ለቅዱስን የታዘዘ ወቅታዊ መልዕክት
ክፍል ሦስት
የመልዕክት ርዕስ
ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል
እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፦ በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል
የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው ? በቀንድህ ዘይቱን ሞልተህ ሂድ በልጆቹ መካከል
ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ አለው ሳሙኤልም
እንዴት እሄዳለሁ ? ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል አለ
1ኛ ሳሙኤል 16 ፥ 1 እና 2
የተወደዳችሁ ወገኖች በክፍል ሦስት ትምህርታችን ላይ የምንመለከተው የመጨረሻና የማጠቃለያ ሃሳብ ነው «
ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል»
ሳሙኤል ለምን ይህንን ሃሳብ መናገር ወደደ ? ሳኦል ምንድነው የሰማው ? ወደ ግድያስ ያደርሱታል ተብለው የሚታሰቡት ነገሮች ምንና ምን ናቸው ? የሚሉትንና የመሣሠሉትን ጥያቄዎች ስናነሳ መልሳችንን ከዚሁ ከመጽሐፍቅዱሳችን እናገኛለን የእሴይ ልጅ የዳዊት መቀባት ለሳኦል እንግዳ ሃሳብ አይደለም የሚቀባው የእሴይ ልጅ ዳዊት እንደሆነ ለሳኦል በግልጽነት ባይታወቀውና ባይነገረውም በምትኩ ግን ንጉሥ ይሆን ዘንድ የሚቀባ ሰው እንዳለ ለሳኦል ተነግሮታል ይህንንም ሃሳብ የምናገኘው በ1ኛ ሳሙኤል 13 ፥ 14 ላይ አሁንም መንግሥትሕ አይጸናም እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበክምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዞታል አለው ይለናል ነገር ግን ሳሙኤል ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል ያለበት ዋናውና ቁልፉ ሃሳብ ሳኦል እንደ ልቡ የሆነ ሰውና በምትኩ የሚነሳ ንጉሥ እንደሚመጣ ያወቀና የተነገረው ቢሆንም ከዚህም ሌላ በቅድምና ለእስራኤል ንጉሥ ይሆን ዘንድ በተፈለገበት ጊዜ ለንግሥናው የሹመት ዙፋን ያበቁ የአስተዳደርንና የአሠራርን ብቃት የሚሰጡ መሠረታዊ የእግዚአብሔር ቃል እውነቶችን ከተሾመበት አንስቶ ለእግዚአብሔር ቃል ታምኖ እስካልታዘዘበት ወይንም የእግዚአብሔርን ቃል እስከናቀበት ድረስ ባሉ የሕይወትና የጉዞ መስመሮች ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ከነቢዩ ሳሙኤል በተደጋጋሚ ሰምቷል ነቢዩ ሳሙኤልም የሳኦልን ሁኔታ ከማንም ይልቅ በአግባብ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በ1ኛ ሳሙኤል 13 ፥ 24 እና 25 ላይ ከምክር ጋራ የሆነ የማስጠንቀቅያ ቃል አስተላልፎለታል የምንባቡ ክፍልም እንዲህ በማለት ይናገራል ብቻ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ያደረገላችሁንም ታላቅ ነገር አይታችኋልና በፍጹም ልባችሁ በእውነት አምልኩት ነገር ግን ክፉ ብትሠሩ እናንተም ንጉሣችሁም ትጠፋላችሁ ታድያ ይህ ለሳኦል በቂ የሆነ ትልቅ ግንዛቤም የሚሰጥ የምክርና የማንቂያ ቃል ነው ሳኦል ግን ከዚህ አልፎ የሚተካው ንጉሥ ሳይቀር በፊት ለፊቱ መጥቶ እስኪቀባ ድረስ እንኳን አይደለም መንቃት የመባነን ነገር እንኳ በጥቂቱም አልታየበትም በመሆኑም ይህ ለሳኦል አሳዛኝ የሕይወቱ ታሪክ ነው እግዚአብሔርም ሳሙኤልን በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው በቀንድህ ዘይቱን ሞልተህ ሂድ በልጆቹ መካከል ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ አለው ሳሙኤልም እንዴት እሄዳለሁ ? ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል ያለው ከዚህ የተነሳ ነው[እንዴት እሄዳለሁ ? ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል ] እንግዲህ ተኝቶ ከርሞ ድንገት ከባነነ ሰው የሚጠበቀው ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም ሳሙኤል እንዳለው ግድያ ነው ግድያ በመንፈሳዊው ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እውነት ስንመለከተው የትክክለኛ ሰዎች ውሳኔና የሕይወት እርምጃ አይደለም ይህን የሚያደርጉ ሰዎች የተሳሳቱና ኮንፊውዢን ውስጥ የገቡ የሕይወት ውሳኔም ያጡና ግራ የተጋቡ ሰዎች ድርጊት ነው ግድያ ወንጀለኞችና ቀማኞች የሚፈጽሙት ተግባር ነው ሳኦል እንግዲ ሳሙኤል ሳያሰልስ በተደጋጋሚ ባስተላለፈለት የእግዚአብሔር ቃል ተጠቃሚ ባለመሆኑ እግዚአብሔር ሳኦልን ተራምዶ ሊሠራ ባለው አዲስ የአሥራር ሂደትና መንግሥታዊ መዋቅር ሳኦል ብዙ የእግዚአብሔር ነገር ያመለጠውና ያለፈው ነውና ተደሳች ሳይሆን ተቃዋሚ ሆኖ እናገኘዋለን ለዚህም ነው እንግዲህ ሳሙኤል ለእግዚአብሔር መልስ ሲሰጥ ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል ያለው ሳኦል ሳይባንን ሳይሆንለትም ቀርቶ እንጂ እግዚአብሔር ጋር ድብቅ አጀንዳ የለም እግዚአብሔር እርሱን ለማወቅና ለማክበር ለወደዱ ሁሉ አጀንዳው ግልጽ ነው ሮሜ 8 ፥ 18 _ 32 ከዚህም ሌላ ሳኦል ከምንም ይልቅ የራሱ ነገር እያሳሰበውና ግድ እያለው የመጣ ሰው በመሆኑ እግዚአብሔር በሳሙኤል በኩል ላመጣቸው የእግዚአብሔር ቃል እውነቶችና መስጠንቀቅያዎች ሳኦል የተዘጋጀ አልነበረም የራሳችን ነገር ግድ ሲለንና ሲያሳስበን ከእግዚአብሔር ቢዝነስ ይልቅ ወደ ራሳችን ቢዝነስ ስንመለስ የምንሆነው እንዲህ ነው የውስጥ ጩኸታችን ሳይቀር የሚሆነው እንደ ሳኦል በድያለሁ አሁን ግን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት፥ እባክህ፥ አክብረኝ ለአምላክህም ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ የሚል ነው 1ኛ ሳሙኤል 15 ፥ 30 እና 31 የበደላችን ኑዛዜ ሳይቀር ከእግዚአብሔር ጋር በስምምነት ለመሄድ ፣ ይህን እግዚአብሔርንም በእውነት ለማምለክ ሳይሆን በሰዎች በአለቆችና በሹማምንቶች እንዲሁም በሕዝብ ፊት ለመክበር አንቱ እንደተባሉ ለመቅረት የሆነ ጥረት በመሆኑ ፍጻሜው የማያምር ነው ሰዎችም ሆኑ አለቆች ስመ ጥር ሆነን አንቱ ቢሉንና ቢያከብሩን የሚጠላ ማንም የለም ይህ የሚሆነው ግን ከእግዚአብሔር ጋር በስምምነት ስንሄድ ነው ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልተን ትእዛዛቱንም ንቀንና በትልቁ በእግዚአብሔር ፊት ተንቀን ሰዎች ታላላቅ ሰዎችም ይባሉ አለቆች ቢያከብሩንና በየአደባባዩም አንቱ አንቱ ቢሉን አንድ ቀን ያ ሁሉ ቀርቶ ምን ሊሉን እንደሚችሉ መናገር አያስፈልገኝምና ለሁላችንም ግልጽ ነው ያን ጊዜ ነው እዩኝ እዩኝ ማለት ይቀርና ደብቁኝ ደብቁኝ የሚመጣው ስለዚህ ሳኦል ጊዜው ካለፈ በኋላ የባነነና የሚባንንም በመሆኑ ጊዜው ያለፈበት ሰው ጥረቱ መሻሻልና መለወጥ መስተካከልም ሳይሆን ቅናት ጥል ክርክር መግደልና የመሣሠሉት የሥጋ ሥራዎች ናቸው በመሆኑም ሳሙኤል እውነቱን ሊነግረን ወዶ እንዴት እሄዳለሁ ? ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል አለ ወገኖቼ ለሳኦል ያለፈበት ጊዜ ለእኛ ግን አላለፈብንም እንደውም ጊዜው አሁን ነው ከጥል ከክርክርና ከቅናቶቻችን እንዲሁም ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው ይለናልና ቃሉ በጥላቻ ካለ መገዳደላችን ባነን የምንመለስበት ጊዜው አሁን ነው እግዚአብሔር ትልቅ ነው ማንንም ደግሞ አይንቅምና ዛሬም አልናቀንም አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁለተኛና ሦስተኛ እድልም እየሰጠን ይገኛል ስለዚህ መመለሳችን ዛሬውኑ ይሁን ወገኖች በዚህ ቃል እግዚአብሔር ይጎብኘን ተባረኩልኝ
ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ
ወደ ሮሜ ሰዎች 13 : 11 - 14
መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ
ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4 : 31 - 32
ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ
|
No comments:
Post a Comment