መጽሐፍቅዱስ በራሱ ሲተረጐም
Let the Bible interpret Itself
ክፍል ሁለት
መጽሐፍቅዱስን በራሱ የምንተረጒምበት ፣ ከሰዎች ፣ ከነገሮች
፣ ከሁኔታዎች እና ከመሣሠሉት ጋርም የማናያይዝበት ምክንያት በ2ኛ ጴጥሮስ 1 ፥ 20 ላይ በተጠቀሰው ቃል መሠረት ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ ስላልመጣና ይህንን የትንቢት ቃል ቅዱሳንም በመንፈስቅዱስ ተነድተው ስለተናገሩት ነው የክፍሉ ሃሳብ እንዲህ ይለናል ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ በማለት ይጠቁመናል ለዚህም ነው ጴጥሮስ አሁንም ከገናናው ክብር በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና
እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፥ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ በማለት የተናገረው ስለዚህ ይህ የትንቢት ቃል በቅዱሱ ተራራ ከተነገረው ከገናናው ክብር በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው ከሚለው ከዚያ ድምጽ ሳይቀር የሚበልጥ ነው ይህን የትንቢት ቃል ማለት የእግዚአብሔርን ቃል ከምንም ሆነ ከማንም ጋር የምናነጻጽረውና የምናወዳድረው አይደለም ይህ የትንቢት ቃል ማለት የእግዚአብሔር ቃል ከሁሉ የሚበልጥ ስለሆነ በጨለማ ስፍራ የሚበራ መብራት ነውና በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህንኑ ቃል እየተጠነቀቅን እናደርጋለን ይህ ማለት ለገዛ ራሳችን ተርጒመን የምንታዘዘዘውና የምናከናውነው ነገር አይደለም ከዚህም ሌላ ለሌሎች ማለት ለነእገሌና ለነገሊት ነው እያልን ተርጉመን የምንሰጠው እነርሱም ብቻ እንዲያከናውነት የምናደርገው አይሆንም ይህ የትንቢት ቃል በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈና በእግዚአብሔር ፈቃድ የመጣ በመሆኑ ቃሉ ደረጃ በደረጃ ወደ ሕይወታችን በመጣ ጊዜ ሁሉ ለትምህርታችንና ለተግሣጻችን የተጻፈ ነውና
የምናደርገው ማለት የምንታዘዘው እየተጠነቀቅን ነው ሮሜ 15 ፥ 4 ፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 3 ፥ 15 እና 16 እንደገናም መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን ትሳደባለህ ትሉታላችሁን ? ስለሚለን መጽሐፉም ሊሻር ስለማይችል መጽሐፉ ያለንንና የሚለንን ሁሉ ነን ዮሐንስ ወንጌል 10 ፥ 35 ዮሐንስ መጥምቁን እንኪያስ ማን ነህ ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ ? ባሉት ጊዜ የሰጠው መልስ እጅግ አስደናቂ ነበር የነቢዩን የኢሳይያስን ትንቢታዊ ቃል በመጥቀስ የመጽሐፉ ቃል አይሻርምና እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ ይለናል ዮሐንስ ወንጌል 1 ፥ 22 እና 23 መሰከረም አልካደምም፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ የተባለለትም ለዚህ ነው ዮሐንስ ወንጌል 1 ፥ 20 ወገኖቼ ምስክርነታችን የእግዚአብሔር ቃል የሚደግፈው የሚያጸድቀው እና የሚያረጋግጠው በሚሆንበት ጊዜ ትክክለኛ ትርጉሙንና ቦታውን የያዘ ስለሚሆን እውነተኛ ነው መጻሕፍት ያልመሰከሩለት በሚሆንበት ጊዜ ግን በሬ ወለደ ዓይነት ይሆንና
ለብዙዎች የመሳት ፣ የማሳሳትም ምክንያት ይሆናል ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር ከዚህ ዓይነቱ የኲሸት አሠራር ይጠብቀን በቃሉ እንደምንመለከተው አሁንም ለመጥምቁ ዮሐንስ ብቻ ሳይሆን ለመሲሁ ለኢየሱስ ሳይቀር መጻሕፍት ምስክሮች ነበሩ ስለናዝሬቱ ኢየሱስ ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል ተብሎለታል ዮሐንስ ወንጌል 1 ፥ 46 እንደገናም በሉቃስ ወንጌል 24 ፥ 44 _ 49 ላይ እርሱም፦ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው በእግዚአብሔር ቃልም የተደገፈ ምስክርነት እንዲኖራቸው እንዲህም አላቸው፦ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ አላቸው ስለዚህ እነዚህ ሐዋርያት በቀረላቸው የአገልግሎት ዘመን ሁሉ የተጻፈውን ቃል ተናገሩ እንጂ የእግዚአብሔርን ቃል ለገዛ ራሳቸው ተርጉመው ለነእገሌ ለእገሌና ለእገሊት ሲሉም የተናገሩበትን ሥፍራ ፈጽሞ አናገኛም ይልቁንም እንደነ ቴዎፍሎስ ላሉ የከበርክ ቴዎፍሎስ ሆይ በማለት ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ ሲሉ ጻፉ ተናገሩ በጥንቃቄም አስተማሩ የሉቃስ ወንጌል 1 ፥ 1 _ 4 ፣ 2ኛ ጢሞቴዎስ 3 ፥ 14 _ 17 በመሆኑም ታድያ መጽሐፉም ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን የሚለን ለዚህ ነው 1ኛ ጴጥሮስ 4 ፥ 11
የእግዚአብሔር ቃል ሕይወታችንን ፣ ኑሮአችንንና አገልግሎታችንን ሁሉ የሚቀድስ ነው በመሆኑም ጌታ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ለእኛም ጭምር እንዲሆን በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው ሲል ማለደልን ዮሐንስ ወንጌል 17 ፥ 17 በመሆኑም በትንቢተ ኢሳይያስ 28 ፥ 9 እና 10 ላይ ደግሞ እውቀትን ለማን ያስተምረዋል ? ወይስ ወሬ ማስተዋልን ለማን ይሰጣል ? ወተትን ለተዉ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው ይለናልና በቃሉ ዙርያ ተቀምጠን ቃሉን ለመማር ባለን ፍላጎት ሁሉ ጡትን ከመጣል ወተትንም ከመተው ጀምሮ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ጥቂት በዚህ እና ጥቂት በዚያ በቃሉ እውቀት ልናድግ ፣ ሕይወታችንን አገልግሎታችንንና ኑሮአችንንም ጭምር በዚሁ በቃሉ ልንቀድስ ይገባል ጥቂት በጥቂት የሆነ እድገት ጊዜውን ጠብቆ ወደ ሙሉ እድገት ይወስደናል ያን ጊዜ መጽሐፍቅዱሱን በራሱ ልንተረጉም ግራ አንጋባም እግዚአብሔር ለዚህ ይርዳን አሜን
ቀሲስ ዮናስ ጌታነህ
No comments:
Post a Comment