Sunday 1 March 2020

#ከሰይጣን_ጋር_የተደረገ_ቃለ_ምልልስ (ተዋስኦተ ጳውሊ ምስለ ሰይጣን)፤#ክፍል#፬_
(#ሰይጣን_የቅዱሳን_መላእክትን_ቃል_ምሥጢር_እንደሚሰማና_ #የሰማው_ከመደረጉ_በፊት_ለሰዎች_በመናገር_እንደሚያስት፤ #ሰይጣን_ከተፈጠረ_ጀምሮ_በዘመን_ብዛት_ሰውን_ያሚያስትበት_ብዙ_ጥበብ_እንዳለው፤ #የክርስቶስ_ሰው_መሆን_ከሰይጣን_የተሰወረ_እንደነበር)
+አባ ጳውሊ፤ ወደ ሰማይ ወጥታችሁ የመላእክትን ቃል ትሰማላችሁን? አለው፡፡
ዲያብሎስ፤ ፈጽመን አንወጣም አለው፡፡
++አባ ጳውሊ፤ ስለምንድነው የማትወጡት? አለው፡፡
ዲያብሎስ፤ ከክብራችን ከተዋረድን በኋላ በቧለሟልነት ሥልጣን ወደዚያ እንቀርብ ዘንድ አይፈቀድልንም አለው፡፡
+አባ ጳውሊ፤ ሰዎች እናንተ ወደ ሰማይ እንደምትወጡና ከመላእክት ጋር እንደምትነጋገሩ የሚናገሩት ዋሽተው ነውን? አለው፡፡ ሰይጣን፤ መላእክት ከምስጋና በቀር አይናገሩምና አዎን ዋሽተው ነው አለው፡፡
++አባ ጳውሊ፤ እንግዲያ ከመደረጉ በፊት አስቀድመህ ለሳኦል ምሥጢር የገለጥክለት በምን አውቀህ ነው? አለው፡፡ /፩ሳሙ.፳፰፥፲፯/
ዲያብሎስ፤ እግዚአብሔር ለሳሙኤል ሲነግረው ሰምቼ ነው አለው፡፡ /፩ሳሙ.፲፮፥፩) እግዚአብሔር ለመላእክቶቹ ምሥጢር ሲነግራቸው እኛም ባለንበት ሆነን እንሰማለን፡፡ ያን ጊዜ ፈጥነን ሄደን ከመደረጉ በፊት ለሰዎች እንነግራቸዋለን፡፡ ሰዎች ሁሉ በየሀገሩ እኛ የነገርናቸውንና በሕልም ያሳየናቸውን ይናገራሉ አለው፡፡
+አባ ጳውሊ፤ ሰዎች ነገርህን እንደምን አምነው ይቀበሉሃል? የመልክህን ክፋት የመዓዛህን ክርፋት አያውቁምን? አለው፡፡
ዲያብሎስ፤ ሰዎች ሁሉ እንደ አንተ ክፉ መሰሉህ? ለአንተ ክፉ መስዬ እታይሃለሁ እንጂ በዚህ ዓለም መዓዛዬን ለማሽተትና መልኬን ለማየት እኔን የሚሹ ብዙ ሰዎች እንዳሉ እነግርሃለሁ፡፡ እነርሱ ወደ እኔ መጥተው እገለጽላቸው ዘንድ ይለምኑኛል እንጂ እኔ ወደ እነርሱ አልሔድም አለው፡፡
++አባ ጳውሊ፤ ሰዎች ስለምን ይወዱሃል? ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው?
ዲያብሎስ፤ እኔን ለማየት በሚፈልጉት መልክ ተመስዬ በመገለጽ ስለማስደስታቸው ነው፡፡
+አባ ጳውሊ፤ መልክህን መለወጥ እንደምን ይቻልሃል አለው፡፡
ዲያብሎስ፤ ይህ የሚያስደንቅ አይደለም ሰይጣን የብርሃን መልአክን ይመስላል ብሎ ጳውሎስ የተናገረውን አልሰማህምን፡፡ /፪ቆሮ.፲፩፥፲፬/
++አባ ጳውሊ፤ የማታውቀውን ምሥጢር ማስመሰል እንደምን ይቻልሃል አለው፡፡
ዲያብሎስ፤ #ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በዘመን ብዛት የሰበሰብኩትና የማውቀው ብዙ ጥበብ አለኝ፡፡ #ነገር ግን የክርስቶስ ሰው መሆን ብቻ ተሰወረብኝ እንጂ አለው፡፡
+አባ ጳውሊ፤ የክርስቶስ ሰው መሆን ስለምን ተሰወረብህ?
ዲያብሎስ፤ ከእኔ የተሰወረበትን ምክንያት አላውቅም፡፡ ነገር ግን አውቄስ ቢሆን ክፉና በጎ ለይተው ያላወቁ ብዙ ሕፃናትን በሄሮድስ አድሬ ባላስገደልኩም ነበር አለው፡፡
++አባ ጳውሊ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ አንተ ፈትነኸዋልና አላውቅም አትበል አለው፡፡
ዲያብሎስ፤ በሰውነቱ ስለሚሠራው ሥራ እንደ ነቢይ፥ እንደ ንጉሥ ይመስለኝ ነበርና ባውቅም እጠራጠር ነበር፡፡ ስለዚህ እፈትነው ዘንድ በእርሱ ላይ ተነሳሁ አለው፡፡
+አባ ጳውሊ፤ እርሱ በእውነት አምላክ መሆኑን ያወቅኸው መቼ ነው አለው፡፡
ዲያብሎስ፤ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ኃይሌን እስከሚያደክመው ድረስ አላወቅሁም ነበር፡፡ መላእክት ሲያመሰግኑት፥ ሙታን ሲነሡ፥ ምድር ሲነዋወጥ፥ ፀሐይ ሲጨልም አየሁ፤ ያን ጊዜ የዓለም ብርሃን፥ የፍጥረታት ፈጣሪ እርሱ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ አወቅሁ አለው፡፡
#የሰይጣናት_አለቃና_ታዛዥ_እንዳላቸው፤ #ገሃነም_ስለመኖሩና_ዲያብሎስ_ለምን_ንስሐ_እንደማይገባ#ክፍል_፭.… #ይቀጥላል_ነገ ይጠብቁን/
/#ዋልድባ_ዋሊ_ገጽ/

No comments:

Post a Comment