Friday 31 July 2020

“ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች”
“ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች”
የመጽሐፍ ቅዱስዋ ኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በርካታ ተረቶች እውቅና
አግኝተዋል፡፡መሠረት አልባ የሆኑ አፈታሪኮች
እውነት ተደርገው ተቆጥረዋል፡፡እውነትም
ተገፍቷል፡፡በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ክስተቶች
ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በመያያዝ ቀርበዋል፡፡
ተተርከዋልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አዲስ ኪዳንና
ብሉይ ኪዳን በመባል በሁለት ይከፈላል፡፡ ብሉይ
ኪዳን ከክርስቶስ በፊት የተፃፈ የአይሁዶች
መጽሐፍ ሲሆን አዲስ ኪዳን ከክርስቶስ በኋላ
የተፃፈ የክርስቲያኖች መጽሐፍ ነው፡፡ ስለ ብሉይ
ኪዳን የክርስቲያን ምሑራን እንዲህ ሲሉ
ጽፈዋል፡- “ብሉይ ኪዳን ረጅም ዕድሜ ያለው
መጽሐፍ ነው፡፡በ1400 ዓመተ ዓለም አካባቢ
ሙሴ የመጀመሪያዎቹን አምስት መጻሕፍት መፃፍ
ጀመረ፡፡ይህም ከ3500 ዓመታት ያህል በፊት
ማለት ነው፡፡የመጨረሻው የብሉይ ኪዳን
መጽሐፍ የተፃፈው በ400 ዓመተ ዓለም ገደማ
ነበር፡፡” (ቲም ፊሎስ፣ የብሉይ ኪዳን የጥናት
መምሪያና ማብራሪያ 1ኛ መጽሐፍ፣የኤስ አይ
ኤም ስነ ፅሑፍ ክፍል፣ መጽሐፍ ቅዱስን
መሠረት ያደረጉ መፃሕፍት፣ አ.አ.፣1998፣ገፅ
12)
በአማርኛውና በእንግሊዝኛው የመጽሐፍ ቅዱስ
ትርጉም ውስጥ “ኢትዮጵያ” የሚል ቃል ይገኛል፡፡
ነገር ግን ብሉይ ኪዳን በተፃፈበት በዕብራይስጡ
ቋንቋ መጽሐፍ ዉስጥ አንድም ስፍራ ላይ
“ኢትዮጵያ/ኢትዮጵያውያን” የሚል ቃል
አይገኝም፡፡”ኢትዮጵያ” /ኢትዮጵያውያን” በሚል
በበተረጎመው ቃል ምትክ በዕብራይስጡ
መጽሐፍ ቅዱስ ዉስጥ የሚገኘው ቃል “ኩሽ/
ኩሻውያን” የሚል ቃል ነው፡፡ (Barnes’
Notes, Bible Commentary, Electronic
Database, Copyright © 1997 by Bible
soft; The New Unger’s Bible
Dictionary Originally Published by
Moody Press of Chicago, Illinois,
Copyright© 1988)
“ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ሲሆን
ትርጉሙ ፊታቸው በፀሐይ (ተቃጥሎ) የጠቆረ
ማለት ነው፡፡(E.A. Wallis Budge, A
history of Ethiopia, Nubia and
Abyssinia, volume one,1928,page5)
“ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ
በስያሜነት የተሰጠው ከክርስቶስ ልደት በፊት
በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነበር፡፡ስያሜውን
በፀሐይ ተቃጥለው የጠቆሩ ለማለት በግሪክ
ቋንቋ “ኢትዮጵያ” ሲል የሰጠው ማኒቶ
(MANETHO) ነበር፡፡ማኒቶ ግብጻዊ የታሪክ
ምሁርና ካህን ነበር፡፡ ማኒቶ በሱዳን ሀገር
ተቋቁሞ ለነበረው ለኩሽ ስርወ መንግስት
“የኢትዮጵያውያን ስርወ መንግስት (Ethiopian
dynasty) ሲል ጠራው፡፡ ማኒቶ የሰጠው ስያሜ
ከሱዳን ሀገር (ኑቢያ) በመነሳት በ713(727)
ዓመተ ዓለም ግብፅን ተቆጣጥሮ እስከ 663
ዓመተ ዓለም (ዓ.ዓ) ያስተዳድር ለነበረው
ሥርወ መንግስት ነበር፡፡ ኢንሳክሎፒዲያ
ኢትዮፒካ እንዲህ ይገልጸዋል፡- “የማኒቶ
(የእርሱ የሰየማት) የኢትዮጵያ ስርወ መንግስት
ከዛሬዋ ኢትዮጵያ ጋር ምንም የሚያገናኛት ነገር
የለም፡፡ የጥንቱ “ኢትዮጵያዊያን” የሚለው ስያሜ
የተሰጠው ጥቁር ቀለም ለነበራቸው ለኑቢያ
መሪዎች ነበር፡፡… ከዛሬዋ ኢትዮጵያ ጋር
ማንኛውንም ግራ መገባትን ለማስቀረት
(ኢትዮጵያ የሚለው የተሰጠው) በመጽሐፍ
ቅዱስ ስም “ኩሽ” ይባል ለነበረው ለ25ኛው
የግብፅ ሰርወ መንግስት (ኑቢያ) ለሚለው
ነው፡፡” (Encyclopedia Aethiopica,
volume two, page405)
ግብጽ ኩሽን በ1520 ዓመተ ዓለም ገደማ
ተቆጣጠረች፡፡ከአምስት ክፍለ ዘመን በኋላ
በ1070 ዓ.ዓ ኩሽ ነፃ ወጣች፡፡ ኩሽ ነፃ
መንግስት ሆና በጀበል በርካ በናፓታ
ተመሠረተች፡፡በከፍተኛ ደረጃ በግብፅ ባህል
ተፅእኖ ሥር ወድቃ የነበረ ሲሆን በግብጽ
ይመለክ የነበረው ጣኦት አሙንም ይመለክባት
ነበር፡፡(Encyclopedia Aethiopica ,
volume 3, page 459)
ከላይ እንደተጠቀሰው ግብፅና ኩሽ (ኢትዮጵያ)
ጉርብትና ብቻ ሳይሆን አንዱ ሌላውን
እስከመምራት የዘለቀ ታሪክ አላቸው፡፡የግብፁ
ፒራሚድም አይነት በኩሽ (በሱዳኗ ኢትዮጵያ)
ተገንብቷል፡፡በመጽሐፍ ቅዱስም ግብፅና
ኢትዮጵያን(ኩሽ) በተደጋጋሚ በአንድት
ይጠራሉ፡- “በዚህም ጊዜ የግብፅ ንጉስ
ኢትዮጵያዊው ቲርሐቅ ሊወጋው በመገሥገሥ
ላይ መሆኑን ሶናክሬም ሰማ” (2ኛ ነገሥት 19፡9
እና ኢሳይያስ 37፡9)
መመስረት በፊት የኩሽን ድንበር የሚያሳይ ካርታ
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ200 ዓ.ዓ ብሉይ
ኪዳን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ ተተረጎመ፡፡
ይህም ትርጉም ሴፕቱዋጀንት በመባል የሚታወቅ
ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ትጉም “ኩሽ”
በሚለው የዕብራይስጥ ቃልን “ኢትዮጵያ”
በሚለው በግሪኩ ትርጉም ተካው፡፡(ቴምፌሎስ፣
ገፅ 14)
በአጭሩ ብሉይ ኪዳን መጀመሪያ በተፃፈበት
በዕብራይስጥ ቋንቋ አንድም ስፍራ ላይ
“ኢትዮጵያ” የሚል ቃል የሌለ ሲሆን ያለው
በግሪኩ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ዉስጥ ነው፡፡
ከግብፅ በስተደቡብ በዛሬዋ ሱዳን የነበረችውን
‹‹የኩሽ መንግስት››ን ጥቁሮች ስለነበሩ
ግሪካውያን ጥቁርነታቸውን ለመግለጽ (ፊታቸው
በፀሐይ ተቃጥሎ የጠቆረ) ለማለት በቋንቋቸው
‹‹ኢትዮጵያ›› አሏቸው፡፡መጽሐፍ ቅዱስ (ብሉይ
ኪዳን) ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ሲተረጎም ስለ
ኩሽና ኩሻውያን መንግስትና ሕዝብ በሚናገረው
ሥፍራ ላይ በግሪክ ቋንቋ “ኢትዮጵያ” የሚለው
ቃል ስለተለመደ “ኩሽ” በኢትዮጵያ ተተረጎሙ፡፡
የክርስትና እምነት ምሁሩ ቴም ፌሎስ ይህን
እንዲህ ያጠቃልሉታል፡- “ኢትዮጵያ ወይም
ኩሽ፡- በፅብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ከግብፅ
በስተደቡብ ቀጥሎ የሚገኘው አገር ኩሽ ተብሎ
ይጠራ ነበር፡፡ ኋላም በሴፕቱዋጀንት የግሪክ
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግሪኮች ይህንን ምድር
ኢትዮጵያ ብለው ጠርተዋል፤ ስለዚህ በመጽሐፍ
ቅዱስ ውስጥ ኩሽና ኢትዮጵያ የአንድ ስፍራ
ሁለት ስሞች ናቸው፡፡ የእንግሊዝኛና የአማርኛ
ትርጉም መጽሐፍ ቅዱሶች ለዚህ ምድር
“ኢትዮጵያ” የሚለውን የግሪክ ስም ይጠቀማሉ፡፡
የኩሽ ወይም የኢትዮጵያ ምድር ከአሁንዋ
ኢትዮጵያ ጋር አንድ አይደለም፤ነገር ግን በዓለም
ታሪክ ውስጥ “ኑቢያ” ተብላ ትጠራ የነበረችው
ዛሬ በሰሜን ሱዳን የምትገኝ አገር ነች፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ መልከዓ ምድር መሠረት ኑቢያ
የመጨረሻዋ ደቡባዊ ክፍል ያለችው አገር ነች፡፡
የአሁንዋ ኢትዮጵያ መጀመሪያ ስምዋን ያገኘችው
ከግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፤ነገር ግን ኢትዮጵያ
ወይም ኩሽ ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ከጠራው
ስፍራ ጋር ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ
አይደለችም፡፡ ” (ቴም ፌሎስ፣ የብሉይ ኪዳን
የጥናት መምሪያና ማብራሪያ 1ኛ መጽሐፍ፣ገፅ
68)
የታሪክ ምሁሩ በጅ እንዲህ ይላል “The
country of the “burnt faces” is none
other than the “Sudan” (ፊታቸው
የተቃጠሉ የተባለው ሀገር ሌላ ሳይሆን ሱዳን
ነች) (A history of Ethiopia, Nubia and
Abyssinia, Vol. 1, page 5)
ኢትዮጵያ እና አክሱም
ከላይ እንደተጠቀሰው ከክርስቶስ ልደት በፊት
በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማኒቶ ነበር
ለመጀመሪያ ጊዜ በግሪክ ቋንቋ ‹ኢትዮጵያ›
የሚለውን ስያሜ የተጠቀመው፡፡የጥንት
ግሪካውያን ጸሐፍት ስለኩሽ ሥርወ መንግስት
(ኢትዮጵያ) በአስገራሚና አስደናቂ እሳቤ ላይ
የታሞላ አመለካከት ነበራቸው፡፡ኢንተርናሽናል
እስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ
እንደሚለው የጥንት ግሪካውያን የኢትዮጵያን
ጂኦግራፊ መረዳት ተስኗቸው ኢትዮጵያ ድንበሯ
እስከ ህንድ እንደሚደርስ ይጽፉ ነበር፡፡/
International Standard Bible
Encyclopedia, Electronic Database
Copyright © 1996 by Bible Suft) ልክ
እንደዚሁ ግራ ከመጋባታቸው የተነሳ የዛሬዋን
(የኛዋን) ኢትዮጵያ “ህንድ” ብለው ሲጠሯትም
እናነባለን፡፡ የአባይ ወንዝ ከዛሬዋ ኢትዮጵያ
እንደሚነሳ ለመግለፅ በአንደኛው መቶ ክፍለ
ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የሲሲሊው
ዲዮዶረስ “የአባይ ወንዝ የሚነሳው ከህንድ ሀገር
ነው” ሲል ጽፏል፡፡ (Encyclopedia
Aethiopica, Volume 3, page 146)
በመጽሐፍ ቅዱስ “ኩሽ” ተብላ የተጠራችውና
በግሪክ ቋንቋ “ኢትዮጵያ” የሚል ትርጓሜ
ያገኘችው የኩሽ (ኢትዮጵያ) መንግስትን ታሪክ
ምሁራን በሦስት ጊዜያት ይከፍላሉ፡፡እነርሱም
የናፓታን (751-542 ዓ.ዓ) ፣የሜሮዌ (542
ዓ.ዓ–339/350 ዓ.ል) እና የኤክስ ቡድን (x-
group) ናቸው፡፡ (Frank M. Snowden,
Blacks in Antiquity: Ethiopians in the
Greco-Roman Experience, page 113)
መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት 10፡6 ላይ
እንደገለፀው ኩሽ ከካም ልጆች አንዱ ነበር፡፡
እርሱም በተራው ሳባ፣ኤውላጥ፣ሰብታ፣ራዕማ እና
ሰበቃታ የሚባሉ ልጆችን ወልዷል፡፡ የኩሽ ልጆች
(ዘሮች) ወደተለያየ የዓለም ክፍል የተበተኑ
ሲሆን የኩሽ ነገዶች በሱዳንም እንዲሁ ትልቅ
ማህበረሰብ ሆነው ነበር፡፡ከፍ ብሎ
እንደተጠቀሰው ግብፃውያን ኩሽን በ1520
ዓመተ ዓለም ገደማ ተቆጣጥረው ከአምስት
ክፍል ዘመናት በኋላ በ1070 ዓ.ዓ ነፃ
ወጥታለች፡፡ ከዚህ በኋላ የኩሽ ስርወ መንግስት
ተመሥርቷል፡፡(Morkot, Roger G. “on the
Priestly Origin of the Napatan
Kings:The Adaptation, Demise and
Resurrection of IDEAS IN Writing
Nubian History” in O’connor, David
and Andrew Reid, eds, Ancient Egypt
in African (Encounters with Ancient
Egypt) (University College London
Institute of Archaeology publication,
page151)
በ727 ዓ.ዓ ገደማ የኩሽ ስርወ መንግስት ንጉስ
ፒየ (piye) 25ኛውን የግብፅ ስርወ መንግስት
(25th Dynasty of Egypt) ወረረ፡፡ እስከ
653 ዓ.ዓ ግብፅንም ገዛ፡፡የዚህ የ25ኛው
ግብፅ ስርወ መንግስት መቀመጫው ናፓታ
(Napata) ሱዳን ነበር፡፡በፒየ እና ቲርሀቅ ጊዜ
ይህ ስርወመንግስት የእድገት ማማ ደርሶ ነበር፡፡
ቲርሀቅ ግማሽ እድሜውን ግብፅን ሲገዛ ያሳለፈ
ሲሆን ከአሦራውያውን ጋርም ተዋግቷል፡፡በ674
ዓ.ዓ በኢሳሀርዶን የተመራውን የወራሪዎቹን
የኦሦራውያን ጦር አሸንፏል፡፡ሆኖም ከሦስት
ዓመታት በኋላ ተሸንፎ ግብፅን ለቆ ለመውጣት
ተገዷል፡፡(Kendall, T.K. Napatan
Temples; a case study form Gebel
Barkal. The mythological Nubian
origin of Egyption Kingship and the
formation of the Napatan state. 10th
International conference of Nubian
studies, 2002).
ኩሽ (በግሪክኛ ኢትዮጵያ) ግብፅን ትገዛ
ስለነበረበት ጊዜ የሚያወሱ የመጽሐፍ ቅዱስ
ጥቅሶች አሉ፡፡ለምሳሌ ስለቲርሐቅ እንዲህ
ተጠቅሷል፡- “በዚህም ጊዜ የግብፅ ንጉሥ
ኢትዮጵያዊው ቲርሐቅ፣ ሊወጋው በመገሥገሥ
ላይ መሆኑን ስናክሬም ሰማ” (2ኛ ነገሥት 19፡9
እና ኢሳይያስ 37፡9)
መጽሐፍ ቅዱስ በዘኁልቁ ምዕራፍ አስራ ሁለት
ቁጥር አንድ ላይ እንደሚገልጸው ነቢዩ ሙሳ
(ሙሴም) (ሰላም በርሱ ላይ ይሁንና) በግብፅ
በነበረበት ጊዜ ኩሻዊት (ኢትዮጵያዊት) ሚስትን
አግብቷል፡፡ የኩሽ ስርወ መንግስት መቀመጫ
ናፓታ በ300 ዓ.ዓ ወደሜሮዌ ተዘዋወረ፡፡
ኢንሳይክሎቲዲያ ኢትዮፒካ በ3ኛ ጥራዝ በገጽ
936-937 ላይ እንደሚገልጸው ሜሮዌ
የምትገኛው ከዛሬው የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም
በስተሰሜን በ180 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡
በግብፅ ተፅእኖ የተነሳ በሜሮዌ ቁጥራቸው
ከሁለት መቶ(200) በላይ ፒራሚዶች
ተሠርተዋል፡፡እነዚህ ፒራሚዶች በሦስት አይነት
የተከፈሉ ሲሆን ምሁራን “ኑቢያን ፒራሚድስ”
ብለው ይጠሯቸዋል፡፡ እነዚህ ፒራሚዶች
በመጠን ከግብጹ ፒራሚዶች ይለያሉ፡፡
በሜሮዌ የሚገኙ የኑቢያ ፒራሚዶች
የኩሽ መንግስት መቀመጫ የነበረችው ሜሮዌ
ንግስቶች የነበራት ሲሆን ሁሉም በወል ስማቸው
በክንዳኬ (ሕንዳኬ) ይጠሩ ነበር፡፡በሜሮዌ
ከነበሩት ክንዳኬዎች (ንግስቶች) ውስጥ
ከ345-332 ዓ.ዓ ከነገሰችው ፔሌክ አንስቶ
እስከ ላሂዲማኒ(306-314 ዓ.ል) ድረስ
ከነበሩት መካከል የአስራ አንዱ ማንነት ሊታወቅ
ችሏል፡፡ከነዚህ መካከል በሐዋርያት ሥራ
ምዕራፍ ስምንት ቁጥር ሀያ ሰባት(8፡27) ላይ
የተጠቀሰችው የኩሻውያን (ኢትዮጵያዊያን)
ንግስት ክንዳኬ የሚያወሳ የአርኪዮሎጂ መረጃ
በሱዳን ካጋ ተገኝቷል፡፡ኢንተርናሽናል እስታንዳርድ
ባብል ኢንሳይክሎፒዲያ እና ዊኪፒዲያ
እንደሚገልጹት እ.ኤ.አ. በ1834 በጊየሴፒ
ፈርሊኒ (Giuseppe Ferlini) የተለያዩ እቃዎች
የተገኙ ሲሆን ጌጣጌጦችም ይገኙበታል፡፡አሁን
በበርሊን እና ሙኒክ (ጀርመን) ሙዚየም
ይገኛሉ፡፡እ.ኤ.አ 1844 በአርኪዮሎጂስቱና
አሳሹ በካርል ሪቻርድ ሊፐሲየስ(Karl Richard
Lepsius) የተለያዩ ስዕሎች እና በርካታ የጥንት
መረጃዎች ተገኝተዋል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ በሐዋርያት ሥራ 8፡27 ላይ
“እነሆ የኢትዮጵያ (ኩሽ) ንግሥት የህንዳኬ
ባለሟልና የሀብት ንብረቷ ሁሉ አዛዥ የሆነ አንድ
ኢትዮጵያዊ ጀንደርባ አገኘ፡፡” ይላል፡፡ ይህ
ኢትዮጵያዊ ግለሰብ እየሩሳሌምን ሊሳለም
እንደሄደ ተጠቅሷል፡፡ይህ ክስተት እ.ኤ.አ
37(ሰላሳ ሰባት) የተፈጸመ ነበር፡፡ይህ የአይሁድ
እምነት ተከታይ ኩሻዊ ግለሰብ ለጸሎት ወደ
ኢየሩሳሌም ሄዶ በዚያ በኢየሱስ ተከታይ
በተሰበከበት ጊዜ የአክሱም ስርወ መንግስት
ክርስትናን ልትቀበል ገና ሦስት መቶ(300)
ዓመታት ይቀራት ነበር፡፡የአይሁድ እምነትም
በአክሱም አልነበረም፡፡አክሱማውያን ጣኦት
አምላኪዎች ነበሩ፡፡ይህን የሚያረጋግጡ
በራሳቸው በአክሱማውያን መሪዎች የተጻፉ
በርካታ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ያረጋግጣሉ፡፡
በሐዋርያት ሥራ 8፡27 የተጠቀሰችው ሕንዳኬ
(ክንዳኬ) የሜሮዌ ንግስት መሆኗን በርካታ
ምሁራን ገልጸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ገና ተፅፎ
ከመሠራጨቱ በፊት እ.ኤ.አ. በ79(ሰባ ዘጠኝ)
የሞተው ፕሊኒ (Pliny) ክንዳኬ የተባለቸው
የሱዳኗ ሜሮዌ ንግስት እንደነበረች ጽፏል፡፡
(The Dictionary of Ethiopian
Biography, from early times to the
end of Zagwe Dynasty, C. 1270 AD.,
Institute of Ethiopian Studies, Addis
Ababa University, 1975, volume
one ,PAGE 43)
ለሜሮዌዋ ንግስት ክንዳኬ አማኒቶሪ የተሰራ
(ይህ በጀበል ባርካ የሚገኘው ስፍራ በዩኒስኮ
በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ነው፡፡)
ከኩሽ መንግስት (ኢትዮጵያ) በኋላ ዘግይቶ
በዛሬዋ ሰሜን ኢትዮጵያ(ትግራይ) ከክርስቶስ
ልደት በፊት በ8-7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን
የደአማት መንግስት ተመስርቶ ነበር፡፡ዋና
ከተማው የሃ እንደሆነ ይታመናል፡፡ሆኖም
ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ክፍለ
ዘመን ወድቃለች፡፡ወደ ተከፋፈሉ ትናንሽ
መንደርነትም(አከባቢነት) ተቀየረች፡፡ብዙም
ሳይቆይ ወደ አከባቢው ከክርስቶስ ልደት በፊት
ከ4ኛው-5ኛው ክፍለ ዘመን ከየመን ሀገር
የደቡብ አረቢያ ስደተኞች (ሳባውያን) መጡ፡፡
በአከባቢው ሰፍረው መኖር ጀመሩ፡፡እንደ ከፊል
ምሁራን እሳቤ የአክሱም መንግስት ከክርስቶስ
ልደት በኋላ በአንደኛው ክፍለ ዘመን በስደተኞቹ
ሳባውያን ተመሠረተች፡፡ሌሎቹ ምሑራን ግን
አክሱም የደአማት ሥርወ መንግስት ቅጥያ
እንደሆነች ያምናሉ፡፡(Stuart Munro-Hay,
Aksum: An African Civilization of Late
Antiquity. page 57 )
ከደቡብ አረቢያ (የመን ሀገር) የመጡት
ሳባውያን ስደተኞች በሀገራቸው ይመለኩ የነበሩ
የጣኦት አምልኮ እምነቶችን ይዘው የመጡ ሲሆን
(አፍሮዳይት)፣ ቬነስ (የግሪኮቹ)፣ የጨረቃ
አምላክ እና የፀሐይ አምላክ የተሰኙ ጣኦታትም
ይገኙባቸዋል፡፡አክሱማውያንም ጣኦት አምላኪ
የነበሩ ሲሆን ይህንን የሚያረጋግጡ በርካታ
የአርኪዮሎጂ መረጃዎች ተገኝተዋል፡፡ለምሳሌ
በየሃ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ5ኛ መቶ ክፍለ
ዘመን እንደተሠራ የሚገመተው አል-ሙቃህ
ይገኝበታል፡፡(The church of Ethiopia A
Panoroma of History and Spiritual,
Ethiopian Orthodox church, Addis
Ababa, 1970, Page 1-2)
ከክርስቶስ በኋላ በመጀመሪያ ክፍለ ዘመን
“አክሱም” የሚለው ሲያሜ ተጀመረ፡፡ እ.ኤ.አ
በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተጻፈው
‹‹ፕሪፕለስ ኦፍ ኤሪቲሪያን ሲ›› (Periplus of
the Erythraean Sea) ላይ አክሱም
ተጠቅሳለች፡፡በዚህ ጽሑፍ ላይ ዞስካሊስ የተሰኘ
የአክሱም መሪ የአዱሊስን ወደብ
እንደሚያስተዳድር ተጠቅሷል፡፡ይህ ‹‹ዞስካልስ››
የሚባለው የመጀመሪያው የአክሱም መሪ
እንደሆነ የሚታመን ሲሆን ንግስናው እ.ኤ.አ በ
100(መቶ) አካባቢ ነበር፡፡(Stuart Munro-
Hay, Aksum: An African civilization of
late Antiquity, page 57) ከክርስቶስ ልደት
በኋላ በ2ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቶሌሚ አክሱም
የአክሱማያን መንግስት መቀመጫ እንደሆነች
ጽፏል፡፡ (Encyclopedia Aethiopica,
Volume one, page186)
እ.ኤ.አ. በአንደኛው ክፍለ ዘመን የኤርትራ ባህር
አከባቢ ካርታ
አክሱምና የመን ታሪካዊ ቁርኝት ያላቸው ሲሆን
እንደ ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ ገለጻ በየመን
ጀበል ሁቡሽ እና ዋዲ ሁቡሸ የሚሰኙ ስፍራዎች
ይገኛሉ፡፡ይህ የአክሱምንና የየመንን ቅርርብ
አመላካች ተደርጎ ተወስዷል፡፡( Encyclopedia
Aethiopica, volume one, page 59)
እ.ኤ.አ. 200(ሁለት መቶ) አክሱም ግዛቷን
ለማስፋፋት በማለም ወደ ደቡብ አረቢያ (የመን)
በአል-መዓፊር ኃይሏን አስገባች፡፡ከሳባ እና
ሂመየር ጎሳዎች ጋር ህብረት ከፈጠረች በኋላ
በየተራ ሁለቱንም አጥቅታለች፡፡ አከባቢውንም
ማስገበርም ቻለች፡፡ የአክሱሙ ንጉሥ ‹‹ገደረተ››
እና ‹‹አዝባህ›› በሦስተኛው ክፍለ ዘመን
መጀመሪያ (እ.ኤ.አ 210) ወደ የመን ጦር
እንዳዘመቱ በየመን የተገኙ የአርኪዮሎጂ
መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡በየመን የተገኘው
የድንጋይ ላይ ጽሁፍ ‹‹ንጉስ ገደረት የአክሱምና
የሀበሻ ነጋሺ” ሲል ይጠራል፡፡በተመሳሳይ
በትግራይ የተገኘውም የድንጋይ ጽሑፍ “ገደረ
ንጉሠ አክሱም” ሲል ይጠራዋል፡፡
(Encyclopedia Aethiopica, volume
one, page 174)
አክሱም በየመን ሀገር የምታስተዳድረው ግዛት
ካገኘችና የአዱሊስ ወደብ የሞቀ የንግድ
ማዕከል መሆን ሲጀምር በአካባቢው ላይ
ኃያልነት እየተሰማት ሄደ፡፡እ.ኤ.አ ከ260-269
ባለው ጊዜ ውስጥ የአክሱም መሪ ወደ ሱዳን
በመዝለቅ የኩሽ መንግስትን(የኢትዮጵያን) ዋና
ከተማ ሜሮዌን አጠቃ፡፡ማስገበርም ቻለ፡፡ይህች
ከጥንት ጀምር “ኩሽ”/ኢትዮጵያ ተብላ ትጠራ
ለነበረው ሥርወ መንግስት ዋና ከተማ
የነበረችው ሜሮዌ በአክሱም ሥር ወደቀች፡፡
( Encyclopedia Aethiopica, volume 3,
page 459)
የአክሱም መሪ ኩሽን (ካሱ ተብላም ትጠራ
ነበር) ጨምሮ ሌሎች ጎሳዎችን ማስገበር ቻለ፡፡
ወደ ሀገሩ አክሱም ተመልሶ በአዱሊስ አቅራቢያ
በድንጋይ በተሰራ ዙፋን ላይ ድሉን ጽፏል፡፡
በአዱሊስ አሪስ ለተባለው ጣኦት መስዋእት
አደረገ፡፡ ጽሁፉም እንዲህ ይላል፡- “እነዚህን
ሁሉ ጎሳዎች በማስገር እኔ ብቸኛውና
የመጀመሪያው የሀገሬ መሪ ነኝ፡፡ይህም የሆነው
የወለደኝ ታላቁ አምላኬ አረስ (አክሱማውያን
ያመልኩት የነበረው ጣኦት) በዋለልኝ ውለታ
ነው፡፡ ሁሉንም ከሀገሬ ጋር የሚዋሰኑትን ነገዶች
በእርሱ (አሪስ) አማካኝነት ከምስራቅ እስከ
ቅመም ሀገር፣ ከምዕራብ እስከ የኢትዮጵያ
ቦታዎች እና ሳሡ፡፡ በራሴ ግዛት ሥር
አደረግኳቸው፡፡ አንዳንድ ቦታ ራሴ ዘመትኩ፡፡
ሌላው ጋር (የጦር አለቆችን) ላኩ፡፡” (G.W.B.
Huntingford, the Historical Geography
of Ethiopia from the first century A.D
to 1704, page 43)
የአክሱሙ ንጉሱ ከላይ የጠቀስነውን ጽሁፍ
“ይህን ያደረግኩት በ27ኛ የስልጣን ዘመኔ ነው”
ሲል ይቋጫል፡፡ ምሁራን ይህ ንጉስ አፊላስ
የተሰኘው የአክሱም መሪ ነው የሚል እምነት
ያላቸው ሲሆን እ.ኤ.አ በ527 አክሱምን
የጎበኘው የግብፁ ሞነክሴ ኮስመስ ጽሁፉን
‹‹ክርስቲያን ቶፖግፊ ኦፍ ኮስመስ›› በተባለው
መጽሐፉ አስፍሮታል፡፡እ.ኤ.አ በ330 ንጉስ ኢዛና
ኤላሚዳ የክርስትና እምነትን እስከተቀበለበት
ጊዜ ከትኛውም የአክሱም መሪ ጋር ተያይዞ
‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለው አልተጠቀሰም፡፡ ንጉስ
ኢዛና ራሱ በድንጋይ ላይ ባስፃፋቸው ጽሁፎች
ጣኦት አምላኪ በፊትና ክርስትናን ከተቀበለ በኋላ
እንኳን ራሱን “የኢትዮጵያ መሪ ነኝ” በማለት
የዛሬዋን ኢትዮጵያን አልገለጸም፡፡ ለምሳሌ አፄ
ኢዛና ክርስትናን ሳይቀበል በነበረበት ጊዜ
የፃፋቸውን የድንጋይ ላይ ፅሁፎች ስንመለከት
ራሱን የተለያዩ አካባቢዎች ገዢ(ንጉሠ ነገስት)
አድርጎ ሲገልፅ ከነዚህ ውስጥ አክሱም፣ሀበሻ
እና ኩሽን (ካሱን) የተለያዩ ሀገራት አድርጎ ነው
የሚናገረው፡፡እንዲህ ሲል ይገልፃል፡- “ኢዛና
የአክሱም፣ሂመየር(የመን ሀገር)፣ሳባ(የመን ሀገር)
፣ሀበሻ፣ራይዳን(የመን ሀገር)፣ሳልሂን(የመን
ሀገር)፣ቤጃ (ኤርትራ)፣ካሱ(ኩሽ-ሱዳን) እና
ሴይሞ (ትግራይ-እንደርታ) ንጉስ፣ንጉሠ ነገስት
የማይሸነፈው የመህሬም (ጣኦት) ልጅ፡፡የቤጃ
ሰዎች(በደዊን) አመፁ፡፡ልንወጋቸው
ወንድሞቻችንን ሲዛናን እና ሀደፋን
ላክንባቸው” (Historical Geography of
Ethiopia, page 48)
ኢዛና ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት
ከ260-269 ባለው ጊዜ ኩሽ (ካሱ) ለአክሱም
ገባር መሆኗን ከላይ ጠቅሰናል፡፡ሆኖም ሌሎች
ግዛቶቹን ጨምሮ “የካሱ/ኩሽ/ ንጉስ በማለት
ነው ኢዛና ባብዛኛው ራሱን ሲጠራ የምናየው፡፡
ከላይ የጠቀስነውንና በግዕዝ ቋንቋ በተጻፈው
ጽሑፉ ኢዛና በቤጃ ሰዎች ላይ ያደረገውን ዘመቻ
ሲተርክልን ራሱን የተለያዩ አካባቢዎች መሪ
አድርጎ ሲገልፅ ከነዚህም ውስጥ አንዷ “ሀበሻ”
እንደሆነች አስፅፏል፡፡ይህንኑም ዘመቻ በቀድሞ
የየመናውያን የሳባ ቋንቋ /በኢፒግራፊክ ሳውዝ
አረቢያን /Epigraphic South Arabian/
ባስፀፈውም ላይ ኢዛና ራሱን የተለያዩ
አካባቢዎች መሪ አድርጎ ይገልፃል፡፡ ንጉስ ኢዛና
ይህንኑ የቤጃ ዘመቻውን በግሪክ ቋንቋ(DAE4)/
DAE=Deutsche Aksum Expedition/
ያስፃፈ ሲሆን አጠቃላይ ይዘቱ አንድ ሆኖ
“ሀበሻ” በሚለው ስፍራ ለመጀመሪያ ጊዜ
“ኢትዮጵያ” በሚል ትርጉም ተተክቷል፡፡
(Huntigford, The Historical Geography
of Ethiopia, page48-49)
አጼ ኢዛና በግሪክ ቋንቋ ያስጻፉትበት ድንጋይ
አጼ ኢዛና የጣኦት አምልኮውን ትቶ ክርስቲያን
ከሆነ በኋላ እ.ኤ.አ በ356 አማጽያንን
ለማጥቃት ሱዳን ዘምቶ በኩሽ(ካሱ) ጥቃት
ፈፅሟል፡፡ይህንንም ድሉን ‹‹ክርስቲያን
ኢንስክሪፕሺን›› (Christian inscriptions)
ተብሎ በሚታወቀው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ኢዛና
ራሱን የሰማይ አምላክ (እግዚአ ሰማይ) እና
የምድር አምላክ (እግዚአብሔር) በማለት
በሚያመልከው አምላኩ ስም ድልን
እንደሚጎናፀፍ ይገልፃል፡፡ የኢዛናን መልዕክተኞች
በመተናኮላቸውና በማመፃቸው ምክንያት ወደ
ኑቢያ (ኩሽ) እንደዘመተም ይናገራል፡፡ “ኑቢያውን
ሲያምፁ የሁሉ ጌታ በሆነውን ኃይል ኖባ ላይ
ጦርነት አካሄድኩ” ሲል ይገልፃል፡፡ ኢዛና ሜሮዌ
ውስጥ ባለችው አጥባራ ላይ ሲደርስባቸው
አማጽያኑ ሸሹ፡፡ለ23 ቀናት አሳዷቸው
አጠቃቸው፡፡ሕዝቡንም ጨፈጨፈ፡፡ ጀልባቸውን
አሰጠመ፡፡ ኢዛና በራሱ አንደበት “በድንጋይ
የተሠራውን ከተማቸውን አቃጣልኩ” ሲል
ጽፏል፡፡ (Historical Geography of
Ethiopia , page 55-56)
በሱዳን ሀገር ሜሮዌ (ኩሽ) የተገኙ
በአርኪዮሎጂ መረጃዎች ኢዛና ወደዚያ
መዝመቱን አረጋግጠዋል፡፡ ኢንሳይክሎፒዲያ
ኢትዮፒካ(ይህ ኢንሳይክሎፒዲያ በተለያዩ
የዓለማችን ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ስለኢትዮጵያ
ጥናት በሚያደርጉ ከ250 በላይ ፕሮፌሰሮቸ ነው
የተዘጋጀው፡፡) በጥራዝ ሦስት በገጽ 939 ላይ
እንዳሰፈረው በሜሮዌ የተገኙ ሁለት የድንጋይ
ላይ ጽሑፎችና ሳንቲም የአክሱም መሪ ኢዛና
ክርስትናን ከተቀበለ በኋላ ሜሮዌን ማጥቃቱን
አረጋገጠዋል፡፡ይህ መረጃ የተገኘው በሜሮዌ
ፒራሜድ አቅራቢያ በግእዝ ቋንቋ የተፃፉና
“የአክሱምና የሂመየር ንጉስ” በሚል በግሪክ
ቋንቋ የተፃፉ ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ ከ260-269 ጀምሮ የአክሱም መሪዎች
ወደ “ሱዳን” (ጥቁር ከሚለው የመጣ ነው)
በመዝመት የኩሽ (ኑቢያን) እንዲሁም በ356
ኢዛና ከፍተኛ ጥቃት ቢፈፅምም ሜሮዌ(ኩሽ)
ሙሉ ለሙሉ በማታንስራራ መልኩ የተመታቸው
በ5ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በአክሱሙ መሪ ታዛና
መሆኑን መረጃ ተገኝቷል፡፡( John Garstan A.
HSAYCE and F.LL .GRIFFITH, Meroe
the city of the Ethiopians, being an
account of a first season’s
excavations on the site, 1909-1910, ,
Oxford at the Claredon Press,
1911,page 3)
ገናና ታሪክ የነበራት ኩሽ (ኢትዮጵያ)
በአክሱማውያን መሪዎች በተደጋጋሚ በደረሰባት
ጥቃት እና በደን ጭፍጭፋ ምክንያት በተከሰተው
ስነምህዳራዊ አደጋ ወድቃለች፡፡ ለመውደቋ
እንደተጨማሪ ምክንያትነት የሚጠቀሱት የሮማ
ንግድ ከሜሮዌ ወደ አዱሊስ ወደብ መዛወሩ እና
የቤጃውያን ወደ አካባቢው መሰደድ ይገኝበታል፡፡
(Encyclopedia Aethiopica, vol. 3,
page 459 and page 937)
የኩሽ መንግስት (ኢትዮጵያ) ፍፃሜዋ ከላይ
ባየነው መልኩ ከተጠናቀቀ በኋላ በግሪክ ቋንቋ
“ፊታቸው በፀሐይ የጠቆረ/ኢትዮጵያ” የሚለውን
ስያሜ በውጭ ሀገር ሰዎች ለአክሱም መሪዎች
መስጠት ተጀመረ፡፡ለዚህ እንደ ተጨማሪ
ምክንያትነት ሊጠቀስ የሚችለው ሜሮዌ(የኩሽ
ዋና ከተማ) በአክሱማውያን እጅ በመውደቋና
እስከ አፄ ካሌብ ዘመን መንግስት(ከክርስቶስ
ልደት በኋላ ስድስተኛ ክፍለ ዘመን) የአካባቢው
ገዢ ስለነበሩ ሊሆን ይችላል፡፡በስደስተኛው ክፍለ
ዘመን የአክሱም መሪ የነበሩት አፄ ካሌብ
ስለድላቸው በግእዝ ቋንቋ ባስፃፉት የድንጋይ
ላይ ጽሁፍ እንደገለፁት የመን ሀገርን፣
ካሱን፣ኑባን ጨምሮ እንደሚገዙ ገልፀው
ራሳቸውን የአክሱማውያንም (ጭምር) መሪ
አድርገው ይገልፃል፡፡ በዚህ በ6ኛው መቶ ክፍለ
ዘመን እንኳን አፄ ካሌብ ራሳቸውን “የኢትዮጵያ
መሪ ነኝ“ ብለው አልገለጹም፡፡(Historical
Geography of Ethiopia, page 63-65)
ነገር ግን አፄ ካሊብ ወደ የመን ነጅራን ሊዘምቱ
ሲዘጋጁ እ.ኤ.አ በ520ዎቹ ወደ አክሱም
የመጣው በግብፅ ሲና ቅድስት ካትሪን ገዳም
(St. Catherine’s monastery) ሞነክሴ
የሆነው ኮስመስ ‹‹ዘ ክርስቲያን ቶፖግራፊ ኦፍ
ኮስመስ›› በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ስለ አክሱም
ጽፏል፡፡በዚህ መጽሐፉ ላይ “ከኢትዮጵያ ዳርቻ
ሁለት ማይል የምትርቀው አዱሊስ (ከተማ)”
ሲል ጠርቷታል፡፡(ኩሽ ሙሉ በሙሉ
ከተደመሰሰችና ከተበታተነች በኋላ ነው ኮስመስ
በ550 ነው መጽሐፉን የጻፈው) ለመጀመሪያ
ጊዜም በውጭ ሀገር ሰዎች ‹‹ኢትዮጵያ››
የሚለውን ስያሜ ለአክሱማውያን ተሠጠ፡፡
አዱሊስም የአክሱማውያን ወደብ እንደሆነችም
ይገልፃል፡፡(The Christian topography of
Cosmas, An Egyptian Monk , Printed
for Hakluyt Society, London, page
55-56)
ምንም እንኳን የአፄ ካሊብ ጦር ወደ የመን
ነጅራን ሲዘምት ቆሞ ያየው ኮስመስ አክሱምን
“ኢትዮጵያ” ሲል ቢጠራትም አፄ ካሌብን ጨምሮ
ከአክሱማውያን መሪዎች ውስጥ የትኛውም
ንጉስ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ሀገሩንም “ኢትዮጵያ”
ሲል አልጠራም፡፡ እስከ አክሱም መንግስት
ዉድቀት ድረስ ይህን የሚያሳይ የዚያ ጊዜ
ማስረጃ የለም፡፡አፄ ካሌብን ጨምሮ በአፄ ኢዛና
ጽሁፍ ላይ “ኢትዮጵያ” እና “አክሱም” የተለያዩ
ሆነው የተገለፁት፡፡በአጼ ኢዛና ጽሑፍ ላይ
“ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል እንኳን የምናገኘው
በግሪክ ባስጻፉት (DAE4) ላይ መሆኑን ከላይ
ማውሳታችን ይታወሳል፡፡ለማጠቃለል
የአክሱማውያን ስርወ መንግስት እስካበቃበት
ድረስ በጊዜው በተፃፈ ጽሑፍ ላይ የትኛውም
የአክሱም መሪ “ኢትዮጵያዊ” እንደሆነ እንዲሁም
የሚገዛትም ሀገር “ኢትዮጵያ” እንደምትባል
የገለጸበት መረጃ የለም፡፡ ኢንሳይክሎፒዲያ
ኢትዮፒካ እንዳገለጸው ሀገራችንን “ኢትዮጵያ”
በማለት መጥራት የጀመሩት የ13ኛ ክፍለ ዘመን
ልሂቃኖች(ኤሊቶች) ነበሩ፡፡(Encyclopedia
AEthipica, volume 2, page397)በአጭሩ
በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰችው “ኢትዮጵያ”
ወይንም በዕብራይስጡ “ኩሽ” በዛሬዋ ኢትዮጵያ
ጋር የተለያዩ ናቸው፡፡
ታሪክን ማሳመር ይሉታል እንዲህ ነው!
ከላይ እንዳየነው የመጽሐፍ ቅዱስዋ “ኩሽ/
ኢትዮጵያ” ከዛሬዋ ውዷ ሀገራችን ጋር
የሚያገናኛት ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በአጋጣሚ
በተፈጠረ የስያሜ ጉዳይ ላይ በመመስረት
በክርስቲያን ታሪክ ጸሐፍት የዛሬዋን ኢትዮጵያን
ከመጽሐፍ ቅዱስዋ ኢትዮጵያ ጋር አንድ
በማድረግ ከጥንት ጀምሮ የክርስቲያን
ሀገር፣የሙሴን ጽላት የሚገኝባት ጽዮን ወዘተ
በማለት ታሪክን ማሳመር ተጀመረ፡፡ለዚህ ክብረ
ነገስት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡አንዳንዶች
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ስምንት ቁጥር ሀያ
ሰባት(8፡27) ላይ “የኢትዮጵያ ሰው” የተባለውን
በመጥቀስ ክርስትና ወደ ዛሬዋ ኢትዮጵያ የገባው
በሐዋርያት ዘመን እንደሆነ አድርገው መጻፍ
ጀመሩ፡፡‹‹ኢትዮጵያ በአዲስ ኪዳንም
ተጠቅሳለች›› የሚለውን አስተጋቡ፡፡ፕሮፌሰር
ኤድዋርድ ኡሊንዶርፍ “ኢትዮጵያና መጽሐፍ
ቅዱስ” በሚለው መጽሐፈቸው ውስጥ
በሐዋርያት ሥር 8፡27 ላይ ተንተርሰው
ሲያብራሩ “በሐዋርያት ሥራ 8፡27 ‹የኢትዮጵያ
ሰው› የክንዳኬ ባለሟል የተባለው የሜሮዌ
ክንዳኬ አገልጋይ ነው፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያን
(የኛዎቹ) ከጥንት ጀምሮ ይህንን ክስተት
ለራሳቸው አድርገው ክንዳኬን ከንግስት ሳባ ጋር
አንድ አደረጉ፡፡ በእርግጥ በአዲስ ኪዳን
ክንዳኬንና በደቡብ ንግስት መካከል ምንም
ግንኙነት የለም፡፡ ነገር ግን ክብረ ነገስት ሁለቱን
በተያየ ጊዜ የነበሩ ሰዎችን አንድ አደረጋቸው፡፡
”(Edward Ullendorf, Ethiopia and the
Bible, Oxford University press, 1968,
page 9-10)
ይህ የኢትዮጵያን የኋላ ታሪክ መጽሐፍ ቅዱሳዊ
(ክርስቲያናዊ) የማድረግ እርምጃ ነበር፡፡
ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ኡሌንዶርፍ እንዲህ ይላሉ፡-
“ንግስት ሳባንና ክንዳኬን አንድ ማድረጋቸው
የኢትዮጵያውያን (ሀገራችንን) የኋላ ታሪክ
ክርስቲያናዊ የማድረግ ወሳኝ እርምጃ
ነው” (Ethiopia and the Bible, page10)
በአጭሩ የተደረገው የኛዋን ኢትዮጵያ ከመጽሐፍ
ቅዱስዋ ጋር አንድ በማድረግ “ኢትዮጵያ
የክርስቲያን ደሴት ነች” ወደሚል ድምዳሜ
ማድረስ ነበር፡፡የሚገርመው “ኢትዮጵያ እጆችዋን
ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” (መዝሙር 68፡
31) የሚለው ተደጋግሞ እንደመፈክር
እንዲለመድ ሲደረግ ሌሎች ጥቅሶች ግን
ተዘንግተዋል፡፡ የተከተሉት ዘዴ ጥሩ ጥሩ
የሆነውን እየመዘዙ ከታሪክ ጋር ማስተሳሰር
ስለሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ
በአሉታዊ ጎን የተጠቀሱትን ጥቅሶች ማንም
አያነሳቸውም፡፡ ለምሳሌ “በኢትዮጵያ ተስፋ
ያደረጉ፣ በግብፅ የተመኩ ይፈራሉ፣ይዋረዳሉም፡፡
”(ኢሳይያስ 20፡5) እንዲሁም “በግብፅ ላይ
ሰይፍ ይሆናል፤በኢትዮጵያ ላይ ጭንቀት
ይመጣል፡፡”(ሕዝቅኤል 30፡4) የሚሉትን
ጥቅሶች የትኛውም ሰባኪ ሲናገር አይደመጥም፡፡
እስካሁን እንደብራራነው “ኩሽ” የሚለውን
የመጽሐፍ ቅዱስ (ብሉይ ኪዳንን) ቃል
“ኢትዮጵያ” በማለት ከክርስቶስ ልደት በፊት
ሴፕቱዋጀንት ቅጂ ተረጓመው፡፡በንጉስ ጀምስ
ትዕዛዝ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ እውቅናና
ተቀባይነት ያለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ
ላይ “ኩሽ” የሚለው ሙሉ በሙሉ ቀርቶ
በኢትዮጵያ ተተክቶ ቀረበ፡፡ይህ መጽሐፍ ቅዱስ
እ.ኤ.አ. በ1611 በዓለም ሲሰራጭ ለክርስቲያኑ
ዓለም “ኢትዮጵያ” የመጽሐፍ ቅዱስዋ ነች የምል
ድምዳሜን ፈጠሮ አረፈው፡፡ስለ ዓለም
ጂኦግራፊ፣በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ስፍራዎች
እና አጠቃላይ ሳይንሳዊ እውቀቶች ሲጎለብቱ
ጥያቄዎች መነሳት ያዙ፡፡ስህተቱ ከምን ላይ
እንደሆነ ታወቀ፡፡በርካታ ምሁራን በአሳማኝ
መረጃዎች በመነሳት በመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ኩሽ››
እንጂ ‹‹ኢትዮጵያ›› የምትባል እንደሌለች
ድምዳሜ ላይ ደረሱ፡፡ከዓለም ታዋቂ በሆኑ
በመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ታርሞ እ.ኤ.አ
በ1978 የታተመው “New International
Version (NIV)” መጽሐፍ ቅዱስ የተፈጠረውን
የስያሜ ስህተት አርሟል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ
(አዲሱ ዓለም አቀፍ ቅጂ) “ኢትዮጵያ” የሚለውን
ስያሜ በማውጣት ወደ ቀድሞ የዕብራይስጡ
ቃል ‹‹ኩሽ›› መልሷል፡፡በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ
“ኢትዮጵያ” የሚል ቃል አንድ ጊዜ እንኳን
አልተጠቀሰም፡፡ “ኩሽ” የሚለው ግን ሀያ ሰባት
ጊዜ ተጠቅሶበታል፡፡ ለምሳሌ መዝሙር 68፡31
“ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር
ትዘረጋለች” በሚለው ስፍራ “Cush will
submit herself to God” (Psalm 68:31)
”ኩሽ ራሷን ለእግዚአብሔር
ታስገዛለች፡፡” (መዝሙር 68፡31) በማለት
እንዳለ አስቀምጦታል፡፡
‹‹ሆሊ ባይብል ጉድ ኒውስ ኢዲሽን›› የተሰኘው
የእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስም ተመሳሳይ
እርምጃ ወስዷል፡፡ይህ ብቻ ሳይሆን ‹‹ኩሽ›› ሲል
መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠራት ምድር በዛሬው ዓለም
ጂኦግራፊ እንደ መንግስት(በቀድሞ ግዛቷ)
ስለሌለች ለዛሬው የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ
ግልጽ እንዲሆን(የቀድሞዋ ኩሽ በዛሬዋ ሱዳን
ስለነበረች) በ‹‹ኩሽ›› ቃል ምትክ ‹‹ሱዳን››
የሚለውን ተክቷል፡፡ለምሳሌ ‹‹ኢትዮጵያ
እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች››
በሚለው መዝሙረ ዳዊት 68፡31 ስፍራ ላይ
‹‹ሆሊ ባይብል ጉድ ኒውስ ኢዲሽን››ን ብናይ
“the Sudanese will raise their hands
in prayer to God” (HOLY BIBLE Good
News Edition. 1992, Psalms 68:31)
‹‹ሱዳናውያን እጆቻቸውን ወደ እግዚአብሔር
ይዘረጋሉ›› ሲል ነው ያስቀመጠው፡፡‹‹ዘኒው
ኢንግሊሽ ባይብል›› ደግሞ ‹‹ኩሽ›› የሚለውን
የዕብራይስጥ ቃል በኑቢያ ተርጉሞታል፡፡ ለምሳሌ
‹‹ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሄር
ትዘረጋለች›› የሚለውን ‹‹ኑቢያ እጆችዋን ወደ
እግዚአብሔር ትዘርጋ›› ሲል ‹‹let Nubia
stretch out her hands to God.” (THE
New English Bible 1970, Psalms
68:31)
የአረብኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ደግሞ ‹‹
ኩሽ›› የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል እንዳለ
አስቀምጦታል፡፡ ለምሳሌ ‹‹ኢትዮጵያ እጆችዋን
ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች›› በሚለው
የመዝሙረ ዳዊት ጥቅስ ላይ ‹‹ኩሽ እጆችዋን
ወደ አላህ ትዘረጋለች›› ሲል ነው የተረጎመው፡፡
እንዲህ ሲልም አስቀምጦታል፡-
” ﻛﻮﺵ ﺗﺴﺮﻉ ﺑﻴﺪﻳﻬﺎ ﺍﻟﻰ ﺍﻟﻠﻪ” ( ﺍﻟﻜﻨﺎﺏ ﺍﻟﻤﻘﺪﺱ ፡
ﻣﺰﻣﻮﺭ 68:31 )
እስካሁን በስፋት እንዳየነው ጉዳዩ ይህን
ይመስላል፡፡በዚህ ጽሁፍ የተዳሰሱት አብዛኛዎቹ
ነጥቦች በምሁራን መካከል የሚንሸራሸሩ
ቢሆንም ለሰፊው ህዝብ እንዳይቀርብ ተደርጎ
ቆይቷል፡፡እኔ እንደምረዳው በኢትዮጵያ ታሪክ
ዉስጥ በርካታ ውሸቶች አስገራሚ ስፍራ
አግኝተዋል፡፡የጽሁፌ አላማ የመጽሐፍ ቅዱስዋ
‹‹ኢትዮጵያ›› ከኛዋ ሀገር (ኢትዮጵያ) ጋር አንድ
እንዳልሆኑ ማሳየት ብቻ ነው፡፡ለዚህም ነበር
‹‹የቷ ኢትዮጵያ›› ስል በርእሱ የጠየቅሁት፡፡በዚህ
መልኩ የተፈጠረው የመጽሐፍ ቅድስዋን ኩሽ/
ኢትዮጵያ ከዛሬዋ ውዷ ሀገራችን ኢትዮጵያ ጋር
አንድ የማድረግ ሂደት መቋጫው ‹‹ኢትዮጵያ››
እና ‹‹ኢትዮጵያዊነት››ን የእምነት ክፍል ወደ
ማድረግ አድርሷል፡፡ጽሁፌን የማበቃው
በኢትዮጵያ በርካታ ውሸቶች ቦታ ማግኘታቸውን
በማስመልከት ዲያቆን ፅጌ ስጦታው በተናገሩት
ንግግር ይሆናል፡፡እንዲህ ይላሉ፡-
“አሁንም እንዋሻለን፡፡መዋሸታችንን ልባችን
እያወቀው ወደ እውነት ለመመለስ ሐፍረት
እየተሰማን እስከ አሁን እንዋሻለን፡፡በብዙ ውሸት
ሀገራችን እውቅና አግኝታለች፡፡ታቦተ ፅዮን
በኢትዮጵያ፣ ግማደ መስቀሉ በኢትዮጵያ፣ ድንግል
ማርያም ተሰዳ የኖረችው በኢትዮጵያ፣ ፃድቃን
የተባሉ ሁሉ የተፈጠሩት በኢትዮጵያ፣መላእክት
የሚዘምሩት በግዕዝ ቋንቋ፣ አዳም ንግበረ
ተብሎ የተፈጠረበት በግዕዝ ቋንቋ፣
ለማርያምም፣ ለጊዮርጊስም
ለአቡዩም፣ለተክልዬም አሥራት የተሰጠች
ኢትዮጵያ፣ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡” (ዲያቆን
ፅጌ ሥጦታው፣ ይነጋል፣አዲስ አበባ፣አፍሪካ
ማተሚያ ቤት፣1997፣ገፅ 133)
አላሁ አዕለም፡፡ቸር እንሰንብ ት፡፡

Image may contain: text

No comments:

Post a Comment