው በማየት የሠፈርና የጓዳኞች ግጭት ያክል ቆጥረው መዘላለፉ ቢቀርና ይቅርታ መጠያየቅ ቢኖር ማለታቸው ለሃሳቡ እንግዳና የሩቅ ሰው አድርገን እንድንቆጥራቸው ሊያደርጉን ሞክረዋል ይሁን እንጂ በዚህ አጋጣሚ ዶክተሩ በዚህ ነገር ገብተው ከሚቸጋገሩ የእኛን ነገር ለእኛ ቢተዉት መልካም ይሆናል ልላቸው እወዳለሁ ይቅርታን በተመለከተ ለይቅርታ ግን የማናችንም ልብ ክፍት ሊሆን ይገባል ብዬ እኔም የዶክተሩን ሃሳብ እጋራለሁ ይሁን እንጂ ግጭቱ ጊዜያዊ ግጭትና በቀላሉ በይቅርታ የሚታለፍም ሆነ የሚፈታ ግጭት አይደለም በእምነት መካከል የሆነ የልዩነት ግጭት ስለሆነ የሚፈታው ባለቤቱ እግዚአብሔር ብቻ ነው እንደገናም መለያየቱም ሆነ ግጭቱ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ሳይሆን ከቤተክርስቲያኒቱ የበላይ ጠባቂ ከሆነው ሲኖዶስ ጋር ነው ማህበረ ቅዱሳን ግን በአባቶችና ተሃድሶ ስንባል ስያሜ ተሰጥቶን ከቤተ ክርስቲያኒቱ በተባረርነው ልጆቿ መካከል ጣልቃ ገብቶ በወንጌሉ ምክንያት የመጣውን ልዩነት እንደ እግዚአብሔር ቃል በቀላሉ እንዳይፈታ የቤተክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪ በመምሰል እያራገበ ፣ እያሟሟቀና እያጣላን ያለ ቡድን ነው ስለዚህ እኛ በአሁኑ ሰዓት ጉዳያችንንም ሆነ ጥያቄያችንን ይስማልንና መፍትሔ ይስጠን የምንለው ቅዱስ ሲኖዶስን ነው ማኅበረ ቅዱሳንን ግን አይደለም ከዚህ የተነሳ ምንም ውስጥ ከሌለና ከማይመለከተው ማህበረ ቅዱሳን ጋር እኛስ ምን ስንል ነው የምንጣላው ? እንደገናስ እንዴትስ ሆነን ነው የምንደራደረውና ይቅርታንስ የምንጠያየቀው ? ይልቁንም ማኅበረቅዱሳንን ለሁልጊዜ የምንመክራቸው አንድ እውነት እንደነበረ አስታውሳለሁ ያም ምንድነው ብትሉኝ አብዛኞቹ የቤተክርስቲያኒቱን የግዕዝ ቋንቋ የማያውቁና ጸዋትወ ዜማውንም ሆነ ቅዳሴውን ያልቀጸሉ በመሆናቸው ምስጢርን እንደሚገባ ያላደላደሉ ናቸው እንደገናም የቤተክርስቲያኒቱን አመሠራረትና የታሪክ እውነት በውል ያላወቁ በመሆናቸው ከዚህ በፊት በነበረው እምነትዋ ቤተክርስቲያኒቱ መጽሐፍቅዱስን መሠረት ያደረገችበትን እምነት ምን እንደሆነ ያልተገነዘቡ ናቸው ከዚህ የተነሳ ከመጽሐፍቅዱሱ ይልቅ ገድልና ድርሳንን በዋናነት ተቀብለው ይህንኑ ገድልና ድርሳን የእምነት አንቀጽ አድርጎ በመጥቀስ የቤተክርስቲያኒቱን እምነትም ሆነ የየግል የእምነት መረዳታቸውን ሊያሳዩን ይሞክራሉ እኛም ታድያ ይህንኑ ደከም ያለ መረዳታቸውን ስለምናውቅ ወደ ትክክለኛው የእግዚአብሔር ቃል መረዳት እንዲመጡ እውነቱን ስለምንነግራቸው በብዙ ይጠሉናል ደግሞም ይጣሉናል ከዚህም ሌላ ይህም አልበቃ ብሎአቸው ከሲኖዶሱም ሆነ ከጳጳሳቱም ጋር ሊያጣሉን የሚሞክሩት በዚህ ምክንያት ነው ምስጢሩ እንግዲህ ይሄ ነው ዶክተር ወዳጄነህ ስለዚህ ወንድሜ ሆይ አንተም በጉዳዩ አስበህበትና ጸልየህ ከልብህም ጋር ተማክረህ መረዳቶችህንና ነገሮችህን ሁሉ አስተካክለህ ዳግመኛ በጥሩ መንፈስና በንስሐ ልብ እንደምንገናኝ አምናለሁ ጌታ እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርክህ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን Contact https://www.facebook.com/yonas.asfaw.39
 Primary: yonasasfaw8@gmail.com yonasgetaneh@ymail.com


No comments:

Post a Comment