Thursday 20 July 2017

የኢየሱስ አማላጅነት ክፍል አራት የኢየሱስ አማላጅነት ክፍል አራት የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሰላም ለእናንተ ይሁን በክፍል አራት ትምህርታችን የምንመለከተው አሁን ላይ ባላችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ሦስት ዓይነት ሰዎች አሉ እነርሱም ፦ 1ኛ ) የኢየሱስን አማላጅነት ጨርሰው የሚክዱ 2ኛ ) ኢየሱስ ያማለደው እስከ መስቀል ሞት ድረስ ብቻ ነው ከዚያ በኋላ ግን በአባቱ ቀኝ በጌትነቱ ስለተቀመጠ አያማልድም የሚሉ አሉ መከራከርያ ጥቅሳቸው ደግሞ ዕብራውያን 5 ፥ 7 ሲሆን እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋራ ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ እግዚአብሔርንም ስለመፍራቱ ተሰማለት እያለ የሚቀጥል ነው 3ኛ ) ሦስተኛዎቹ ደግሞ ኢየሱስ አሁንም ስለ እኔ ይማልዳል ብለው የሚያምኑ ናቸው ዕብራውያን 7 ፥ 23 _ 25 ታድያ ይህንን መጠይቅ ወደ እያንዳንዳችን ስመልሰው ከእነዚህ ከሦስቱ መካከል እኛ በየትኛዎቹ ጎራ ነን ? መልሱን ለእናንተ ለአንባቢዎችና ለትምህርቱ ተከታታዮች እተወዋለሁ በእኔ በኩል ግን ለትምህርቴ ተከታታዮች እንደ ተጻፈልን እንደ እግዚአብሔር ቃል ለማስተላለፍ የምፈልገው ሰዎች ሁሉ ከዚህ የትምህርት ግርታና ግራ መጋባት ውስጥ ጨርሰው እንዲወጡ ፦ 1ኛ ) ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ እንዲያምኑ ( ሮሜ 9 ፥ 1 _ 5 ) 2ኛ ) ክርስቶስ በሥጋ ከድንግል እንደተወለደ አውቀው ወላዲተ አምላክ የሚለውን የእምነት አስተሳሰብ ወላዲተ ኢየሱስ በሚለው እንዲተኩ ወይንም እንዲለውጡ ( ምንጭ ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ ሠረቀ በሥጋ እምድንግል ዘእንበለ ዘርዓ ብዕሲ ወአድኀነነ ትርጉም እንበለ ዘር ማለትም ያለ ወንድ ዘር ክርስቶስ ከድንግል በሥጋ ተወለደ የሚለውን ትርጉም የሚሰጠን ነው የሰኞ ውዳሴ ማርያም ) 3ኛ ) ክርስቶስ በሥጋ እንደ ሞተ እንያዲምኑ ( 1ኛ ጴጥሮስ 3 ፥ 18 ) 4ኛ ) በሦስተኛውም ቀን ሲነሳ በሥጋውም ጭምር የተነሳ አምላክ ነው እንጂ ሥጋውን ጥሎ የተነሳ አምላክ አለመሆኑን እንዲያውቁ እና እንዲያምኑ ይህንንም የምንረዳው ሀ ) ቶማስን፦ ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን ማለቱ ከዚህ የተነሳ ቶማስም ጌታዬ አምላኬም ብሎ መመለሱ ኢየሱስም ስላየኸኝ አምነሃል ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው ማለቱ ( ዮሐንስ ወንጌል 20 ፥ 26 _ 31 ) ለ ) እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ ከማር ወለላም ሰጡት ተቀብሎም በፊታቸው በላ ይለናልና ይህንን ማድረጉ ( የሉቃስ ወንጌል 24 ፥ 36 _ 43 ) ሐ ) ከዚያም መልስ 40 ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነገር እየነገራቸው በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን ማሳየቱ ( የሐዋርያት ሥራ 1 ፥ 3 ) መ ) ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ ማለቱ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ መቀበሏ ( የሐዋርያት ሥራ 1 ፥ 9 ) ሠ ) ከዚህም ሌላ መላዕክት በድምጻቸው እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለምን ቆማችኋል ? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት እንዲሁ ይመጣል ማለታቸው ( የሐዋርያት ሥራ 1 ፥ 10 እና 11 ) ረ ) ይህንንም ሁኔታ ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስቀድሞ መናገሩ ነገር ግን እላችኋለሁ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው በዚያን ጊዜ ሊቀካህናቱ ልብሱን ቀዶ ተሳድቦአል እንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለምን ያስፈልገናል ? እነሆ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል ምን ይመስላችኋል ? አለ ይለናል ( የማቴዎስ ወንጌል 26 ፥ 62 _ 68 ) በዚህ ቃል መሠረትም ይህ ሊቀካህናት ብቻ ሳይሆን ዛሬም የኢየሱስን በአምላክነቱ ብቻ ሳይሆን በሰውነቱም ጭምር በኃይል ቀኝ መቀመጥና በሰማይ ደመና መምጣት የሚያሳምማቸው የዘመናችን አውጣኪ ሊቃነ ካህናት ልብሳቸውን መቅደዳቸው የማይቀር ዕዳ ሆኖባቸዋል ስለዚህ ባገኙት የፌስቡክ ድኅረ ገጾች ሁሉ ኢየሱስ በአምላክነቱ ብቻ ሳይሆን በሰውነቱም ጭምር የሰራውንና የሆነውን ነገር በሰሙ ቁጥር ሲቆጡ ፣ ሲሳደቡና ከበዛው ብስጭታቸውም የተነሳ ልብሶቻቸውን ሳይቀር ሲቀዱ እነርሱም ሲቀደዱ እናያቸዋለን ደግሞም እንሰማቸዋለን ለዚህ ሁኔታቸው የምንሰጣቸው መልስም ከሰሙን!! እኛ ሳንሆን እውነቱን የገለጠው የመጽሐፍቅዱሱ ቃል ነውና ሳትበሳጩ ፣ ሌላም ሌላም ደረጃ ላይ ሳትደርሱ ከመጽሐፉ ሃሳብ ጋር በጊዜ ተስማሙ ነው የምንላቸው ኢየሱስ በሰውነቱም ጭምር ወደ ሰማይ መውጣቱ ፣ ማረጉና በአብ ቀኝ መቀመጡ በአምላክነቱ ለመቀመጥ ብቻ ሳይሆን ለአስታራቂነትና ለአማላጅነትም ጭምር ነው ይህንንም የዕብራውያን ጸሐፊ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል ፦ _ ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀካህናት አለን እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት ( ዕብራውያን 8 ፥ 1 እና 2 ) ታድያ በዚህ ቃል መሠረት ለእኔስ እንዲህ ያለ ሊቀካህናት የለኝም የሚል ሰው ካለ የለኝም ያለው ለራሱና ራሱ ስለሆነ ምርጫው ነውና መብቱ ነው እንላለን ቃሉ በተገለጠለት ጊዜ ግን ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀካህናት ለእኔም አለኝ ማለቱ አይቀርምና አሁን ላይ ባለው ነገሩ ቃሉን በፍቅር እንነግረዋለን እንጅ ልናስጨንቀውም ሆነ ልናስገድደው አንፈልግም _ በዕብራውያን 7 ፥ 26 ላይ ደግሞ እንዲህ ያለ ሊቀካህናት አለን ብቻ ሳይሆን ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀካህናት ይገባናል እያለ ሊቀካህናቱ ይገባናል የተባለበትን ዝርዝር ሁኔታ በጥልቀት ያስረዳል ( ዕብራውያን 7 ፥ 26 _ 28 ) ስለዚህ እኛ የሰው ልጆች ዛሬ ክርስቶስ በሰውነቱም ጭምር የመነሳቱን ፣ የማረጉን ፣ በአብ ቀኝም የመቀመጡንና የማማለዱን ጭምር ክደን እንዲህ ያለ ሊቀካህናት የለኝም ፣ አያስፈልገኝምም ከምንል ይልቅ አለኝ ያስፈልገኛል ማለቱ አማራጭ የሌለው ውሳኔያችን ቢሆን በበለጠና በተሻለ ሁኔታ ይህ ውሳኔያችን ደግሞ ደኅንነታችንን ሙሉ እና እርግጠኛ ያደርገዋል እንጂ የሚጎድልብን ነገር የለም አባቶችም በትምህርታቸው አያይዘው ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ ሊያሳዩን ፦ ዳግመኛ በችንካር በጦር የቆሰለውን የእኛን መከራ ተቀበለ አሉን ( ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 2 ፥ 6 _ 7 ) ቅዱስ ባስልዮስም " የሁሉ ፈጣሪ እንደ እኛ ያለ ሞትን በሥጋ ሞቶ ለሰው ሁሉ ሕይወትን ሰጠ " በማለትም ነገረን ( ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 15 ፥ ቁጥር 2 _ 3 ) ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ ከመንፈስቅዱስ የተነሳ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ ሲል የቅዳሴው መጽሐፍ ደግሞ ተናገረን ( ቅዳሴ ሠለስቱ ምዕት ቊጥር 5 እና 6 ) ውድ ወገኖቼ ሆይ እዚህ ላይ ሃይማኖተ አበውንም ሆነ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴን መረጃዎች ማቅረቤ እነዚህን መጻሕፍት በመጽሐፍቅዱሳችን ከተጻፈው ቃል ጋር እኩል ሥልጣን ለመስጠትና እነዚህም መጻሕፍት የመጽሐፍቅዱስ ያክል ሥልጣን ያላቸው ናቸው ለማለት ብዬ ሳይሆን ቤተክርስቲያኒቱ ከዚህ በፊት በነበረው ዘመኗ የእውነትን ቃል የተቀበለችና የምትሠብክ መሆኑን እነዚህ መጻሕፍቶችዋ የሚጠቁሙ በመሆናቸው ወደ ትክክለኛው የመጽሐፍቅዱሱ ቃል እውነት እንድትመለስ ለመርዳት ነው በመጨረሻም ልል የምፈልገው ከመጽሐፍቅዱሳችንም ሆነ ከአባቶች ትምህርት በመነሣት ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የሚታመን መንፈስ ከእግዚአብሔር ነው ስለሚል ከእነዚህ እውነቶች የተነሣ እኔና እናንተም ስለ ክርስቶስ ያለንን መረዳት አስተካክለን ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ በመታመን ከእግዚአብሔር ልንሆን ይገባል 1ኛ ዮሐንስ 4 ፥ 1 _ 6 አለበለዚያ ግን ክርስቶስ ኢየሱስ በሥጋ እንደመጣ ካልታመንን የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ያገኘናል በምትኩም ከእግዚአብሔር መሆናችን ይቀርና ከሰይጣን እንሆናለ ለዚህም ነው ዮሐንስ በመልዕክቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ነው ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል አሁንም እንኳ በዓለም አለ ያለን ቸሩ መድኃኔዓለም ጌታ ከዚህ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ይጠብቀን መረዳታችንንም አስተካክሎ ፣ እኛም የእውነቱንና የስሕተቱን መንፈስ በዚሁ በተገለጠው ጌታ አውቀን በዚህ በትክክለኛውና በተገለጠው እውነተኛ ቃል ጌታ እግዚአብሔር ይምራን ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ God bless u all http://www.Facebook.com/yonas.asfaw.39 https://www.youtube.com/yF76GIi_rCQ yonasasfaw8@gmail.com

No comments:

Post a Comment