Monday 14 January 2019

የኢየሱስ ደቀመዝሙር መሆን የክፍል ሦስት ትምህርት የኢየሱስ ደቀመዝሙር መሆን የክፍል ሦስት ትምህርት የተወደዳችሁ ወገኖች ሰላም ለእናንተ ይሁን :: የኢየሱስ ደቀመዝሙር መሆን በሚለው የክፍል ሦስት ትምህርቱ መምህር ጌታቸው እንደ መግቢያና የትምህርቱም መንደርደርያ አድርጎ በማቅረብ ኢየሱስ ራሱ ሕይወቱ የሚጠና ሳብጀክት ነው በማለት ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁትም በእርግጥ ሰምታችሁታልና እውነትም በኢየሱስ እንዳለ ተምራችኋል በሚል ለኤፌሶን ክርስቲያኖች የተጠቀሰውን ቃል በመጥቀስ ክርስቶስን በትክክል እየተማርንና እያጣጣምን በፍቅር ተባብረን በማስተዋል ወደሚገኝበት ወደ የመረዳት ባለጸግነት እንድንደርስ የእግዚአብሔርንም ምስጢር እርሱንም ክርስቶስን እንድናውቅ መጋደል እንደሚገባን አስታውሶናል :: ከዚህም ሌላ ይህንኑ አስመልክቶ ረቢ ወዴት ትኖራለህ ? ብለው ለጠየቁ ደቀመዛሙርት የሚኖርበትን መጥታችሁ እዩ በማለት መጥተው እንዲያዩ የተጋበዙ ደቀመዛሙርት ከእርሱ ጋር በመዋላቸው ያተረፉትን ነገር በመግለጽ ከጌታ ጋር በመዋል የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ትልቅ ግንዛቤ በመስጠት እውነትን እንድንጨብጥ አድርጎናል :: ከዚህም ባሻገር ዛሬ ወዳዘጋጀልን የትምህርት ሃሳብ በመግባት እና በማብራራት ደግሞ ፣ እውነተኛ የጌታ ደቀመዝሙር ለመሆን ከራስ ባርነት ነጻ መውጣት ያስፈልጋል በማለት የዮሐንስ መጥምቁን የሕይወት ባግራውንድና አገልግሎቱንም ጭምር በመጥቀስ ፣ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት ከራሱ ባርነት የተላቀቀ በመሆኑ ለኢየሱስና ለኢየሱስ ብቻ የኖረበትን ወርቃማ የቅድስና ሕይወት ከጥሩ ትንታኔ ጋር እንደሚገባ አብራርቶ አስተምሮናል :: ውድ ወገኖቼ ሆይ መምህር ጌታቸው ባስተማረን መሠረት እንግዲህ በሕይወታችን ለሌሎች መኖርን የከለከለን በእኛነታችን ውስጥ ያለና ሳናውቀው እኛነታችንን አስሮ የያዘን ፣ ለራሳችንም ብቻ ባርያ ያደረገን ነገር ነው :: እርሱም ስም ፣ ገንዘብ ፣ መልክ ፣ እውቀት ፣ ዝና የመሣሠሉት እና በሕይወታችንም በቅለው አልነቀል ያሉን ነገሮች ናቸው :: እንደ ጳውሎስ የወንጌሉ እውነት ገብቶን ለእኔ ረብ የሆነውን እንደ ጉድፍ እቆጥራለሁ ብለን እስካልተውነው ድረስ የእኛን ሕይወት ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ሰዎች ሕይወት ጨምድደው የሚይዙ ትልቅ በሽታዎች እንደሆኑ መምህር ጌታቸው አጠንክሮ ነግሮናል :: ስለዚህ የምንለው ነገር ቢኖር እግዚአብሔር ይፈውሰን ነው :: ወገኖቼ እንግዲህ ይህንን አስደናቂ ትምህርት ከሰማንበት ጊዜ ጀምሮ ለሌሎች መኖርን መለማመድ ፣ የውድድር ሕይወትን ማቆም ፣ ሌሎችን ሪስፔክት እያደረጉ ማገልገልም ሆነ መገልገል ከዚህም ሌላ የደቀመዝሙር ሕይወት ለበላይ አካል መታዘዝ ብቻ ሳይሆን ለበታቾቻችንም ሳይቀር የመታዘዝ ሕይወት ስለሆነ በመታዘዝ ሕይወት ለመኖር ራስን መስጠት ፣ ሰልፊሽ ወይም ስግብግብ ከሆነ ሕይወት ለመላቀቅ መሞከር ፣ ሌላው ቀርቶ በተሰማራንበት በማንኛውም የሥራ ገበታ ጉልበታችንንም ሆነ እውቀታችንን አሟጠን መስራት እንጂ ለደሞዝና በደሞዛችን ልክ ብቻ ለመስራት መሞከር በራሱ የደቀመዝሙርነት ሕይወት አለመሆኑን በማስገንዘብ መምህር ጌታቸው አሁንም ከዚህ ቃል ጋር አያይዞ እንዲህ ሲል አስደናቂ ቃል ነገረን በዚሁም ቃል ወንድምህ አንድ ምዕራፍ እንድትሄድ ቢጠይቅህ ሁለተኛውን ሂድለት በማለት ታዛዥነታችን ፍጹምና ምሉዕ ማድረግ እንዳለብንም ከብዙ ማስተዋል ጋራ መከረን ጌታ ዘመኑን ይባርከው :: ወንድማችን መምህር ጌታቸውን ስላስተማርከን ትምህርት አሁንም ጸጋው በእጥፍ ይብዛልህ ልለው እፈልጋለሁ :: ተከታዩ የክፍል አራት ትምህርት ሰኞ ይቀጥላል ለዚህ ፕሮግራም መሳካት ጸልዩ:: ሰዎችንም መጋበዝ አትርሱ :: ትምህርቶቹም በፌስቡክ ብቻ ሳይሆን በዩቲዩብም ጭምር ስለሚለቀቁ እየገባችሁ መከታተል ትችላላችሁ :: ጌታ እግዚአብሔር ይባርካችሁ :: ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment