Tuesday, 9 June 2015

ብዙ ዓይነትና ተለዋዋጭ የሆኑ ጥቅሶችን በአንድ ባለቤት ባለው ነገር ውስጥ ማነጻጸር Comparing Various Verses on the Same Subject ክፍል አምስት ንዑስ ክፍል ሁለት







ብዙ ዓይነትና ተለዋዋጭ የሆኑ ጥቅሶችን በአንድ ባለቤት ባለው ነገር ውስጥ ማነጻጸር  

Comparing Various Verses on the Same Subject


ክፍል አምስት


ንዑስ ክፍል ሁለት


ብዙ ሕዝብ ዮሐንስ ወንጌል 3 16 መሠረት በማድረግ ያምናል በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና ዮሐንስ ወንጌል 3 16 ታድያ ኢየሱስን በማመን ሁላችንም በቀላሉ የምንፈልገውና የምናደርገውም የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ነው በመሆኑም ይህንን ሁኔታ ዛሬም በንዑስ ክፍል ሁለት ላይ ልናነሳው ከምንፈልገው የእግዚአብሔር ቃል ሃሳብ ጋር በማያያዝ የምንመለከተው ይሆናልና ተከታተሉ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 19 ቊጥር 16 እና 17 ላይ እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር
ላድርግ አለው እርሱም፦ ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ አለው ይለናል ጌታችን ኢየሱስ በእርሱ ከማመን ሌላ ይህንን ሰው የጠየቀውም ሆነ የመለሰለት ነገር የለም ለወጣቱ ሰው የዘላለምን ሕይወት ስጦታ ለመቀበል የእግዚአብሔርን ሕግጋት መታዘዝ እንዳለበት ነገረው በመሠረቱ የዚህ የወጣቱ ሰው ጥያቄ መልካምና ተፈላጊ የሆነ ጥያቄ ዛሬም ጭምር ወደዚህ የዘላለም ሕይወት ያልገባ  ሰው ሁሉ ሊያነሳው የሚገባ ተገቢ የሆነ ጥያቄ ነው ታድያ ዛሬ ግን ወደ ዘላለም ሕይወት የመግባት ጉዳይ ግድ ብሏቸው ይህን ጥያቄ የሚያነሱ ይኖራሉ ብለን ብናስብም እንኳ እጅግ በጣም በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት ሰዎች ከሚያነሱ በቀር አብዛኛው ሰው ጥያቄው የተለየ ነው እንደገናም ጥያቄውን ወደ አምላኩ ይዞ ይምጣና ያንሳ ቢባል እንኳ የሚያነሳው በዚህ ምድር ላይ ሳለ ያላሟላውንና ሊሟላለት የሚፈልገውን ነገር ብቻ ነው ለዚህ ነው መጽሐፍቅዱሳችን የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ በማለት አንድን ባለጠጋ ሰው  እርሻው እጅግ ፍሬያም የሆነችለት  ምሳሌ በማንሳት  ይህ ሰው ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ፧ ብሎ በልቡ አሰበ በማለት ይጀምርና እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፥ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ ነፍሴንም አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ እግዚአብሔር ግን አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል፧ አለው ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው እያለ በዝርዝር ሲናገር የምንመለከተው የሉቃስ ወንጌል 12 16 _ 31 እዚህ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ይህንን ቃል በምሣሌ ሲያስቀምጥ ገንዘብ ማግኘትን መልበስንና መብላት መጠጣትን እየተቃወመ እንዳልሆነ ለሁላችንም ግልጽ ሊሆን ይገባል እርሱ ሊል የፈለገው ገንዘብ ማግኘቱ መልበሱና መብላት መጠጣቱ እንዳለ ሆኖ ልናስቀድመው የሚገባን ግን የእግዚአብሔርን መንግሥት ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ ነው ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት ጉዳይ የዘላለም ነገር ነውና ሰዎች ግን ካለማስተዋል የተነሳ ይህንን ትተው ማለት የዘላለም መንግሥቱን ነገር ትተው የሚያልፍን ባለጸግነት ተስፋ ያደርጋሉ ለዚያም ሲጋደሉና እርስ በእርስ ሳይቀር ነገሩ የጥቅም ጉዳይ ይሆንና አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ሲነሳ ይስተዋላል ታድያ እኛ ዛሬም ሳይገባን ቀርቶ በከፍተኛ ሁኔታ እርስ በእርስ ሳይቀር ብንጋደልበትም መጽሐፍ ቅዱሳችን ግን የሚያልፍ ባለጸግነት ይለዋል ለዚህ ነው በ1ኛ ጢሞቴዎስ 6 17 _ 19 ላይ በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው የሚለን የሚያልፍ ባለጸግነት በአገልግሎት መሐል በወንድሞች መሐል በዘመዶች በጓደኞችና በመሳሰሉት ሳይቀር መሐል እየገባ ደም እስከመቃባት ያድርስ እንጂ ባለጸግነቱ የበዛ ሆኖ ጐተራ አፍርሼ በማስባል ሌላ ጐተራ ለመሥራት የሚያስመኝ ቢሆንም መጽሐፍቅዱሳችን ግን እውነተኛ ነውና የሚያልፍ ስለሆነ የሚያልፍ ባለጸግነት ነው ይለዋል ደግሞም ይህን የሚያልፍ ባለጸግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸውም ስላለን እንኳን ተስፋ ልናደርግበት ልንጣላበትና ሌላም ሌላም ደረጃ ልንዳረስበት የሚገባም ባለመሆኑ የሚያልፍ ነው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፪ ላይ የተጻፈለት ሰው ጐተራም ሳይሰራ ጐተራ አፍርሼ ሌላ ጎተራ እሰራለሁ በሚል ምኞት ነው የቀረው ታድያ ዛሬም በዘመናችን ይህን በመሠለ ምኞት የቀሩ ያጠራቀሙትን እንኳ ሳይበሉ ለሌሎች የሆነባቸው ብዙዎች ናቸው የሚጠቅመው ግን ሁሉም ነገር አስፈላጊያችን ሆኖ ወደ እኛ ቢመጣም እንኳ ለእኛ በቅድሚያ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለጸጋ መሆን ነው በእግዚአብሔር ዘንድ ባለጸጋ የሆነ ሰው ብልጽግናው የሚያልፍበት አይደለም እስከ ጽዮን ድረስ ተከትሎት ሄዶ በእግዚአብሔር ፊት የሚያሸልመው ይሆናል በዚህ ምድርም ሳለ ብዙዎችን ይጠቅምበታል እርሱም ይጠቀማል ስለዚህ በእግዚአብሔር ፊት ጥያቄያችን ሊሆን የሚገባው ሁልጌዜ የሚያልፍ ባለጸግነትን ያማከለ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ወጣቱ ሰው እንደጠየቀው ዓይነት የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘውና በእግዚአብሔር ዘንድም ባለጸጋ የሚያደርገን ሊሆን ይገባል ይህን ደግሞ ትእዛዛቱን በመጠበቅ  እና ትእዛዛቱንም በመታዘዝ ውስጥ  የምናገኘው ነው የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስንታዘዝ የዘላለምን ሕይወት እናገኛለን የዘላለምን ሕይወት የተራበ በማብላትና በማጠጣት የታረዘንም በማልበስ  የምናገኘው አይደለም የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 16 ላይ የተጻፈውን ቃል አሜን ብለን ስንቀበልና ለዚህ ቃል ስንታዘዝ ነው የዘላለምን ሕይወት የምናገኘው ይህ ቃል እኛን ለማጥመድ ሲባል ከሰዎች ኪስ ሆን ተብሎ ታስቦበት የወጣ ቃል ሳይሆን የጌታችን ቃልና የጌታችን ትእዛዝ ነው በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና ስለሚለን ቃሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረንና እንዳንጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ በወደደበት በእርሱ ማመን ተቀዳሚ ምርጫችንና መታዘዛችን ሊሆን ይገባል  ይህ ደግሞ የጌታ ትእዛዝ ነውና  ከዚህ ውጪ ለእኛ ሕይወት የሆነና የተዘጋጀም ሕይወት የለም በዚህ እውነትና የጌታ ትእዛዝ ቃል አምነን ሳንድን በሌላ በምንም ልንድን አንችልም ጌታ እግዚአብሔር በዚህ እውነተኛ ቃል ይገናኘን ተባረኩልኝ



ቀሲስ ዮናስ ጌታነህ








No comments:

Post a Comment