Tuesday 1 March 2016

ትምህርት አራት ፦ የትምህርቱ ርዕስ ፦ የተስፋን ቃል ስለ መቀበልና ስለ መጠበቅ ( ዕብራውያን 10 ፥ 23 ፤ ሮ...የትምህርቱ ዋና ዋና ሃሳቦች የትምህርቱ ርዕስ ፦ የተስፋን ቃል ስለ መቀበልና ስለ መጠበቅ ( ዕብራውያን 10 ፥ 23 ፤ ሮሜ 4 ፥ 18 ) 1ኛ ) እግዚአብሔር በመጀመርያ ለሰው ልጆች የሰጠው ተስፋን ነው በቲቶ መጽሐፍ ምዕራፍ 1 ፥ ቊጥር 1 እና 2 ላይ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእግዚአብሔር ለተመረጡት እምነት እንዲሆንላቸው በዘላለምም ሕይወት ተስፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ፤ ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ ሰጠ፥ ይለናል ቲቶ 1 ፥ 1 እና 2 ስለዚህ የተስፋን ቃል የምንቀበለው በቃሉ ተስፋን ከሰጠን ከማይዋሸው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው ለምን ስንል ፦  ሀ ) የተስፋን ቃል የሰጠ የታመነ ነውና ዕብራውያን 10 ፥ 23  ለ ) የተስፋን ቃል መቀበል እንደሚያስፈልገንና ጥቅምም እንዳለው የዕብራውያን ጸሐፊ ነገረን ጥቅሙም በዚሁ የተስፋ ቃል የዘላለምን ርስት ማግኘት ነው ለዚህ ደግሞ ኢየሱስ የሐዲስ ኪዳን መካከለኛ ሆነ ዕብራውያን 9 ፥ 15  ሐ ) እግዚአብሔር ተስፋን የሰጠ በመሆኑ የተስፋን ቃል በመቀበል ዙርያ አብርሃም ያደረገው ፦ ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ ይለናል ሮሜ 4 ፥ 18 ፤ ዘፍጥረት 15 ፥ 5  መ ) ይህንኑ የተስፋን ቃል በመቀበል ጉዳይ አሁንም አብርሃም የተስፋን ቃል የተቀበለ የመጀመርያው የወንጌል ተሰባኪ አማኝ በመሆኑ ስለዚህ ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤ እርሱም፦ ለብዙ አሕዛብ አባት አደረግሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ለሙታን ሕይወት በሚሰጥ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ በሚጠራ ባመነበት በአምላክ ፊት የሁላችን አባት ነው ተባለ ሮሜ 4 ፥ 17 ፤ ገላትያ 3 ፥ 8 እና 9 ፤ ዘፍጥረት 17 ፥ 5 ፤ ዮሐንስ ወንጌል 5 ፥ 21 2ኛ ) የዕብራውያን ጸሐፊ እንደተናገረው የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ ይለናልና ዕብራውያን 10 ፥ 23 ታድያ የተስፋችንን ምስክርነት ፣ የተሰጠንንም የተስፋ ቃል የምንጠብቀው እንዴት ነው ? ስንል አሁንም የእግዚአብሔር ቃል የሚሰጠን መልስ አለ  ሀ ) በ2ኛ ቆሮንቶስ 1 ፥ 20 ላይ እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና፥ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ስለ ክብሩ በእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ ደግሞ ነው ይለናል በመሆኑም በእርሱ የተሰጡ ተስፋዎች አዎን የሚሆኑት በእርሱ ነውና እኛም በእርሱ አማካኝነት ለእግዚአብሔር ክብር አሜን የምንለው በእርሱ ምክንያት ነው  ለ ) አብርሃም ለብዙ አሕዛብ አባት አደረግሁህ ተብሎ በተጻፈው ቃል መሠረት አሁንም አብርሃም አባት የሆነው አሜን ብሎ የተስፋውን ቃል ተቀብሎ ባመነበት አምላክ ምክንያት ነው ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ ይለናል ሮሜ 4 ፥ 18 ፤ ዘፍጥረት 15 ፥ 5  ሐ ) ይሁን እንጂ አብርሃም ተስፋን ይዞ አምኖ ያልቀረ ነበረ የመቶ ዓመት ሰው ሆኖ ሳለ የራሱም ሰውነት ሆነ የሣራ ማኅፀን ምውት እንደነበረ እያወቀ በእምነቱ አልደከመም ይለናል ታድያ አብርሃም የራሱም ሰውነት ሆነ የሣራ ማኅፀን ምውት እንደነበረ ያወቀ ቢሆንም በእምነቱ ያለመድከሙ ጉዳይ ገሃዳዊውን እውነትና ነባራዊውን የራሱን ሰውነት እንደገናም የሣራን ምውት ማኅፀን ሁኔታ ከመካድ አንጻር አልነበረም ሮሜ 4 ፥ 19  መ ) ስለ አብርሃም የሮሜ መጽሐፍ በእርግጠኝነት በእምነቱ አልደከመም ያለን ቢሆንም በመጀመርያው የማመን ዘመኑ የተስፋው ቃል በጊዜው ወደ እርሱ በመጣ ሰዓት ግን በሕይወቱ ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ እንደነበር የዘፍጥረት መጽሐፍ በቅድምና ይነግረናል ሚስቱ ሣራም እንደዚሁ በመጣላት የእግዚአብሔር መልዕክት ትልቅ የሆነ የእምነት ቀውስ ውስጥ ገብታ እንደነበር የክፍሉ ሃሳብ ያስተምራል ዘፍጥረት 17 ፥ 17 ፤ ዘፍጥረት 18 ፥ 11 - 15  ሠ ) ነገር ግን አብርሃም ብቻ ሳይሆን ሣራ ራሷ ደግሞ ከዚያ ትልቅ ከሆነ የእምነት ቀውስና ከፍተኛ ከሆነ ጥርጣሬ ውስጥ ወጥታ ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፥ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች ዕብራውያን 11 ፥ 11 እና 12  ረ ) በዚህ ጉዳይ አሁንም አብርሃም በእምነቱ ያልደከመ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብር የሰጠ ፣ የእግዚአብሔርንም ተስፋ ቃል ያልተጠራጠረ ነበር ሮሜ 4 ፥ 20 ፤ የማቴዎስ ወንጌል 9 ፥ 1 _ 8  ሰ ) እንደገናም ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፥ በእምነት በረታ እንጂ በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም በመሆኑም ከዚህ ሃሳብ በመነሳት ይኸው አብርሃም እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም በሙሉ ልብ እርግጠኛ ነበር የሚለውን እውነት ያስጨብጠናል ሮሜ 4 ፥ 21 ፤ ዘፍጥረት 18 ፥ 14 ፤ የማቴዎስ ወንጌል 19 ፥ 26 የተወደዳችሁ ቅዱሳን የትምህርቱ ሃሳብ በአጭሩ እንግዲህ ይህንን ይመስላል ከዚህም ባሻገር በቪዲዮ የተለቀቁ ተከታታይ ሃሳቦች ስላሉ እነዚህን የተለቀቁትን ትምህርቶች እየገባችሁ በመስማት ለሌሎችም ሼር እንድታደርጉአቸው በአክብሮትና በትሕትና እጠይቃለሁ ጌታ በነገር ሁሉ ይባርካችሁ አሜን የJoshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለ ራዕይ ቀሲስ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment