Friday 27 September 2019

ፍጥረት ሁሉ ማንን ለማመስገን ተፈጠረ ? በተአምረ ማርያም መጽሐፍ መሠረት እመቤታችንን ወይስ እ/ርን ( Part 1 ) ==== ፍጥረት ሁሉ ማንን ለማመስገን ተፈጠረ ? የተወደዳችሁ ወገኖች ሰላም ለእናንተ ይሁን ፍጥረት ሁሉ ማንን ለማመስገን ነው የተፈጠረው ? የተአምረ ማርያም የስድሳ አራቱ እትም የዘወትር መቅድም ቁጥር 7 ላይ ፍጥረት ሁሉ እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረ ይላልና ፣ የተፈጠርነው እመቤታችንን ለማመስገን ነው ? ወይንስ እግዚአብሔርን ለማመስገን ? መጽሐፍቅዱሳችን በኤፌሶን 1 ፥ 12 ላይ በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ እንደተፈጠርን ይናገራል እንጂ እመቤታችንን ለማመስገን እንደተፈጠርን አይነግረንም ስለዚህ የተፈጠርንበት ዓላማ ጌታን የማመስገን ዓላማ ስለሆነ ጌታንና ጌታን ብቻ እናመሰግናለን :: የአሮን እህት ነቢይቱ ማርያምም እየዘመረች እንደተናገረችው ለእግዚአብሔር ብቻ እንዘምራለን ኦሪት ዘጸአት 15 : 1 ፣ 20 እና 21:: ታድያ የተአምረ ማርያም መጽሐፍ ከዚህ የእግዚአብሔር ቃል እውነት ሊያወጣን ፍጥረት ሁሉ እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረ በማለት ሌሎች አዋልድና ድርሳናት የተባሉ የኦርቶዶክስ መጻሕፍትን አጋዥ በማድረግ የማርያምን ፈጣሪነት ሊያሳየን ብቻዋን ታላላቅ ብርሃናትን ለፈጠረች ለድንግል ማርያም ኑ እንስገድላት ለእርስዋም እንገዛ ሲል ጥሪ አቀረበልን ( ምንጭ የየካቲት ኪዳነ ምሕረት ዚቅ ገጽ 144 ) :: የማርያም ሲገርመን መርቆርዮስ የተባለ ለክርስቶስ ሰማዕት መሆኑ እንኳ በውል የማይታወቀውን ሰማዕት ነው ብላ አምናና ተቀብላ ፈጣሪ አድርጋም በማቅረብ ሰማይን በከዋክብት የሸፈንክ ምድርን በዕጽዋት ወይም በአበቦች ያስጌጥክ መርቆርዮስ ሆይ ለስምህ እገዛለሁ በኃይልህም አመሰግናለሁ ወደ አንተ የመጣውን የሥጋ ለባሽን ሁሉ ጸሎት ስማ ይቅርታህንም አታዘግይብን ብርሃንህንና እውነትህን ላክ እነርሱም ይምሩኝ ወደ ቅድስናህ ተራራ ወደ መቅደስህ ይውሰዱኝ የሚለውን ተረት ተረት እንድንቀበልና ፈጣሪንና ሥራውን ሁሉ ለመርቆሬዎስ ሰጥተንና መርቆሬዎስንም በፈጣሪ ቦታ ተክተን መርቆሬዎስን እንድናመሰግንና ወደ እርሱም እንድንጸልይ ነገሩን :: በመሆኑም ወገኖቼ ሆይ የተፈጠርንበት ዓላማ ማንን የሚያመሰግን ሊሆን ይገባዋል ? እኛስ ማንን ነው ማመን ያለብን ? አዋልድና ድርሳናት የተባሉ የኦርቶዶክስ የተረት መጻሕፍትን ወይስ መጽሐፍቅዱስን ? የተፈጠርነው ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ስለሆነ ማመስገን ያለብን እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና ያለውን እግዚአብሔርን ብቻ ነው ( ትንቢተ ኢሳይያስ 66 ፥ 1 - 3 ) :: ነገር ግን ፍጡርን በፈጣሪ ቦታ ተክቶና የፈጣሪንም ምስጋና ለፍጡር ሰጥቶ ፍጡርን ማመስገን እግዚአብሔርን አንተ የለህም አምላክም አይደለህም ማለትን የሚያመለክት በመሆኑ ጌታ እግዚአብሔር ይህን ከመሠለ ክህደት ይጠብቀን ነው የምለው :: ጌታ እግዚአብሔር አሁንም ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ አትስገድላቸው አታምልካቸውም እያለን ከዚህም ሌላ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው ክብሬን ለሌላ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም ሲልም እየተናገረን ( ዘጸአት 20 ፥ 1 - 6 ፤ ትንቢተ ኢሳይያስ 42 ፥ ) የእግዚአብሔርን አምላክነትና የአምላክነቱንም ሥራ ለፍጡር በመስጠት ወደ ፍጥሩ አምልኮ መመለስ ማለት ግን ለእኔ ትልቅ መታወር ነው እግዚአብሔርንም በእግዚአብሔርነቱ መጠን አለመረዳት ነው ( ሮሜ 1 : 20 - 25 ):: ለዚህም እግዚአብሔር ያስበን ከማለት በስተቀር ሌላ የምለው የለኝም :: ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንንም እግዚአብሔር በቃሉ ይፈውሳት እስራቶችዋንም ከላይዋ ላይ ይበጥስላት :: ለተጨማሪ መረጃ የተለቀቀውን ቪዲዮ ተከታተሉ ተባረኩ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment