Friday, 22 September 2017
ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ( ክፍል አስራ ስድስት ) ቊጥር ፫ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ( ክፍል አስራ ስድስት ) ቊጥር ፫ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሰላም ለእናንተ ይሁን በዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው በሚለው የክፍል አስራ ስድስትና የቊጥር ፫ ትምህርታችን ላይ ለኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት ብዙ አስረጂ የሆኑ ጥቅሶች ቀርበዋል እኔ ግን በዋናነት በዚህ ጽሑፌ ላይ ላሰፍረው የፈለኩት መናፍስት ሳይቀሩ ለእግዚአብሔር ልጅ እውቅና በመስጠት ኢየሱስ ሆይ የእግዚአብሔር ልጅ ካንተ ጋር ምን አለን ? ጊዜው ሳይደርስ ልታሰቃየን መጣህን ? እያሉ የጮሁበትን እውነት ነው ለማሳየት የፈለኩት የማቴዎስ ወንጌል 8 ፥ 29 እንመልከት ከዚሁ ጋር በተያያዥነት የሚቀርብ ሌላም የመጽሐፍቅዱስ እውነት አለ አጋንንትም ደግሞ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ እየጮሁም ከብዙዎች ይወጡ ነበር ገሰጻቸውም ክርስቶስም እንደሆነ አውቀውት ነበርና እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም ይለናል የሉቃስ ወንጌል 4 ፥ 41 በሌላም ክፍል ላይ በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኩስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለን ? ልታጠፋን መጣህን ? ማን እንደሆንህ አውቄያለሁ የእግዚአብሄር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ ይለናል ኢየሱስም ለዚሁ ክፉ መንፈስ አሁንም መልስ ሲሰጥ ዝም በል ከእርሱም ውጣ አለው ብሎ ነው የእግዚአብሔር ቃል የሚነግረን የማርቆስ ወንጌል 1 : 24 ን ይመልከቱ ታድያ የናዝሬቱ ኢየሱስ በተደጋጋሚ ትክክለኛ መሲህነቱን ፣ ክርስቶስነቱን ፣ የእግዚአብሔር ልጅነቱንና ቅዱስነቱን አንስተው ጊዜው ሳይደርስ ሳይቀር እንዳያጠፋቸው በብዙ ልመና የተማጸኑትን የእጋንንትን ምስክርነት ባለመቀበል ዝም ብለው ብቻ እንዲወጡ የተናገረበትን ሃሳብ ስንመለከት ምን እናስባለን ? ኢየሱስ ይህን እውነታዊነት ሲያይ ትክክል የሆነውን ምስክርነት ያልተቀበለበት ምክንያት ምንድርነው እንላለን ? መልሱ ለእኔ እንደሚገባኝና መጽሐፍቅዱሴም እንደሚያስተምረኝ ጌታችን ኢየሱስ ይህንን ምስክርነት መስማት የሚፈልገው ከአጋንንት ሳይሆን ከዳኑና ከዚሁ ከአጋንንት እስራት ከተፈቱ ከሰዎች ልጆች ነው ለዚህም ነው በብዙ ሰንሰለት ታስሮ በመቃብርና በተራራ ይጮህ የነበረውን ይህንን ሰው ከዚሁ ከሌጌዎን የአጋንንት እስራት ከፈታው በኋላ ወደ ቤትህ በቤተሰቦችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደማረህ አውራላቸው ያለው ይህም ሰው ሄዶ ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት በቤቱና በቤተሰቦቹ ዘንድ ብቻ ሳይሆን አሥር ከተማ በሚባል ሀገር ይሰብክ እንደነበርና ሁሉም ይደነቁ እንደነበር የክፍሉ ሃሳብ ያስተምረናል የማርቆስ ወንጌል 5 ፥ 1 _ 20 ከዚሁ ጋር በማርቆስ ወንጌል 16 ፥ 9 ላይ ከሳምንቱ በመጀመርያው ቀን ማልዶ በተነሳ ጊዜ አስቀድሞ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለመግደላዊት ማርያም ታየ ስለሚለን በሉቃስ ወንጌል 8 ፥ 2 ላይ ደግሞ አሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ ከክፉዎች መናፍስትና ከደዌም ተፈውሰው የነበሩ አንዳንድ ሴቶች እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም የሄሮድስ አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐናም ሶስናም ብዙዎች ሌሎችም ሆነው በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበር ስለሚለን በተያያዥነት ልንመለከተው እንችላለን ውድ ወገኖቼ ሆይ መጽሐፍ ሲናገር ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይስአር ግብሮ ለጋኔን ይለናል ወደ አማርኛው ስመልሰው ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ የሚለውን ትርጉም የሚሰጠን ነው 1ኛ ዮሐንስ መልዕክት 3 ፥ 8 ን ይመልከቱ የዲያብሎስ ሥራ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የፈረሰው በዚሁ በእግዚአብሔር ልጅ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው ታድያ ጌታችን ኢየሱስ ሥራውን ያፈረሰበት ብቻ ሳይሆን አለቅነቱን የሻረበት ሥልጣኑንም ገፎ ድል በመንሳት ጭምር በግልጥነት እያሳየ ያዞረው ነው እነዚህ ጥቅሶች የተናገርኩትን ሃሳብ በግልጥ የሚያብራሩ ስለሆኑ አስተውለው ይመልከቷቸው ኤፌሶን 2 ፥ 1 እና 2 ፤ ቆላስያስ 2 ፥ 14 እና 15 ፤ ዕብራውያን 2 ፥ 14 እና 15 ከዚህ የተነሳ አሁን የአምላካችን ማዳንና የክርስቶስም ሥልጣን ሆኖአል በቀንና በሌሊት የሚከሰንም የወንድሞች ከሳሽ ተጥሏል እኛም ከበጉ ደምና ከምሥክራችን ቃል የተነሳ ድል ነስተነዋል ራዕይ 12 ፥ 7 _ 12 እንመልከት በመሆኑም ታድያ መጽሐፍቅዱሳችን ይህንን እውነት በግልጥነት እያስቀመጠልን ሰዎች ግን ዛሬም በዘመናችን ከአጋንንት እስራት ለመፈታትና ከደዌያቸውም ለመፈወስ ሲሉ መቊጠርያና በትረ መስቀል ወደያዙ ባሕታውያንና አጥማቂ ነን ባይ ሰዎች እየሄዱ በበትረ መስቀሉ ግንባራቸው እስኪቆስል ድረስ ይጠፈጠፋሉ እንደገናም ይህ አልበቃ ብሎአቸው አጋንንቱ ከውስጣቸው እንዲወጣ ተብሎ ወፋፍርና ድቡልቡል በሆኑ የእንጨት መቁጠርያዎች ጀርባቸው እስኪመለጥ ድረስ ይደበደባሉ እንደገናም በማለዳ ከቧንቧ በተቀዳ የበርሜል ቀዝቃዛ ውሃ ይነከራሉ ነገር ግን ከስቃዩ ብዛት የተነሳ የድረሱልኝ ያክል ከሚጮህና ከሚሰቃይ ሰው በስተቀር በዚያ ፈውስም ሆነ ድህነት የለም አጋንንት የሚወጣውም ሆነ ደዌ የሚፈወሰው ከላይ ባብራራሁት ቃል መሠረት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ብቻ ነው ጌታችን ኢየሱስ አጋንንትን እንዲያስወጡና ሕሙማንን እንዲፈውሱ ለሐዋርያቱ ትዕዛዝ ሰጥቶአቸዋል ይሄ ትዕዛዝ ታድያ ለእኛም ይሄ እምነት ላለንና አሜን ብለን ትዕዛዙን በመቀበል ልንተገብረው ለወደድን ሁሉ ይሰራል የማቴዎስ ወንጌል 10 ፥ 8 ከዚህም ሌላ እባቡንና ጊንጡን ይረግጡ ዘንድ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ የሚጎዳችሁ ምንም የለም ብሎአቸዋል የሉቃስ ወንጌል 10 ፥ 17 _ 20 ይህንን ያደረጉት ግን ሐዋርያቱ እንዲሁ ከሜዳ ተነስተው ሳይሆን አምነው ነው ለዚህም ነው በማርቆስ ወንጌል 16 ፥ 17 እና 18 ፥ ላይ ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ እባቦችን ይይዛሉ የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ ያለን ስለዚህ አጋንንትን ለማስወጣትም ሆነ ድውያንን እጅ ጭኖ ለመፈወስ በመጀመርያ በክርስቶስ ኢየሱስ አምኖ የዳነ ትክክለኛ አማኝና ዳግምም የተወለደ ክርስቲያን መሆን ያስፈልጋል በክርስቶስ ኢየሱስ ብቸኛ አዳኝነት ያላመነና ዳግምም ያልተወለደ ሰው ይህንን ነገር ለማድረግ አይችልም ከዚህ የተነሳም ነው እንግዲህ የአስቄዋ ልጆች ጉድ የሆኑት አጋንንቱ እናንተ እነማን ናችሁ ? አላቸው አቆሰላቸው ፣ ደበደባቸው ፣ አሸነፋቸው ታድያ አንዳንዴ የማን መሆናችንን ሳናውቅና ሚናችንንም ሳንለይ በምንሰጠው አገልግሎት የአስቄዋ ልጆች ዕጣ ፈንታ የእኛም ይሆናል የሐዋርያት ሥራ 19 ፥ 11 _ 20 ከዚህ የተነሳ ይህን የሚያደርጉ ባሕታውያን እና አንዳንድ አጥማቂ ነን ባይ ሰዎች ዛሬ ላይ ባይመስላቸው ውሎ አድሮ እንደ አስቄዋ ልጆች ያለ ጉዳት ማጋጠሙ አይቀርምና ራሳቸውም ተጎድተው ሕዝባችንንም እንዳይጎዱ ሊያስቡበት ሊጠነቀቁም ይገባል እላለሁ ሕዝባችንንም ማሳሳት የለባቸውም ብዬ ጽኑ የሆነውን ምክሬንም ላስተላልፍላቸው እወዳለሁ የቤተክርስቲያኒቱ አመራርና የሲኖዶስ አባላትም ለዚሁ ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በእንዲህ ዓይነት ተግባር ተሰማርተው ፍጹም ርህራሄ በጎደለው የጭካኔ ድርጊት ፣ መጽሐፍቅዱሳችንም በማያዘው መንገድ አጋንንትን ካላስወጣን ፣ ደዌንም ካልፈወስን ሲሉ በመቊጠርያና በበትረ መስቀላቸው ሕዝቡን የሚቀጠቅጡትን ባሕታውያንና አጥማቂ ነን ባይ ሰዎችን ከወዲሁ በጊዜ ፣ ነገር ሳይበላሽ ፣ ሃይ ፣ ተዉ ፣ ተከልከሉ ሲል ሊገስጻቸው ፣ እገዳም ሊጥልባቸውና ሊያስቆማቸውም ይገባል እላለሁ ይሁን እንጂ ይህንን ሥራ በተገቢው መንገድ እናካሂዳለን ሲሉ የሚፈልጉት ከሆነም ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት በመላክ እንዲማሩና ትክክለኛውንም መጽሐፍቅዱሳዊ እውቀት አግኝተው እንዲያገለግሉ ቢደረግ ቤተክርስቲያኒቱ ይበልጥ መልክ ያላትና የተስተካከለች ትሆናለች ከጥፋትም ትድናለች ስል አስተያየቴን አክዬ በመጻፍ ለሚመለከተው ሁሉ አቤቱታዬን ለማቅረብ እወዳለሁ ጌታ እግዚአብሔር ለኦርቶዶክሳዊትና ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያናችን ትክክለኛ የተሃድሶ ዘመን ያምጣልን ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ God bless u all http://www.Facebook.com/yonas.asfaw.39 https://www.youtube.com/yF76GIi_rCQ yonasasfaw8@gmail.com
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment