Saturday, 16 June 2018
ለተሐድሶ የተሰጠ መልስ ክፍል 1 በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፤ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፤መጋቢ ሐዲስ እሸቱ እና ዲያቆን ያረ...ያበሳጨን ፣ ጠበኛም ያደረገን ፣ አልፎም በሕይወታችን ያታገለንና ያስለቀሰን ወንጌል ፣ ሌባ ሆኖ የሚሰርቀን ሳይሆን ሕይወት ሆኖ ሊያድነን የመጣ ነው ሥርዓትህን እማር ዘንድ ያስጨነቅኸኝ መልካም ሆነልኝ። መዝሙረ ዳዊት 119 : 71 ከመልአኩም ጋር ታግሎ አሸነፈ፤ አልቅሶም ለመነው። በቤቴልም አገኘው፥ በዚያም ከእኛ ጋር ተነጋገረ። ትንቢተ ሆሴዕ 12 : 5 የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ኦርቶዶክሳውያን እናቶችና አባቶች እንዲሁም ይህን ትምህርት የተከታተላችሁ ወገኖች በሙሉ እንደምን ሰንብታችኋል ከተወደደው የእግዚአብሔር አገልጋይ ቢንያም ወርቅነህ ጋር የለቀቅነው የዛሬው መልዕክት በጣም ወሳኝና አስፈላጊ የሆነ የጊዘው መልዕክት ነውና ደግማችሁ በማዳመጥ እንድትጠቀሙ እንድትባረኩበትም ለማስተላለፍ እወዳለሁ:: በነገው ዕለት ቅዳሜም የምንነጋገርበት ትምህርት በተለመደው ሰዓት ይቀጥላል ::ስለዚህ ለማናችሁም መቅረት አይፈቀድም :: የዛሬው መልዕክት ግን በመረጥኩት የትምህርት አርዕስትና አስረጂ ጥቅሶች መሠረት የቀጠለ ነው :: ይሁን እንጂ ታድያ ይህንንም እንድል የሆንኩበት ዋነኛ ጉዳይ ከብዙዎቻችን ሕይወት ውስጥ ከሚወጣው ብስጩነት ፣ ንዴት ፣ ቁጣ ፣ መሳደብ አልፎም ሄዶ ከውስጣችን ፈንቅሎ ከወጣው ልቅሶና ምሬት የተነሳ እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ስለገባን ውጤቱ ከእግዚአብሔር ቃል አኳያ ምን ሊሆን እንደሚችል ከመረዳትና ከመገንዘብ አንጻር ነው :: ለዚህም ሁኔታ አንድ ስማቸውን መጥቀስ የማያስፈልገኝ አባት ማለትም ጳጳስ ናቸው በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ መሠረት ተቆርቁረው ሲያለቅሱ ሰማናቸው :: እኔም የማከብራቸውና የምወዳቸው ቀደምት አባታችን እንደመሆናቸው መጠን ፣ ልቅሶአቸው ከንክኖኝ ብፁዕ አባታችንን ምን ሆድ የሚያስብስ ነገር ቢገጥማቸው ነው እንዲህ ተንሰቅስቀው ማልቀሳቸው ? ብዬ በጉዳዩ በማዘን የተለቀቀውን የቪዲዮ መልዕክት ፍጻሜ ለማየት ስሞክር ለካስ የብጹዕ አባታችን ትልቁ ስጋታቸውና ልቅሶአቸው እንደገናም ፣ በልቅሶአቸውም ለሕዝባቸው ሊነግሩትና ሊያስተላልፉት የፈለጉት መልዕክት ፣ እንዳትሠረቁ ፣ ራሳችሁንም እንዳታሰርቁ ተጠንቀቁ የሚል ነው :: እንደ ብፁዕ አባታችን አመለካከት ይሰርቀናል ሲሉ የሰጉበትና ያለቀሱበት ትልቁ ወሬ ፣ በኢየሱስ ምክንያት የመጣ የኢየሱስ ወሬ ነው :: ታድያ ይሄ ትልቁ በኢየሱስ የተገኘ የኢየሱስ ወሬ የብዙዎችን ሕይወት የሠረቀ ነው ብለን ባናስብም ኢየሱስ ሕይወት ሊሆነን ሊበዛልንም የመጣ ጌታ በመሆኑ የብዙ ሰዎችን ሕይወት የለወጠ ነው :: በመሆኑም ታድያ ብዙዎቹ ብፁዕ አባታችን እንዳሉት ፣ በኢየሱስ ተሠርቀው ሳይሆን ተለውጠው ወደ ኢየሱስ የመጡ ናቸው :: ኢየሱስ እንደዚያ እንደ ክፉው ሰይጣን ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ የመጣ ጌታ ሳይሆን ሕይወት ሊሆንልንና ሊበዛልን የመጣ ጌታ ነው የዮሐንስ ወንጌል 10 ፥ 10 :: ኢየሱስ እውነተኛ የበጎች በር ፣ በበሩም የሚገባ ጌታና መልካምም እረኛ ስለሆነ መስረቅ ወይንም ስርቆት የሚባል ነገር በእርሱ ዘንድ አይታሰብም :: ለዚህ ጌታ አንድ እውነት እንደ ቃሉ የምንናገርለት ነገር ቢኖር ፣ ከዚህ በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምጼንም ይሰማሉ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ በማለቱ ፣ ከዚህ ወርቃማ እና አምላካዊ ቃል የተነሳ ስርቆት ብለን ብናስብ ኃጢአት ይሆንብናል :: ነገር ግን አንድና አንድ እውነት ከዚህ በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ያለው ኢየሱስ ነውና እርሱ ሁሉን የሚችል ጌታ በመሆኑ ማምጣቱ አይቀርም የዮሐንስ ወንጌል 10 ፥ 16 :: ስለዚህ ከዚህ መጽሐፍቅዱሳዊ እውነት አንጻር ብጹዕ አባታችን በመሪር እንባቸው ፣ ኢየሱስን ይሰርቀናል ሲሉ ሳይሆን ይለውጠናል ሲሉ የሰጉ አስመስሏቸዋል :: ይህ ብቻ አይደለም ይሄ ጀግና ኢየሱስ መለወጥ ከጀመረ ማንንም የማይምር በመሆኑ ፣ በኢየሱስ ምክንያት እንደ ሰደድ እሳት የተቀጣጠለው የወንጌሉ እውነት በመለወጥ ጉዳይ ከያዘ በቀላሉ የማይለቅ በመሆኑ ፣ ጳጳሱ ብፁዕ አባታችን ጨንቋቸው እንዳትሠረቁ ራሳችሁንም እንዳታሰርቁ ሲሉ ሕዝቡን በእንባ ተማጸኑ :: ታድያ ይህንን የብፁዕነታቸውን ጽኑ ልቅሶ አይቼ ወዲያው እኔም ለእኚህ አባት ካዘንኩበት ሰመመኔ ፈጥኜ ነቃሁና አንድ ነገር አሰብኩ :: ያዘንኩላቸው ስለማውቃቸው ፣ አረጋዊ አባትና ብፁዕ አባታችንም ስለሆኑ በመንፈሴ ሳይሆን በሥጋዬ ነው ብዬ አስተዋልኩ :: አስከትዬም የለውጥ ያለህና በአባቶቻችን አፈርን ሲሉ በመጽሐፎቻቸው ወደ አባታቸው ወደ እግዚአብሔር ፣ እንዲሁም ወደ ሕዝባቸውም ጭምር የጮሁትን ጠንካራ የመጽሐፉ አዘጋጆችና የለውጥ አራማጆች የሆኑ የተሃድሶ አገልጋዮችን ጽሑፍ ሳስታውስ ፣ የብጹዕ አባታችን ልቅሶ ፣ ሹሉዳው እንደተነካ እንደ ያዕቆብ ለመለወጥ የሆነ ልቅሶ እንደ ሆነ ገባኝ እና እግዚአብሔርን ማመስገን ጀመርኩኝ :: ታድያ ይህ ልቅሶ ያዕቆብ ጋ የቀረ ብቻ ሳይሆን ፣ ተንከባሎ መጥቶ ብፁዕነታቸው ጋር የደረሰ ፣ በዚህም ሳያቆም ብዙዎች ቤት ውስጥ ሳይቀር ሳይታሰብ በድንገት የገባ መሆኑን ሳስብ ደግሞ ጌታን ለማመስገን ነፍስም አልቀረልኝ :: ለምን ብትሉ በአባቶቻችን አፈርን ፣ የለውጥ ያለህንና ሌላም ሌላም ሲሉ የጻፉ ሰዎች በመጽሐፎቻቸው የጮሁትን ጩኸት እግዚአብሔር ስለሰማ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን ለውጥን ፈልጋው ሳይሆን ሳትፈልገውም ቢሆን የግድ ጉያዋና መቅደስዋ ፣ ካቴድራሎችዋና መንበረ ጵጵስናዎችዋ ድረስ ሳይቀር እየገባ ፣ ከክብር ወደ ክብርም እየለወጣት ይገኛል :: ክብሩ ለእግዚአብሔር ይሁንለት :: ከዚህም ሌላ ይህንን ለውጥ እያደረገ ያለው እግዚአብሔር ስለሆነ ፣ ይህን እግዚአብሔርን ማንም አያቆመውም :: ይህ የለውጥ ውሽንፍር ደግሞ ወንጌላውያን አማኞች ቤተክርስቲያን ድረስ በመግባት ፣ በለውጥ ያልተቃኙ አማኞችንና አንዳንድ ሥጋውያን ፓስተሮችን ሳይቀር መለወጡ አይቀርም ብዬ አምናለሁ :: ለውጥ ደግሞ ለውጥ ነውና ፣ አንድ ጊዜ በምድሪቱ ላይ ይምጣ እንጂ ሰዎችን አይመርጥም ፣ በዚህ ጉዳይ ፣ እኔም በዘመኔ ለእግዚአብሔር እውነት ያልተገኙና በመንፈስቅዱስ ያልተሞሉ ፣ የመንፈስቅዱስም ተቃራኒዎች የሆኑ ትልልቅ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ፣ ጊዜያቸው መጥቶ መንፈስቅዱስ ሲያንደባልላቸው ፣ በመንፈስቅዱስም ሲሞሉ በዓይኔ በብረቱ አይቻለሁ :: ይህ ብቻ አይደለም ከዚሁ ከመንፈስቅዱስ ሙላት የተነሳም በብዙ አገልጋዮች ሕይወት ተለጥፎ ያለ አቡዋራና ጥቀርሻ እንዲሁም ያልተገራ ባሕርዮቻቸው ጭምር በዚሁ በመጣው በመንፈስቅዱስ ሙላት ከውስጣቸው ተራግፎላቸውና ተቀይረው ተመልክቻለሁ :: ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና ስለዚህ ይህ እውነት የገባን ክርስቲያኖች ሁሉ ለኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ፣ ክርስቶስ ለራሱ ሊያደርጋት ለሚፈልጋት ቤተክርስቲያን ሳይቀር በትጋት እንጸልይ በማለት መልዕክቴን በዚሁ እደመድማለሁ አባ ዮናስ ጌታነህ ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry የተሃድሶ አገልጋይ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment