Friday 17 February 2017

የግጥም መነባንብ 


የግጥሙ ርዕስ እስመ ተዐረዩ እስመ ተዐረዩ


Related image


ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም.............. እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና  ይለናል  ( ዘጸአት 20 3 _ 6  )






እስመ ተዐረዩ  እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ አሉ ግነዩ ግነዩ 

የተመረጡ ግን የተለዩ የሉም 

ኃጢአት ነግሦበታል ፍጥረታዊው ዓለም 

በጨለማው ገዢ ፍጥረት ተንከራቶ 

ከፍርድ በታች ሆኖ ምላሱ ተዘግቶ 

ሁሉ ኃጢአት ሠርቷል የእግዜር ክብርም ጎድሏል 

ኃያሉ አምላካችን በቃሉ ተናግሯል 

እስመ ተዐረዩ ከወዴት ይመጣል ?

በክብሮሙም ብንል ሐሰት ያስብለናል 

ስብሐተ ፈጣሪስ የሚገባው ማነው ?

ከአምላካችን በቀር ያለ የሚኖረው 

ፍጹም የለምና ለእርሱ የተሳነው 

መጽሐፉ ያላለውን ለምን እንላለን ?

ላንጨምር ላንቀንስ ቃሉ ወስኖብን 

ላልተገባ ነገር ተላልፎ ያሰጠናል 

ዕድል ፈንታችንም ከቅድስቷ ሀገር ከጽዮን ይጎላል 

ከመጽሐፉ ውጪ የከንቱ ነው ከንቱ 

ፍጹም አታንብቡ እንዳትሳሳቱ 

ያልተጻፈ ሲያነብ በለመደው ሰይጣን 

ሔዋን ተታለለች ሃሳቡን በማመን 

እውነት የሚመስል ውሸት ነገር አለው 

መጀመርያም ሰይጣን የሐሰት አባት ነው 



Image result for you shall not make for yourself a carved image


ወእምዝ ይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ ሑር እምድኅሬየ ሰይጣን ጽሑፍ ለእግዚአብሔር አምላክከ ትስግድ ወኪያሁ ባሕቲቶ ታምልክ 

ወንጌል ዘማቴዎስ ምዕራፍ ቊጥር  



ያን ጊዜ ኢየሱስ ሂድ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እር ሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው 


የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 4 10 







የተወደዳችሁ ወገኖች የፌስቡክ ጽሑፎቼንና የመነባንብ ግጥሞቼን እንዲሁም በቪዲዮ የሚለቀቁትን መልዕክቶችና ትምህርቶችን ሁሉ የምትከታተሉ ቅዱሳን የእግዚአብሔር ሕዝቦች በሙሉ የጌታ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ በዛሬው ዕለት እስመ ተአረዩ  እስመ ተዐረዩ ትርጉም  ተመርጠዋልና ፣  ተመርጠዋልና የሚለውን የግጥም መነባንብ ያቀረብኩት ለኦርቶዶክሳውያን አማኞች ትምህርት ለመስጠት ቢሆንም መልዕክቱ ግን ሁላችሁንም አንባቢዎች የሚመለከት ስለሆነ በማስተዋል እንድትከታተሉ በጌታ ፍቅር ሆኜ ለማሳሰብ እወዳለሁ 

ይሄ ግጥም የተዘጋጀው በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መስከረም 17 ዕለት በሚከበረው የመስቀልና የደመራ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከሚጸለየው የመስተብቊዕ ጸሎት በከፊል  ተወስዶ ነው  ይህ የመስተብቊዕ ጸሎት ይህንን በዓል ምክንያት በማድረግ ከፍ ባለ ድምጽና ዜማ የበዓሉ ተረኛ ቄስ ሆኖ በተሰየመው ገባሬ ሰናይ ቄስና ገባሬ ሰናይ ዲያቆን የሚዜም ቢሆንም ከዚህ በዓል ባሻገር በሌሎች ጊዜያቶችም ከበዓሉ ጋር የተገናኙ ማለትም መስቀል ተኮር በዓላት ሲኖሩም ይህ የመስተብቊዕ ጸሎት በጸሎትና በዜማም መልክ ሆኖ ይጸለያል ይዜማል ጸሎቱም መስተብቊዕ ዘመስቀል በመባል ይታወቃል መስተብቊዕ የግዕዝ ቃል ሲሆን መስተብቊዕ ማለት መማለድ መለመን ማለት ነው አስተበቁአ ማለደ ለመነ ከሚለው የግዕዝ ግሥ ወይንም አረባብ  የመጣ ነው ሃሳቡን ስጠቀልለው መስተብቊዕ ዘመስቀል ማለት የመስቀል የምልጃ ወይንም የልመና ጸሎት ማለት ነው ታዽያ በዚህ የመስቀል የልመና ጸሎት ውስጥ በእንተ ዝንቱ አዘዙ መምህራነ ቅዱስ ወንጌል አምሳለ ፈጣሪ ልዑል ንስግድ ለመስቀል ወለማርያም ድንግል የሚለው ቃል ተጽፎ እናገኝበታለን ወደ አማርኛው ስተረጉመው የልዑል ፈጣሪ ምሳሌ ለሆኑት ለማርያምና ለመስቀል እንስገድ የሚል ነው ለምን ስንል የቅዱስ ወንጌል መምህራን አዘውናልና ይለናል እንደገናም በመቀጠል የጸሎት መጽሐፉን እንደዚሁ ወረድ ብለን ስናነበው  እነዚሁ የቅዱስ ወንጌል መምህራን የተባሉት የልዑል  ፈጣሪ ምሳሌ ለሆኑት ለማርያምና ለመስቀል እንስገድ ሲሉ ያዘዙበትን ምክንያት ይናገራል ውድ ወገኖቼ ሆይ ታድያ እኔም በግጥሙ መነባንቤ ላይ ይህንን ምክንያት መነሻ በማድረግ ነው እስመ ተአረዩ  እስመ ተአረዩ ትርጉም  ተመርጠዋልና ተመርጠዋልና  የሚለውን የግጥሙ ዋነኛ አርዕስ አድርጌ  ሃሳቤን በግጥም መልክ ላቀርብላችሁ የወደድኩት  ታድያ እነዚሁ የቅዱስ ወንጌል መምህራን የልዑል የፈጣሪ ምሳሌ ለሆኑት ለማርያምና ለመስቀል እንስገድ ሲሉ ያዘዙበትን ምክንያት መጽሐፉ ሲዘረዝርልን እንዲህ አለ ለእሉ ክልዔቱ ( ፪ቱ ) ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም አሜን ይለናል ወደ አማርኛው ስተረጉመው ለሁለቱ ፍጡራን ማለትም ለማርያም እና ለመስቀል የፈጣሪ ምሥጋና ይገባቸዋል በክብራቸው ተመርጠዋልና ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ አሜን ይላል የጸሎት መጽሐፉ እንግዲህ እነዚህ የቅዱስ ወንጌል መምህራን የልዑል ፈጣሪ ምሳሌ ለሆኑት ለመስቀልና ለማርያም እንድንሰግድ ያዘዙት በክብራቸው ስለተመረጡ ነውና የፈጣሪ ምሥጋና ከዛሬ ጀምሮ እስከ ለዘላለሙ ይገባቸዋል ስለዚህ ስግደቱንም ሆነ ምሥጋናውን ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር በእኩልነት ስጡአቸው እንጂ እንዳታሳንሱአቸው እያሉን ነው በመሆኑም ታድያ የእነዚህ የቅዱስ ወንጌል መምህራን ትዕዛዝ ትክክለኛ ከወንጌል ቃልና ከቅዱስ መጽሐፍ የወጣ  ትዕዛዝ ነው ወይ ? እነዚህስ የቅዱስ ወንጌል መምህራን የተባሉት ትክክለኛ የወንጌል መምህራን ናቸው ? ወይስ የሌላ ? ስንል መልሱን መጽሐፍቅዱሳችን በተገቢው መንገድ ግልጽ አድርጎ ይመልስልናል  ለምን ስንል እምነት ከመስማት  መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ከእግዚአብሔር ቃል የወጣ እምነት ለእኛ በፍጹም  የለንምና ነው ሮሜ 10 17 እንመልከት በዚህ የጸሎት መጽሐፍ ውስጥ እነዚህ የቅዱስ ወንጌል መምህራን በተናገሩት መሠረት ማርያምና መስቀል የልዑል ፈጣሪ ምሳሌ ናቸውና ስግደትም ሆነ የፈጣሪ ምሥጋና  ይገባቸዋል የሚል በመጽሐፍቅዱሳችን ውስጥ የተጻፈ አንድም ቦታ የለም ፈጣሪ አምላካችንንም የሚመስለው በምድርም ሆነ በሰማይ ምንም ዓይነት ፍጥረት የለም እንደገናም ፍጥረት ፍጥረት ነው ፈጣሪ ደግሞ ፈጣሪ ነውና በምንም መልኩ አመሳስለን ምስጋናም ሆነ ስግደት የምናቀርብለት ፍጥረት በምድርም ሆነ ከምድር በታች እንዲሁም በሰማይ ባሉ ፍጥረታት መካከል የለም ጌታም በትንቢተ ኢሳይያስ 46 : 5 ላይ በማን ትመስሉኛላችሁከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁእንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ?ብሎናል መቼም አንዳንዴ አይታወቅምና ድንገት አንዱ ሾጥ  ያረገው   ሾልኮና ሞቅም ብሎት ይህንን የፈጣሪ ምሥጋና እና ስግደት እኔም ያስፈልገኛልና  ልቀበል  ብሎ ቢነሳ ክብሩን ለሌላ ምሥጋናውንም ለተቀረጹ ምስሎች መስጠት የማይፈልግ ጌታ ወዲያው በቅጽበት ያዋርደዋል እርምጃንም ይወስድበታል እንጂ ፍጹም አይተወውም ይህንንም  እኔ እግዚአብሔር ነኝ  ስሜ ይህ ነው ክብሬን ለሌላ ምሥጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም ሲል በቃሉ ተናግሯል ትንቢተ ኢሳይያስ 42  8 ደግሞም በክብሩ የሚመጣበትን አይወድምና ይህ አይሆንልኝም ብሏል 1ኛ ሳሙኤል 2 ፥ 30  እንደገናም በዘጸአት 20  3 _ 6 ላይ ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና  ይለናል በዘዳግም  4  15 _ 24  ላይ እግዚአብሔር በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ መልክ ከቶ አላያችሁምና እጅግ ተጠንቀቁ እንዳትረክሱ፥ የተቀረጸውን ምስል የማናቸውንም ነገር ምሳሌ፥ በወንድ ወይም በሴት መልክ የተሠራውን……… አለን በዮሐንስ ወንጌል  4  22 _ 24 ላይ ደግሞ እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል ይለናል ከእነዚህ እና ከመሣሠሉት ቃሎች የተነሳ ታድያ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለምና  ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ ስለተባልን ከእርሱ በቀር ሌሎች አማልክት የሉንም አይሆኑልንምም  የተቀረጸውንም ምሳሌ ለእኛ አናደርግም  አንሰግድም  አናመልክምም ደግሞም መልክ አላያችሁምና ተጠንቀቁ ተብለናልና ስለዚህ ይህንን አምላካችንን የምናመልከው መልክ አይተን  ቅርጽና ምስል አበጅተን  ሥዕሎችንም ስለን  በቤታችንም አምጥተን በመስገድና በማምለክ አይደለም እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ የምናመልከው በእውነትና በመንፈስ ነው ስለዚህ ወገኖቼ እነዚህ የቅዱስ ወንጌል መምህራን ናቸው የተባሉት ታድያ ከየት አምጥተው ነው ለሁለቱ ፍጡራን ለማርያምና ለመስቀል የፈጣሪ ምሥጋና ይገባቸዋልና እንስገድላቸው በክብራቸው ተመርጠዋልና ሲሉ ያዘዙን ? በቅዱስ ወንጌሉ ላይ ስናይ ለእነዚህ ፍጡራን የፈጣሪ ምስጋና ስጡ ስገዱ የሚል ቃል አላነበብንም አማልክት አይኑርህ  አትስገድላቸው  አታምልካቸውም የተቀረጸ ምስል ለአንተ አታድርግ  አታምልክ  መልክ አላየህም ፣ ምስልን ለአንተ አታድርግ  እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ በእውነትና በመንፈስ አምልክ ነው የሚለን ቃሉ ስለዚህ ችግሩ ያለው በመጽሐፍቅዱሳችን ቃል መሠረት  የቅዱስ ወንጌል መምህራን  የተባሉት ጋር ነው በመሆኑም እነዚህ የቅዱስ ወንጌል መምህራን የተባሉት ትክክለኛ ያልሆኑና ያልተጻፈ የሚያነቡ ስለሆኑ እንደ ወንጌሉ ቃል እንደ መጽሐፍቅዱሱም እውነት የተሳሳቱ እና አሳሳች መምህራን ናቸው  እንጂ የቅዱስ ወንጌል መምህራን አይደሉም ስለዚህ እኛም  ትዕዛዛቸውን አንቀበልም ሌሎችም እንዳይቀበሉ በእንዲህ መልኩ እንናገራለን ፣ እናስተምራለን  እናስጠነቅቃለን ሐዋርያው ጳውሎስም ለዚህ ነው በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን እላለሁ  ያለን  ገላትያ 1  6 _ 9  ወገኖቼ ሆይ ልዩ ወንጌል በገላትያ ክርስቲያኖች ዘመን ብቻ ሳይሆን ዛሬም የቅዱስ ወንጌል መምህራን አዘዙን በተባለው መንገድ የሚታመንና የሚደረግ  ሁሉ  አሁንም ልዩ ወንጌል ነውና እኛም  እንደ ጳውሎስ እንዲህ ያለውን አስተምህሮ እንዲሁ የተረገመ ይሁን እንላለን የተጠራንበትም ሆነ የዳንበት ወንጌል የክርስቶስ የጸጋው ወንጌል በመሆኑ ፊታችንን የምናዞርበት የተለየ ወንጌል የለንም  እንደገናም  መዳን በሌላ በማንም ስለሌለ የምንድነው በኢየሱስ ብቻ ነው ስግደት አምልኮም የሚቀርበው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ ከእግዚአብሔር ውጪ ለሌላ አንሰግድም ሌላም አናመልክም የሐዋርያት ሥራ 4  12  ፊልጵስዩስ 2  9 _ 11  1 የጴጥሮስ መልእክት 4 : 11  የማቴዎስ ወንጌል 4  10 እና 11 ወደ ግጥሜና የመነባንቤ ሃሳብ ስመልሳችሁ ደግሞ የግጥሜ  ጥቂቱ ሃሳብ የግዕዝ ቃላቶች የተቀላቀሉበት በመሆኑ እንደሚከተለው ልተረጉመው እወዳለሁ እስመ ተዐረዩ እስመ ተዐረዩ  በክብሮሙ አሉ ግነዩ ግነዩ ያልኩት ግነዩ ማለት አመስግኑ ማለት ሲሆን ገነየ አመሰገነ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ በመሆኑ እስመ ተዐረዩ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ አሉ ግነዩ ግነዩ ማለት እነዚህ የፈጣሪ ምሥጋና ይገባቸዋልና እንስገድላቸው የተባሉት ማርያምና መስቀል የወንጌል መምህራኑ እንዳዘዙትም ሆነ ደራሲው እንዳለው      " ተመርጠዋልና  ተመርጠዋልና  በክብራቸው ! አመስግኑ አመስግኑ አሉ "የሚለውን ሃሳብ ስለሚይዝልኝ ነው ይህንን ለግጥሜ እንደ ዋና አርዕስት አድርጌ  የግጥሜ ወይም የመነባንቤ የመጀመርያና የመነሻ ሃሳብ እንዲሆን የወሰድኩት ቢሆንም መጽሐፍቅዱሳችን ግን አሁንም    ሁሉ ኃጢአትን ከመስራቱ የተነሳ የእግዚአብሔር ክብር የጎደለው ነውና በክብሩ የተመረጠም ሆነ አልፎ ሄዶ የፈጣሪ ምሥጋናን የተቀበለ  የፈጣሪም ምሥጋና ሊሰጠው ሊሰገድለት የተገባ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ የለምና  በማለት የመስተብቊዕ ዘመስቀልን ሃሳብ በእንዲህ መልኩ አፍርሶታልና የመጽሐፍቅዱሱ ሃሳብ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ የእግዚአብሔር ቃል ያለንን ብቻ ሰምተንና ይዘን እርሱን እግዚአብሔርን እንከተል ለማለት ይህቺ መልዕክት በግጥም መልክና የታሪኩን ይዘትም ጠብቆ በሚያብራራ መጽሐፍቅዱሳዊ የቃል ገለጻ ተዘጋጅታ ወደ እናንተ ደርሳለች   አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው አሜን 


Image result for turning to a different Gospel




«Do not turn to a different gospel» 



«ወደ ልዩ ወንጌል አትመለሱ»



Image result for turning to a different Gospel


Image result for turning to a different Gospel












ወይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ 


የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ 


ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry 


ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ 



















No comments:

Post a Comment