Thursday 12 July 2018

ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች የሚለው ለማን ነው ? ( መዝሙር 45 ፥ 9 ) ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች የሚለው ለማን ነው ? ( መዝሙር 45 ፥ 9 ) ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምኢ ዕዝነኪ ርስዒ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ እስመ ፈተወ ንጉሥ ስነኪ እስመ ውእቱ እግዚእኪ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥ እርሱ ጌታሽ ነውና መዝሙረ ዳዊት  45 : 9 - 11 የተወደዳችሁ ቅዱሳን ሰላም ለእናንተ ይሁን ዛሬ በዚህ ትምህርት ውስጥ መዝሙረ ዳዊትንና ቅዳሴ ማርያምን በንጽጽር ወደ እናንተ በማቅረብ ፍርዱን ለእናንተ እተዋለሁ :: በቅዳሴ ማርያም መጽሐፍ ላይ ቅዳሴ ማርያምን ደረሰ ስለተባለው አባ ሕርያቆስ የቅዳሴ ማርያም መጽሐፍ እንዲህ ይለናል :: የብህንሳ ኤጲስቆጶስ አባ ሕርያቆስ አምላክን ስለወለደች ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያም በመንፈስቅዱስ የደረሰው የቊርባን ቅዳሴ ይህ ነው ይለንና ልመናዋና በረከትዋ ከአገልጋይዋ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን ይለናል :: አያይዞም ጐሥዓ ልብየ ቃለ ሰናየ ፣ ጐሥዓ ልብየ ቃለ ሰናየ ፣ ጐሥዓ ልብየ ቃለ ሰናየ ወአነ አየድዕ ቅዳሴሃ ለማርያም አኮ በአብዝኆ አላ በአውሕዶ ወአነ አየድዕ ውዳሴሃ ለድንግል አኮ በአንኆ በቃለ ዝንጋዔ አላ በአኅድሮ ወአነ አየድዕ ዕበያቲሃ ለድንግል:: ወደ አማርኛው ስተረጉመው ልቡናዬ በጎ ነገርን አወጣ ፣ ልቡናዬ በጎ ነገርን አወጣ ፣ ልቡናዬ በጎ ነገርን አወጣ እኔም የማርያምን ቅዳሴ እናገራለሁ በማብዛት አይደለም በማሳነስ ነው እንጂ እኔም የድንግልን ውዳሴ እናገራለሁ መዘንጋት ባለበት ቃል በማስረዘም አይደለም በማሳጠር ነው :: እኔም የድንግልን ገናንነትዋን እናገራለሁ እያለ ይናገራል ( ምንጭ የቅዳሴ ማርያም መጽሐፍ ) ከዚሁ ጋር በንጽጽር መዝሙረኛው ዳዊት የተናገረውን እንመልከት:: ጐሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ ወአነ አየድዕ ግብርየ ለንጉሥ ከመ ቀለመ ጸሐፊ ዘጠበጠበ ይጽሕፍ ልሳንየ ይሴኒ ላህዩ እምውሉደ እጓለ እመሕያው ተክዕወ ሞገስ እምከናፍሪከ በእንተ ዝ ባረከከ እግዚአብሔር ለዓለም ወደ አማርኛው ስተረጉመው ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ እኔ ሥራዬን ለንጉሥ እነግራለሁ አንደበቴ እንደ ፈጣን ጸሐፊ ብርዕ ነው ውበትሕ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል ሞገስ በከንፈሮችሕ ፈሰሰ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ባረከህ እያለ ይቀጥላል ( መዝሙር ( 45 ) በሙሉ ተመልከቱት ) የተወደዳችሁ ወገኖች ንጽጽሩን በማስተዋል ሆናችሁ ስትመለከቱት መዝሙረኛው ዳዊት ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ እኔ ሥራዬን ለንጉሥ እነግራለሁ እያለ ስለ ንጉሡ ውበት እግዚአብሔርን እየባረከ ይቀኛል ይዘምራል :: አባ ሕርያቆስ የቅዳሴ ማርያም ደራሲ ነኝ የሚለው ደግሞ በመንፈስቅዱስ የደረስኩት ነው በማለት ልቡናዬ በጎ ነገርን አወጣ ፣ ልቡናዬ በጎ ነገርን አወጣ ፣ ልቡናዬ በጎ ነገርን አወጣ እኔም የማርያምን ቅዳሴ እናገራለሁ በማለት ማርያምን ከፍ ባለ ምስጋና ማወደስ ጀመረ :: ስለዚህ ልቡናችን መልካም ነገር ማፍለቅም ሆነ ማመስገን ያለበት መዝሙረኛው ዳዊት እንዳለው ለንጉሡ ለጌታችን ነው ? ወይስ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ እንደተናገረው ለማርያም ነው ? ለማን ጐሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ እንበል ? ማርያምን ልቡናዬ በጎ ነገርን አወጣ ወይም አፈለቀ ስንል እንድናወድሳት መጽሐፍቅዱስ ያስተምረናል ? መጽሐፍቅዱሳችን አሁንም እንደነገረን በዚህ ነገር ምስጋና መስጠት ያለብን ለእግዚአብሔር ብቻ ነው :: ማርያምንም ከእግዚአብሔር ጋር በእኩልነት አወድሱአት ሲል ግን አልጻፈልንም :: እንደገናም በውኑ አባ ሕርያቆስ ልቡናዬ በጎ ነገርን አወጣ ሲል በመንፈስቅዱስ ማርያምን እንዲያመሰግን መንፈስቅዱስ መርቶታልን ?ይህንን ያልኩበት ከላይ በገለጽኩት መሠረት መዝሙረኛው ዳዊት ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ እኔ ሥራዬን ለንጉሥ እነግራለሁ በማለት ሲያወድስ የተመለከትነው በትንቢታዊ ቃል ሳይቀር የተነገረለትን ንጉሣችንን ኢየሱስን ነው :: ታድያ አባ ሕርያቆስ እንዳለን የማርያምን ቅዳሴ በመንፈስቅዱስ ነውና የደረስኩት ፤ በተደረሰው በመንፈስቅዱስ አማካኝነት ጌታ መሆኑ ቆርቶ ማርያምን ጐሥዓ ልብየ ቃለ ሰናየ ማለትም ልቡናዬ በጎ ነገርን አወጣ ስትባል ነው መመስገን ያለባት ይለናል :: ይህንን ማለቱ ደግሞ መዝሙረኛው ዳዊት ጐሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ ወአነ አየድዕ ግብርየ ለንጉሥ ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ እኔ ሥራዬን ለንጉሥ እነግራለሁ እያለ ማመስገኑ ተሳስቶ ነውና ለማርያም ውዳሴ በመስጠት ደረጃ ትክክለኛው የመንፈስቅዱስ ደራሲ እኔ አባ ሕርያቆስ ነኝ እያለን ነው :: እኛ ግን የምናምነው ትክክለኛው እኔ ነኝና ልቡናችን በጎ ነገርን አፍልቆ ማርያምን እናመስግን ያለንን ሕርያቆስን ሳይሆን መጽሐፍቅዱሳችን በመሰከረልን ቃል መሠረት ምስጋና ፣ ቅዳሴም ሆነ ውዳሴ የሚሰጠው ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ የምንቀበለውም ሆነ ተቀብለን የምናመሰግነው የዳዊትን ምስጋና ምስጋናችን በማድረግ ነው :: እንደገናም ሕርያቆስ ማርያምን ሊያመሰግን በመንፈስቅዱስ ቢያላክክም የተሳሳተው ሕርያቆስ እንጂ መንፈስቅዱስ አይደለምና የዳዊትን ምስጋና ምስጋናችን አድርገን ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ በማለት ንጉሥ ዳዊት በትንቢታዊ ቃል ለንጉሡ ለኢየሱስ በሰጠው መሠረት እኛም ለንጉሣችን ለኢየሱስ ከፍ ያለ ምስጋናን እንሰጣለን :: ወገኖች ጽሑፉን አንብቡት ተጠቀሙበት ደግሞም ተባረኩበት ሰላም ሁኑ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን Contact https://www.facebook.com/yonas.asfaw.39
 Primary: yonasasfaw8@gmail.com

No comments:

Post a Comment