Friday 6 January 2017

ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና ሉቃስ ወንጌል 2 ፥ 11እስመ ናሁ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኅን ዘውእቱ ክርስቶስ እግዚእ ቡሩክ በሀገረ ዳዊት ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና ሉቃስ ወንጌል 2 ፥ 11 የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች አረጋውያን አባቶች ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሕዝበ እግዚአብሔር ምዕመናን በቅድሚያ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ ከዚህ በመቀጠል በ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry በኩል የተዘጋጀ የልደት መልዕክት ስላለ እርሱን እንደሚከተለው አቀርብላችኋለሁ እና ተከታተሉ መልዕክቱም በቪድዮ ጭምር የተዘጋጀ ስለሆነ ተባረኩበት እግዚአብሔርንም በቃሉ አክብሩት በዳዊት ከተማ የተወለደልን መድኃኒት ክርስቶስ ጌታ የሆነ ነው የተወለደው ለእኛ ስለሆነ ተወልዶላችኋል ተባልን ወይቤሎ መልአክ ኢትፍርሁ እስመ ናሁ እዜንወክሙ ዐቢየ ዜና ፍሥሐ ዘይከውን ለክሙ ወለኲሉ ዓለም እስመ ናሁ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኅን ዘውእቱ ክርስቶስ እግዚእ ቡሩክ በሀገረ ዳዊት ወደ አማርኛው ስተረጉመው መልአኩም እንዲህ አላቸው እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና ይለናል የሉቃስ ወንጌል 2 ፥ 10 እና 11 በመሆኑም ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች መባሉ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ስለተወለደ ነው መድኃኒትነቱ ለሕዝቡ ሁሉ ነውና ስለዚህ ይሄ መድኃኒት ለእኔ አያስፈልገኝም የሚል ከሰው ወገን ማንም የለም ሊኖርም አይችልም ለምን ስንል ሁሉ ኃጢአትን ሠርቷል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል የሚል የእግዚአብሔር ቃል ተጽፎልናልና እንደገናም የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው በመሆኑም ኃጢአት ሰዎችን ሁሉ ከክብር ያጎደለ ብቻ ሳይሆን ክፍያ ወይም ደሞዝም ጭምር ሆኖ ሰዎችን የገደለ ነው ሮሜ 3 ፥ 23 ፤ ሮሜ 6 ፥ 23 ይሁን እንጂ ኢየሱስ የኃጢአትና የሞት መድኃኒት ሆኖ ተወለደ ለዚህም ነው ወትወልድ ወልደ ወትሰምዮ ስሞ ኢየሱስሃ እስመ ውእቱ ያድህኖሙ ለሕዝቡ እምኃጢአቶሙ ያለው ወደ አማርኛው ስተረጉመው ልጅም ትወልዳለች እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ በማለት የሚናገር ነው የማቴዎስ ወንጌል 1 ፥ 21 የሞት መድኃኒት ስለመሆኑ ደግሞ ወይቤላ እግዚእ ኢየሱስ አነ ውእቱ ትንሣኤ ወሕይወት ዘየአምን ብየ እመኒ ሞተ የሐዩ ወኩሉ ዘሕያው ወየአምን ብየ ኢይመውት ለዓለም ተአምኒኑ ዘንተ በማለት ተናግሮአል አሁንም ይህንን ወደ አማርኛው ስተረጉመው ኢየሱስም ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል ሕያው የሆነ የሚያምንብኝ ሁሉ ለዘላለም አይሞትም ይህን ታምኛለሽን አላት እያለ ይነግረናል የዮሐንስ ወንጌል 11 ፥ 25 _ 27 ይህ ጌታችን መድኃኒት ሆኖ የተወለደልን ጌታ በመሆኑ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች ነው ስለዚህም ሐዋርያው ጳውሎስ ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው በማለት ከኃጢአተኞችም ዋናው እርሱ መሆኑን ከነገረን በኋላ ባለማወቅ ስላደረግሁ በዚሁ ጌታ ምሕረትን አገኘሁ አለን 1ኛ ጢሞቴዎስ 1 ፥ 12 _ 17 ውድ ወገኖቼ ሆይ ይህ የተወለደልን ጌታ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን መድኃኒት ስለሆነ በዚሁ ጌታ ምሕረትን ያገኘው ጳውሎስ ብቻ ሳይሆን ቃሉ እንደሚነግረን የሰው ዘር በሙሉ ማለት ሁላችንም ልንቀበለው የተገባ መሆኑን በግልጽ ያሳውቀናል ኢየሱስ የመጣውም ጻድቃንን ሊጠራ ሳይሆን ኃጢአተኛችን ሊያድን ነው ስለዚህ በስሙ ንስሐና የኃጢአት ሥርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል እስከ አሁኑ እስከዚች ሰዓት ድረስም እየተሰበከ ይገኛል አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይድረሰው ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment