Sunday 1 March 2020

"የቅዳሴ ማርያምን ዜማ የደረሰው ቅዱስ ያሬድ አይደለም" አቡነ መልኬጼዲቅ
"የቅዳሴ ማርያም መግቢያ አንድምታ ተረት ተረት ነው" አቡነ መልኬጼዲቅ



የአቡነ መልኬጼዲቅ እብደት - ለሊቀጳጳሱ ጸልዩላቸው!
------------------------
"የቅዳሴ ማርያምን ዜማ የደረሰው ቅዱስ ያሬድ አይደለም" አቡነ መልኬጼዲቅ
"የቅዳሴ ማርያም መግቢያ አንድምታ ተረት ተረት ነው" አቡነ መልኬጼዲቅ
"ቅዳሴ ላይ አሓዱ አብ ከተባለ በኋላ መውጣት መግባት ይቻላል:: ቅዳሴው ገና አልተጀመረም"
"ቅዳሴ መሃል ላይ ከቅዱስ በኋላ የሚባለው ኪዳን ይውጣ:: ቅዳሴውን በ15 ደቂቃ ያሳጥርልናል"
"ቅዳሴ ሓዋርያትን የጻፉት ሓዋርያት አይደሉም:: ውሸት ነው" አቡነ መልኬጼዲቅ
ብዙው ኦርቶዶክሳዊ ምዕመን ሰሞኑን የውጭው ሲኖዶስ ጸሓፊ የሆኑት አቡነ መልከጼዲቅ ( የቀድሞው ሊቀ ስልጣናት ሃብተማርያም ወርቅነህ) ስለ ኦርጋን በሰጡት ትምህርት ግራ ተጋብቶ
" ሊቀጳጳሱ ምን ነካቸው" ሲል መክረሙ ይታወሳል:: በርካታ ምዕመናንና ካህናትም ለሊቀጳጳሱ ኦርጋንን በተመለከተ ላቀረቡት እንግዳና ሓዲስ ትምህርት የማያዳግም ምላሽ ሰጥተዋቸዋል:: እጅግ በርካታ ሕዝብም ቁጣውን አሰምቷል:: ሊቀጳጳሱም በበኩላቸው " ይህን የሚያስተባብርብኝ ማኅበረ ቅዱሳን ነው እንጂ ኦርጋን የተፈቀደ ነው" በማለት ማኀበሩ ላይ ዘመቻ ከፍተዋል:: በመላው ዓለም የሚገኙ ወዳጆቻቸው ባዘጋጁት የቴሌ ኮንፈረንስ ላይም ይገኙ ዘንድ ጋብዘዋል:: ሰራዊቶቻቸው ማኅበረ ቅዱሳን ላይ የስድብ ናዳ ለማውረግ " ክተት ሰራዊት" ላይ ናቸው::ዘመቻ ኦርጋን::
እንደኔ ግን አቡነ መልኬጸዲቅ የተዋህዶን ሃይማኖት በመሸርሸርና ኑፋቄን በመዝራት ብዙ የሚጠየቁበት ነገር አለ:: ምክንያቱም ሊቀጳጳሱ መስመር ከሳቱ ቆይተዋል::
ሊቀጳጳሱ በ2011 ዓ.ም ቶሮንቶ ካናዳ ያሳተሙትን " የቅዳሴያችን ይዘት " የተሰኘውን መጽሓፍ እንደ አብነት ላንሳ:: አቡኑ በዚህ መጽሓፋቸው ላይ ለጆሮ ለመስማት የሚሰቀጥጡ : ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የቤተ ክርስትያን የአብነት ትርጓሜ ትምህርትን የሚያራክሱ ጽሁፎችን ጽፈዋል::ጥቂቶቹን እንይ::
"የቅዳሴ ማርያም መግቢያ ታሪክ ተረት ተረት ነው" አቡነ መልኬጼዲቅ
-----------------------------------------------
በዚሁ መጽሓፋቸው የቅዳሴ ማርያምንና የውዳሴ ማርያምን መግቢያ ትርጓሜ "ተረት ተረት ነው" ሲሉ በድፍረት ጽፈዋል:: እንደሚታወቀው ቅዳሴ ማርያምን የጻፈው የግብጹ አባ ሕርያቆስ ( የብህንሳ) ሲሆን ውዳሴ ማርያምን ደግሞ የጻፈው ኤፍሬም ሶርያዊው ነው::
የቅዳሴ ማርያም መግቢያ ሐተታ እንደሚነግረን እመቤታችን ኤፍሬምንም አባ ሕርያቆስንም በደመና ጠቅሳ አምጥታ ; ኤፍሬም ሶርያዊ ውዳሴዋን ; አባ ሕርያቆስ ደግሞ ቅዳሴዋን እየነገሩት ቅዱስ ያሬድ ዜማ ለሁለቱም ደርሷል::
በደብረ ታቦር ላይ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመንና በግዜ የማይገናኙትን ሙሴና ኤልያስን አምጥቶ እንዳናገራቸው ማለት ነው:: ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ተነጥቆ በብሔረ ሕያዋን ይኖር የነበረ ሲሆን ፤ ሙሴ ደግሞ ሞቶ ተቀብሮ በአጸደ ነብስ ይኖር የነበሩ የተለያዩ ዘመን ሰዎች ቢሆኑም ፣ ሁለቱንም ከሺህ አመት በኋላ አምጥቶ አናግሯቸዋል:: ማቴ 17

ሙሴና ኤልያስ የኖሩበት ዘመን ከ900 ዓመት በላይ ልዩነት ቢኖረውም ፣ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሙሴንም ኤልያስንም አምጥቶ በታቦር ተራራ ላይ አናግሯቸዋል:: የቅዳሴ ማርያምም ትርጓሜ መግቢያ ታሪክ ከዚህ የተለየ አይደለም:: ሶርያዊው ኤፍሬምና ግብጻዊው አባ ሕርያቆስ በቦታና በግዜ ቢለያዩም ለቅዱስ ያሬድ ድርሰታቸውን እየነገሩት ዜማውን ሊደርስ ችሏል:: በሃይማኖት የማይቻል የሚመስል ነገር ሁሉ ይቻላል::ለሓዋርያት 72 ቋንቋ የገለጸ አምላክም ለኤፍሬም ፣ ለአባ ሕርያቆስና የቅዱስ ያሬድ የሚግባቡትን ቋንቋ እንዴት አይገልጽላቸውም::
"5 ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ።" ሐዋ 2 :5
"የቅዳሴ ማርያምን ዜማ ያሬድ አልደረሰውም"
-------------------------------------------
አቡነ መልኬጼዲቅ እን እንዲህ ሲሉ ተመጻድድቀዋል የቅዳሴያችን ይዘት መጽሓፍ ገጽ 46 -
" ቅዳሴ ማርያም መቼ ወደ ሃገራችን እንደተመለሰ: ማን እንደተረጎመው .. በቂ ማስረጃ የለውም::በተረት ተረት መልክ የሚነገረው ግን ቅድስት ማርያም አባ ሕርያቆስን ከብህንሳ : ኤፍሬም ከሶርያ ጠቅሳ ቅዱስ ኤፍሬም ወዳለበት አምጥታ አንተም ቅዳሴዬን አንተም ውዳሴዬን እየነረጋችሁት እሱ በዜማ ይድረስልኝ ብላ ነገችው" የቅዳሴያችን ይዘት ገጽ 46 -
እውነት ይህ የኑፋቄ ትውከት ከአንድ ሊቀ ጳጳስ የሚጠበቅ ጽሁፍ ነው :: ለስንት ዘመናት ሊቃውንት ሲማሩትና ሲያስተምሩት የነበረውን ትውፊትና የትርጓሜ ታሪክ " በስጋ ሊመስል የማይቻል ስለሆነ ተረት ተረት ነው" ማለት ከአንድ ሊቀጳጳስ የሚጠበቅ ይሆን? አንድምታ ተረት ተረት ነው ብሎ የሚያስተምር ሊቀጳጳስ ላይ እንድረስ? ወይ ዘመን!
የሊቀ ጳጳሱ ሐዲስና እንግዳ ትምህርት በዚህ አላቆመም በዚሁ መጽሓፋቸው ገጸ 92 ላይ
"በቅዳሴው በኩል ዜማውን ቅዱስ ያሬድ እንዳቀነባበረው ጎልቶ የሚነገርለት በቅዳሴማርያም ላይ ነው::በ እርሱም ላይ ቢሆን ዓረፍተ ዘመን የሚገታው ስለሆነ አባባሉ ትክክል አይደለም"
እስከዛሬ ባለው በቤተክርስትያን ትምህርትም ሆነ ሊቃውንት እንደተጻፈውም እንደተነገረውም የዚህ ቅዳሴ ዜማ ደራሲ ቅዱስ ያሬድ ነው:;ይህንን ማንናውም የቤተ ክርስትያን መጻሕፍትና የሊቃውንት ጉባኤም የሚያስተምረው ትምህርት ነው:: (ከቅዳሴ ማርያም ትርጋሜ ባሻገር : የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000ዓ.ም የሚለውን የሊቃውት ጉባኤን መጽሓፍ ገጽ 111 ይመልከቱ) :: እሳቸው የቅዳሴ ማርያምን ትርጓሜ ስለማይቀበሉት ብቻ ደራሲው ቅዱስ ያሬድ አይደለም እያሉን ነው:: ማን ደረሰው ሊሉን ይሆን?
"ኪዳን ከቅዳሴ መሃል ይውጣ:: ቅዳሴውን በ15 ደቂቃ ያሳጥረዋል"
-------------------------------------------------------------
በቅዳሴው ደራሲዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ሊቀጳጳሱ የቅዳሴያችንንም ይዘት አብጠልጥለውታል::በዚሁ መጽሓፋቸው ገ ጽ 118 ላይ
" የኛ ቤተ ክርስትያን በኋላ የመጣውን እና ዝም ብሎ የገባውን ያለ ምንም ውሳኔ ተቀብላ ኪዳን ማድረስን ደምብ አድርጋ ያዘችው:: እየቆየም እምድኅረ ፍጻሜ ኪዳን የሚል ጽሁፍ መግባት ጀመረ" ካሉ በኋላ በዚሁ አንቀጽ መጨረሻ ላይ
" ኪዳኑ ሲፈጸም አቡነዘበሰማያቱ ሲጸለይ ከኪዳኑ ጋር 15 ደቂቃ ይወስዳል:: የቅዳሴውን ጊዜ የሚያራዝመው ይሄ ሁሉ ነው"
በማለት ቅዳሴ ላይ የሚደገመው ኪዳን እንዲወጣና እሱ ቢወጣ ቅዳሴውን በ15 ደቂቃ እንደሚያሳጥረው እየሞገቱ ነው::
በትንሳኤ ማተሚያ ቤት ታትሞ የወጣው የመዝገበ ቅዳሴ ( ንባብና ትርጓሜ) የቅዳሴ ሰዓትን በተመለከት ዝርዝር ነጥቦች ተጽፈዋል:: እያንዳንዱ ሰው ከፈጣሪ ከተቀበለው ከ 24 ሰዓታት ውስጥ አስራት ማውጣት እንዳለበትና በቤተክርስትያን የሚደረገው ቅዳሴ ርዝመትም ( የ 24 ሰዓት አስር ፐርሰንት 2.4 ሰዓታት) በዚህ መልኩ እንደሰራ ያትታል:: የጸሎተ ኪዳን ንባብና ትርጓሜ ( ኮከበ ጽባሕ ማተሚያ ቤት የታተመ ) እንደሚያስረዳውም ከሆነ ይህ ኪዳን ክርስትያን የሆነ ሁሉ ሊያደሰው የሚገባ ጸሎት እንደሆነ ቅዳሴ ላይም ከ ቅዱስ በኋላ ሊባል የሚገባው መሆኑን በማያሻማ ቋንቋ ጽፎታል:: አባ መልኬ ጸዴቅ ከየት እያመጡ ይሆን ይሄን እንግዳና ሓዲስ ትምህርት የሚያስታውኩት::ቅዳሴ ስለረዘመ ይጠር የሚል ሊቀጳጳስ ???? እኔ ይደንቀኛል!!!
"ራሱን የማይጠብቅ መልዓክ ካለ ይረገጥ"
---------------------------------------------
ባደግንበት በቤተ ክርስትያናችን ትውፊት መሰረት "አሓዱ አብ " ከተባለ በኋላ ስለ ቅዳሴው ክብር መግባት መውጣት ይቆማል:: በቅዳሴ ወቅት ሕብስቱና ወይኑ ወደ ፍጹም የክርስቶስ ስጋና ደም ( ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሃደው) ስለሚቀየር ቅዱሳን መላእክት : ቅዱሳን ስውራን በመስዋዕቱ ዙርያ በመርበብ ቅዱስ ፣ ቅዱስ እያሉ እንደሚያመሰግኑ የቅዳሴ ትርጓሜ ያብራራል:: ምክንያቱም የሚፈተተው ስጋና ደም ልክ በ ዕለተ ዓርብ የፈሰሰው ደምና የተቆረሰው ስጋ ስለሆነ:: ስለሆነም ቅዳሴ ከተጀመረ በኋላ በተለይም አሓዱ ከተባለ በኋላ ሰማያውያን መላ ዕክት እና ምድራውያን ሰዎች በጋራ ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት ስር ዓት ስለሆነ : አሓዱ ከተባለ በኋላ ም ዕመናን ወዲህ ወዲያ እንዳይሉ ሥር ዓት አለ:: ይህ ለዘመናት የኖረ የቅዳሴ ሥር ዓት ነው::
ሊቀ ጳጳሱ ግን " አሓዱ ሲባል ቅዳሴው አልተጀመረም:: ቅዳሴ ላይ አሓዱ ከተባለ በኋላ አትንቀሳቀሱ እየተባለ የሚነገረው ስህተት ነው " እያሉ አዲስ ድርሰት ጽፈዋል::
ሌሎችም ብዙ ለማንበብ የሚከብዱ ነገሮች ጽፈዋል::
እንደ እንደኔ አቡነ መልኬጼዲቅ ሊጠየቁ የሚገባው ኦርጋን ላይ ባለው አስተምህሯቸው አይደለም:: ከዛ የባሱ ኑፋቄዎችን እያስተማሩ ነው:: ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጡትን ያባቶቻችንን ትምህርቶች "ተረት ተረት" እስከማለት የሚደርስ ድፍረት ላይ ናቸው:: አባቶቻችን በገዳም ተወስነው : በቆሎ ጾመው በስንት ድካም የገነቡትን ሥር ዓተ ቤተ ክርስትያን እያፈረሱት ነው:: ሃይማኖትን በስጋዊ ሚዛን እየመዘኑ የሚያሳዝን ድቀት እና የሃይማኖት ወጅብ ውስጥ እየገቡ ነው::
አባ መልኬጼዲቅ የተሳለቁበት ቅዳሴ ማርያምና የሳቸው የ እብደት ጽሁፍም ጎን ለጎን
Ze addis

No comments:

Post a Comment