Friday 20 December 2019

የዘመኗ ቤተክርስቲያን መልክ

የተወደዳችሁ ወገኖች ሰላም ለእናንተ ይሁንን :: ዛሬ በፊታችሁ ይህንን ርዕስ ወደ እናንተ ይዤ የቀረብኩበትን ምክንያት እንደሚከተለው አብራራለሁ :: የዘመኗ ቤተክርስቲያን መልክ የሎጥና የአብርሃም ዘመን መልክ እየሆነ ከመጣ ሰንበትበት ብሎአል :: እንዴት ለሚለው ጥያቄ ምላሼን እነሆ ብያለሁና ተከታተሉኝ ::
ሎጥና አብርሃም በመጽሐፍቅዱሳችን ቃል መሠረት ዘመዳሞችና ሎጥም የአብርሃም የወንድሙ ልጅ እንደሆነ ከቃሉ እናነባለን ኦሪት ዘፍጥረት 12 : 5 :: ይሁን እንጂ አብራም የእግዚአብሔር ጥሪ ደርሶት ከሀገሩና ከዘመዶቹ ተለይቶ በወጣ ጊዜ ሎጥ አብሮት አልተጠራም ፣ ማለትም የእግዚአብሔር ጥሪ አልደረሰውም ፣ እንዲሁ አብርሃምን ተከትሎ የወጣ መሆኑን አሁንም ቃሉ በግልጥ ይነግረናል ኦሪት ዘፍጥረት 12 ፥ 4 ፤ ኦሪት ዘፍጥረት 13 ፥ 1 :: ታድያ በእግዚአብሔር ተጠርቶ የወጣው አብራም በከብት ፣ በብርና በወርቅ እጅግ በበለጠገበት ወራት ፣ ከአብራም ጋር የሄደው ሎጥ ደግሞ የላምና የበግ መንጋ ድንኳንም ነበረው በአንድነትም ይቀመጡ ዘንድ ምድር አልበቃቸውም ፣ የነበራቸው እጅግ ነበረና በአንድነት ሊቀመጡ አልቻሉም የአብራምንና የሎጥን መንጎች በሚጠብቁት መካከልም ጠብ ሆነ በዚያም ዘመን ከነአናውያንና ፌርዛውያን በዚያች ምድር ተቀምጠው ነበር ይለናል ቃሉ ዘፍጥረት 13 ፥ 2 - 8 :: ይሁን እንጂ ይህ ጠብ ሲጀመር የሎጥና የአብራም እንጂ በሁለቱም በኩል ያለ የጠባቂዎቹ ጠብ አለመሆኑን አብራም በትክክል ጠንቅቆ ያወቀ ነውና አብራም ሎጥን እንዲህ አለው :: እኛ ወንድማማች ነንና በእኔና በአንተ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ አንተ ግራውን ብትወስድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ አንተም ቀኙን ብትወስድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ አለው ይለናል ::
ውድ ወገኖቼ ሆይ የዘመኗ ቤተክርስቲያን መልክ ያልኩት እንግዲህ ከዚህ ታሪክ ተነስቼ ነው :: ሎጥ ከአብራም ጋር በፈጠረው ግጭት የአብራምንና የሎጥን መንጎች በሚጠብቁት መካከል ጠብ እንደሆነ ሁሉ ዛሬም በዘመናችን ባለች ቤተክርስቲያን ውስጥ አንድ ሎጥ ብቻ ሳይሆን ብዙ ችግር ፈጣሪ ሎጦች አሉና እነዚህ ሎጦች አብራምን ከመሰሉ በእግዚአብሔር ተጠርተው የእግዚአብሔርን ጥሪ ተግባራዊ ከሚያደርጉና ወደ ፍጻሜም ከሚወስዱ ሰዎች ጋር በሚፈጥሩት ግጭት አንድ መንጋና አንድ ሕዝብ ሆኖ በሚኖረው በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ትልቅ የሆነ መበጣበጥና ጦርነት ይፈጠራል :: ታድያ ሎጥ ሰላማዊ መስሎ አብራምን ተከትሎ እንደወጣ ሁሉ እነዚህም በአሁን ዘመን ላለች ቤተክርስቲያን የጠብ መንስዔ የሆኑ ሎጦች አብራምን ከመሰሉ የእግዚአብሔር ጥሪ ከደረሳቸው ሰዎች ኋላ ኋላ ተከትለው የወጡ ሰዎች ቢሆኑም ሰላማዊነታቸው ግን የሚፈልጉትን እስኪያገኙ ድረስና ቢያገኙም የማይጠግቡም ሆነ በቃኝ የማይሉ በመሆናቸው ያሻቸውን ሁሉ ሊያገኙ በወደዱት መጠን ማግኘት እስከ ቻሉ ድረስ ብቻ ነው :: ድንገት ቀና ያሉ እና ቀናም የሚሉ በመሆናቸውም የሚያነሱት ረብሻ መጠን የሌለውና ገደቡንም የሳተ ስለሆነ መቋጫም ሆነ እልባት ልናበጅለት አይቻለንም :: እነዚህን የመሰሉ ሰዎችን መገላገል የሚቻለው ቀኝና ግራ ሳይሉ ሁሉንም ዕድል ለእነርሱ አሳልፎ በመስጠትና የወደዱትንም እንዲያደርጉ በመፍቀድ ብቻ ነው :: ቊሳዊና ማቴሪያሊስት ስለሆኑ ወንድምነት የሚባለው ቋንቋ እንዲህ ላሉ ሰዎች ግልጽ አይደለም አይገባቸውምም :: ከወንድምነት ይልቅ ገንዘብን ጥቅምንና ክብርንም ጭምር ያስቀደሙ በመሆናቸው ወንድምነት ለተባለው የቤተሰብነት ሕይወት የታወሩ ናቸው :: ከእነርሱ ሳይሆን ከመንጋው መካከል በሚነሳው ብጥብጥ በጥባጭነታቸው የሚታወቅ መሠርይ ሰዎች ናቸው :: የዘመኗ ቤተክርስቲያን ሎጦች ላማራቸው ፣ ለመረጡትና ለለመለመው ነገር ካልሆነ በስተቀር ለመንፈሳዊው ነገር ዓይኖቻቸው የማይነሳና ማየትም የማይችሉ ምድራዊና ሥጋውያን ሰዎች ናቸው ::
ሎጥ ዓይኑን ያነሳውና እንደ እግዚአብሔር ገነት አምሳል የሆነችውን ዞአርን የመረጠው አብራም ቀኝና ግራ ሳይል ሁሉንም ምርጫ ለእርሱ ከሰጠውና ከተወለት በኋላ ነው :: እስከዚያ ድረስ ግን ሰላማዊ መስሎ በእረኞች መካከል እየገባ ጠብን የሚጭርና የሚያቀጣጥል ጉድጓድንም መንፈሳዊ ለሆነው ለአጎቱ ለአብራም የሚምስ ሰው ሆኖ የተገኘ ነው :: ስለዚህ የጠብ መነሻና መገኛ የሆነው ሎጥ በእውነተኛው በእግዚአብሔር ሰው በአብራም ካልሆነ በስተቀር በሌላው ሰው በፍጹም የሚታወቅ አይደለም :: የዘመናችን ሎጦችም እንደዚህ ናቸው :: በእውነተኞቹ በእግዚአብሔር ሰዎች ካልሆነ በስተቀር ጠብን የጀመሩም ሆነ የቀሰቀሱ እነርሱ መሆናቸው ጨርሶ አይታወቅም :: ይልቁንም መንፈሳዊና የሚጸልዩልን ናቸው ብለን ምስጢራችንንም ሁሉ ዝክዝክ አድርገን ልንነግራቸው እንችላለን :: እነርሱ ግን ዓይን ያወጡና በእግዚአብሔርም ስም መነገድን የለመዱ ስለሆኑ እኽ ብለውም ሆነ ተቆርቋሪ መስለው ይሰሙናል ፣ ነገር ግን ከቀናት በኋላ ለሞታችን የሚሆንን ጉድጓድ ሲምሱብን እናገኛቸዋለን :: የዘመናችን የቤተክርስቲያን ሎጦችም ታድያ እንዲህ በመሆናቸው ዓይን ያውጡ ሌቦች ናቸው :: ተከትለው ወጥተው ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ባነሱት ረብሻና ብጥብጥ ምክንያት ዋናና ፊተኛ መሆንን የሚፈልጉ በመሆናቸው ዓይናችንን ከፍተን ልናያቸውና እንደሚገባም ልናውቃቸው ይገባል እላለሁኝ ::
ሎጥ አብራም ዕድሉን ሁሉ ለእርሱ ሰጥቶትና ለቆለት በመረጠው ምርጫ ምክንያት አንዱ ከሌላው እርስ በእርሳቸው ተለያዩ በማለት የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል ኦሪት ዘፍጥረት 13 : 11 :: የዘመናችን የቤተክርስቲያን ሎጦች ግን እንዲህ አይደሉም እናንተ እንኳ ማንነታቸውን አውቃችሁ ጠብን ከመጥላት የተነሳ ወንድምነት ይበልጣልና እስቲ ዕድሉን ሁሉ ልስጠው እርሱም የወደደውን ያድርግ ስትሉ ሁሉንም ነገር ብትተዉላቸው ፣ እነዚህ ሰዎች ግን እጅግ የተለዩ ፣ በአብራምም ዘመን ዓይነት እንደነበረው ሎጥ ያይደሉ በመሆናቸው ኃጢአታቸው ገጦና ፈጦ የወጣ ሆኖ ሳለ በኃጢአታቸው ተጸጽተው ንስሐ የማይገቡ መንፈስቅዱስም የማይወቅሳችው ናቸው :: ከዚህም ሌላ የመረጡትን ዞአር የያዙ እንኩዋ ቢሆኑም እጅግ በጣም ራስ ወዳዶችና ጥቅመኞች እንዲሁም ሃይማኖት ለበስ ፖለቲከኞች በመሆናቸው እንደ አብርሃሙ ዘመን ዓይነቱ ሎጥ በቀላሉ የሚፋቱአችሁ አይሆኑም :: እራሳቸውን ሎጦች ሳይሆን አብራሞች አድርገው የሚቆጥሩ በመሆናቸውም እናንተን የሎጥ ያክል ቆጥረው በሄዱበት መንገድ ሁሉ ተከትላችኋቸው እንድትሔዱ ፣ የራሳችሁ ምርጫ ቢኖራችሁም እንኳ ከእናንተ ምርጫ ይልቅ የእነርሱ ምርጫ እንደሚበልጥ አምናችሁና ተቀብላችሁ ምርጫቸውንም ምርጫዬ ነው ብላችሁ አጽድቃችሁ እንድትከተሏቸው መጣላታቸውንና መናከሳቸውን ባለማቆም የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ :: ይህንንም የሚያደርጉት አንድ ዓይነቶችና አንዱም ከሌላው የማይሻል ፣ የማይለይም ስለሆኑ ነው መጽሐፍቅዱሳችን በመጽሐፈ ምሳሌ 27 ፥ 17 ላይ ብረት ብረትን ይስለዋል ሰውም ባልንጀራውን ይስላል እንደሚል ፣ በእነርሱ ዘንድ አንዱ ከሌላው የተሻለ ሆኖ ባልንጀራውን የሚስል አይደለም :: በአጠቃላይ ሁሉም የማይሳሳሉ ዱልዱሞችና ከእጅ አይሻል ዶማዎች ናቸው :: እንደነዚህ ካሉ ፈጣጦች ፣ በሚሰሩት መልካም ያልሆነ ሥራም ከሚጸጸቱ ይልቅ ዓይኔን ግንባር ያርገው ሲሉ በከተሞች ሁሉ ከሚንቀሳቀሱ አወናባጅ ሎጦች እግዚአብሔር ይጠብቃችሁ ይጠብቀን ተባረኩልኝ ::
አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment