Sunday, 14 June 2015

ክፍል አምስት ንዑስ ክፍል አራት ብዙ ዓይነትና ተለዋዋጭ የሆኑ ጥቅሶችን በአንድ ባለቤት ባለው ነገር ውስጥ ማነጻጸር Comparing Various Verses on the same Subject በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል ይለናል የማቴዎስ ወንጌል 10 ፥ 22

ክፍል አምስት


ንዑስ ክፍል አራት


ብዙ ዓይነትና ተለዋዋጭ የሆኑ ጥቅሶችን በአንድ ባለቤት ባለው ነገር ውስጥ ማነጻጸር




Comparing Various Verses on the same Subject  




በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤
እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል ይለናል            
           
    
      

                   የማቴዎስ ወንጌል 10 22





በዚህ ንዑስ ክፍል አራት የምንመለከተው በሁሉም ስለ ስሙ መጠላትን ነው መጽሐፍቅዱሳችን በማቴዎስ ወንጌል 10 22 ላይ በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል ይለናል ታድያ ስለ ስሙ የምንጠላው የእግዚአብሔርን ቃል ከማመናችን የተነሳ ነው መጽሐፍቅዱሳችን አሁንም በማርቆስ ወንጌል 8 38 እና በሉቃስ ወንጌል 9 26 ላይ በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል ይለናል ስለዚህ የቱንም ያህል ስለ ስሙ የመጠላት ኃይል ቢመጣም  የተጠላነው ከቃሉ የተነሳ ነውና በቃሉ ፈጽሞ ልናፍር አይገባም ስለዚህ ነው እንግዲህ በዕብራውያን 2 1 _ 4 ላይ ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን ? ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት በማለት የተናገረን ስለዚህ ከምንሰማቸው ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ ከሆኑ  የእግዚአብሔርም ቃል በትክክል ከማይመሰክርላቸው ከሰዎች አስተሳሰብና ትምህርቶችም የተነሳ ስተን እንዳንወድቅ ለዚህ ለሰማነው ለእግዚአብሔር ቃል አብልጠን ልንጠነቀቅ ይገባናል እያለን ነው የዕብራውያን ጸሐፊ የነገረን ይሄ የሰማነው ቃል በመጀመሪያ በጌታ የተነገረ የሰሙትም ለእኛ ያጸኑት እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ የመሰከረለት  በመሆኑ ከዚህ የተነሳ ለመዳን  የበቃንበት ለአገልግሎትና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ በረከቶችን ለመካፈል  የደረስንበት ነው  በሰማነው ቃል ነው ዛሬ ላይ ለደረስንበት መንፈሳዊ መረዳት የደረስነው ስለዚህ አንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር በመታመን እራሳችንን ከሰጠንና ለእርሱ ከታዘዝን  እስከ መጨረሻው መሄድ አለብን እንጂ ወደኋላ ማለት የለብንም በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 9 21 ላይ እርሱ ግን፦ የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል በሽማግሌዎችም በካህናት አለቆችም በጻፎችም ሊጣል ሊገደልም በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባዋል ብሎ ለማንም ይህን እንዳይናገሩ አስጠንቅቆ አዘዘ ይለናል ታድያ ጌታ ኢየሱስ ይህንን ነገር ለማንም እንዳይናገሩ አስጥንቅቆ ቢያዝም በዚህ ነገር እስከመጨረሻው ሄዷል ለዚህም ነው በሉቃስ ወንጌል 13 31 _ 35 ላይ በዚያን ሰዓት ከፈሪሳውያን አንዳንዱ ቀርበው ሄሮድስ ሊገድልህ ይወዳልና ከዚህ ውጣና ሂድ ባሉት ጊዜ እንዲህ አላቸው ይለንና ሃሳቡን ይቀጥላል ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፥ በሦስተኛውም ቀን እፈጸማለሁ በሉአት ዳሩ ግን ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ይጠፋ ዘንድ አይገባውምና ዛሬና ነገ ከነገ በስቲያም ልሄድ ያስፈልገኛል ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ፥ እናንተም አልወደዳችሁም እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል እላችኋለሁም፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም በማለት ሲናገር የተመለከትነው በሉቃስ ወንጌል 9 51 እና 52 ላይ የሚወጣበትም ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና በፊቱም መልክተኞችን ሰደደ ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንድ ወደ ሳምራውያን መንደር ገቡ ፊቱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ስለ ነበረ አልተቀበሉትም የሚለን  ጌታችን ኢየሱስ  ይህ ዓይነት የሕይወት አቋም ስለነበረው ነው በዚያን ጊዜ እከተልሃለሁ ሲሉ ተናግረው በመጨረሻ ግን የየግል ምክንያቶቻቸውን በመደርደር ወደኋላ ላሉ ሰዎችና ዛሬም ላይ ፈራ ተባ እያልን ከዛሬ ነገ በሚል ሕይወት ውስጥ ተቀምጠን በተመሣሣይ ሁኔታ ላለን ለእኛም ጭምር ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም ሲል ጌታችን የተናገረው የሉቃስ ወንጌል 9 57 _ 62 ይህ ጌታ ኢየሱስ የሕይወት መስዋዕትነት የከፈለበት እና እኛን የታደገበት ወደፊትም ሌሎችን የሚታደግበት የመስቀሉ ሞትና የትንሣኤው ምሥጢር በጊዜ ውስጥ ተሸጋግሮ ወደ እኛ ሲመጣ እኛ በቀላሉ ለሌሎች የምናስተላልፈው አይሆንም ይህ ሁኔታ ታድያ ዛሬም ላይ ላለነው ለእኛ ለአገልጋዮች መናገርን ብቻ ሳይሆን ሕይወትንና የሕይወት መስዋዕትነትንም የሚጠይቅ አገልግሎት መሆኑን ጳውሎስ በእርግጠኝነት የተገነዘበ በመሆኑ በ1ኛ ቆሮንቶስ 9 27 ላይ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ በማለት ተናገረን ሐዋርያው ለሌሎች ሰብኮ ራሱ የተጣለ እንዳይሆን ሥጋውን እየጎሰመ ማስገዛቱ አገልግሎት ማለት የመድረክ ላይ ስብከት ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዊ የሕይወት መሰጠት ጭምር በመሆኑ በስብከቱ ብቻ ሳይሆን በሕይወቱም ባለ ምሳሌነት  እስከመጨረሻው መሄድ የሚፈልግ በመሆኑ ይህን ተናገረ ታድያ ዛሬ ላይ ይህንን ቃል ወደ እኛ ሕይወት አምጥተን ስንመለከተው ብዙዎቻችን አሁንም በስብከታችን ብዛትና በንጝግራችን  በብዙ ወደፊት የሄድንበትን በዚያው ልክ ደግሞ በሕይወት ተሞክሮአችን እና በኑሮአችን በብዙ ወደ ኋላ የቀረንበትን ሁኔታ እናይበታለን ስለዚህ በዚህ በእኛ ዘመን ሕይወትና አገልግሎት ሕይወትና መዝሙር ሕይወትና ስብከት  በብዙ ያልተጣጣሙበት ፍጹም ሊገናኙም ያልቻሉበት ብለን ብንናገር ከእውነት የራቅን አንሆንም አባቶች ሲተርቱ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ እንዲሉ የእኛም ነገር እንዲህና እንዲያ ሆኗልና በዕብራውያን ምዕራፍ 11 የተጻፈላቸው አባቶች ግን ሕይወታቸውና አገልግሎታቸው አንድ ዓይነት ስለሆነ ማለት የሚሰብኩ የሚያስተምሩ የሚዘምሩ ሌላም ሌላም ልንለው እንችላለን ብቻ ሳይሆኑ የሰበኩትንና ያስተማሩትንም ጭምር የሚኖሩ  ስለሆኑ እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ በማለት ቃሉ ይነግረናል ታድያ ዛሬ  ማነው ? በእንዲህ ዓይነት ሕይወት ሆኖ እንደነዚህ አባቶች የሰበከውን ሊኖር ዋጋ እየከፈለ ያለ ? ዛሬ ግን አብዛኛው አገልይ ወደ ፑልፒቱ ቢጠጋ ፣ የፑልፒቱ አገልግሎት የእርሱ ቢሆንና ባያመልጠው ደስተኛ ነው ከዚያ መልስ ያለችዋን የመከራ ሕይወት ግን ፈጽሞ አይፈልጋትም እንደውም የከፋ ነገር ቢመጣ ጴጥሮስ የተጠቀመውን ቃል እርሱም እንደሚደግመው አሁን ላይ  ካለውና ከሚታየው ሕይወት መረዳት እንችላለን  ቃሉ እንደሚነግረን  ጴጥሮስም ከቤት ውጭ በአጥሩ ግቢ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድም ወደ እርሱ ቀርባ አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው እርሱ ግን፦ የምትዪውን አላውቀውም ብሎ በሁሉ ፊት ካደ ወደ በሩም ሲወጣ ሌላይቱ አየችውና በዚያ ላሉት ይህ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ አለች ዳግመኛም ሲምል ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ካደ ጥቂትም ቈይተው በዚያ ቆመው የነበሩ ቀርበው ጴጥሮስን አነጋገርህ ይገልጥሃልና በእውነት አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ አሉት በዚያን ጊዜ ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ሊራገምና ሊምል ጀመረ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ ጴጥሮስም፦ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ ይለናል የማቴዎስ ወንጌል 26 69 _ 75 ጌታ እግዚአብሔር በሁሉ ራሳችንን ያስቀደምንና የተሻልን ያደረግን የመድረክ ላይ  አርበኞች ብቻ ከመሆን ያድነን ከዚህ ይልቅ የሰበክነውን በጥቂቱም ቢሆን ልንኖር የምንጸልይ በጓዳችንም የምንተጋ የልብ ሰዎች ያድርገን ዛሬ እንዲህ ከሆንን ለነገው መከራ ጌታ የምናልፍበትን ጸጋ ይሰጠናል ነገር ግን ይህ አልሆንልን ብሎ በሽሚያና በግፍያ ባገኘነው የመድረክ ጉራ ከረዩ  ያዙኝ ልቀቁኝ ማለታችን ለያዥ ለገራዥ ሳይቀር ማስቸገራችን  የነገው ውርደታችንን እንደ ጴጥሮስ  ያፋጥነዋል ጴጥሮስስ በመራራ ልቅሶ ተመልሶአል እኛ ግን ይሄ ሁሉ የንስሐ ዕድል ላያጋጥመን ይችልና እንጐዳበታለን ስለዚህ ዛሬውኑ ከወዲሁ እንድናስብበት ነገርንም ሁሉ በልክ አድርገን በጓዳችን እንድንጸልይ በጌታ ፍቅር ላሳስብ እወዳለሁ ሌላው የፍየል ሌጦ መልበሱ መደብደቡ መዘበቻ መሆኑ ጊዜ ይቆይ እንጂ በአንድም በሌላም መንገድ መምጣቱ አይቀርም ይሁን እንጂ ይህ እንኳ ባያጋጥም እንደነዚህ አባቶች የተሰጠንን የተስፋ ቃል አምኖ መሞቱ ትልቅ ነገር እኮ ነው ወገኖቼ ዛሬ ግን ብዙዎቻችን ከዚህ በተለየ መልኩ ሰዎች እስኪደክሙ እስኪታክቱና ከደርቡም ላይ ሳይቀር እስኪወድቁ ድረስ የምንናገር አገልጋዮች እንጂ ቃሉን ከምንናገር ውጪ ይህ ቃል ለእኔ እንድወርሰውና እንድሆነው የተሰጠኝ ቃል ነው ስንል ባይፈጸም እንኳ አምነን የምንሞት አገልጋዮች ብዙም አንገኝም ዛሬ ብዙ ንግጝር ብዙ ቃላትና  የቃላት ቅንብር አለ ጌታ ግን ጥቂት እምነት አጥቷል አሁንም ይሄ ጌታ በምሕረቱ ያስበን የተወደዳችሁ ወገኖች ይህንን ትምህርት በዚሁ እቋጨዋለሁ ጌታ በዚህ ትምህርት ሁላችንንም ይባርከን ሕይወታችንንም ይጐብኝ በማለት እሰናበታለሁ



ቀሲስ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment