ጠቃሚ ምክር
( ክፍል ሦስት )
ከሰማኋቸውና ካነበብኳቸው
የዕለት እንጐቻ
አንድ ወንድም ወደ አንድ አገልጋይ መጥቶ ብዙ ሃሳቦች ወደ ልቡናዬ መጥተው እያስቸገሩኝ ነው ብሎ ጠየቀው :: አገልጋዩም እንዲህ ሲል መከረው :: በውስጥህ ያለውን አየር ተንፍሰህ ወደ ውጪ አውጣውና መልሰህ አየር ወደ ውስጥ አስገብተህ ተንፍስ አለው :: ይህም ወንድም አገልጋዩ እንዳለው በውስጡ ያለውን አየር ተንፍሶ ወደ ውጪ አስወጣውና መልሶ አየር ወደ ውስጥ አስገብቶ ተነፈሰ:: አገልጋዩም እንደገና ይህንን ወንድም እንዲህ ሲል መከረው :: ከዚህ በኋላ አንዴ ወደ ውስጥ ያስገባኸውን አየር ተንፍሰህ ወደ ውጪ አስወጥተሃልና መልሰህ አየር ወደ ውስጥህ አታስገባ አለው :: ይህም ሰው አልችልም አለ :: አገልጋዩም ይህንን ሰው መልሶ አየህ ወደ ልቡናህ መጥተው የሚያስቸግሩህንም ሃሳቦች እንደዚህ ወደ ውስጥህ አለማስገባት ትችላለህ አለው ይባላል ::
አንድ ዘማሪ እንዲህ ሲል ዘመረ ፦—
አላስተናግድም በሬንም አልከፍትም
ከኢየሱሴ ሌላ እንግዳ አልፈልግም …………………
አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ
የሕይወትህ መውጫ ከእርሱ ነውና
የአፍህን ጠማማነት ከአንተ አውጣ ሐሰተኞቹን ከንፈሮችም ከአንተ አርቅ
( መጽሐፈ ምሳሌ 4 ፥ 23 እና 24 )
እርሱም አለ ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ ሃሳብ ዝሙት መስረቅ መግደል ምንዝርነት መጎምጀት ክፋት ተንኮል መዳራት ምቀኝነት ስድብ ትዕቢት ስንፍና ናቸውና ይህ ክፉ ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውንም ያረክሰዋል
( የማርቆስ ወንጌል 7 ፥ 14 - 23 )
በቀረውስ ወንድሞች ሆይ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ በጎነት ቢሆን ም ስጋናም ቢሆን እነዚህን አስቡ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል
( ፊልጵስዩስ 4 ፥ 8 እና 9 )
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነውን ነገር ምን እንደሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ
( ሮሜ 12 ፥ 1 - 3 )
ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ በአዕምሮአችሁ መንፈስ ታደሱ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ
( ኤፌሶን 4 ፥ 22 - 24 )
አባ ዮናስ ጌታነህ