Wednesday 20 April 2016

( ትምህርት ሰባት ) የትምህርት ርዕስ ፦ በከባድ ሕመም ፣ በከባድ መከራ ጊዜ የሚሰጥ የእግዚአብሔር ተስፋ Part 1Part 1 የትምህርቱ ዋና ዋና ሃሳቦች የትምህርት ርዕስ ፦ በከባድ ሕመም ፣ በከባድ መከራ ጊዜ የሚሰጥ የእግዚአብሔር ተስፋ 1ኛ )ትምህርቱ ሲጀምር የመከራን ዓይነቶች ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በማጣቀስ ክርስቲያን ከመከራ ጋር የተያያዘ ሕይወት ያለው መሆኑን በሰፊው ይተነትንና ጌታ እግዚአብሔር በዚህ በከባድ ሕመምና በከባድ የመከራ ጊዜ የሚሰጠው ተስፋ አለ በማለት ይቀጥላል ከባዱ ሕመምና ከባዱ መከራ ደግሞ የአንድ ጊዜ መከራ ወይንም የአንድ ሌሊት ችግር ሳይሆን ሊገፋ የማይችል ዓመታትን ያስቆጠረ የረጅም ጊዜ ስቃይና የጨለማ ሕይወት መሆኑን ያበስራል ኢዮብ 5 ፥ 6 እና 7 ፤ ኢዮብ 14 ፥ 1 ፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 3 ፥ 3 ፤ ፊልጵስዩስ 1 ፥ 29 እና 30 ፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1 ፥ 8 _ 11 ፣ 15 _ 18 ፤ መዝሙር 45 ( 46 ) ፥ 1 እና 2 ታድያ ሰዎች በቀላሉ ሊወጡትና ሊገላገሉት የማይችሉትን ይህንን የረጅም ጊዜ የጨለማና የሰቆቃ ሕይወት ያለ እግዚአብሔር ተስፋ በራሳቸው ወይም በማንነታቸው ፍጹም ሊዘልቁትም ሆነ ሊወጡት አለመቻላቸውን ይጠቁማል ስለዚህ ይህ የእግዚአብሔር ተስፋ የቃሉ አማኞች ለሆኑ ለክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር በእጅጉ አስፈላጊ የሆነ ተስፋ በመሆኑ ይህንን በቃሉ ውስጥ ያለን የእግዚአብሔር ተስፋ አማኝ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የሰው ዘር የሆነ በሙሉ ሊያምነው ሊቀበለው ሊያጣጥመውና ሊወደው ተስፋም ሊያደርገው የሚገባ እውነት መሆኑን ከትምህርቱና ከቃሉ እውነት አንጻር አበክሬ ለማስገንዘብ እወዳለሁ 2ኛ )ተስፋ ማጣትን በተመለከተ ፦ መጽሐፍቅዱሳችን በኤፌሶን 2 ፥ 11 _ 19 ላይ ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና ይለናል ወገኖቼ እንግዲህ ይህ ቃል ከእስራኤል መንግስት ርቀው ለተስፋው ቃል ኪዳን እንግዶች ሆነው በዚህ ዓለም ተስፋን አጥተው ከእግዚአብሔር ተለይተው ያለ ክርስቶስ ለነበሩ አሕዛብ የተነገረ ቢሆንም ይሄ ጉዳይ ያለክርስቶስ የሆነና ከእግዚአብሔር የተለየ የሰውን ዘር ሁሉ የሚመለከት በመሆኑ ክርስቶስ የሌለው ማለትም ክርስቶስን የሕይወቱ ጌታና አዳኝ አድርጎ ያልተቀበለ የሰው ዘር ሁሉ ክርስቶስ እስከሌለውና ከእግዚአብሔር እስከተለየ ድረስ ተስፋ ያጣ መሆኑን የክፍሉ ሃሳብ ያስተምረናል ተስፋ ማጣት ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር በብዙ ርቀት ውስጥ ያለ የአሮጌው ሰው ማንነትን የሚያመለክት ነው ይህ የአሮጌው ሰው የማንነት ሕይወት የሰላም መታጣት ያለበት የቅናት የጥል የክርክር የነፍሰ ገዳይነት እና የመሣሠሉት የአመጽ ሥራዎች የሚገለጹበት ሕይወት ነው ታድያ ተስፋ ማጣት ሲኖር የሰላም መታጣት አለና እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው ነገሮች ሁሉ በሰዎች ሕይወት ውስጥ በጉልህ ይንጸባረቃሉ በመሆኑም ይህ ክፉ ባሕርይ የሚገለጥበት አዳማዊ ሕይወት የሰውን ልጅ በኑሮው እና ከእግዚአብሔር ጋር ባለ ዘላለማዊ ሕይወቱም ጭምር ተስፋ ያሳጣና ሰላምንም የከለከለ ነው ከዚህም ሌላ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር እንዲሁም ሰው ከሰው ጋር ማለትም ወንድም ከወንድሙ ጋር ተጣልቶና ተጠላልቶ ተፈራርቶና ተራርቆም እንዲኖር ያደረገ ክፉኛ ባሕርይ ነው ይህንን ነው እንግዲህ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ለሰው ዘር ሁሉ በመሞትና ደሙንም በማፍሰስ የሰው ልጅ በሙሉ ያጣውንና ከቶውንም ቢሆን ሊያገኘው የማይችለውን ተስፋና ሰላም የመለሰለት ስለዚህ ይህንን ጌታ ኢየሱስን ያመነ ማንኛውም የሰው ዘር ሁሉ ከተስፋ ማጣት ወጥቶ በአሁኑ ሰዓት ተስፋውንና ሙሉ የሆነ ሰላሙን ያገኘ ነው ከዚህም ባሻገር ከእግዚአብሔርም ሆነ ከሰው በራቀ ሕይወት የሚመላለሰው ማንነቱ በክርስቶስ ደም ምክንያት ከእግዚአብሔርም ሆነ ከሰው ጋር የመቅረብ ዕድሉን አምጥቶለታል ለዚህ ነው ኢሳይያስ በትንቢቱ ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው ያለን ትንቢተ ኢሳይያስ 9 ፥ 1 እና 2 ጭንቀት ራሱን የቻለ ተስፋ ማጣትና የሰላም መደፍረስ ያለበት ሕይወት በመሆኑ ክርስቶስ ለሌለው እና ከእግዚአብሔር ለራቀ ለሰው ልጆች ሁሉ የሆነ ከባድ የመከራ፣ የጨለማ፣ የሰቆቃና የሞት ጥላ ያለበት ሕይወት ነው በመሆኑም እርሱን በማመናችን ምክንያት ለዘላለም እስከወዲያኛው የሚያሳርፈን ጌታ በመጣልን ጊዜ ግን ኢሳይያስ በትንቢቱ እንደነገረን ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም የሚል ቃል ታወጀልን ወገኖቼ ይህንን ታላቅ የምሕረት አዋጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ብቻ ሳይሆን ዛሬም እኔም የእግዚአብሔር ባርያ የሆንኩት በተራዬ ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም ስል ይህን እውነት ላልሰሙ ሁሉ ይሰሙና ከችግሮቻቸውም ነጻ ይወጡ ዘንድ አውጃለሁ 3ኛ )ሦስተኛው ተስፋ ደግሞ ጌታ እግዚአብሔር ረጅሙን የአራት መቶ ሰላሳ ዓመት የግብጽ ባርነትና የሰባውን የባቢሎን የምርኮ ዓመት እስራኤል ባርያ ሆነው በገፈገፉበት ጊዜ አስቀድሞ ለእምነት አባታቸው ለአብርሃምና ለራሳቸው ለእስራኤል የሰጠው ተስፋ ነበር በመሆኑም እንግዲህ ይሄ የእግዚአብሔር ተስፋ ነው እስራኤልን እነዚህን ሁለቱን ረጃጅም የምርኮ ዓመታት በተስፋ እንዲከርሙ ያደረገው እስራኤል በግብጽ ሳሉ በዚህ ተስፋ ውስጥ ስለነበሩ ዮሴፍን ያላወቀ አዲስ ንጉሥ ተነስቶ ገባሮች ቢያደርጋቸውና ቢጠበብባቸውም እነርሱ ግን እንዳስጨነቋቸው መጠን እንዲሁ በዙ እጅግም ጸኑ ይለናል በባቢሎንም እንዲሁ ምርኮ ሆነው በሄዱ ጊዜ የተነገራቸው የተስፋው ቃል የሚፈጸም ነውና እንዲሁ ያጸናቸው ነበር ዘፍጥረት 15 ፥ 13 እና 14 ፤ ዘጸአት ምዕራፍ 1 በሙሉ ፤ ኤርምያስ 29 ፥ 10 4ኛ ) በትንቢተ ኤርምያስ 46 ፥ 28 በተነገረው ቃል መሠረት ጌታ እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁና፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፤ በመጠን እቀጣሃለሁ፥ ያለ ቅጣትም አልተውህም ማለቱ የሰው ልጆችን ከልቡ አለማስጨነቁ እና ቢያሳዝንም እንደ ምሕረቱ ብዛት የሚራራ መሆኑን አይተንበታል ከዚሁ ጋራም ንጉሥ ዳዊትን ሰይጣን አንቀሳቅሶት ሕዝብ ቆጠራ ውስጥ በገባ ጊዜ ጌታ እንዴት እንደራራለትና እንደማረው በሰፊው ተመልክተናል 1ኛ ዜና 21 ፥ 1 _ 30 ፤ ሰቆ ኤርምያስ 3 ፥ 22 እና 23 ፣ 31 _ 33 ወገኖቼ ሆይ የትምህርቱ ይዘት ይህን የሚመስል ሲሆን ይህንኑ አስመልክቶ ግን ቀጣይነት ያላቸው በቪዲዮ የተለቀቁ ትምህርቶች ስላሉ እነዚህኑ ትምህርቶች ከዚሁ ጽሑፍ ጋር በማገናዘብ በማስተዋል እንድትከታተሉአቸውና ለሌሎችም ሼር እንድታደርጉት በትሕትና እና በአክብሮት እጠይቃለሁ ጌታ እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይባርካችሁ የJoshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለ ራዕይ ቀሲስ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment