Saturday 6 April 2019

የመምህር ምህረተ አብ አሰፋ የሐሰት ትምህርት በእግዚአብሔር ቃል ሲጋለጥ ለተከታታይ ሳምንት እውነተኛው ቃል ይነገራ...የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ቅዱሳን ወገኖች በሙሉ ሰላም ለእናንተ ይሁን :: ከዚህ በመቀጠል መምህር ምህረተ አብ አሰፋ የተባለው ሰው በኦስሎ ከተማ በልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን ባገለገለበት ወቅት ኤካቦድ ክብር ከእስራኤል ለቀቀ በሚል ርዕስ ነበርና ያገለገለው ፣ በዚህ አገልግሎት ውስጥ በሴሎ የነበረውን የካህኑ የዔሊንና የልጆቹን አገልግሎት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር በማገናኘት ምንም እንኩዋ ታቦቱ ከእስራኤል የተማረከ ሆኖ ክብር ከእስራኤል የለቀቀ ቢሆንም ዛሬም ታቦቱ ፣ ደመራው ፣ ጥምቀቱ ፣ ገናው ሆያሆዬው ፣ ቡሄው ፣ ቅዳሴው ፣ ጸበሉ ፣ ጾሙ ፣ ስግደቱ ፣ ሕማማቱ ፣ ፋሲካው እና የመሣሠሉት ሁሉ በሌለበት የሚወለድ ልጅ ስሙ ኤካቦድ ነው ሲል ተናግሮአል :: ይህንንም ሃሳቡን ወደ ሕዝቡ በማምጣት የተናገረውን ነገር ሕዝቡም አምኖ የተቀበለው መሆኑን ለማረጋገጥ አይደለም ወይ አረ በማርያም ንገሩኝ ? ሲል የማርያም ወዳጅ ለመምሰል በማርያም ስም ሕዝቡን ተማጥኖአል :: ይህም በሕዝቡ ዘንድ የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ለመምሰልና ተቀባይነትን ለማግኘት የሚደረግ ያላሰለሰ ጥረትና ብርቱ ትግል መሆኑን ከዚሁ ሰው አነጋገር ለመገንዘብ ችያለሁ :: አያይዞም ክብር አለ ? ጽላቱ አለ ? ቅዳሴው አለ ? ጸበሉ አለ ?መስቀል አለ ? ካህናት አሉ ? ዝማሬው አለ ? ማስቀደስ አለ ? ወዘተርፈ እያለ ከጠየቀ በኋላ ፣ ስለዚህ ስትመጡ ሁሉም ነገር ተሟልቶላችኋልና ኤካቦድ አይደላችሁም ሲል ሕዝቡን በባዶ ሜዳ እንዲሁ እልል ያሰኘበትን ስብከትና የቪዲዮ መረጃ በእጄ ስላገኘሁ ይህን ስብከት ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ቃል ስመለከተው ትክክል ባለመሆኑና ምላሽ የሚያስፈልገው መሆኑንም ስላመንኩበት ከመጀመርያ እና ከስብከቱ መነሻ ጀምሮ ከተናገራቸው ሃሳብ በመነሳት የሚከተሉትን መልሶች ለእናንተ ለአድማጮች አዘጋጅቻለሁ :: ቪዲዮዎቹ በየተራ ለተከታታይ ሳምንታት የሚለቀቁ ስለሆኑ እንድትከታተሉአቸው ስል ለማሳሰብ እወዳለሁ :: ለሌሎች ሼር ማድረግንም አትርሱ ተባረኩ :: እስከ ጊዜው ግን ለትውስታ ያክል ይህ ሰው ከተናገራቸው ጥቂቱን ሃሳብ ከዚህ አጭር የቪዲዮ ክሊፕ እንድትከታተሉና የየራሳችሁንም ትሕዝብት እንደ እግዚአብሔር ቃል እንድትወስዱ እጋብዛለሁ :: ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተማሪ ብላ የሾመቻቸው መምህራን የውላችሁ እንዲህ ናቸው :: ለዚህ ሕዝብ የሞተለትን ጌታ መስበክ ሲገባቸው የሚሰብኩት ከበሮንና ጸናጽልን ፣ ጸበልንና እመትን የመሳሰሉትን ነው :: ለእነዚህ የስሕተት አስተማሪዎች እነዚህ ነገሮች እስካሉና እስከተሟሉ ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኤካቦድ አይደለችም :: ወገኖቼ ሆይ ስለዚህ እነዚህን የስሕተት አስተማሪዎች ስረዳቸው ኤካቦድ የሚለው ሃሳብ በራሱ ለእነዚሁ የስሕተት አስተማሪዎች ግልጽ አይደለም :: ምንም እንኩዋ ኦቶርዶክስ ቤተክርስቲያን በከበሮና በጸናጽል አያሸበሸበች ስትዘምር ብትገኝ ፣ ቅዳሴ ቢኖራት ፣ ማኅሌቱን ብትቆም ፣ ሰዓታቱንም ብታደርስ ክብርዋ ግን ከበሮና ጸናጽል ፣ ማኅሌቱና ሰዓታቱ አይደለም :: ክብርዋ ኢየሱስ ነው :: ስለዚህ ክብርዋ የሆነውን ኢየሱስን ነው ወደ ቤትዋ ልትመልስ የሚገባው :: ታድያ ይሄን እውነት በእርግጠኝነት እንድንቀበል መጽሐፍቅዱሳችን ነግሮን ሳለ ሕዝቡ ይህንን የመጽሐፍቅዱስ እውነት አምኖ እንዳይቀበልና እንዳይድን እነዚህ የስሕተት መምህራን ክብርህ ጸናጽል ፣ ከበሮ ቅዳሴና ሰዓታት እንዲሁም ካህናትና የመሳሰሉት ናቸው ሲሉ ይህንን ምስኪን ሕዝብ እንዲሁ በደረቁ እልል እያስባሉ ያታልሉታል :: ይህን ታድያ እንደ እንደ እግዚአብሔር ቃል ስመለከተው የጤንነት ነው አልለውም :: ስለዚህ እኔም በመጨረሻ የምለው ነገር ቢኖር ቢሆን ቢሆን እነዚህን የሐሰት መምህራን ጌታ ዓይናቸውን ያብራ ነው :: ካልሆነም ግን በስራቸው ያለውን ምስኪን ሕዝብ ከእጃቸው ያስመልጠው ዘንድ ምልጃዬም ሆነ ልመናዬ እንዲሁም ጩኸቴም ነው :: ወገኖቼ ሆይ ይሄ ልመናም ሆነ ጩኸት ታድያ የእኔ ብቻ ሳይሆን የእናንተም እንዲሆን እናገራለሁ :: ለማንኛውም ግን ከዚህ አጭር ክሊፕ መልስ ተያይዘው ያዘጋጀሁዋቸው ቪዲዮዎች ይለቀቃሉ እንድትከታተሉት አሁንም በድጋሜ አሳስባለሁ ለሕዝባችንም ይሁን ለእነዚህ የሐሰት መምህራን ጌታ ማዳኑን እንዲያደርግ አጥብቃችሁ ጸልዩላቸው በነገር ሁሉ ጌታ ይባርካችሁ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment