Sunday 8 December 2019

ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም

የተወደዳችሁ ወንድሞችና እህቶች ሰላም ለእናንተ ይሁን


እነሆኝ እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም ይላል ( ዕብራውያን 2 ፥ 12 )


ውድ ወገኖቼ ሆይ ይህንን ቃል ልብ ብለን ተመልክተነዋል ? ከኢየሱስ በላይ ሐዋርያ ፣ ከኢየሱስ በላይ ነቢይ ፣ ከኢየሱስ በላይ እረኛ  ሊያውም ትልቅ እረኛና የእረኞችም አለቃ የሆነ ፣ ከኢየሱስ በላይ ወንጌላዊ ፣ ከኢየሱስ በላይ መምህር  ፣ ከኢየሱስ በላይ ሊቀ ካህን ሊያውም በሰማያት ያለፈና በአባቱ ቀኝ የተቀመጠ ትልቅ ሊቀ ካህን ፣ ከኢየሱስ በላይ ንጉሥ ሊያውም የእሾህ አክሊል ብቻ ሳይሆን  የክብርና የምሥጋናን ዘውድ ተጭኖ የታየ ንጉሥ እንደ እርሱ ያለ ማንም የለም :: ይሁን እንጂ ታድያ እንዲህ ያለው ጌታ ነው እንግዲህ ብዙዎቹ ሐዋርያ ፣ ነቢይ ፣ እረኛና የመሣሠሉትን ተብለው ስለተጠሩ ብቻ ወንድሞች ሊሉን ባፈሩበት በዚህ ዘመን ወንድሞች ብሎ ሊጠራን ያላፈረው :: ከዚህ የተነሣ እንግዲህ ዛሬ ዘመናችን ነው ወይንም በሌላኛው አባባል ዘመን መጥቶልናል ሲሉ  በእንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ተጠምደው ላሉ የዘመኑ እረኛ ፣ ነቢይ ፣ ሐዋርያና የመሣሠሉትን ሲባሉ ለተጠሩ ሰዎች እኛም የምንሰጣቸው ምላሽ  ከኢየሱስ ጋር ልትፍቁት የማትችሉት ወንድምነት ውስጥ የገባን ስለሆነ ወንድምነታችን ቀረባችሁ እንጂ አልቀራችሁብንም ነው ::  ደግሞም ክርስቶስ ወንድሞች ብሎ በመጥራት የሰጠን ወንድምነት የማያሳፍርና በመቤዠት ውስጥ የመጣ  የዘላለም  ወንድምነት ስለሆነ እናንተ ደግሞ ይህ ምስጢር ሳይገባችሁ ነውና ሐዋርያ ፣ መጋቢ ፣ ነቢይና የመሳሰሉትን የተባላችሁት ወንድሞች ብለን ስንጠራችሁ የሚያሳፍራችሁ ፣ የምትበሳጩ  ፣ የምታኮርፉና  የምትቆጡ ከዚህ የተነሳም ወንድምነታችንንም ጭምር ልትቀበሉት የምትቸገሩ ብትሆኑም  የተቤዠን ጌታ ግን ወንድሞቼ ብሎ ሊጠራን እኛም ወንድማችን ልንለው አያፍርብንም ፤ ደግሞም  ይሄ ጉዳይ ለእርሱ ደስታው እንጂ ችግሩ አይደለም :: በተለይ በወንጌላውያን ቤተክርስቲያን አንድን ፓስተር ወይንም አንድን ሐዋርያ አንድ አማኝ ድንገት እንኩዋን አፉን አዳልጦት ወንድም እገሌ ቢለው ፓስተሩ ፣ ሐዋርያውም በሉት ሌላው የሚሰማውን ስሜት በተለይ በዚህ ዘመን ሁላችንም እናውቀዋለን :: አንዳንዱማ  ሐዋርያ ፣ ነብይ እና የመሣሠሉትን ተብዬ ተጠርቼ ሳለ ለምን ወንድም ብላችሁ ጠራችሁኝ ? ሲል ከመጠን በላይ ያኮርፍና ላያገኘን ምሎና ተገዝቶ ፣ መንገዱንም አሳብሮ ይሄዳል በየከተማችን ያለ የመጋቢዎች ኩርፍያማ ከዚህም የባሰ ነው :: እግዚአብሔር ያስበን ወገኖቼ :: ከእኛ በፊት የአገልግሎት ቅድሚያና ብልጫም የነበረው ጳውሎስ እኮ ፣ ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ ተብሎ እስካሁን እስከ እኛ ዘመን ድረስ ይነገርለታል 2ኛ ጴጥሮስ 3 ፥ 15 እና 16 :: ታድያ ወንድማችን ጳውሎስ ወንድማችን ስለተባለ ወንድም ተብዬ ተጠርቻለሁና ተዋርጃለሁ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ እንዴ አላለም :: ሐዋርያነቱንም ቢሆን እኮ ይገባኛል ብሎ በይገባኛል መንፈስ ያልተቀበለ በመሆኑ ወንድም ተብሎ መጠራቱ ለእርሱ ደስ ያሰኘው እንጂ የቆረቆረው አልሆነም 1ኛ ቆሮንቶስ 15 ፥ 9 – 11 ::  ደግሞም ከሐዋርያነት ይልቅ ወንድምነት እንደሚበልጥ በትክክል የተረዳና የገባው ስለሆነ እንደ እኛ አይደለም :: እኛ ብንሆን ግን እንደዚህ  ጳውሎስ እንደተጠራበት አጠራር ቅንነትንና ወዳጅነትን ተላብሶ  ወንድማችን ሲል በአደባባይ የጠራንን ሁሉ ልናጠፋው እንቅልፍ አይወስደንም :: እንደገናም ቤተክርስቲያንዋም የእኛ እንጂ የእርሱ ስለልሆነች ኮንትራቱ እንዳለቀ ሠራተኛ ከቤተክርስቲያን ምክንያት ፈጥረን አስፈንጥረን እናባርረዋለን :: ጌታ ዓይኖቻችንን ይክፈትልን ይህንን ያክል በአጭሩ ካልኩ እንግዲህ ይበቃኛል :: በዚህ ምንባብ ተጠቀሙ ተባረኩ ::


…..ጳውሎስም፦ ወንድሞች ሆይ፥ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባላውቅ ነው፤ በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል አትናገር ተብሎ ተጽፎአልና አላቸው
የሐዋርያት ሥራ 23 : 1 – 5


አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment