ይህ በ Joshua Breakthrough
Renewal Teaching and Preaching Ministry
_ ስር እየተዘጋጀ የሚቀርብላችሁ መንፈሳዊ ትምህርት ነው ዛሬ ለትምህርታችን እንደ መነሻ ሃሳብ አድርገን የምንመለከተው ሃይማኖተ አበው በተባለው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት አንጋፋ መጽሐፍ ተብሎ ከሚጠራው ውስጥ ተጽፎና ሰፍሮ የሚገኝ ነው ቤተክርስቲያኒቱም አመክንዮ ዘሐዋርያት በሚለው የእምነት አንቀጽዋ ላይ አስፍራው ትገኛለች ሃሳቡም እንዲህ የሚል ነው እና እንከታተለው
ወአረቀ ትዝምደ ሰብእ ምስለ እግዚአብሔር ሊቀ ካህናቲሁ ለአብ
ትርጉም _ የአብ ሊቀካህናት የሆነው እርሱ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ
ሃይማኖተ አበው
አመክንዮ ዘሐዋርያት
ምዕራፍ ሰባት
ክፍል አንድ
ቁጥር 23
የተወደዳችሁ ወገኖች ይህ ክፍል ከመጽሐፉም ሃሳብ እንደተመለከትነው የኢየሱስ ክርስቶስን አስታራቂነትና ሊቀካናትነት የሚናገር ሲሆን ያስታረቀውም ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር እንደሆነ በግልጽነት ይነግረናል መጽሐፉን እንደ መጽሐፍቅዱስ ሥልጣን ቃል በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈ፣ ቅዱሳንም በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የጻፉት መጽሐፍ ነው በማለት በእኩልነት ከመጽሐፍቅዱስ ጋር የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለን በእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን ልክ ባናወዳድረውና ባናስተያየውም በውስጡ የተጻፉት አንዳንድ ሃሳቦች የእግዚአብሔርን ቃል የሚደግፉ በመሆናቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለማስተማር በአስረጂነት ልንጠቅሳቸው እንችላለን ሌላውና ዋናው ልንገነዘበው የሚገባው ሃሳብ ግን የመጀመርያዪቱ እናት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ጥንተ መሠረቷ የእግዚአብሔር ቃልና የወንጌል እውነት ስለሆነ ትክክለኛ የኢየሱስ ክርስቶስን ሊቀካህናትነት ሰውንም ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ አምና በትክክል ብቸኛ አስታራቂነቱንና አማላጅነቱን የምትሰብክ መሆንዋን ከተጻፈው የመጽሐፉ ክፍል መገንዘብ እንችላለን ለዚህ ነው እኔም ይህንን የሃይማኖተ አበውን መጽሐፍ መጥቀስ የፈለኩት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እናት ቤተክርስቲያናችን ወደ ጥንተ መሠረቷ ተመልሰን የእምነት መግለጫዎችዋንና ዶክትሪኖችዋን ሳይቀር
በእግዚአብሔር ቃል ስንፈትሽ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ፍጹም የማይቃረኑና ትክክለኛም ናቸው ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ወንጌል ገባን የእግዚአብሔርን ቃል አነበብን ተረዳን የምንል የቃሉ አማኞች ፣ አገልጋዮች ፣ አስተማሪዎች፣ ወንጌላውያንና መጋቢዎች ቤተክርስቲያኒቱን ምንም ነገር እንደሌላት አድርጎ በመቁጠር ልንመለከታትና በዚያው መንገድ ልንቀርብ ተገቢ አይደለም ከዚህ ይልቅ ነገርዋን ወደሚያውቁ ዶክትሪንዋና ፣ የእግዚአብሔር ቃል መሠረትዋን ቋንቋዋንና ባህሏንም ጭምር በጥልቀት ወደተገነዘቡ በጌታም ቤት የቆዩ የቃሉ አማኞችና አገልጋዮች ጋር ጠጋ ብሎ በመመካከር በመረዳዳትና ሲያስፈልግም በትሕትና በመማር የሞያ ማሻሻያዎችንም ጭምር በመውሰድ ሕዝባችንን ወደ ትክክለኛው የእግዚአብሔር ቃል እውነትና የወንጌል ቃል መንፈሳዊ ጉልበት አግኝቶ በተገቢው መንገድ ማምጣት ይቻላል ከዚያ ውጪ ግን ሥራ እናበላሻለን እንጂ የምናመጣው ለውጥ የለም በዚህ ውስጥ ግን በመልካም ምሳሌነቱ ልጠቅሰው የምፈልገው በፓልቶክ ውስጥ ያለ የክርስቲያን ፕላስ ኦል መሪና ባለራዕይ የሆነውን ፓስተር ዮሐንስ ተፈራን (@መልካምን) ሲሆን በዚህ በመልካም ምሳሌነቱ ላመሰግነው እወዳለሁ ምክንያቱም መልካም በቤተክርስቲያን ውስጥ ከተሰጠው የእረኝነት አገልግሎት ሌላ በዚሁ የፓልቶክ ሩም ውስጥ መሪና ባለራዕይ ሆኖ ለረጅም ዘመናት ልዩ ልዩ ፕሮጋራሞችን በመንደፍ ሕዝቡ በተለያዩ ጸጋ ባላቸው ሰዎች እየተጠቀመና የእግዚአብሔርንም ቃል እየተመገበ እድገቱ ሙሉ እንዲሆን ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ ሰው ነው ፕሮግራሞቹ ደግሞ በሰዓት የተወሰኑና የተለኩ በመሆናቸው የተንዛዙና አሰልቺዎች አይደሉም
ሰዓታቸውን ጠብቀው ተጀምረው በሰዓት ያልቃሉ ለቀጣዩ ባለተረኛም በጊዜ ይለቃሉ ያስረክባሉም በዚህ ውስጥም ሩሙ ውጤታማ ሆኗል የፕሮግራሞቹ ይዘትና ቅንብር መዝረክረክ የሌለበትና መልካምም ስለሆነ ፓስተር መልካምንም እንዲሁ ውጤታማ አድርጎታል
ከዚህም ሌላ በጣም የሚደንቀኝ ሀገር አቀፍ የኦርቶዶክስ ተሃድሶ ለማምጣት እግዚአብሔር ላስነሳቸው ሰዎች ፓስተር ዮሐንስ በር መክፈቱ ነው ፓስተር ዮሐንስ ለነዚህ ሰዎች በር በመክፈት
አገልግሉ በማለት ዝም ብሎ የተቀመጠ ብቻ ሳይሆን ከእነርሱም ጋር ሆኖ በፕሮግራሙ በመገኘትና የፕሮግራሙንም ይዘት በመከታተል አብሮ ሆኖም በመሥራት በማበረታታት አንዳንዴም የግዕዝ ቋንቋዋንም ሳይቀር ጠቀስቀስ እያረገና የዜማ ቅላጼዋን እያረከረከ በኅብረት የሚያገለግል ነው
እነዚህ ሰዎች ፓስተር ዮሐንስ በደስታ ባይቀበላቸውና በሩን ባይከፍትላቸው በዚያው ባሉበት ከሚያገለግሉ በቀር ይህንን ራዕያቸውንና እውቀታቸውን ለሌሎች ክርስቲያኖች ለማካፈል አይችሉም ነበር የራዕይ መከፋፈልና መቀባበል ደግሞ ለእግዚአብሔር ሥራ አስፈላጊና ዋናም ነገር ነው ፓስተር ዮሐንስን እኔም በቅርቡ አውቀዋለሁ ከፓስተርነት ይልቅ ወንድምነትንና ወዳጅነትን የሚያስቀድም ጥሩ የወንጌል ልብ ያለው እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ ለለውጥና ለእድገት ያስነሳው የእግዚአብሔር ሰው ነው ጌታ ዘመኑን ይባርክ እላለሁ ወደ ተነሳሁበት የትምህርት ክፍል ስመለስ የሃይማኖተ አበው መጽሐፍ እንደገናም የእናት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተክርስቲያን የእምነት መግለጫ ወአረቀ ትዝምደ ሰብእ ምስለ እግዚአብሔር ሊቀ ካህናቲሁ ለአብ ስንተረጉመው የአብ ሊቀካህናት የሆነው እርሱ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ ይለናል እንግዲህ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የአብ ሊቀ ካህናት በሆነው በክርስቶስ የታረቀ ከሆነ ሌሎች አስታራቂዎች ለምን አስፈለጉ ? በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፍቅዱስ ብቻ የሚል ቢሆን ሰዎች ባለማወቅ ዛሬም አፋቸውን ሞልተው የእናንተ መጽሐፍ መጽሐፍቅዱስ ነው እንዲህ የሚለው ብለው እንደሚናገሩት በሆነላቸው ነበር ለነገሩ መጽሐፍቅዱ ሱም የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ጎራ ተለይቶበት የእናንተ የእኛ የሚባል አይደለም መጽሐፍቅዱስ የሁላችንና አንብቦም ሊረዳው ሊጠቀምበት የወደደውም ሁሉ የሚጠቀምበት የእግዚአብሔር
መጽሐፍ ነው የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍቅዱስ የጎራ ልዩነትን የሚያፈርስ ነው እንጂ
የእናንተ የእኛ አስብሎ
በጎራ የሚያስቀምጥ አይደለም ነገር ግን ይህን የኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅነትና የአብ ሊቀ ካህናትነት መጽሐፍቅዱስ ብቻ የሚናገር ሳይሆን ሃይማኖተ አበው የተባለው አንጋፋ የኦርቶዶክስ መጽሐፍና የኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ የተባለውም አመክንዮ ዘሐዋርያት በትክክል ይናገራል እንግዲህ የኢየሱስ ክርስቶስን ሰውን ከአባቱ ጋር ያደረገውን የማስታረቅ አገልግሎት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካላመነችበት ስለምን በእምነት መግለጫዋ በአመክንዮ ዘሐዋርያት ላይ አሰፈረችው ? ካሰፈረችው ደግሞ አሁን ላይ
ያለችዋ ኦርቶዶክስ አስተማረችው ባንልም የመጀመርያዋ ጥንታዊት ኦርቶዶክሳዊት ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊቷ አስተምራ ዋለች እንላለን ደግሞም ይህ እውነት በእኛም ዘመን ላይ እንደተጻፈ አግኝተነዋልና በእርግጠኝነትም አስተምራዋለች ብለን እናምናለን የዛሬዋ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ግን ይህን ግልጽ እውነት የእምነት መግለጫዬ ነው እያለች እያነበበችም ስለምን ለማስተማር እንደከበዳት ለእኛም ግልጽ አይደለም ከዚህም ሌላ ይህንን የኢየሱስን የአስታራቂነት እውነቱን አግኝተው የሚያስተምሩትን በውስጧ ያሉትን ሰዎች አማላጅ አስታራቂ ሆኖ ሳለ ፈራጅ ብቻ ነው ስትል ትቃወማለች ታሳድዳቸውማለች
ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅነትና የአብ ሊቀካህናት መሆኑም ግን በመጽሐፍቅዱስ ላይ ብቻ ሳይሆን በመጽሐፏ እንደገናም በእምነት መግለጫዋ በአመክንዮ ዘሐዋርያት ላይ ሳይቀር ተጽፎና በግልጽ ሰፍሮላት ይገኛል ይህ እንግዲህ መሠረታዊ የእግዚአብሔር ቃል መልስና የዛሬዋ ማለትም የአሁንዋ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተክርስቲያን ልትቀበለው የሚገባ እውነት እንደሆነ እኛም አበክረን ለመናገር እንወዳለን ይሁን እንጂ በጣም የሚደንቀው የአሁንዋ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በእምነት መግለጫዋ ላይ ተጽፎላት ካለው የኢየሱስ አማላጅነት ይልቅ ሌሎች አማላጆች እንዳሉ ብትሰብክና ብትናገር ይቀላታል ነገር ግን ሌሎች አማላጆች ኖረውና የሚያስታርቁን ቢሆኑ ኖሮ የኢየሱስን ብቸኛ አስታራቂነትና የአብ ሊቀካህናትነትን መጽሐፍቅዱስም ሃይማኖተ አበውም ሆነ የራሷ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የእምነት መግለጫ በግልጽ ጽፎ አያስቀምጥልንም ነበር ስለዚህ ይህ ተጽፎ ያገኘነውና የሰፈረልን በመጀመርያ ለእኛው ለራሳችን ኢየሱስ አንተ ከአብ ጋር ያስታረቅከኝ አማላጄ ነህ ብለን እንድናምነው አምነንም ደግሞ ሌሎች እንዲያምኑ የምናስተምረው ነው እንጂ እንዲሁ ሰፍሮና ተጽፎ የተገኘ እኛም የእምነት መግለጫ እያልን እንዲያው በደመ ነፍስ የምናነበው የምናነበንበውና የምንደግመው ብቻ አይደለም ስለዚህ ኢየሱስ ዛሬም የአብ ሊቀ ካህናት ነው ያማልደናል ያስታርቀናል ወደሚለው የማመንና የማስተማር አገልግሎት እንምጣ መቼም ስለሰው ልጆች ደሙን አፍስሶ ከአብ ጋር ያስታረቀው የማስታረቅንም አገልግሎት በሰማይ ሳይቀር የሚያካሂደው ኢየሱስ እያለ ሌሎች ፍጡራንና መላዕክትንም ጭምር ያስታርቁናል ማለት ፍጹም ጭፍንነትና አላዋቂነትም መሆኑን ሌላው ቢቀር በቀላሉ ከኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ ማግኘት እንችላለን ይህንን እውነት አሻፈረኝ ማለቱ ደግሞ አውቆ የተኛን ሰው ቢቀሰቅሱት አይነቃም ዓይነት ነውና በጊዜው በእርሱ ቅስቀሳ እየተጣደፉና እየተላጉ ወደዚህ እውነት መድረስ ስለማይቀር ለእርሱ አሳልፈን እንሰጣለን ነገር ግን አሁንም በጽኑ ይህን ለምታነቡ ሁሉ ከመጽሐፍቅዱሳችን ሳይቀር የምንነግራችሁ የሰዎችና የመላዕክትን አማላጅነት ሳይሆን የኢየሱስን ብቸኛ አማላጅነት እና አስታራቂነት ነው በዕብራውያን 2 ፥ 17 እና 18 ላይ በግዕዙ ቃል እንዲህ ይላል ወእንበይነ ዝንቱ ርቱዕ ይትመሰሎሙ ለአኀዊሁ በኲሉ ከመ ይኩኖሙ መሐሬ ወሊቀ ካህናት ምእመነ ዘመንገለ እግዚአብሔር ከመ ይሥረይ ኃጢአተ ሕዝብ እስመ በዘአመከርዎ ወአሕመምዎ ክህለ ረድኤቶሙ ለሕሙማን ትርጉም ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና ይለናል ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀካህናትና አስታራቂ ነው የምንልበት ትልቁ ምክንያት የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል የተገባው ስለሆነ ነው ታድያ አንባቢዎቼ ሆይ እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ ? የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት ከኢየሱስ ውጪ ሌላ ከወዴት ልናገኝ እንችላለን ? ምክንያቱም መጽሐፍቅዱሳችን ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና ይለናል ሮሜ 3 ፥ 11 _ 20 እንግዲህ ቃሉ እንዲህ እንደሚነግረን ሁሉ ከተሳሳተና በአንድነትም የማይጠቅም ከሆነ እንደገናም አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ከሆነ ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ አረ ለመሆኑ የትኛው ጀግና ነው ምንም ሳይነካካው ሊምረን ያለ የታመነ ሊቀካህን ? ከመላዕክት ወገን እንዳንል መላዕክት የሰውን ሥጋ አልለበሱም እንደገናም እነዚሁ መላዕክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ሲሉ እንኳ ፊታቸውንና እግሮቻቸውን በክንፎቻቸው ይሸፍኑ ነበር ኢሳይያስ 6 ፥ 1 _ 5 በአጠቃላይ እግዚአብሔርን አንድስ እንኳ ያየው የለም በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው ነው የሚለን ዮሐንስ ወንጌል 1 ፥ 18 ይህ የተረከው ልጁ ኢየሱስ ደግሞ በዕብራውያን 2 ፥ 14 _16 መሠረት እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም የተባለለት ጌታ ነው ለዚህ ነው ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና ሲል ይኸው የዕብራውያን ጸሐፊ የነገረን ስለዚህ ከኢየሱስ ውጪ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት ሌላ እግራችን እስኪነቃ ድረስ ብንፈልግ አናገኝም ልንፈልግም አንችልም ለእግዚአብሔር በሆነው የኃጢአትን ሥርየት ለመስጠት ብቸኛው አማላጅ ኢየሱስ ብቻ ነው ሊቀካህናትነቱም እንደ ብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት በሞት ያልተሻረ ስለሆነ ክህነቱ ዛሬም በሰማይ ቀጥሏል ዕብራውያን 7 ፥ 23 _ 25 ለዚህ ነው የዕብራውያን ጸሐፊ አሁንም እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ ያለን ዕብራውያን 4 ፥ 14 _ 16 ይህንን ትምህርት እንግዲህ ዛሬ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት አብራርቼ የጻፍኩት ስለሆነ ትምህርቱን እየፈለጋችሁ አንብቡት እስከዚያው ግን በሌላ ትምህርት እስከምንገናኝ ድረስ የጌታ ጸጋና ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን በማለት የምሰናበታችሁ
ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ
ተባረኩልኝ ለዘላለም
No comments:
Post a Comment