Saturday 12 January 2019

አስደናቂ የሆነውና ወደ ጌታም ማዳን የመጡበት የመሪጌቶች የሕይወት ምስክርነት ( ክፍል አንድ )አስደናቂ የሆነውና ወደ ጌታም ማዳን የመጡበት የመሪጌቶች የሕይወት ምስክርነት የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ቅዱሳን ወገኖች በሙሉ ሰላም ለእናንተ ይሁን::ከዚህ በመቀጠል አስደናቂ የሆነውን የእነዚህን መሪጌቶች ወደጌታ ማዳን የመጡበትን የሕይወት ምስክርነት አቅርበናል :: ከዚያ በፊት ግን ፦————————————— 1ኛ ) የሕይወት ታሪካቸውን ፣ ከተማሩበት ትምህርት አንጻርም ያላቸው ሞያ ምን እንደሚመስል በዝርዝር አቅርበውልናል :: ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት አዋቂና ባለሞያ ነን ሊሉ ሞያቸውንም ሊያሳዩ ፈልገው ሳይሆን አንዳንድ ሰነፍ ኦርቶዶክሳውያን የወንጌልን እውነት ላለመስማት ሲሉ ጆሮዎቻቸውንም በመድፈን በምትኩ የእነዚህን በወንጌል እውነት የተዋጁ መሪጌቶች ፣ የእኛ መሪጌቶች አይደሉም ፣ ሻሹንም ከመርካቶ ገዝተው የጠመጠሙ ናቸው በማለት ስም እያጠፉ ስላሉ እነዚህ መሪጌቶች በዚህ የምርግትና ትምህርት ውስጥ ለዓመታት ዋጋ ከፍለውና በብዙ እንግልት ተምረው አልፈው የሞያው ባለቤት መሆናቸውን ለመጠቆም ሲባል ሞያውንና ይትበሃሉን ከነዜማው ከነአቋቋሙና ከነቅኔው በትክክል ሊያስደምጡን ችለዋል :: 2ኛ ) እንደገናም የክርስቶስ ሕይወት እንዴት እንደበራላቸውና እንዴት ወደ ጌታ ማዳን እንደመጡ መስክረውልናል :: በዚህም ውስጥ ከነገረ ድኅነት አንጻር የተሃድሶ እንቅስቃሴ እንዴት እንደሆነና ምን እንደሚመስል ፣ ቤተክርስቲያኒቱም መሠረታዊውን የእግዚአብሔር ቃል እውነት የለቀቀችና ከእውነትም ቃል የወጣች በመሆንዋ ወደ ትክክለኛ መሠረትዋ መመለስ እንዳለባት የሚጠቁሙ እውነቶችን በመናገር መሠረታዊ የእግዚአብሔር ቃል ተሃድሶ ማድረግ እንዳለባት በጽኑ ተናግረዋል ፣ አስረድተውማል :: 3ኛ ) አዋልድ መጻሕፍት በመጽሐፍቅዱሱ ቃል ሲመዘን የሚል ዲቪዲ ከቁጥር አንድ እስከ አራት የሠሩ ሲሆን ፣ አዋልድ መጽሐፍ ምን እንደሆነና የመጽሐፍቅዱሱ ቃል ደግሞ ምን እንድሚመስል ትርጉሙንና ዝርዝር ሃሳቡን ጭምር በአጭሩ አቅርበዋል :: በቀጣዩ ክፍለ ጊዜያቸው ደግሞ በውስጡ ያለውን ሃሳብ ከመጽሐፍቅዱሱ ቃል ጋራ ምን ያህል የሚጋጭ መሆኑን ሊያሳዩን ይሞክራሉ :: ስለዚህ ቅዱሳን ወገኖች ለእነዚህ አገልጋዮችና የእግዚአብሔር ባሮች ወደፊት ባለ ዘመናቸው ፣ ከፊት ለፊታቸው ብዙ ነገር የሚጠብቃቸው ሰዎች ስለሆኑ በጽናት ቆመው የእግዚአብሔርን ሥራ እንዲሰሩና አገልግሎታቸውንም እንዲፈጽሙ በትጋት ልንጸልይላቸው ልናበረታታቸውም ይገባል እላለሁ:: በክፍል ሁለት መልዕክታቸውና ትምህርታቸው እስከምንገናኝ ሰላም ሁኑ የምላችሁ አባ ዮናስ ጌታነህ የስምዓ ጽድቅ ሐዋርያዊ ኦርቶዶክስ ተሃድሶ መሥራችና መሪ ተባረኩ

No comments:

Post a Comment