Thursday, 16 August 2018
በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ተሰግስገው የገቡ ፣ እግዚአብሔርን የተኩ ፣ የአማልክት አምልኮዎች ( ክፍል አምስት ) (...በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ተሰግስገው የገቡ ፣ እግዚአብሔርን የተኩ ፣ የአማልክት አምልኮዎች ( ክፍል አምስት ) ( ቊጥር 5 ) ተፈስሒ ማርያም ለአዳም ፋሲካሁ ወማዕዶታ ለሔዋን እንተ ይእቲ አፅመ ገቦሁ ትርጉም ፦ የአዳም ፋሲካ የሆንሽ ከጎኑም ለወጣችዋ ለሔዋን መሻገርያዋ የሆንሽ ማርያም ደስ ይበልሽ ( መጽሐፈ ሰዓታት ገጽ 79 ) 5ኛ ) ከእርሱም እስከ ነገ ምንም አያስቀሩ ከእርሱም አጥንትን አይስበሩ እንደ ፋሲካ ሥርዓት ሁሉ ያድርጉት ( ዘኊልቊ 9 ፥ 12 ) የተወደዳችሁ ወገኖች ይህ በዘኊልቊ 9 ፥ 12 ላይ የተጻፈው የብሉይ ኪዳን ቃል በጥላነት የሚያመለክተን የፋሲካ በጋችን የሆነውን ኢየሱስን ነው ( የዮሐንስ ወንጌል 1 ፥ 29 ):: ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶልናልና ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾ አይደለም ይለናል ( 1ኛ ቆሮንቶስ 5 ፥ 7 እና 8 ) :: እንደገናም በዘኊልቊ 9 ፥ 12 መሠረት ከእርሱም እስከ ነገ ምንም አያስቀሩ :: ከእርሱም አጥንትን አይስበሩ:: እንደ ፋሲካ ሥርዓት ሁሉ ያድርጉት የሚለው ቃል በዮሐንስ ወንጌል 19 ፥ 36 እና 37 ለተጻፈው ቃል አሁንም በጥላነት የሚያገለግል ነው :: ቃሉም እንዲህ ይላል :: ይህ የሆነ ከእርሱ አጥንት አይሰበርም የሚል የመጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው :: ደግሞም ሌላው መጽሐፍ የወጉትን ያዩታል ይለናል :: ይህ የሚያሳየን ታድያ ጌታ እኛን ከመውደዱና ለእኛም መሥዋዕት በመሆኑ ምክንያት በኤፌሶን 5 ፥ 2 ላይ በተጻፈው ቃል መሠረት ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ በፍቅር ተመላለሱ የሚለውን ቃል ያስጨብጠናል :: ታድያ ክርስቶስ እኛን በመውደዱ ምክንያት ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ በመስጠቱ ምልልሳችንን ሳይቀር ለውጦ የፍቅር ምልልስ አደረገው :: ከዚህም ሌላ እኛም እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ ተብለናልና ፣ በእግዚአብሔር በአምላካችን እንደተወደድን ገብቶን ፣ እግዚአብሔርን የምንከተል ሆንን :: ለዚህ ሁሉ ክብር የበቃንበት ምስጢር ግን ክርስቶስ እኛን በመውደዱ ምክንያት ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ በመስጠቱ ነው :: ሌላኛውና ሁለተኛው ሃሳብ አሁንም በዘኊልቊ 9 ፥ 12 በተጻፈው ሃሳብ መሠረት እስከ ነገ ድረስ ከእርሱ ምንም ካላስቀሩ ከእኛም ምንም መቅረት የለበትም የሚለውን ሃሳብ እንድንይዝ ቃሉ ያስገነዝበናል :: ይህ ማለት ደግሞ እኛም ፈጽመን ወይንም ጨርሰን መለወጥ እንዳለብን የሚጠቁመን ቃል ነው :: በዘጸአት 12 ፥ 14 እና 15 ላይ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን :: ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፥ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፤ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ሆኖ ለዘላለም ታደርጉታላችሁ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያም ቀን እርሾውን ከቤቶቻችሁ ታወጣላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ። እርሾን በተመለከተ ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ እርሾ በመጽሐፉ ቃል መሠረት ያልተፈለገ በመሆኑ ለብሉይ ኪዳኑ እሥራኤል ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያም ቀን እርሾውን ከቤቶቻችሁ ታወጣላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ የሚል ትዕዛዝ ተላለፈ :: ይህንን እውነታ አሁንም ወደ ሐዲስኪዳኑ ሕይወት ስናመጣው ፣ ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶልናልና ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾ አይደለም የሚለውን እውነተኛውን ትምህርታዊ የሆነ የሕይወት መርሆና ትርጉምን ይሰጠናል :: ዛሬ ታድያ ክርስቶስን ባመኑ ፣ በሚያገለግሉም ክርስቲያኖችና አገልጋዮች ሳይቀር ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶ ሳለ በእነዚሁ ወገኖች ሕይወት ላይ ግን ክፉ የሆነ አሮጌ የግፍ ፣ የቅንዓት የክፋትና የዓመጸኝነት…. እርሾ አለ :: እንደገናም በእውነትና በቅንነት ቂጣ በዓልን ማድረግ የለም :: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ትምህርቱ ፣ ደቀመዛሙርቱን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንዲጠበቁ አስጠነቀቀ ( የማቴዎስ ወንጌል 16 ፥ 6 ፤ 12 ):: ለዚህም ነው ጳውሎስ በዘመናችን ላለን ጤናማ ክርስቲያኖች ጭምር መልዕክት ስለነበረው ፣ የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኛለሁና የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ፍርዱን ሊሸከም ነው በማለት የነገረን ( ገላትያ 5 ፥ 9 ) :: በክቡር በክርስቶስ ደም እንደ ተዋጀ ያወቀ ሰው በሕይወቱ እርሾ እንዲኖርበት አይፈቅድም ፣ መፍቀድም የለበትም ( ዘዳግም 16 ፥ 3 ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 1 ፥ 19 ) ከዚህ በመቀጠል ለዚህ ትምህርት ማጽኛ እንዲሆን ፣ ጌታ በሌሊት ከመኝታዬ ቀስቅሶ የተናገረኝን ቃል እንደሚከተለው አስቀምጣለሁ :: ለቤተክርስቲያንና ለቅዱሳን ዕድገት እንዲሁም የሕይወት ከፍታ አስቸጋሪ የሆኑ ፣ ለዘመናት አልለወጥ ብለው በቤቱ እንደ ጉቶ ተተክለው ለቀሩ ክርስቲያኖች ፣ 1ኛ ) በግድ በመከራና በጣር እንደሚለወጡ ጌታ ይናገራል ( ዘፍጥረት 32 ፥ 22 _ ፍጻሜ ፤ ትንቢተ ኤርምያስ 31 ፥ 18 _ 20 ):: 2ኛ ) በበቃኝ እና በልመለስ እንደሚለወጡም ጌታ ይናገራል ( የሉቃስ ወንጌል 15 ፥ 11 _ ፍጻሜ ፤ ሰቆቃወ ኤርምያስ 5 በሙሉ ):: በመቀጠልም የተባረከው የጥንቱና የጠዋቱ ዘማሪ የሆነው መጋቢ ታምራት ኃይሌ ፦ በእንባና በጣር በጭንቅ በመከራ በእሳት ውስጥ አልፎ ሕይወቴ ተገራ ማዕበሉም ነፋሱም ሰራኝ ደህና አድርጎ ጠላት ለክፉ ሲል ሆነልኝ ለበጎ………. የሚለውን መዝሙር ከትምህርቴ ጋር ስለሚሄድ እርሱን በመጋበዝ የቊጥር 5 ትምህርቴን አጠቃልላለሁ ተባረኩ ወንድማችን የጥንቱና የጠዋቱ መጋቢና ዘማሪ ታምራት ኃይሌ እጅግ በጣም የተወደደና የተከበረ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው :: በመዝሙሮቹ ውስጥ ያሉት መልዕክቶች መጽሐፍቅዱሳዊና ከመንፈስ ቅዱስ የተገኙ ከመሆናቸው የተነሳ ዘመናትን አቋርጠው አሁን ላይም እየተደመጡ ያሉ በመሆናቸው ትውልድን የሚመሠርቱ የሚያንጹና አቅጣጫንም ጭምር የሚያስይዙ መዝሙሮች ናቸው :: ታድያ እነዚሁ መዝሙሮች መዝሙር ብቻ ሳይሆኑ ስብከቶች መልዕክቶችና ትምህርቶችም ጭምር ናቸው :: በመሆኑም ዛሬ ላይ ባዘጋጀሁት ትምህርትም የወንድማችን መጋቢና ዘማሪ ታምራት ኃይሌ መዝሙር በእጅጉ የጠቀመኝ በመሆኑ ከትምህርቴ ጋር አያይዤ ይህን መዝሙር ለእናንተ ለአድማጮች ለመጋበዝ ወድጃለሁ እና እባካችሁ ተጋበዙልኝ ስል በፍቅር እጠይቃለሁ:: ወንድማችንንም ጌታ ይባርክህ ዕድሜና የአገልግሎት ዘመንም አብዝቶ አትረፍርፎ ይጨምርልህ በሉልኝ ተባረኩ ከጸአተ ግብጽ ኦርቶዶክሳዊና ሐዋርያዊ የተሃድሶ አገልግሎት ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ አስፋው
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment