Thursday, 8 June 2017

ሥዕል ከክርስትና በፊት የነበረው ገጽታ ( ዘጸአት 25 ፥ 18_ 21 ) ክፍል አንድ ሥዕል ከክርስትና በፊት የነበረው ገጽታ ( ዘጸአት 25 ፥ 18_ 21 ) ክፍል አንድ ሁለት ኪሩብ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ በሥርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ ከሥርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሠራዋለህ ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደላይ ይዘረጋሉ የሥርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ ፊታቸውም እርስ በእርስ ይተያያሉ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ሥርየት መክደኛው ይመለከታሉ ዘጸአት 25 ፥ 18_ 21 የተወደዳችሁ ወገኖች የዚህ ትምህርት ተከታታዮች በሙሉ ይህንን የሥዕል ትምህርት በዛሬው ዕለት አንድ ብለን ጀምረናል የእግዚአብሔር ስም ብሩክ ይሁን ወደ ሃሳቡ ስገባ ሥዕል ከክርስትና በፊት በቤተ አሕዛብም ሆነ በቤተ አይሁድ የታወቀና ከአምልኮት ጋር የተያያዘ ነበር በቤተ አሕዛብ እንጨት ጠርቦ ደንጊያ አለዝቦ ማምለክ የተለመደ ነበር እንዲያውም የሮማ ነገሥታት አማልክት ተብለው ከመመለካቸው በላይ ከሞቱ በኋላ ሥዕላቸው በደንጊያ እና በእንጨት እየተቀረጸ ሲመለኩ መኖራቸው በታሪክ ይታወቃል ክርስትና በመጣ ጊዜ ከክርስትና ጋር ያጣላቸው ይኸው ልማዳቸው ነው በክርስትና ትምህርት ሲታይ ግን ይህ አምልኮ ጣኦት ነው ይህንን የሥዕል ትምህርት በምናጠናቅቅበት ጊዜ እንግዲህ በቤተ አሕዛብ እንጨትና ድንጋይ ጠርቦና አለዝቦ የሚደረገውን አምልኮ በሰፊው የምናየውና የምንዳስሰውም ይሆናል አሁን ግን የምናልፈው ወደ ሥዕል አገልግሎት ነው ሥዕል በቤተ አይሁድ እንደ አሕዛብ ሳይሆን በታቦተ ሕጉ በጽላተ ኪዳኑ ላይ ሥዕለ ኪሩብን እንዲሰራ ራሱ እግዚአብሔር ሙሴን አዞት ነበር ታድያ እነዚህ የኪሩቤል ሥዕሎች ከታቦቱ አይለዩም ምክንያቱም ታቦት የእግዚአብሔር መገለጫ ዙፋን ስለሆነ የመንበረ ጸባኦት አምሳል ናቸውና የሚሳሉትም እንደሚናተፍ አውራ ዶሮ ሆነው ነው የንጉሥ አንግቻ ንጉሡ በተቀመጠበት በዙፋኑ ፊት ነቃ ቆጣ ብሎ እንደሚቆም እነዚህም ኪሩቤል በታቦቱ ላይ ባለው የእግዚአብሔር መገለጫ ዙፋን እንዲሁ ናቸው ከዚህ በመቀጠል የኪሩቤልን አገልግሎት ማወቅ ለምትፈልጉ ኪሩቤል የእግዚአብሔር መቀመጫዎችና የእግዚአብሔርንም መኖርያ የሚጠብቁ ምሳሌዎች መሆናቸውን የሚገልጹ ጥቅሶችን እሰጣችኋለሁ ፣ መጽሐፍቅዱሳችሁን ከፍታችሁ አንብቧቸው 1ኛ ሳሙኤል 4 ፥ 4 ፤ 2ኛሳሙኤል 6 ፥ 2 ፤ 2ኛ ነገሥት 19 ፥ 15 ፤ መዝሙር 99 ፥ 1 ከዚህ የተነሳ ሙሴ ሁለት ኪሩብ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ ፣ ኪሩቤልን በታቦቱ ላይ እንዳሉ አድርገህ ሳላቸው ወይንም ቅረጻቸው ስለተባለ ብቻ እኛም ተነስተንና ይህንኑ ቃል መነሻ አድርገን በእግዚአብሔር ስምም ይሁን በሰዎች እንዲሁም በመላዕክት ስም የምንስለውና የምንቀርጸው ምስልም ሆነ ሥዕል የለም ሙሴ ሥራልኝ የተባለበትን ምክንያት ተነጋግረናል እኛ ግን ሥዕልን የምንስልበትም ሆነ የምንቀርጽበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደገናም መጽሐፍቅዱሳዊ የሆነ መረጃ የለንም እንደውም የተባልነው ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሆኑልህ በላይ በሰማይ ካለው ከምድርም በታች በውሃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ አትስገድላቸው አታምልካቸውም………….. ነው ዘጸአት 20 ፥ 1 _ 6 ፤ ከዚህም ሌላ እግዚአብሔር በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ መልክ ከቶ አላያችሁምና እጅግ ተጠንቀቁ እንዳትረክሱ የማናቸውንም ነገር ምሳሌ……………. እንዳታደርጉ ነው የተባልነው እንደውም እግዚአብሔር ከሰማይ ሁሉ በታች ላሉት አሕዛብ ሁሉ የሰጣቸውን ጸሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንና የሰማይን ሠራዊት ሁሉ ባየህ ጊዜ ሰግደህላቸው አምልከሃቸውም እንዳትስት ተጠንቀቅ ነው ያለን ዘዳግም 4 ፥ 15 _ 20 ወደ አዲስ ኪዳኑ የአምልኮ ሥርዓት ሄደን ስንመለከት ደግሞ በሐዲስ ኪዳንም አብ የሚሻው አምልኮ የእውነትና የመንፈስ አምልኮ ነው እንጂ በሥዕልና በምስል ላይ የተመረኮዘ አምልኮ አይደለም ስለዚህም እግዚአብሔር መንፈስ ነው የሚያመልኩትም በእውነትና በመንፈስ ያመልኩታል አብም እንዲህ ያለውን ይሻልና ተብሎ ነው የተጻፈልን ዮሐንስ ወንጌል 4 ፥ 23 እና 24 የብሉይ ኪዳኑ የእሥራኤል መሪ ሙሴ ሁለት ኪሩብ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ ወይም ቅረጽ ፣ ሣል ቢለውም እንኳ ሙሉ የሆነ አምላካዊ መረጃ አግኝቶ የእግዚአብሔርንም ዓላማ መሠረት አድርጎ ሙሉ የሆነ ነገር ነው የሠራው ከዚህ የተነሳ ሥዕለ ኪሩብን ሥሎ ወይንም ቀርጾ ታቦትን ሳይሠራ አልቀረም የኪዳኑን ታቦት ሰርቶ ደግሞ መቅደሱንና ማደርያውን አልሰራም አላለም ሁሉንም ለእግዚአብሔር ዓላማ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሠራ ትምህርቱን ወደፊት የምንመጣበትና በሰፊው የምንዳስሰውም ጉዳይ ስለሆነ እያብራራነው እንሄዳለን ስለዚህ ሙሴ ገና ለገና ኪሩብን ቅረጽ ፣ ሣል ወይንም ስራ ተብሏልና እኛም እንዲሁ ተነስተን ሥዕልን እየሳልንና እየቀረጽን ካልቻልንም ደግሞ ከየገበያው ፈረንጅ ለልዩ ልዩ ዓላማ የሳላቸውን ሥዕሎችና ፎቶዎች እየሰበሰብን የአምላካችን የእግዚአብሔር ፣ የቅዱሳን መላእክትና የቅዱሳን ሰዎች ሥዕለ አድህኖ ነውና ምሥጋናና ስግደት ልንሰጣቸው ይገባል ስንል የተለየ ቦታ አስቀምጠንና መጋረጃ ጋርደን የምንሰግድለት ምንም ዓይነት ሥዕልና ምስል ለእኛ የለንም እንዲህ ማድረግ ደግሞ ጣኦትን ማምለክ ስለሆነ እነዚህ ሰው ሰራሽ የሆኑ ምስልና ሥዕሎችን ከፊታችን ማራቅና ገለል ማድረግም ያስፈልገናል ስግደትም ለእግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ የምንሰግደው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው ከእግዚአብሔር ውጪ ለሌላ ስለማንሰግድ ይህ ሲገባን ደግሞ ያን ጊዜ እግዚአብሔርን በእውነትና በመንፈስ ማምለክ እንጀምራለን በተደባለቀው ነገር ውስጥ ግን እግዚአብሔርን ብንጠራው እግዚአብሔር በዚያ አይገኝም እግዚአብሔር ብቻውን አምላክ ስለሆነ እኛም የምናመልከው ብቻውን ለሆነ አምላክ ክብር በመስጠት ነው 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1 : 17 ፣ ወደ ሮሜ ሰዎች 16 : 25 _ 27 ፣ 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6 : 16 እንደገናም ስሩ ወይንም አድርጉ ያልተባልነውን መስራት የለብንም ፣ መስራትም ሆነ ማድረግም አንችልም ትምህርቱ የሚያስተምረን እንግዲህ ይህንን እውነት ነው የክፍል ሁለት ትምህርት ይቀጥላል ጌታ ዘመናችሁን ይባርክ ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ http://www.Facebook.com/yonas.asfaw.39 https://www.youtube.com/yF76GIi_rCQ yonasasfaw8@gmail.com

No comments:

Post a Comment