Friday 6 December 2019

የተወደዳችሁ ወገኖች ሰላም ለእናንተ ይሁን ከቪዲዮው መልዕክት በተጨማሪ ይህንን ጽሑፍ በማስተዋል እንድታነቡ እጋብዛለሁ ተባረኩልኝ

ከዳተኛይቱ ይሁዳ አንድ ቀን በሙሉ ልብዋ ተመልሳ እግዚአብሔርን እንደምትወድ ከጌታ ቤት በአንድም በሌላም መንገድ የከዱና የኮበለሉ ሰዎች እንደዚሁ አንድ ቀን ተመልሰው እግዚአብሔርን ይወዳሉ :: ይህም የሚሆነው በእኛ ቀን ሳይሆን በእግዚአብሔር ቀን ነው :: ይህን ስል ግን እያንዳንዳችን ክርስቲያኖች ማድረግ የሚገባንን የበኩላችንን ነገር ሁሉ አናድርግ አንምከር አናስተምር አንገስጽ ማለቴ አይደለም ፣ ነገር ግን ያ ሁሉ እንዳለ ሆኖ እግዚአብሔር ደግሞ ብቻውን በሚያደርገው ነገር ከዳተኛይቱ ይሁዳ በሙሉ ልብዋ ወደ እግዚአብሔር እንደተመለሰች ከመንግሥቱም ሆነ ከቤቱ የጠፉና የኮበለሉ ሰዎች ደግሞ እንዲሁ በእግዚአብሔር ክህሎት ወደ ቤቱ ይመለሳሉ :: ለዚህም ነው ጌታ እግዚአብሔር በትንቢተ ኤርምያስ 31 ፥ 22 ፤ በትንቢተ ኤርምያስ 3 ፥ 14 - 22 ላይ ከዳተኛ ልጆች ሆይ እኔ ባለቤታችሁ ነኝና ተመለሱ ፣ በእውቀትና በማስተዋል የሚመሯችሁን እረኞች እሰጣችኋለሁ ያለው :: እንደገናም እኔም የተመረጠችውን ምድር የትኛውም ሕዝብ ያላገኘውን የተዋበች ርስት ልሰጥሽ እንደ ወንዶች ልጆቼ ምንኛ በደስታ ልቊጠርሽ አልሁ :: አባቴ ብለሽ የምትጠሪኝ እኔንም ከመከተል ዘወር የማትዪ መስሎኝ ነበር :: የእስራኤል ቤት ሆይ ለባልዋ ታማኝ እንዳልሆነች ሚስት ስታታልሉኝ ኖራችኋል ይላል እግዚአብሔር በማለት ይህንን መልዕክት በነቢዩ በኤርምያስ ለከዳተኛዋ ይሁዳም ሆነ ለእስራኤል ቤት ተናገረ :: ታድያ ይህንን መልዕክት በነቢዩ በኩል ማምጣቱ እስራኤል ዘወትር አምላኩዋ ያደረገላትን ሁሉ ማስታወስ ነበረባት :: በእርሱ ብቻ በመታመን እርሱንም ማምለክ ነበረባት ፣ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ረስታዋለች ከልብዋም አውጥታ ጥላዋለች ከዚህ የተነሳ በትንቢተ ኤርምያስ 2 ፥ 32 ላይ ጌታ እግዚአብሔር በውኑ ለእስራኤል ምድረበዳ ወይስ የጨለመች ምድር ሆንሁበትን ? ሕዝቤስ ስለምን እኛ ፈርጥጠናል ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አንተ አንመለስም ይላል ? በውኑ ቆንጆ ጌጥዋን ወይስ ሙሽራ ዝርግፍ ጌጥዋን ትረሳለችን ? ሕዝቤ ግን የማይቆጠር ወራት ረስቶኛል በማለት ሲናገር እንመለከታለን :: እንግዲህ ሕዝቤ ተብላ ወደ አንተ አንመለስም ስትል የማይቆጠር ወራት አምላኳን የረሳች እስራኤል ናት በሙሉ ልብዋ ወደ እግዚአብሔር ተመልሳ በዚሁ በትንቢተ ኤርምያስ 3 ፥ 21 መሠረት እግዚአብሔር አምላካቸውን በመርሳት መንገዳቸውን አጣመዋልና የእስራኤል ሕዝብ ጩኸት አሳዛኝ ልቅሶ ባድማ ከሆኑት ኮረብታዎች ተሰማ የሚለን ::

ይህንን መልዕክት በተለቀቀው ቪዲዮ የሰማችሁም ሆነ ለማንበብ ፈቃደኛ ሆናችሁ መልዕክቱን የምታነቡ ሁሉ በእግዚአብሔር ተስፋ አይቆረጥምና ለጠፉ ሰዎች በፍቅር ሆናችሁ የመናገርም ሆነ የመመስከር ፋይላችሁን አትዝጉ ደግሞም ፈራጁ እያለ እናንተንም ሆነ ሁላችንን ስላልተቀበሉን ፣ ስላልተቀበሏችሁ ፣ ስላላስተናገዱን ስላላስተናገዷችሁ መጸለይ አለበለዚያም እነርሱን በግል ሄዶ ማነጋገርና ማመካከር መጨረስ የሚገባንንም እዚያው በግል መጨረስ ነው እንጂ ከብስጭትም ሆነ ከመመረር የተነሳ እንዲሁ መድረኩ ስለተገኘ ብቻ እነዚሁኑ ሰዎች በየሶሻል ሚዲያው ገበናቸውን አውጥተን የውይይት አጀንዳ ባናድርጋቸው ፣ ደግሞም እንደ ጳውሎስና በርናባስም እስከ መከፋፋት ደርሰን ባንለያይባቸው እንደገናም ነገ የሚሆነውን አናውቅምና ከዚህም ሌላ ከጌታ ዘንድ ምን ዓይነት መንፈስ እንደሆነላችሁ አታውቁም እንባላለንና በችኮላ ተናደን የፍርድን ቃል በላያቸው ባንናገር የተሻለ ነው የሚሆነው :: እነዚህን ጥቅሶች በማስተዋል አንብቧቸው የሉቃስ ወንጌል 9 ፥ 51 - 56 ፤ የሐዋርያት ሥራ 15 ፥ 36 - 41 ፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 4 ፥ 11 ፤ ፊልሞና ቊጥር 8 - 25 :: ዛሬ ላይ ሁላችንም ማለት ይቻላል ብለን ብለን ተስፋ የቆረጥንባቸውን ሰዎች በነገው ሕይወታቸው እግዚአብሔር ወደ ቤቱ በምን ዓይነት መንገድ ጠርቶና መልሶ እንደሚጠቀምባቸው ከአንዳንዶች በቀር አብዛኞቻችን ላናውቅ እንችላለን :: ይህ ሲባል ግን የተግሳጽም ሆነ የዘለፋ እንዲሁም የምክር መልዕክቶችን ጌታ እንደሰጠን መጠን አንናገር አናስተላልፍ እያልኩ አለመሆኔን በግልጽ ልትረዱልኝ ይገባል :: እንደውም መጽሐፍቅዱሳችን የሚለን በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር ነው የሚለን ትንቢተ ኢሳይያስ 58 ፥ 1 እንመልከት :: ከዚህ በመቀጠል መጋቢ ተስፋዬ ጋቢሶ የእስራኤልም ሆነ አሁን ላይ ያለ የሐዲስ ኪዳን ሕዝብን አሳዛኝ ጩኸትና የመመለስ ልቅሶ እንዲህ በማለት አስደናቂ በሆነው የመዝሙር ስንኞቹ እና ዜማው ገልጾታልና እርሱን እጋብዛችኋለሁ ተከታተሉ ::

አዝ፦ ያ ፡ ተከራታቹ ፡ ኮብላይ ፡ ወገናችን

መቷል ፡ እንደገና ፡ እሰይ ፡ ደስ ፡ ይበለን

ያ ፡ ተከራታቹ ፡ ኮብላይ ፡ ወገናችን

መቷል ፡ እንደገና ፡ እሰይ ፡ ደስ ፡ ይበለን (፪x)



በመዳኑ ፡ ምክንያት ፡ መላዕክት ፡ ፈንጭተው

በአገልግሎቱም ፡ ብዙ ፡ ሰዎች ፡ ረክተው

ያንን ፡ ሰው ፡ በቃሉ ፡ እንቅፋት ፡ እግኝቶት

ወድቆ ፡ የነበረው ፡ አዳኙንም ፡ ከድቶ



አዝ፦ ያ ፡ ተከራታቹ ፡ ኮብላይ ፡ ወገናችን

መቷል ፡ እንደገና ፡ እሰይ ፡ ደስ ፡ ይበለን

ያ ፡ ተከራታቹ ፡ ኮብላይ ፡ ወገናችን

መቷል ፡ እንደገና ፡ እሰይ ፡ ደስ ፡ ይበለን (፪x)



መርዶውን ፡ እየሰሙ ፡ ሰዎች ፡ አልቅሰውለት

ጌታ ፡ እንዲያስነሳው ፡ ከልብ ፡ ጸልየውለት

በመራራ ፡ ጩኸት ፡ ለአምላኩ ፡ ነግረውለት

መልሶ ፡ እምጥቶታል ፡ እግዚአብሔር ፡ አዝኖለት



አዝ፦ ያ ፡ ተከራታቹ ፡ ኮብላይ ፡ ወገናችን

መቷል ፡ እንደገና ፡ እሰይ ፡ ደስ ፡ ይበለን

ያ ፡ ተከራታቹ ፡ ኮብላይ ፡ ወገናችን

መቷል ፡ እንደገና ፡ እሰይ ፡ ደስ ፡ ይበለን (፪x)



የውድቀቱን ፡ ምክንያት ፡ ነግሮ ፡ አስጠንቅቆታል

ወንድሞቹ ፡ ቀድሞ ፡ ጌታ ፡ አምጥቶለታል

ተስፋን ፡ እየናቀም ፡ በወጥመድ ፡ ቢገባም

ጌታ ፡ ቸር ፡ ነውና ፡ አይጨክንበትም



አዝ፦ ያ ፡ ተከራታቹ ፡ ኮብላይ ፡ ወገናችን

መቷል ፡ እንደገና ፡ እሰይ ፡ ደስ ፡ ይበለን

ያ ፡ ተከራታቹ ፡ ኮብላይ ፡ ወገናችን

መቷል ፡ እንደገና ፡ እሰይ ፡ ደስ ፡ ይበለን (፪x)


ያን ፡ ጨካኝ ፡ አንበሳ ፡ በግልጽ ፡ አሳፍሮ

በብረቱ ፡ በትር ፡ መንጋጋውን ፡ ሰብሮ

ዳግም ፡ አምጥቶታል ፡ እግዚአብሔር ፡ ይመስገን

ሙሾው ፡ ተለውጧል ፡ እሰይ ፡ ደስ ፡ ይበለን



አዝ፦ ያ ፡ ተከራታቹ ፡ ኮብላይ ፡ ወገናችን

መቷል ፡ እንደገና ፡ እሰይ ፡ ደስ ፡ ይበለን

ያ ፡ ተከራታቹ ፡ ኮብላይ ፡ ወገናችን

መቷል ፡ እንደገና ፡ እሰይ ፡ ደስ ፡ ይበለን (፪x)

አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment