Monday, 13 August 2018

በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ተሰግስገው የገቡ ፣ እግዚአብሔርን የተኩ ፣ የአማልክት አምልኮዎች ( ክፍል አምስት ) ( ቊ...በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ተሰግስገው የገቡ ፣ እግዚአብሔርን የተኩ ፣ የአማልክት አምልኮዎች ( ክፍል አምስት ) ( ቊጥር 4 ) ተፈስሒ ማርያም ለአዳም ፋሲካሁ ወማዕዶታ ለሔዋን እንተ ይእቲ አፅመ ገቦሁ ትርጉም ፦ የአዳም ፋሲካ የሆንሽ ከጎኑም ለወጣችዋ ለሔዋን መሻገርያዋ የሆንሽ ማርያም ደስ ይበልሽ ( መጽሐፈ ሰዓታት ገጽ 79 ) 4ኛ ) እሥራኤል ያደረጉት ፋሲካ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው ሙሴም ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች ተናገራቸው በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በሲና ምድረ በዳ ፋሲካን አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ ይለናል ( ዘኍልቍ 9 ፥ 4 እና 5 ) የመጀመርያው ፋሲካ የተደረገው በግብጽ ነበር ( ዘጸአት ምዕራፍ 12 ን በሙሉ ተመልከቱ ) ውጤቱ ፦ 1ኛ ) የእሥራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ አደረጉ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ :: በዚያም ቀን እግዚአብሔር የእሥራኤልን ልጆች ከሠራዊታቸው ጋር ከግብጽ ምድር አወጣ የሚል ነው ( ዘጸአት 12 ፥ 50 እና 51 እንመልከት ) 2ኛ ) በመጀመርያው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን ከራምሴ ተጓዙ ከፋሲካ በኋላ በነጋው የእሥራኤል ልጆች ግብጻውያን ሁሉ እያዩ ከፍ ባለ እጅ ወጡ :: በዚያም ጊዜ ግብጻውያን እግዚአብሔር የገደላቸውን በኩሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር በአማልክቶቻቸውም ደግሞ እግዚአብሔር ፈረደባቸው ይለናል ( ዘኊልቊ 9 ፥ 3 እና 4 ) ፋሲካ ታድያ እንዲሁ ዝም ተብሎ ፣ ወርና ዓመት ተቆጥሮ የሚደረግ አይደለም :: ወራትንና ዓመታትን ቆጥረን ዘመናትንም ቀምረን የምናደርገውን ፋሲካ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ካላደረግነው በሕይወታችን ላይ ለውጥንና መሻገርንም የሚያመጣ አይሆንም :: የባሕል ፋሲካ ብቻ ሆኖ ይቀርና እኛም ዕለታዊ ሳይሆን ዓመታዊ ኑዛዜዎችን የለመድን ስለሆንን ፣ ከአልጋ ወድቄያለሁና የመሣሠሉትን ኑዛዜዎች ለነፍስ አባት ተብዬዎች ለይስሙላ ያህል እየተናዘዝን ፣ ለዚህም ማካካሻ ቅጣት የሚሆነንን ጥብጣቤ ስንል ጀርባችንን በወይራ ተቸብችበንና ተጠብጥበን አርባ ፣ ሰማንያ ፣ መቶና ከዚያ በላይ እየሰገድን ፣ ከዚያም መልስ ወደ ቤታችን ሄደን በቤታችን የተዘጋጀውን ጉልባን እየሰለቀጥን ፣ ከዚህም ሌላ ትንሣኤ ላይ ደረስን ስንል ደግሞ ዶሮአችንን ፣ ክትፎአችንንና ግብዣችንን ከምናሳድድ ውጪ ሌላ ነገር አናውቅምና በሕይወታችን የሚታይብን ለውጥ የለም :: በዚህ ውስጥ ግን ኢየሱስ በእኛ ጥብጣቤና ስግደት የሚገለጽ ባሕላዊ ፋሲካችን ስላልሆነ ለእኛ ለሁላችን በደል በብረት ጅራፍ ተገርፎ ደማልን:: አልፎም በመስቀል ላይ በመሞት ደሙ እንደ ጅረት ፈሶ የኃጢአትን ሥርየት ሰጠን :: ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ሞቶ አልቀረም ፣ ለአንቀላፉት ሁሉ በኩራት ሆኖ ከሙታን በመነሳት እኛን ያመንበትን አጸደቀን ( ሮሜ 4 ፥ 24 እና 25 ) ከዚህ የተነሣ ፋሲካ ዛሬ ለእኛ ባሕላዊ አይደለም :: ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር ሙሴ በግብጽ በተደረገው የመጀመርያው ፋሲካ ላይ አጥፊው የበኩሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨት በእምነት አደረገ የሚለን:: ስለዚህ ሙሴ በጊዜው ያደረገው ፋሲካ ባሕላዊ የወይራ መቸብቸብና ጥብጣቤ ያለበት ፣ ጉልባን የተበላበት ፣ ከዚያም መልስ እንኳን አደረሳችሁ እየተባለ በየትያትር ቤቱ ሳይቀር ኮንሰርት ተዘጋጅቶ እስክስታና ጭፈራ ስካርና ዳንኪራ የተካሄደበት ፋሲካ አልነበረም :: ሙሴ ባደረገው ፋሲካ ውስጥ ደም መርጨት ስለነበረ አጥፊው የበኩሮችን ልጆች አልነካም ( ዕብራውያን 11 ፥ 23 _ 30 ) :: ይህንን ሃሳብ ወደ ሐዲስ ኪዳን ስናመጣው በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች ፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል የሚለን ለዚህ ነው ዕብራውያን 12 ፥ 22 _ 24 በመሆኑም እኛ የሐዲስ ኪዳን አማኞች ዛሬ ላይ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሰናል ይሁን እንጂ ከዚያም መልስ በሙሴ የደም መርጨት ዘመን የታየውን ውጤት ስንመለከተው የእሥራኤል ልጆች ግብጻውያን ሁሉ እያዩ ከፍ ባለ እጅ ወጡ :: በዚያም ጊዜ ግብጻውያን እግዚአብሔር የገደላቸውን በኩሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር በአማልክቶቻቸውም ደግሞ እግዚአብሔር ፈረደባቸው የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን :: በመሆኑም ዛሬም ላይ ፋሲካ ይህንን ቃል በሰማነው ሰዎች ሕይወት ላይ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሆኖና ተደርጎ እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ ካላመጣ ( ራዕይ 12 ፥ 7 _ 12 ) ፣ እኛንም አሻግሮ ወደምንናፍቃት ጽዮንና አዕላፋት የበኩራት ማኅበር ካላደረሰን ( ዕብራውያን 12 ፥ 18 _ 24 ) ፋሲካው አሁንም ባሕላዊ ነው ሁለተኛው ፋሲካ የተከበረው ከአንድ ዓመት በኋላ በሲና ነበረ በእስራኤል አለመታዘዝና እግዚአብሔር በእርስዋ ላይ በወሰነው ፍርድ ምክንያት እስራኤል ወደ ተስፋይቱ ምድር እስከምትገባ ድረስ ፋሲካን አላከበረችም ( ዘኊልቊ ምዕራፍ 14 ን በሙሉ እንመልከት ) ስለዚህ አሁንም የእኛ ፋሲካ በቃሉ መሠረት የተደረገና በተስፋ ቃል የሆነ ነውና ከእኛነታችን አልፎ ሌሎችንም የሚወርስ ነው :: ስለዚህ ለዚህ ጉዳይ እኛ ሁላችን ክርስቲያኖች ልንነሳና ውስጣችንንም በዚህ በተሰጠው የተስፋ ቃል ልናጸና ፣ የተናገረንንም የተስፋ ቃል እስከመጨረሻው በማመን አጽንተን ልንይዝ ይገባል:: የተወደዳችሁሁ ወገኖች ትምህርቱ በዚህ ያልተቋጨ በመሆኑ በሚቀጥለው ክፍለ ጊዜያችን ቁጥር 5 ብለን እንቀጥላለን ተባረኩ ከጸአተ ግብጽ ኦርቶዶክሳዊና ሐዋርያዊ የተሃድሶ አገልግሎት ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ አስፋው

No comments:

Post a Comment