Sunday 26 August 2018

እንደ መጽሐፍ ቅዱስ.. የንስሓ አባት መሆን ያለበት ማን ነው ? የመልዕክት ርዕስ የንስሐ አባት ኢየሱስ ወይስ ኦርቶዶክሳዊው ቄስ ? የተወደዳችሁ ወገኖች ሰላም ለእናንተ ይሁን እንደምን አላችሁ :: የንስሐ አባቱ ኢየሱስ ወይስ የኦርቶዶክሱ ቄስ ? በሚል ርዕስ ዙርያ ያነሳናቸውን ነጥቦች እንደ እግዚአብሔር ቃል እውነት ስናያቸው በጣም አስተማሪና ገንቢ የሆኑ ሃሳቦችን የምናገኝባቸው ጉዳዮች ሆነው አግኝተናቸዋል :: በመጀመርያው የጥያቄ መወያያችን ላይ ቄሶች የኢየሱስን ሥልጣነ ክህነት ለምን ይጋፋሉ ? ስንል በመጠይቅ መልክ ያነሳነው ሃሳብ ለቀሳውስቱ ምቾት ባይሰጥና ቀሳውስቱንም ሥልጣኔ ተነካ ፣ መብቴ ተደፈረ እያስባለ የሚያነጫንጫቸው ፣ የሚያተክናቸውና የሚያደብናቸው መሆኑን ብናውቅም እየተጋፉት ያሉት ፣ የማይጋፉትን ፣ ሊጋፉት ቢያስቡም እንኳ ጨርሶ ሊጋፉት የማይችሉትን እና የማይሆንላቸውን ከዚህም ሌላ በመጋፋታቸው ብዛት በራሳቸው ተጎድተው ከጥቅም ውጪ የሚሆኑበትን እውነት በመንገር ፣ የኢየሱስን የክህነት ሥልጣን ከሚጋፉበት ዓመጽ ወጥተውና አቅማቸውንም አውቀው በጨዋ ደንብ አርፈው እንዲቀመጡ ለማስገንዘብና ለመምከር ነው :: የኢየሱስን ሥልጣን በተመለከተ በተለይም የዛሬዎቹ ቀሳውስት ከእውቀት ነጻ በመሆናቸው መጽሐፍ ቅዱሱን በአግባቡ ሊያነቡት ቀርቶ የራሳቸውን የእምነት መግለጫ እንኩዋ ለማንበብ ጊዜ የሌላቸው:: በመሆኑ የእምነት መግለጫው ምን እንደሚልና በውስጡም ምን እንደተጻፈ አያውቁትም :: ምናልባትም እነዚህን ቀሳውስት እንዲህ ያባከናቸው የዝክሩና የተዝካሩ የድግሱም ብዛት ይሆናል ብዬ ገምታለሁ :: ዛሬ ግን ይህንን እውነት እኔ ወንድማቸው ላነቃቸውና ከተሳሳተው ተግባራቸውም ልመልሳቸው እናገረዋለሁ :: አመክንዮ ዘሐዋርያት የእምነት መግለጫ እንዲህ ይላል «ዘኪያሁ ይሴፈዉ ምጽአቶ ኲሎሙ አሕዛብ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘሠረፀ እምይሁዳ ወእምሥርወ ዕሤይ ዘሥልጣኑ ዲበ መትከፍቱ ሎቱ ስብሐት ወአኰቴት ዕበይ ወባርኮት ውዳሴ ወማኅሌት ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም አሜን »ይህንን ወደ አማርኛው ስንተረጉመው «አሕዛብ ሁሉ መምጣቱን በተስፋ የሚጠባበቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ከይሁዳ ከዕሤይም ሥር የተገኘ ሥልጣኑ በትከሻው ላይ የሆነ ነው ለእርሱ ምስጋና ገናንነት ክብር በረከት ውዳሴ ቃለ መዝሙርም ይገባዋል ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን » ይለናል ::ከዚህ እንቊ ከሆነ እና መጽሐፍቅዱሳዊ እውነት ሆኖም ከተጻፈ የቤተክርስቲያኒቱ የእምነት መግለጫ ተነስተን ነው እንግዲህ እኔና አባታችን አባ ተክለ ማርያም የኦርቶዶክስ ቄስ ሆይ ሕዝቤን ልቀቅ ይልሃል !!እግዚአብሔር ያልነው የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስን አይደለም ኦርቶዶክሳውያን አማኞች አሕዛብ ሳይቀር መምጣቱን በተስፋ የሚጠባበቁት ናቸው :: የመጣው ደግሞ ከሥልጣን ጋር ስለሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከይሁዳ ከሤይም ሥር የተገኘ ሥልጣኑ በትከሻው ላይ የሆነ ነው ለእርሱ ምስጋና ገናንነት ክብር በረከት ውዳሴ ቃለ መዝሙርም ይገባዋል ሲል የእምነት መግለጫችን ነገረን:: ታድያ ይሄ ኢየሱስ ምስጋናና ገናናነት ሲባል ዝም ብሎ የተዘመረለት ጌታ እኮ አይደለም :: በሥልጣኑ የሠራው ትልቅ የማዳን ሥራ ስላለ ነው ውዳሴ ፣ ቃለ መዝሙርም ይገባሃል የተባለው :: በመሆኑም በሥልጣኑ ካደረገው የማዳን ሥራ አንጻር ዛሬ አይሁድ እንደሚገዘሩት እኛም እንደ አይሁድ አንገዘርም :: ለዚህም ነው ይኸው የእምነት መግለጫ ኢንትገዘር እንከ ከመ አይሁድ ነአምር ከመ መጽአ ዘይፌጽም ኦሪተ ወነቢያተ ያለን :: ትርጉሙም እንግዲህ እንደ አይሁድ አንገዘር ኦሪትንና ነቢያትን የሚፈጽማቸው እንደመጣ እናውቃለን ማለት ነው :: አያ ቄሱ ግን ኦርቶዶክሳውያኑ ሥልጣኑ በትከሻው ላይ ሆኖ ነፍሳቸውን ለማዳን የመጣላቸውን ኢየሱስን ብቻ ተስፋ እንዳያደርጉ ፣ ይሄ ኢየሱስ ኦሪትና ነቢያትን እንዳልፈጸማቸው አድርጎ በመቁጠር ፣ ወደ ብሉይ ኪዳኑ ሥርዓት ተመልሶና የብሉይ ኪዳኑ የፍርባው ብዛትም ሆነ ተረፈ መስዋዕቱ ፊቱ ድቅን እያለበት ፣ ሽታውም ናላውን እያዞረው ፣ ውልም እያለው ስለተቸገረ ፣ ይህቺ ሁኔታ ደግሞ ለምዕመኑ ሳይቀር ምስጢር ሆና ለእርሱ ግን ትልቅ ጥቅም የምታስገኘው ፍርምባና ተረፈ መስዋዕት እንዳትቀርበት ፣ ኢየሱስ ሥልጣኔን እባክህ ተጋራኝ ወይንም አግዘኝ ያለው ይመስል ወደ ኢየሱስ ተጠግቶ ከኢየሱስ ትከሻ ላይ ሥልጣኑን ሊያወርድ ሲጣጣር የኢየሱስንም ሥልጣን ሲጋፋ ይታያል :: ይህ ታድያ አንዳንድ ጩሉሌ የመርካቶ ኪስ አውላቂዎች በርቀት ሆነው በአንድ ሰው ላይ የሆነ ነገር ካዩ ፣ ጋሽዬ ይሄን ነገር እኮ እኔ ብይዘው ፣ ብረዳዎት እንደሚሉት ፣ ከቻሉም ደግሞ እንደ ጭልፊት ነጥቀው ለመብረር እንደሚጣደፉት ዓይነት በመሆኑ ፣ በኢየሱስ የክህነት ሥራም ላይ ያያቄሱ ድርጊት ከዚህ አይተናነስም እና እንዲሁ ነው :: እዚህ ላይ ለትምህርቴ ማጠናከርያ አንድ ምሳሌ በማከል መልዕክቴን እጠቀልላለሁ :: በአንድ መንደር ውስጥ ሕዝቡ የቅዳሜ ገበያ ሲል ከቤቱ እንደሚወጣ ያወቀች እብድ ማንም ሳይቀድማት በጠዋት ተነስታ « ነግረናል ቤት ይቃጠላል ብለናል አለች »አሉ :: መንደረተኛውም የዚህችን ዕብድ ብርቱ ማስጠንቀቅያ አላወቀም ፣ አልገባውምና ጀመራት ደግሞ ይህቺ ዕብድ ፣ ዛሬ ደግሞ ምኑን ከምን ይዛ ነው እንዲህ የሚያስለፈልፋት ? ብሎ ይህቺን ዕብድ ማንም ሰው አባከና ሳይላትና ቦታም ሳይሰጣት ሁሉም ወደ ገበያው ጥርግ ብሎ ሄደ :: ከዚያም መንገዱን እያጋመሰው እያለ ዕብዷ ሴት የእያንዳንዱን ሠፈረተኛ ሰው ቤት በእሳት ለኮሰችና እሳቱ ሲንቦገቦግና ቤታቸውን ሲያቃጥል ሠፈረተኛው ወየው ቤታችን ተቃጠለ ጉድ ሆንን ብሎና ከመንገዱም ተመልሶ ወደ ሠፈሩ ሲመለስ ይህቺ ዕብድ ጠዋት ማንም ከእንቅልፉ ሳይነሳ ትናገረው የነበረውን ቃል በመድገም «ነግረናል ቤት ይቃጠላል ብለናል » አለቻቸው ይባላል :: መልዕክቴን ስጠቀልለው እኔም ሆንኩ አባታችን አባ ተክለ ማርያም የምናስተላልፈው መልዕክት ዛሬም ይህንኑ ቃል በመድገም ነው «ነግረናል ቤት ይቃጠላል ብለናል » ተባረኩ እብዶች ብንሆን፥ ለእግዚአብሔር ነው፤ ባለ አእምሮዎች ብንሆን፥ ለእናንተ ነው ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ ፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች  5 : 13 - 15 ወስብሐት ለእግዚአብሔር ዘእንበለ ወላዲቱ ድንግል ወዘእንበለ መስቀሉ ክቡር አሜን

No comments:

Post a Comment