Friday, 26 June 2015

የትምህርት ርዕስ የጌታ እራት ክፍል አንድ

 የትምህርት ርዕስ



የጌታ እራት






ክፍል አንድ



የተወደዳችሁ ወገኖች በቅድሚያ የጌታ ጸጋና ሰላም ለሁላችሁ ይሁን እያልኩ ሰላምታዬን በማስቀደም ስጀምር ከዚህ በመቀጠል ግን ወደዚህ ወደምጀምረው አዲስ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ከመምጣቴ በፊት በኦድዮ የሚተላለፍ በፓወር ፖይንት የተደገፈ የጋብቻ ትምህርት መጀመራችን ይታወሳል እርሱ እንዳለና እንደተጠበቀ ሆኖ በተከታታይ የሚቀጥልና የሚቀርብ ሲሆን ከዚሁ ጋራ ግን ጐን ለጐን ይህን የጌታ እራት ትምህርት በጽሑፍ ለእናንተ ለአንባቢዎች ለማቅረብና አብሬም ለማስኬድ ስለፈለግሁ ነው ወገኖች እንግዲህ ሁለቱም ትምህርቶች በጣም ጠቃሚ የሆኑ  ፣ ልንከታተላቸውና እንደሚገባም ልናውቃቸው የሚገቡ ትምህርቶች ናቸው የጎደልነውና በእጅጉም የተጐዳነው በእነዚህ አንጋፋ በሆኑ ሁለት ትምህርቶች ማለትም 1 ) የጌታን እራት ምስጢር ጠንቅቆ አለማወቅና ለዚያም እውነት አለመኖር  2) የትዳር ትምህርት ጉድለት እንዲሁም የመረዳት ማነስና አለማወቅ ነው እንግዲህ ጌታ በረዳን መጠን እነዚህን ሁለት የትምህርት አርዕስቶች ይዘን ለእናንተ ይህንን ትምህርት በማስተዋል ለምትከታተሉ ሁሉ የምናቀርበው ይሆናል እንዳልኳችሁ የጋብቻው ትምህርት በኦድዮ የሚተላለፍ ሲሆን የጌታ እራት ትምህርት ግን በጽሑፍ በተከታታይ ለእናንተ ለአንባቢዎች የማቀርበው ነው

       የጌታ እራት ቅዱስ ቁርባን ማለት ሲሆን በእንግሊዘኛው ደግሞ Holy communion ( ሆሊ ኮሚኑየን )  በመባል የሚታወቅ ነው ይህንን የጌታ እራት በመውሰድ የሚለማመዱ ሰዎች መሠረት ሊያደርጉት የሚገባ አንድ የመጽሐፍቅዱስ እውነት አለ እርሱን መሠረት አድርገው ነው ይህንን የጌታ እራት መውሰድ ያለባቸው የመጽሐፍቅዱሱ ክፍልም እንዲህ ይላል በ1ኛ ቆሮንቶስ 10 16 ላይ የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይለደምን ? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን ? ይለናል ታድያ ለብዙ ሰዎች ይሄ ቃል ግልጽ ካለመሆኑ የተነሳ ይመስላል በጌታ እራት አወሳሰድ ጊዜ ብዙ መዝረክረክ የሚታየው ብዙዎች ይሄን ቃል ካለመረዳት የተነሳ የጌታ እራት ሆኖ ስለቀረበና በቤተክርስቲያንም ስለተዘጋጀ ብቻ እንዲሁ ተነስተው ይወስዳሉ ይህ የጌታ እራት ግን ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው የበረከት ጽዋ እንዲሁም ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው የምንቆርሰው እንጀራ ነው ታድያ በእውቀት ማነስ ውስጥ ሆነንና እንዲሁ በዘፈቀደ ብድግ ብለን የምንወስደው የቤታችን እንጀራና የጓዳችን ጽዋ አይደለም ይህን ከክርስቶስ ደም ጋርና ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለውን የበረከት ጽዋና የምንቆርሰውን እንጀራ ስንወስድ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ማድረጋችንን በቅድሚያ እንደሚገባ ልንረዳና ልናስተውል ይገባል በዚህ የበረከት ጽዋና በዚህ እንጀራ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ማድረግ የሚገባው ሰው ደግሞ በቅድሚያ በምን መንገድ ወደዚህ ነገር መቅረብ እንዳለበት እኔ ወንድማችሁ ለእናንተ ለወገኖቼ መንገር አይጠበቅብኝም ይሁን እንጂ ዛሬ ግን እኛ ሁላችንም ከዚህ ነገር የጐደልን ነን እንዲሁ ባወጣው ያውጣው ብለንና በዘፈቀደ ሆነን ነው ወደዚህ የበረከት ጽዋና እንጀራ የምንቀርበው ታድያ ክርስቶስም በዚህ ገበታ ውስጥ እየታዘበን ነው እንደገናም በዚህ አቀራረባችን የእግዚአብሔርን ገበታ በድርጊታችን  የተነቀፈ እናደርገዋለን በትንቢተ ሚልክያስ 1 7 ላይ በመሠዊያዬ ላይ ርኩስ እንጀራ ታቀርባላችሁ እናንተም ያረከስንህ በምንድር ነው ? ብላችኋል የእግዚአብሔር ገበታ የተነቀፈ ነው በማለታችሁ ነው ይለናል እንደገናም በትንቢተ ሚልክያስ 1 12  ላይ እናንተ ግን፦ የእግዚአብሔር ገበታ ርኩስ ነው ፍሬውና መብሉም የተናቀ ነው በማለታችሁ አስነቀፋችሁት ይለናል ለዚህ ነው ይህንን ሃሳብ ከሐዲስ ኪዳኑ ሃሳብ ጋር ስናያይዘው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ጅራፍ ይዞ መነሳት ያስፈለገው ከነዚህም ነገሮች የተነሳ ነው በማቴዎስ ወንጌል 21 12 ላይ ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠ ይለናል እንደውም በአንዳንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያኖች እነደተመለከትኩት ወገኖች ዛሬም የሚያስፈልገን እንግዲህ ይሄ  የጌታ ጅራፍ ነው ይህ ዓይነቱ ነገር ጌታ እራሱ ባዘጋጀው ጅራፍ እንጂ በልመናና በማባበል መቅናት አይችልም ይለመን ቢባልና እንለምን ወይም እንለመን  ብንልስ እስከመቼ ይሆናል ጌታ እግዚአብሔር ልዑል አምላክም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሰለጥን የሚወደውንም እንዲሾምበት እስክታውቅ ድረስ የተባለው ንጉሥና እና ማኔቴቄልፋሬስ የተባለውም የዛው ተከታይ ዋልጌ ንጉሥ ተለምነው የቀኑ አልነበሩም የእግዚአብሔር ፍርሃት ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር እውቀት ይመጡ ዘንድ ያልፈለጉትንና ሊሆኑም የማይሹትን እንዲሆኑ ያደረጋቸው ከእነርሱ ኃይል በላይ የሆነ ልዩ አስገዳጅ ኃይል መጥቶባቸው ነው ( ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 4 እና ምዕራፍ 5 በሙሉ እንመልከት )ያለነው የእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ነው ዕቃ ዕቃ እየተጫወትን ወይንም የቤታችንን ሻይና ቡና እየተገባበዝን አይደለም ያለነው በቤት ያለ ሻይ ቡና ለግብዣ ሲመጣና ሲቀርብ እንኳ በብዙ ጥንቃቄና ክብር ነው የጌታችን የበረከት ጽዋና እንጀራ ግን በቤት ያለ ሻይና ቡና ያክል እንኳ ከበሬታ አልተሰጠውም የመጣና እግር ያደረሰው ሁሉ ዘርፎ የመሄድ ያክል የጌታን እራት እንዲያው በዘልማድና በደቦ ዘርፎም ይሁን ተሻምቶ ብቻ  ወስዶ ይሄዳል ይህ እንግዲህ ላስተዋለውና ለተረዳው ሰው እጅግ በጣም የሚያሳዝን ልብንም የሚሰብር ነገር ነው የሌላውን አላውቅም እንጂ እኔ በበኩሌ ግን ባየሁት ነገር ልቤ  በጣም አዝኖ በቤቴ እየጸለይኩ እገኛለሁ እግዚአብሔር በዚህ ነገር አብያተ ክርስቲያናትንና አገልጋዮችን አጥቢያ ቤተክርስቲያኖችንም ጭምር ይፈውስ በአንዳንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያኖች ደግሞ የዚህ የጌታ እራት ቅዱስነት ሳይሆን የሚታያቸው ቶሎ ብሎ የሚታያቸው የራሳቸው ነገር ነውና ይህን የጌታ እራት የሚያቀርቡት ማን ከእነርሱ ጋር እንደሆነ እና ማን ከእነርሱ ጋር እንዳልሆነ በዚህ በጌታ እራት አወሳሰድ ለመፈተንና ለማወቅ ነው ይህ ደግሞ ትልቅ ዓመጽና የድፍረት ኃጢአት የክፋትም ሥር ስለሆነ እግዚአብሔር ይገስጸው ከማለትና ለእግዚአብሔር ፍርድ አሳልፈን ከመስጠት በቀር የምንለው የለም መጽሐፍቅዱሳችን በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲህ ይላል የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል ? በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና፤ ደግሞም፦ ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው( ዕብራውያን 10 29 _ 31 )ወገኖቼ የጌታ እራት ማን ከእኛ ጋር እንደሆነና እንዳልሆነ የምንፈትንበትና የምንለይበት ሳይሆን እኛኑ ራሳችንን ፈትነን የምንቀርብበት እራት ነው አረ ጌታ እግዚአብሔር ይቅር ይበለን ማስተዋልንም ይስጠን መጽሐፍቅዱሳችን አሁንም የሚለው እንዲህ ነው ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን ስለዚህ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ ለመብላት በተሰበሰባችሁ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ ማንም የራበው ቢኖር ለፍርድ እንዳትሰበሰቡ በቤቱ ይብላ የቀረውንም ነገር በመጣሁ ጊዜ እደነግጋለሁ 1 ቆሮንቶስ 11 27 _ 34 ወገኖቼ  የጌታን እራት ለመብላት በተሰበሰብን ጊዜ እርስ በእርስ መጠባበቅ የሚባል ነገር ዛሬ የለም ለምን ስንል ወንድም ለወንድሙ ግድ የሚሰኝበት ጊዜ ላይ አይደለንማ ያለነው ርቦን ከሆነ ቃሉ እንደሚነግረን በቤታችን እንብላ ምክንያቱም  በበላነው መብል ምክንያት የበላነው ሳንለይ እና ሳይገባን ነውና ለፍርድ እንበላለን ከዚህም ሌላ ከዓለም ጋር እንኮነናለን በጌታም እንገሠጻለን አያሌዎች አንቀላፍተዋል ይለናልና ደግሞ ይህ ብቻ ሳይበቃን ከዚህም ሌላ  መድከም መታመምና ማንቀላፋት በብዙ ለእኛ ይሆናል  ስለዚህ ከዚህ ሁሉ ለመጠበቅ የጌታ እራት የምንሰጥ እኛ  ከእኛ ጋር እንዲሆን የምንፈልገውን እና በዙርያችን ያለውን ምዕመን ሳይሆን መፈተን ያለብን ራሳችንን ነው ፈትነን ወደዚህ እራት መቅረብ ያለብን እንደገናም የጌታ እራት የሰዎች ከእኛ ጋር ለመሆናቸው እና ላለመሆናቸው መፈተኛ አይደለም ከእኛ ጋር ሆነው ከዚህ ከሚወዳቸው ጌታ ጋር ባይሆኑስ ? ምን ልንል ነው በዚህ ነገራችን ሰውንም ግብዝና ይበልጥ ለእግዚአብሔር ፍርድ የተዘጋጀ ተላልፎም የተሰጠ እናደርገዋለንና ከዚህ ክፉ ነገራችን ፈጥነን እንመለስ  ወገኖቼ ሰዉ ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣው ጌታን ፈልጎ ነውና በአምላኩ ራሱን ችሎ ይቁም የጌታም ይሁን የተጠራው በቅድሚያ የጌታ ሊሆን ነው ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያን የሚመጡትና የጌታንም እራት የሚወስዱት ከእኛ ጋር እንዲሆኑ ሳይሆን በቅድሚያ ከጌታ ጋር እንዲሆኑ ነው ደግሞም ከጌታ ጋር የሆነ ሰው ነው ከእኛም ከእያንዳንዳችን ጋር ሲሆን ደስ የሚለው ከጌታ ጋር ሳይሆን ከእኛ ጋር ቢሆን ለእኛ ምን ይጠቅመናል ? ለጌታ ያልሆነ ሕዝብ ይመስለናል እንጂ ለእኛም አይሆንምና በአጓጉል ዘዴያችን የያዝነውን ሕዝብ በቶሎ እንልቀቅ  መልሰንም ለጌታ እንስጠው እናስረክበው ለጌታ ሊሆን ያለውን ሕዝብ ደግሞ ለራሳችን አድርገን ከሆነ እንደውም ከጌታ ለይተነዋልና በጌታ እንጠየቃለን እንደገናም ይህ አሠራር ቲፎዞን የመፈለግ አሠራር ስለሆነ ጌታ በብዙ ይጸየፈዋል እኛንም ይቀጣናል እኛ አገልጋዮች ደግሞ ሰዎችን የጌታ ልናደርግ ተጠራን እንጂ በጌታ ቤት ቲፎዞ ልንሰበስብ አልተጠራንም እግዚአብሔር ከዚህ ነገር ፈጥኖ ያውጣን ይፈውሰንም ቅዱሳን ወገኖች በቀጣዩ የክፍል ሁለት ትምህርት እስከምንገናኝ ጌታ እግዚአብሔር እንግዲህ በዚህ ትምህርት ሁላችንንም ይገናኘን ተባረኩልኝ ለዘላለም በማለት እሰናበታለሁ
Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለ ራዕይ

ቀሲስ ዮናስ ጌታነህ



ቀሲስ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment