Thursday, 11 May 2017

ታቦትን ተሸክሞ ማውጣት የቀረው መቼ ነው 2ኛ ዜና መዋዕል 35 ፥ 3 — 6 ክፍል አስራ ሁለትታቦትን ተሸክሞ ማውጣት የቀረው መቼ ነው እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት ለእግዚአብሔርም ለተቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አለ ፦ " ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ሸክም አይሆንባችሁም " …………………. 2ኛ ዜና መዋዕል 35 ፥ 3 — 6 ክፍል አስራ ሁለት የተወደዳችሁ ወገኖች ሰላም ለእናንተ ይሁን ዛሬ በክፍል አስራሁለት የተማማርነውን እንደሚከተለው በአጭሩ ለማብራራት እወዳለሁ የትምህርቱ ርዕስ ታቦትን ተሸክሞ ማውጣት የቀረው መቼ ነው ? የሚል ነው የሰሎሞን ቤተመቅደስ እስኪሠራ ድረስ በእርግጥም ታቦቱ ከቦታ ቦታ ይዘዋወር ነበር ነገር ግን ፦ 1ኛ ) ቤተመቅደሱ ተሠርቶ ታቦቱ ወደ ቤተመቅደሱ ከገባ በኋላ ግን ካህናቱ ታቦቱን ተሸክመው ስለመውጣታቸው መጽሐፍቅዱስ አይናገርም 2ኛ ) እስራኤል ጠላት በበረታባቸው ጊዜ ጠላትን ለማሸነፍ ካህናት ታቦቱን ተሸክመው እንዲያወጡ የሚል ሕግ የለም 3ኛ ) በመጽሐፍቅዱሳችን ቃል መሠረት የተሰቀለው አምላክ መከበሩና መንገሡ ቀርቶ በየጊዜው ታቦት ወጣ እየተባለ ታቦቱ ብቻ ነገሠ ከበረ ሕዝቡም ወደ አምልኮ ባዕድ ኮበለለ መባሉ ትልቅ ነቀፋ ነው ለዚህም ነው 1ኛ ቆሮንቶስ 12 ፥ 1 _ 3 ፤ ገላትያ 4 ፥ 8 _ 11 የተጻፈልን ታድያ ለእነዚህ መጽሐፍቅዱሳዊ እውነታዎች ኦርቶዶክሳውያን አማኞች የሚሰጡት ምላሽ አለና እስቲ መልሶቻቸውን እንዲሁም የሚያቀርቡትን ሃሳብ እንመልከት 1ኛ ) በዔሊ ዘመን ፍልስጥኤምን ለመዋጋት የወጣውን ታቦት እንደገናም በኢያሱ ዘመን ታቦቱን ይዞ በመጓዝ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ለመውረስ የነበረውን የጉዞ ሂደት በመጥቀስ በብሉይ ኪዳን በእግዚአብሔር ቸርነትና ትዕዛዝ ካህናቱ ታቦቱን ተሸክመው እንዲወጡ ተደርጎ ካህናቱም ታቦታቱን ተሸክመው በመውጣት በታቦቱ ያደረ ኃይለ እግዚአብሔር ፣ ለእስራኤል ሕዝብም ያደረገውን ድንቅ ሥራ ለማሰብና እግዚአብሔርን ለማመስገን ነው ታቦት የምናወጣው ይላሉ ይህ ግን ሙሉ መልስ አይሆንም ለምን ስንል በዔሊም ዘመን ይሁን በኢያሱ ዘመን የወጣው ታቦት ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩና በጉዞ ላይ እያሉ የወጣ ታቦት ነው ወጣ ቢባል እንኳ ይህ የሆነው ወደ ሰሎሞን መቅደስ ከመግባቱ በፊት የሆነ ነው በመሆኑም እስራኤል በሰሎሞን ዘመን በመቅደሱ ያስቀመጡትን ታቦት እንዳላወጡት ሁሉ እኛም በጦርነት ኃይለኞች ለመሆንም ይሁን በዓል አድርገን ለማንገስ የምናወጣው ታቦት የለም እንደገናም ዛሬ ላይ በሐዲስ ኪዳን ዘመን እየኖርን በአንድ ልደታ በሦስት በዓታ በአምስት አቦ እያልን ቀንና ወርን መድበን ታቦት እንድናወጣ የሚመሠክርልንምንም ዓይነት መጽሐፍቅዱሳዊ ማስረጃ የለንም የሐዲስኪዳኑ ለሁልጊዜም የምናወጣው ታቦታችን ኢየሱስ ነውና 2ኛ ) ከባዕድ አምልኮ የተለየን ነን ለማለት ታቦትን በማውጣት ረገድ ዛሬ ላይ በሐዲስ ኪዳን ታቦት የምናወጣው ለሥጋውና ለደሙ የክብር ዙፋን እንዲሆንና ስሙ የተጻፈበትም ቅዱስ ታቦት ስለሆነ ስግደትና አምልኮ ለመስጠትም ነው ከዚህም ባሻገር በታቦቱ ረቂቅ ኃይሎች በማስተላለፍ በረከቱን ያበዛልናል ይላሉ ለዚህም መጽሐፍቅዱሳዊ መልስ በቪዲዮ ተሰጥቶበታልና ትምህርቱን ያድምጡ ትምህርቱ በብዙ ማብራርያዎች የታገዘ ስለሆነ በእነዚህ ሃሳቦች ብቻ የተጠቃለለ አይደለም ስለዚህ ሰፊውን ግንዛቤ ለማግኘት አሁንም በቪዲዮ የተለቀቀውን ትምህርት እንድታዳምጡ ግብዣዬ ነው የዛሬው ትምህርት ያላለቀ በመሆኑ በቀጣዩ የሁለተኛው ክፍለጊዜ ትምህርት ይጠቃለላል እስከዚያው የጌታ ጸጋና ሰላም ከእናንተም ከእኔም ጋር ይሁን በማለት የምሰናበታችሁ ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ http://www.Facebook.com/yonas.asfaw.39 yonasasfaw8@gmail.com

No comments:

Post a Comment