Tuesday 27 February 2018

ለሰዎች ዕድል መስጠት ( ትንቢተ ኢሳይያስ 40 ፥ 11 ፣ ዘፍጥረት 33 ፥ 13 _ 14 ) ክፍል አንድለሰዎች ዕድል መስጠት ( ትንቢተ ኢሳይያስ 40 ፥ 11 ፣ ዘፍጥረት 33 ፥ 13 _ 14 ) ክፍል አንድ በዚህ ትምህርት ውስጥ በመጀመርያ ለሕይወታችን መዳን ቅድሚያውን ሰጥቶ ለሁላችንም ዕድል የሰጠንን እግዚአብሔርን የምናይበት ነው በመሆኑም ከዚህ እውነት ተነስተን ደግሞ እኛም ለሌሎች እንዲሁ እድል መስጠት አለብን ይሁን እንጂ ለሰዎች ዕድል ሰጠን ማለት ግን ከእውነት አፈገፈግን ወይንም በእውነት ላይ ዋሸን ማለት አይደለም በማለት በጊዜው የሆነውን እውነት ለማሳየት የቪዲዮ ማስረጃዎችን ማቅረቤ ይታወሳል በዚህ ውስጥ ግን ሊቀጠበብት ዶክተር ዘሪሁን ሙላቱ የትምህርቴ መነሻና ዋነኛ ሃሳቤ ናቸው ለምን ብትሉኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ መምህርና ሊቀ ጠበብት የሆኑት ዶክተር ዘሪሁን ሙላቱ አውቀውት ይሁን ሳያውቁ ብቻ ልክ እንደ እኛ በሰማይ ቅዱሳን የማማለድ ስራ አይሰሩም ብለው እርፍ ያሉበትን የቃላት መልልስና ንግግር አቅርቤ ነበርና አሁን ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለማወቅ ፈልጌ ነው እንደኛ ተሃድሶ ተብለው ተባረዋል ? ወይንስ አይ እኔ ተሃድሶ አይደለሁም ተሳስቼ ነው ይህንን ያልኩት ሲሉ ቤተክህነትን ይቅርታ ጠይቀው ተመልሰዋል የሚለው የእኔም ጥያቄ ስለነበረ ነው እነ መሪጌታ ሙሴና መሪጌታ ጽጌ በጊዜው በነበረው ውይይት ላይ ሊቀጠበብቱ የመጽሐፍቅዱሱን እውነት ፍርጥ አድርጎ በመናገር በሰማይ ያሉ ቅዱሳን ፍርድ ከተሰጠ በኋላ አንዳቸው ለአንዳቸው ተነጋግረው ያስታርቃሉ ወይንም ያማልዳሉ የሚል የቤተክርስቲያን ትምህርት የለም በማለታቸው ምክንያት ሊቀጠበብቱ ተሃድሶ ስለሆኑና እኛንም ስለመሰሉ ጌታን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን ሲሉ ተደምጠዋል ስለዚህ እኔም የኚህን የሊቀጠበብቱን የመጨረሻ ሁኔታ ለመስማትም ሆነ ለማወቅ ስለጓጓሁ ይህንን ጽኑ የሆነውን ምስክርነታቸውን ሰምቼ በብዙ ሃሴት በማድረግ እስካሁን ድረስ እየጸለይኩላቸው እገኛለሁ ስለዚህ ይህንን ሁኔታም የምታውቁ ሰዎች ሊቀ ጠበብቱን አፈላልጋችሁ በመጠየቅ የነገሩን መጨረሻ ብታውቁና ብታሳውቁን ፣ እንደገናም እኚሁኑ ሊቀጠበብት ዶክተር ዘሪሁን ሙላቱን በዚሁ በመሠከሩት የእግዚአብሔር ቃል እውነት እንዲጸኑና እስከመጨረሻው እንዲሄዱ እንዳያፈገፍጉም ጠጋ ብላችሁ ብታበረታቷቸው ብትጸልዩላቸው እና የሚሆነውን ነገር ሁሉ ብታደርጉ በጣም ደስ ይለኛል ጌታ እግዚአብሔር ዘመናችሁን ይባርክ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን Contact https://www.facebook.com/yonas.asfaw.39 Primary: yonasasfaw8@gmail.com

Friday 23 February 2018

ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናን ተገቢውን የእግዚአብሔር እውነት እንዲያገኙ ለመምህር ልዑለቃል የተሰጠ ምላሽና የማስገንዘብ...ራሳችሁን ሁኑ እንጂ አታፈግፍጉ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም ወደ ዕብራውያን ሰዎች የተላከ ምዕራፍ 10 : 32 - 39 ይመልከቱ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሰላም ለእናንተ ይሁን ተባረኩ እስካሁን ድረስ በተለቀቁት ቪዲዮዎች በብዙ እንደተባረካችሁ አምናለሁ ተስፋም አደርጋለሁ መጽሐፍቅዱሳችን በግልጽ እንደሚነግረን ወንጌልን በተመቻቹ መድረኮችና በተዋቡ ፑልፒቶች ዙርያ ብቻ የምንሰብከው ሳይሆን በእስር ቤትና በፈተና በማስጠንቀቅያና በዛቻ ውስጥም ሆነን የምንሰብከው እውነት ነው ይሁን እንጂ በዚህ ውስጥም እንኳ ሆነን ጌታ በሰጠን የተስፋ ቃሉ መሠረት ስንጸልይ በራሱ በመንፈስቅዱስ አማካኝነት ቃሉን በግልጥነት ወደምንናገርበት አደባባይ እንሸጋገራለን የሚወስደን መንፈስም በላያችን ላይ ይመጣል እንጂ ወደ ኋላችን ልናፈገፍግ ምክንያት የሚሆኑንን ሃይማኖታዊ ቃላቶችን እየተጠቀምን መንሸራተትና ከእውነት ወንጌል የምናፈገፍግ አንሆንም የሚያፈገፍጉ ሰዎች ማምለጫ የሚሆናቸውን የትኛውንም ዓይነት መንፈሳዊ ቃላቶችን ቢጠቀሙም እግዚአብሔር ግን የሚያውቃቸው በመንሸራተታቸው እና በማፈግፈጋቸው ስለሆነ የሚሰጣቸው መልስ ይህንን የሚመስል ነው ነገር ግን ግማሽ በነቀፋና በጭንቅ እንደ መጫወቻ ስለ ሆናችሁ ግማሽም እንዲህ ካሉት ጋር ስለ ተካፈላችሁ፥ ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ መከራ በሆነበት በትልቅ ተጋድሎ የጸናችሁበትን የቀደመውን ዘመን አስቡ የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ እንግዲህ ታላቅ ብድራት ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም ወደ ዕብራውያን ሰዎች የተላከ ምዕራፍ 10 : 32 - 39 ይመልከቱ የሚያፈገፍጉ ሰዎች እንዳልኳችሁ የትኛውንም ዓይነት ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ቃላቶችን ቢጠቀሙ ጌታ እግዚአብሔር አፈግፋጊዎች እንጂ በሳሎች አይላቸውም እንደገናም ከአዋቂዎችና ከአስተዋዮች ጎራም አይመድባቸውም ታድያ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ሐዋርያው የሕይወታቸውን ዓይነት እንድናውቅ ግልጽ አድርጎ ነግሮናል በገላትያ 6 ፥ 11 _ 16 መሠረት በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና አለን ስለዚህ ከዚህ የተነሳ ለሚያፈገፍጉ ሰዎች ቦታ የለንም ለወደፊቱም አይኖረንም ነገር ግን የሚያፈገፍግ ሰው ጥሩ የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ምክር የሚያስፈልገው ነውና ከማፈግፈጉ ተመልሶ በትክክለኛ ቦታው እንዲሆን የሚያስችል በቂ የሆነ ምክር ልንሰጠው ዝግጁዎች ነን ስለዚህ ከእነዚህ ሃሳቦች በመነሳት ይህንን ቪዲዮ ለምትከታተሉ ወገኖቼና አድማጮቼ በሙሉ የምናገረው አንድና አንድ እውነት የሚያፈገፍግ ሰው በብዙ ሰዎች ልብ ውስጥ የሚታሰበው አዲስ ወደ ጌታ የመጣና የጌታ አማኝ የሆነ ሰው ነው ተብሎ ነውና አስተያየቱም ሆነ ምክሩ ፣ ጸሎቱ ፣ የፕሮግራም ግብዣውና ማንኛውም መንፈሳዊ የተባለ ነገር ሁሉ የሚዥጐደጐደው እንዲህ ላለ ሰው ነው ይሁን እንጂ ይህን ሁኔታ በትክክለኛው በእግዚአብሔር ቃል መነጽር ከተመለከትነው የሚያፈገፍጉ በአብዛኛው ለክርስትናው አዲስ የሆኑ ብቻ ሳይሆኑ በተለይም ዛሬ ላይ በእኛ ዘመን በጌታ ቆየሁ ፣ ስም ያለኝ አገልጋይ ነኝና ወዘተርፈ የሚለው ሰው ሁሉ ዓይን ያወጣ ማፈግፈግና መንሸራተት እጥፍም ብሎ መሄድና አላዋጣ ሲል ደግሞ ላሽ ማለትን የሚያሳይበት ጊዜ ላይ ደርሰናል አንዳንዱ ደግሞ ማፈግፈጉ ለራሱ እንኳ እስከማይታወቀው ጊዜ ድረስ ከሌላው ጋር በግብዝነት አብሮና ተተያይዞ ሲያፈገፍግ ይታያል ይህንን ማፈግፈግ ታድያ ባሳለፍኩት የክርስትና ጒዞና የአገልግሎት ቆይታ በብዙ አገልጋዮች ሕይወት ውስጥ አይቼዋቻለሁ በመሆኑም መልዕክቴን ስጠቀልል አሁን ላይ ያላችሁ ማናችሁም የፕሮቴስታንት አገልጋዮች ፓስተሮች ልትሆኑ ትችላላችሁ እንደገናም ከኦርቶዶክስ የወጣችሁ ተሃድሶዎችና ሌሎችም እራሳችሁን ሁኑ ፣ አታፈግፍጉ ፣ አታፈግፍጉ ፣ አታፈግፍጉ ስል ደግሜ ደጋግሜ በመናገር ጽኑ የሆነውን ወንድማዊ ምክሬን ለእናንተ ለወገኖቼ ማስተላለፍ እወዳለሁ ተባረኩልኝ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

Saturday 17 February 2018

በምድራችን የሚሰራ ስውር የመናፍስት ሥራ የተገለጠበት አስደናቂ የክፍል ሁለት ትምህርት

.... ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከአዳኟ ከኢየሱስ የተፋታችበት የቁልቁለቱ መንገድ ክፍል አራት ( ቊጥር 2 )የተቋቋመች ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከአዳኟ ከኢየሱስ የተፋታችበት የቁልቁለቱ መንገድ ክፍል አራት ( ቊጥር 2 ) ክፍል አራት የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንዴት ናችሁ ተባረኩ ከኢየሱስ ጋር የተፋታችዋ ቤተክርስቲያን ቊልቊለት የሄደችበትን የቊጥር ሁለት ትምህርት አሁን አቀርባለሁ የሉቃስ ወንጌል 21 ፥ 28 ላይ ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቧልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሱ ይለናል በመሆኑም ዛሬ ቤዛዋን ያወቀች ቤተክርስቲያን ልትሆን የሚገባት እንዲህ ነው ቤዛዋ ማለትም ለበደልዋ ሥርየት ሊሰጣት ምትክ ሆኖ የሞተላት ኢየሱስ እርስዋን ስለማጽደቅ በመነሣት የተቤዣት ፣ የታደጋትና ያዳናት በመሆኑ አድራሻዋን በሰማይ ያደረገች ናት ቤዛዋ የሆነውን ዳግመኛም መጥቶ የሚወስዳትን ጌታ ከመጠበቅ ታክታና ምስጢሩም አልገባ ብሏት ምድር ምድር የምታይና የምትመለከት ልትሆን ግን አይገባትም ለሁልጊዜም አሻቅባና ራስዋን በተስፋ ቃል አንስታ ተመልሶ ሊመጣ ሊወስዳትም ያለውን ኢየሱስን በመጠበቅ ወደ ሰማይ የምታይ መሆን አለባት ይህንን የሚያደርጉ ደግሞ የቤዛነት ምስጢር የገባቸውና በኢየሱስ የዳኑ ፣ የጸደቁ ሰዎች ሁሉ ናቸው ከኢየሱስ የተፋታችውና የቊልቊለቱን መንገድ የተያያዘችዋ ቤተክርስቲያናችን ግን ቤዛዋ ኢየሱስ ብቻ ባለመሆኑ ለዚህ እውነት አልታደለችም ከኢየሱስም ይልቅ አፍዋን ሞልታ ቅድስት ማርያም ቤዛዊተ ኩሉ ዓለም ወደ አማርኛው ሲተረጎም የዓለም ሁሉ ቤዛ ቅድስት ማርያም ሆይ የሚለውን ትርጉም የሚሰጠን ነውና ይህንን ስለምትል ይህ ብቻ አይደለም መስቀል ቤዛዬ የነፍሴም መድኃኒት ነው ፣ ከዚህም ሌላ ኃይሌና ከጠላቴ ከሰይጣንም ነጻ አውጪዬ ነው በማለት ቤዛዋ የሆናትንና ሊሆናትም ያለውን ኢየሱስን ለመጠበቅ ዝግጁ ወይም የተዘጋጀች አይደለችም ከሁሉ በላይ በጣም የገረመኝ ደግሞ ክርስትናን በመቀበልና በትምህርተ ወንጌል ቀዳሚ ሆና ሳለ እርስዋ ግን የኋሊት ተጐትታና የወረደ ነገር ውስጥ ገብታ የቃዡ ፣ የዞረባቸውም ባሕታውያን በየገደሉ ውስጥ የጻፉትን ገድላትና ድርሳናትን የእምነት መመርያዋ አድርጋ በመውሰድ ማርያምና መስቀሉ ቤዛዬ ናቸው ማለትዋ ሳያንሳት ይባስ ብላ የኃጢአታችንን ቤዛ መቃብሩን የሰጠን ተክለኃይማኖት እያለች የተክለኃይማኖትን መቃብር ቤዛዬ ነው ማለቷ ፣ ይህ ብቻ አይደለም እዳሪው ማለትም ተቅማጡን እንኩዋ ሳይቀር እንደ ስቅለቴ ደም እቆጥርልሃለሁ የሚል ቃልኪዳን ጌታ ሰጥቶታልና በማለት ተቅማጥን ከክርስቶስ ደም ጋር አንድ አድርጋ ቆጥራ ለኃጢአቷ ሥርየት እንዲሆን መቀበልዋ ጉድ ከጉድም ጉድ የሚያስብላት ሆኗል ይህንን ጉድ ነው እንግዲህ እኔም ግራ ቢገባኝ ከኢየሱስ ጋር የመፋታትና የቊልቊለቱ መንገድ ያልኩት መቼም ተቅማጥና እዳሪ እንደ ክርስቶስ የስቅለቱ ደም ተቆጥሮ የኃጢአት ይቅርታን ያሰጣል እየተባለ እንደገናም የተክለሐይማኖት መቃብር ቤዛዬ ነውና የመሣሠሉትን ሲባል ተደማምሮ እየተነገረ ይህቺን ቤተክርስቲያን ከኢየሱስ ጋር ነች ከኢየሱስም አልተለያየችም ወይም አልተፋታችም ማለቱ የእናንተን አላውቅም እንጂ ለእኔ ከሆነ ግን ፍጹም ውሸትና ከውሸትም በላይ የሆነ የዲያብሎስ እንዲሁም የጥልቁ ውሸት ነው ብዬ ነው የማምነው ስለዚህ መፋታት ብቻ ሳይሆን ከመፋታትም አልፋ ገልሙታና ወድቃ ተገኝታለች የተወደዳችሁ ወገኖች ይህቺ ቤተክርስቲያን አሁንም ስሕተትዋ እየበዛ መጥቶ በእርሱ በኩል በመስቀሉ ደም ሰላምን አድርጎ በምድር ወይም በሰማይ ያሉትን ለራሱ እንዲያስታርቅ የፈቀደበትን እውነትና ኢየሱስም ይህንን እውነት ለመፈጸም ከሞት በኋላ በመንፈስ ሕያው ሆኖ ሄዶም በወህኒ ለነበሩት ነፍሳት የሰበከበትን ፣ ነጻ ያወጣበትንም እውነት ወደ ጎን በማድረግ ( ቆላስያስ 1 ፥ 19 እና 20 ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 3 ፥ 18 _ 2 )በተክለ ሐይማኖትም ይሁን በክርስቶስ ሰምራ እንዲሁም በድርሳነ ሚካኤል በተጻፉልን የገድላትና የድርሳናት ሃሳብ መሠረት ሊቆጠሩ የሚያቅቱ ነፍሳት ተመርተው ከሲኦል መውጣታቸውን ጽሑፎቹ ይተርኩልናል ስለዚህ ከዚህ የተነሳ ክርስቶስ በምድርም ይሁን በሰማይ ያሉትን ለራሱ እንዲያስታርቅ መፍቀዱ እንደገናም ይሄው ክርስቶስ በመንፈስ ሕያው ሆኖና ሄዶ በወህኒ ለነበሩት ነፍሳት መስበኩ ከእነዚህ ከተጻፉት ገድላትና ድርሳናት አንጻር ተረት ተረትና ቀልድም ነው እያለችን ነው የአሁንዋ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በዚያው መጠን ደግሞ የኦርቶዶክስ ገድላትና ድርሳናት መጻሕፍቱም ትክክለኞቹና ነፍሳትንም ነጻ አውጪዎቹ እኛ ነን እያሉን ይገኛሉ ምን እነርሱ ብቻ የዚሁ የገድላቱና የድርሳናቱ ዋነኛ ሰባኪዎቹም የሚሉን ይህንኑ ነው ነገር ግን አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ በስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ መጽሐፋቸው በገጽ 48 አሁን ላይ መጽሐፍቅዱስዋን ጥላ የገድልና የድርሳናት ተከታይ ለሆንችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንም ሆነ ለዘመኑ የገድላትና የድርሳናት ሰባኪዎች እንዲህ ሲሉ ሙሉ መልስ ሰጡ መልሱም ከዚህ የሚከተለው ነው ይደልወነ ናጽምዕ ቃላተ መለኮት ከመ ኢይባዕ ውስተ አልባቢነ ቃል ነኪር ትርጉም ባዕድ ቃል ወደ ልባችን እንዳይገባ ቃላተ መለኮትን ማድመጥ ይገባናል አሉ ይህ ቃላተ መለኮት የተባለው ደግሞ አሸናፊው የእግዚአብሔር ቃል ነው የሐዋርያት ሥራ 19 ፥ 19 እኚህ አባት ታድያ ዛሬ በሞት የተለዩን ሆነው በመካከላችን ባይኖሩም ትተውልን የሄዱት መጽሐፍና አባታዊ ምክራቸው ግን ለዘላለም ከእኛ ጋር የሚኖር ነው ስለዚህ ከዚህ በኋላ ባለ ዘመናችን እኛም ጠቃሚ በሆነው መጽሐፍቅዱሳዊ ምክራቸው ተጠቃሚዎች ሆነን ወደ ተጻፈልን የመጽሐፍቅዱስ እውነት በመመለስ በመጽሐፍቅዱሱ ቃል ብቻ እንድናምን እግዚአብሔር ይርዳን አሜን ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

Tuesday 13 February 2018

የተቋቋመች ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከአዳኟ ከኢየሱስ የተፋታችበት የቁልቁለቱ መንገድ ...የተቋቋመች ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከአዳኟ ከኢየሱስ የተፋታችበት የቁልቁለቱ መንገድ ( ቊጥር 1) ክፍል አራት የተወደዳችሁ ወገኖች ሰላም ለእናንተ ይሁን የዛሬው ትምህርት ደግሞ ትውልድ የተሰጠውን የእግዚአብሔር እውነት የሚፈልግበትና ጌታ በሰጠው እውነት ላይም እስከ መጨረሻው ቆሞ የሚታገልበት በመሆኑ ይህንንና እነዚህን በመሣሠሉ ትምህርቶች እየተጠቀመ ሊነቃ ሊመረምር በብዙ ሊረዳና ሊገነዘብ ይገባል እላለሁኝ በሐዋርያዊው ሰላማ ከሣቴ ብርሃን የተመሠረተች የመጀመርያዋ ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ቤተክርስቲያን ያቋቋማት ሐዋርያው ሰላማ ከሞተ በኋላ ጥሩ ሁኔታ አላጋጠማትም ከእርሱ በኋላ የተነሱት ሰዎች ጤናማዋን የወንጌል ቤተክርስቲያን ማን ማንን ሊመራ ይችላል በሚል ፉክክር የማን ቤት ጠፍቶ የማን ይበጅ ቀረርቶ ሲሉ ተርተውና በተረታቸውም እርስ በእርሳቸው ሳይቀር ተደባድበው ባለመስማማት ከሣቴ ብርሃን ሰላማን የሾሙት ግብጻውያን ስለሆኑ ግብጻውያን ይምሩን ሲሉ ለግብጻውያን አሳልፈው ሰጧት ግብጻውያንም ለ1600 ዓመታት በጨለማና በባርነት ገዟት ታድያ ሰላማ የመሰረታት ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ቤተክርስቲያን ውድቀቷ የጀመረው ያኔ ነው በዚህም ውስጥ ዘመን መምጣቱ አይቀርምና ዘመን ስለመጣልኝ ነጻነቴን አውጄ ከዚህ ባርነት ወጣሁ ብትልም ነገር ግን አሁንም በዚሁ በባርነቱ ምክንያት ለዓመታት የጣለችውን ወንጌል እንደሚገባ ልታነሳው ያልቻለች በመሆንዋ ዘርዓ ያዕቆብ የተባለው ንጉሥ በ15 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ተነስቶ ይህቺን ያላገገመችና ከቁስልዋም ፈጽሞ ያልተፈወሰችን ቤተክርስቲያን ወደማትፈልገው አቅጣቻ በመምራት ይባስ ብሎ ከአዳኝዋ ከኢየሱስ ለይቶ አፋታት በጅማሬዋና በቅድምና ዘመንዋ በተቀበለችው ጌታ አማካኝነት ወደላይ መውጣት የሚገባትን ይህቺኑ ቤተክርስቲያንም ወደታች አውርዶ የቁልቁለቱን መንገድ እንድትመርጥና በዚያው መንገድ ላይ እየተንደረደረች እንድትወድቅ እንድትንከባለልም አደረጋት የተወደዳችሁ ወገኖች በቪዲዮ የተለቀቀው ትምህርት እንግዲህ ይህንኑ አስመልክቶ የተነገረ ነው በመሆኑም ትምህርቱ ታድያ ቤተክርስቲያንዋ በተመሠረተችበት በቅድምና ዘመንዋ ያመነችው መጽሐፍቅዱሳዊ እውነት ምን እንደሆነ የሚገልጽ ሲሆን ይሄ መጽሐፍቅዱሳዊው እውነት ደግሞ በመጽሐፍቅዱሱ ላይ ሠፍሮ ያለ እውነት ብቻ ሳይሆን ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እስከ ዛሬ ድረስ በምትጠቀምባቸው የቅዳሴ ፣ የሰዓታት ፣ የዚቅ ፣ የድጓ እንዲሁም የሃይማኖተ አበው እና የመሣሠሉት መጻሕፍት ውስጥ በትክክል ተጽፎና ሰፍሮ የሚገኝ ነው ይሁን እንጂ እነዚህን የመሠሉ የቃሉ እውነቶች በበተክርስቲያን መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈውና ሰፍረው ቢገኙም ደፋሩ ዘርዓያዕቆብ ግን ለእነዚህ ተጽፈው ላሉ እውነቶች ቦታ ባለመስጠት ሥልጣኑን ተገን አድርጎ እንደ ተአምረ ማርያም ያሉ የወንጌሉን እውነት የሸፈኑ የጨለማ መጻሕፍትን በመጻፍ ከዚህም ሌላ መጻሕፍትን በማያውቁ ፣ ቅዠት ናላቸውን ባዞረውና በተወናበዱ የዋሻ ፣ የገድል ነዋሪ ባሕታውያን የተጻፉ ገድላትና ድርሳናትን በመሰብሰብ ምን የመሰለችዋን ኦርቶዶክሳዊት የወንጌል ቤተክርስቲያን እስከዛሬ ድረስ የአሮጊቶች ተረት መከማቻና መጠራቀምያ አደረጋት ቅዱሳን ወገኖቼ ትምህርቱ በስፋት የሚጠቁመን አሁንም ይህንኑ እውነት ነው ታድያ ተጨባጭ የሆነውን ይህን እውነት ለሕዝባችን ለመስጠት እያንዳንዱን ሃሳብ በጥልቀት በተናጠልና በዝርዝር የምናይበት ትምህርት ስለሆነ ሰፊ ትንታኔ ለመስጠት በዚህ አርዕስት ዙርያ ለተወሰኑ ጊዜያቶች እንቆያለንና በማስተዋል እንድትከታተሉ ጥሪዬን ለእናንተ ለወገኖች በፍቅር ማስተላለፍ እወዳለሁ ግንዛቤያችሁ ይበልጥ እንዲጨምር ግን ይህንኑ የተለቀቀውን ቪዲዮ ደግማችሁ ስሙት ጌታ ዘመናችሁን ይባርክ ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

Monday 5 February 2018

በከሣቴ ብርሃን አባ ሰላማ የተቋቋመችው የመጀመርያዋ ኦርቶዶክሳዊት ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ኅብረት ያለፈችባቸው መ...በከሣቴ ብርሃን አባ ሰላማ የተቋቋመችው የመጀመርያዋ ኦርቶዶክሳዊት ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ኅብረት ያለፈችባቸው መንገዶች ክፍል ሁለት የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሰላም ለእናንተ ይሁን ትምህርቱ በእግዚአብሔር ጸጋና እርዳታ በእናንተም በቅዱሳኑ ጸሎትና እገዛ ቀጥሎ ዛሬ የክፍል ሁለትን ትምህርት ይዤ ቀርቤያለሁ ቤተክርስቲያን ሁልጊዜ በክርስቶስ ላይ የተመሠረተች በምትሆንበት ጊዜ ለሁል ጊዜም ትፈተናለች ይሁን እንጂ የተመሠረተችበት ዓለቱ ጽኑ ስለሆነ አትወድቅም እንደገናም የገሃነም ደጆች አይችሏትም በሰላማ ከሣቴ ብርሃንም ጊዜ የተመሠረተችው ቤተክርስቲያን በሐዋርያዊው አባ ሰላማ የተቋቋመች ቤተክርስቲያን ብትሆንም የተመሠረተችው በክርስቶስ ላይ እንጂ በሐዋርያዊው አባ ሰላማ ላይ ባለመሆኑ ባለፈችባቸው መንገዶች ሁሉ መሠረትዋ የሆነው ጌታ በሌላ አነጋገር በራሱ ላይ የመሠረታት ኢየሱስ ባለ ድል አድርጎአታል ( የማቴዎስ ወንጌል 16 ፥ 15 _ 19 ) ትምህርቱን በሰፊው በተለቀቀው ቪድዮ በኩል ስለምትከታተሉት ታሪኩን መድገም አያስፈልገኝም ነገር ግን የታሪኩን ዳራና ጠቅለል ያለውን መልዕክት በአጭሩ ለማስታወስ ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ክርስቲያኖች በነበሩት ነገሥታት ብርታትና በሕዝብዋም ጠንካራ ከሆነው መጽሐፍቅዱሳዊ እውቀት የተነሣ ከቄሣር ቁንስጣ የተላከውን መልዕክት ያልተቀበለችና በፍሬምናጦስ አባ ሰላም ምትክ መንፈሳዊ መሪዋ ሊሆን ተልኮ የመጣውን አርዮሳዊ እና ሕንዳዊ ቴዎፍሎስን አሳፍራ የመለሰች ነበረች ይህንንም ያደረገችው ከቃሉ የመረዳት ጉልበት ጭምር ብቻ ሳይሆን ከሮማ ቄሣሮች ተጽዕኖ ሳይቀር ነጻ በሆነ ጥላ ሥር ስለነበረች ጭምር ነው ታድያ ይህንን የአርዮስ ትምህርት ተቀብላ ቢሆን ኖሮ እንደገና ዘመን መጥቶ በእስክንድርያው መሪ በቴዎዶስዮስ ዘመነ መንግሥት ፈጽሞ የተወገዘውን ኑፋቄ አርዮስን ከአዕምሮዋ አስወጥቶ በምትኩ ታድሶ የጸናውን የኒቅያን የእምነት መግለጫ ( ጸሎተ ሃይማኖትን ) ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት እንድትቀበል የማድረግ ዕድሉ የመነመነ በሆነ ነበር ስለዚህ በደገኛው ሐዋርያዋና መሪዋ ፍሬምናጦስ በተሰኘው አባ ሰላማ ብርታትና አርቆ አስተዋይነት ቀደም ብላ የኒቅያን የእምነት መግለጫ እንደ እግዚአብሔር ቃል በሆነ መረዳት ድቅቅ አድርጋ በመማርዋና በመገንዘብዋ በኋላ ላይ በለሰለሰ መንገድ በአታላይነት ሊገባ የሞከረውን አርዮሳዊ ኑፋቄና መልዕክተኛውን ቴዎፍሎስን በመጡበት አኳኋን መመለስ እንድትችል አድርጓታል ይህ ብቻ አይደለም ለወደፊቱም ትምህርተ መለኮትዋን በመልካም ጐዳና ለመምራት ያስቻላትን ዕድልና ጸጋ በቸርነቱ እንደሰጣት ያረጋግጥልናል እኔም ታድያ ከዚህ ትምህርት የተነሳ ሳላመሰግናቸው የማላልፋቸው አንድ እውነተኛ አባቴና መንፈሳዊ መሪዬ የነበሩ ስላሉ በቀድሞ ስማቸው ሊቀ ሥልጣናት አባ ሃብተ ማርያም ሊቀ ጵጵስናን ከተቀበሉ በኋላ ደግሞ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የተባሉትን አባት ሳላመሰግን አላልፍም እኚህ አባት እኔ በነበርኩበት ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የትምህርት ቤታችን ዲን ነበሩ በጣም ተራማጅና መጽሐፍቅዱሳዊ አስተሳሰብ የነበራቸው በመሆኑ ያደረጉብን ብዙ የብዙ ብዙ በጎ ተጽእኖዎች ነበሩ እያንዳንዱን አሁን ዘርዝሬ አልጨርሰውም ነገር ግን ዋናውና ትልቁ በጎ ተጽዕኖ የእምነት መግለጫችሁንና ማብራርያውን ከነ ጥሬ ንባቡ እንዲሁም የቃሉ ትርጉም ጋር በቃላችሁ አጥኑ ይሉን ነበር ፈተናውም የሚመጣው ከዚሁ የእምነት መግለጫ ነበረና ይህንን ፈተና ያላለፈ ከበድ ያለ እርምጃ ይወሰድበት ስለነበር እኛም ታድያ እርሳቸውንም ሆነ የሚወስዱብንን እርምጃ ስለምንፈራ አልጋችንን ለቀን የምንማርበት የክፍል ወለል ላይ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ቁጭ ብለን እናጠና ነበር በጊዜው የነበረው የአባታችን ጭካኔ ያማረረንና የክፍል ወለል ላይ ያሳደረን ቢሆንም አሁን አሁን ላይ ሳስበው ለአባታችን ዕድሜ ዘመን ይጨመርልዎ እርስዎ የሚያውቁት ምስጢር ስላለ ነው እንዲህ ጠንክረን የእምነት መግለጫችንን እንድናጠናና እንድናውቅ ያደረጉን በማለት ልባርካቸው ወደድኩ አባታችን ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ እውነተኛ አባታችንና የወንጌል መምህራችን ኖት ትላንት ለማጥናት በከፈልነው ዋጋ ብንከፋም ዛሬ ላይ ጠንክረው በወሰዱት እርምጃ ያስጠኑን የእምነት መግለጫ የትም ሳንሄድ በእምነታችን መሠረት ላይ እንድንተከልና ሌላውንም እንድንተክል ያስቻለን በመሆኑ ዕድሜና ዘመንን ይጨምርልዎ ብድራትዎትንም በላይ በሰማይ እግዚአብሔር ይክፈልዎት ተባረኩልኝ በማለት ላመሰግንዎት እወዳለሁ የተወደዳችሁ ወገኖች ለዚህ ነው እንግዲህ እንዴት እንደተቀበልክና እንደ ሰማህ አስብ ጠብቀውም ንስሐም ግባ በማለት በትምህርቴ ማጠቃለያ ላይ የገለጽኩት ( ራዕይ 3 ፥ 3 ) እንዴት እንደተቀበለና እንደ ሰማ ያወቀ ሰው የተቀበለውንም እንዴት እንደሚጠብቅ ያውቃልና በቀላሉ ለስሕተት ትምህርት የተጋለጠ አይሆንም ከዚህም ሌላ ለሚጠይቁት ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጀ ነው 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3 : 15 ታድያ ለዛሬዋም ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ያለኝ መልዕክት የተቀበለችውና እየተቀበለች ያለው መልዕክት ከማን መሆኑን እንድትረዳ እንዴት እንደተቀበለች ማወቅ ይኖርባታል የሚል ነው ጌታ ያልሰጣትን ይዛ ወይም ተቀብላ ከሆነ ደግሞ ብትጠለው ፈውሷ ይበዛል እንጂ አትጎዳም የሚል መልዕክት አስተላልፋለሁ ከዚህ በመለስ ደግሞ ቪዲዮውን ደግማችሁ ስሙት ትባረኩበታላችሁ ጌታ ዘመናችሁን ይባርክ ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

Friday 2 February 2018

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አመሠራረት ( ክፍል አንድ ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አመሠራረት ( ክፍል አንድ ) የተወደዳችሁ ወገኖቻችን እንዴት ናችሁ ተባረኩ ይህንን ትምህርት ዛሬ ለእናንተ አንድ ብለን ጀምረነዋል የምንወዳት አንጋፋዋ ኦርቶዶክሳዊትና ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያናችን በ325 ዓመተ ምሕረት የመጀመርያው ሐዋርያችን በሆነው ፍሬምናጦስ ተብሎ በቀዳሚነት በተጠራውና አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን በተባለው ሰው ነው የተቋቋመችው ይህ ሰው ክርስትናን ከእስክንድርያ ይዞልን ሲመጣ የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት ያደረገ ክርስትናና የእምነት መግለጫንም ጭምር ይዞልን የመጣና በዚሁ መሠረትም ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት የምትለዋን ማኅበር ወይንም ቤተክርስቲያን ያቋቋመ ነው ታድያ ቤተክርስቲያንም ሆነ የቤተክርስቲያንን የእምነት አቋም የሚገልጸው የእምነት መግለጫ መሠረቱ የእግዚአብሔር ቃል ሲሆን ቤተክርስቲያን የገሃነም ደጆች የማይችሏት ጠንካራ ትሖናለችና ሥራው ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሰው በጣም አስደሳች ነው የሚሆነው የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የእምነት ሐዋርያችን አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ያደረገው እንግዲህ ይህንን ነው እንደ ዛሬው ዘመን አገልጋዮች ደርሶ ቤተክርስቲያንን የተከለና ስምም ያወጣ አይደለም ቅድሚያውን ይዞ ከዓለም አቀፍዋ ቤተክርስቲያን መሪ ከ20ኛው ፓትርያርክ ከሐዋርያው አትናቴዎስ የኤጲስቆጶስነትንና የሐዋርያነትን ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ይኸው አትናቴዎስ 27 የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሲል በቃለ ቡራኬ የደነገገበትን ውሳኔ በመቀበል 27 ቱን የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትና 39ኙን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በአንድ ላይ አስተባብሮ ይዞ በመምጣት በዚህ በእግዚአብሔር መንፈስ በተጻፉ 66 ቱ ቅዱሳት መጻሕፍት አማካኝነት ወንጌልን ነገሥታት ጓዳ ድረስ በመግባትና በመስበክ ማኅበሩን ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት በማለት የመሠረተ ብቻ ሳይሆን እምነቱንም በመንግሥት ደረጃ ሳይቀር ታውጆና ብሔራዊ ሃይማኖት ሆኖ በመንግሥት ሰነድም ጸድቆ የደርግ መንግሥት እስከ ተሻረበት ዘመን ድረስ ምድሪቱ የክርስቶስ እንድትሆን ያደረገ ታላቅ የቤተክርስቲያን ባለ ውለታና ለእኛም ምሳሌ የሆነን የእምነት ሐዋርያ ነው ይህ ሰው ሰው ይህንን ሁሉ ወደ ማድረግ የመጣው ትክክለኛውን 66 ቱን ቅዱስ መጽሐፍ ማለት መጽሐፍቅዱስን አምኖና ተቀብሎ የአገልግሎቱም መሠረት አድርጎ ስለተነሳ ነው ለዚህም ነው በዚህ በተሃድሶ አገልግሎት ከ50 ዓመት በላይ በአገልግሎት የገፉና ዛሬ በመካከላችን በሕይወት የሌሉ መጻሕፍቶቻቸውና ሥራዎቻቸው ግን ዛሬም ድረስ ሕያው ሆኖ ማንነታቸውን እየገለጸ ያለ ታላቁ ሊቅ አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ በስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ መጽሐፋቸው ላይ ከዓለም አቀፋዊቷ ቤተክርስቲያን ሐዋርያና ከእስክንድርያው ፓትርያርክ አትናቴዎስ በሐዋርያችን አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን አማካኝነት ሲያያዝ መጥቶ እኛ ጋር የደረሰው ይሄ እምነት መሠረቱ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ጠንቅቀው ያወቁና የተረዱ በመሆናቸው እንደገናም ቤተክርስቲያኒቱን ዛሬም ላይ ቢሆን ወደ መሠረቷ ሊመልሳት የሚችለው ይኸው የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ስለተገነዘቡ ፦ በሃይማኖተ አበው ያለ የዮሐንስ አፈወርቅን ሃሳብ በማንሳት ይደልወነ ናጽምዕ ቃላተ መለኮት ከመ ኢይባዕ ውስተ አልባቢነ ቃል ነኪር አሉን ትርጉም ባዕድ ቃል ወደ ልባችን እንዳይገባ ቃላተ መለኮትን ማድመጥ ይገባናል ሲሉ ሃይማኖተ አበው ላይ በሠፈረው የአባቶች መጽሐፍ ከመከሩን በኋላ ባዕድ ቃል ያሉበትን ሃሳብ ሊያብራሩልን ስለፈለጉ ደግሞ እንዲህ አሉን ያለንን በመገንዘብ በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ተወስነን ከቊርዓንና እነርሱንም ከሚመሳስሉ ልዩ ልዩ የልብ ወለድ መጻሕፍት እምነት እንርቃለን በማለት ተናገሩ ( ምንጭ ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ ገጽ 48 ) መልዕክቴን ስጠቀልለው በእምነታችን ተመሥርተንና ጸንተንና እስከ መጨረሻውም ኖረን በፊቱ ለመቆም አለቃ መሠረት በመጽሐፋቸው ላይ አሁን ድረስ እንደነገሩን ቃላተ መለኮትን በማድመጥ መኖር ይሁንልን ታቦቱም በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠበት ቀን ጀምሮ ወራቱ ረዘመ፥ ሀያ ዓመትም ሆነ፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ አዝኖ እግዚአብሔርን ተከተለ መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 7 : 1 እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፦ በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ …..ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ንጉሥን ለፈለጉ ሕዝብ ነገራቸው ( ሳሙኤል ቀዳማዊ 8 : 7 ,10 ) ሕዝቡ ግን የሳሙኤልን ነገር ይሰማ ዘንድ እንቢ አለ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይሁንልን እኛም ደግሞ እንደ አሕዛብ ሁሉ እንሆናለን፤ ንጉሣችንም ይፈርድልናል፥ በፊታችንም ወጥቶ ስለ እኛ ይዋጋል አሉት ሳሙኤልም የሕዝቡን ቃል ሁሉ ሰማ፥ ለእግዚአብሔርም ተናገረ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፦ ቃላቸውን ስማ፥ ንጉሥም አንግሥላቸው አለው ( መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 8 : 10 , 19 - 22 ) ሕዝቡም ሁሉ ሳሙኤልን፦ ንጉሥ በመለመናችን በኃጢአታችን ሁሉ ላይ ይህን ክፋት ጨምረናልና እንዳንሞት ስለ ባሪያዎችህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉት ( መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 12 : 19 ) ሳሙኤልም ሕዝቡን አለ፦ አትፍሩ በእውነት ይህን ክፋት ሁሉ አደረጋችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ አምልኩት እንጂ እግዚአብሔርን ከመከተል ፈቀቅ አትበሉ ምናምንቴ ነውና የማይረባንና የማያድን ከንቱን ነገር ለመከተል ፈቀቅ አትበሉ ( መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 12 : 23 ) ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች አለ ( የሐዋርያት ሥራ 3 : 23 ) ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን