Thursday, 5 February 2015

ሳሙኤልን ያሳሰበውና ግድ ያለው ነገር


ለቅዱስን የታዘዘ ወቅታዊ መልዕክት

 

 

ክፍል ሁለት

 

 

ሳሙኤልን ያሳሰበውና ግድ ያለው ነገር

 

 

ሳሙኤልም ሳኦልን አላበጀህም አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን

ትዕዛዝ አልጠበክም ዛሬ እግዚአብሔር መንግሥጥን በእስራኤል

ላይ ለዘላለም አጽንቶልህ ነበር አሁንም መንግሥጥ አይጸናም

እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል እግዚአብሔርም

ያዘዘህን አልጠበክምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አለቃ ይሆን

ዘንድ አዝዞታል አለው

 

     1  ሳሙኤል 13 13 እና 14

 

በክፍል አንድ ትምህርታችን ላይ ሳኦልን ያሳሰበውና ግድ ያለው ነገር የአክብረኝ ነገር በመሆኑ እርሱም፦ በድያለሁ አሁን ግን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት፥ እባክህ፥ አክብረኝ ለአምላክህም ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ አለው ሳሙኤልም ከሳኦል በኋላ ተመለሰ ሳኦልም ለእግዚአብሔር ሰገደ የሚለውን ሃሳብ አንስተን ሳኦል ከማንምና ከምንም ይልቅ ክብሩን ያስቀደመ ሰው በመሆኑ ሳሙኤል ሳኦልን በመተባበር ትክክልም እንደሆነ በመግለጽ ከእርሱ ጋር ተመልሶ በሕዝቡ ሽማግሌዎችና በእስራኤል ፊት ሳኦል መንግሥቱ የጸና እና ለሌላም የማይሰጥ እውነተኛ ንጉሥ ነው በማለት በእግዚአብሔር ፊት ሳይቀር ከእርሱ ጋር በመስገድና በማምለክ እንዲያከብረው ተምኔቱንም እንዲፈጽምለት ያደረገውን ሙከራና የሳሙኤልንም ከአንተ ጋር አልመለስም ሲል የወሰደውን እርምጃ እንዲሁም አለመስማማት በሰፊው ተመልክተናል አያይዘንም በዚህ በክፍል ሁለት መልዕክት ታድያ የምናየው የዚሁ የሳሙኤልን ያሳሰበውንና ግድ ያለውን ነገር ከሳኦል ጋር በማነጻጸር ይሆናል ሳሙኤልን ያሳሰበውንና ግድ ያለውን ነገር  ሳኦል ካሳሰበውና ግድ ካለው ነገር በብዙ ይለያል ሳኦል ከምንም በላይ ቅድሚያ በመስጠት ያሳሰበውና ግድ ያለው ነገር በእስራኤልና በእስራኤል ሽማግሌዎች ፊት የነበረው ክብሩ ማንነቱ መንግሥቱ ሲሆን ሳሙኤል ደግሞ ያሳሰበው ነገር ሳኦል ከምንም ይልቅ እንዲጠብቀው ታዞ ያልጠበቀውና ያቃለለውም የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ነው በመሆኑም እነዚህን ሁለቱን የሳኦልና የሳሙኤልን ግድ የተሰኙበትን ሃሳቦች በንጽጽር ተመልክተን እኛም የየራሳችንን አቋም  ወይም መንገድ እንይዛለን ማለት ነው ነገር ግን  እኛንስ የትኛው ነገር ግድ ሊለን ይገባል ? ንጉሥ ሳኦልን ግድ ያለው ነገር ? ወይስ ሳሙኤል ? መልሱን ለእናንተ ለአንባቢዎች እየተውኩ በመቀጠልም እግዚአብሔር የሚያስተምረንን እውነቶች እንደሚከተለው እንመለከታለን ሳሙኤል ሳኦል ካሳሰበውና ግድም ካለው ነገር ይልቅ ሳኦል እንዲያደርግ ታዞ ያልፈጸመው የእግዚአብሔር ሃሳብ አሳስቦት ግድም ብሎት  ሳኦልን አላበጀህም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቅህም ያለ ቢሆንም ጉዳዩ ግን በዚሁ ሳሙኤል ምስጢር ሆኖ የቀረ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ደርሶ ከመለኮታዊው አምላክ ከእግዚአብሔር ለዚሁ ለንጉሥ ሳኦል የተላለፈ  እና የማይለወጥ ውሳኔም  የመጣ በመሆኑ ሳሙኤል   በመልዕክቱ እርግጠኛ ነበርና እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀደዳት፥ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጣት የእስራኤል ኃይል እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይዋሽም አይጸጸትምም አለው  ወገኖቼ ለሁለ ነገራችን የኔ ለምንለው ክብራችንና ማንነታችን ሥልጣናችን ሊሆን ይችላል ዘውዳችን ንግሥናችን ዙፋናችን አገልግሎታችን የአገልግሎት ስማችን መሪነታችን አስተዳዳሪነታችን ወዘተርፈ ለዚህ ነገሮቻችን መጠብቅ ምክንያቱ ግን እነዚህ ነገሮች ሳይሆኑ ምክንያቱ ወይም መሠረቱ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ መጠበቃችን ነው በነዚህ ነገሮቻችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመሪነትና በቀዳሚነት ካልጠበቅን እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከእኛ ጋር አይሆኑም ዛሬ ላይ ባይሆንም ለእኛም ባይመስለንም ቀስ በቀስ ግን ከእኛ እየተንሸራተቱ እየከዱንና እየጣሉን መሄዳቸው አይቀሬ ነው ንጉሥ ሳኦልን ንግሥናው ቅባቱ ዘውዱ ዙፋኑና ክብሩ እየከዳው የሄደው ቀስ እያለ ነው ሳኦል ንጉሥ ነኝ ብሎና ዘውድ ጭኖ ቤተመንግሥት ዙፋን ላይ ቢቀመጥም ንጉሥ እንዳይሆን አቅም ያሳጡት ብዙ ነገሮች ነበሩ በዚህም ምክንያት ክፉ መንፈስ ይጫወትበት እንደነበር ከመጽሐፉ እናስተውላለን ዛሬም ቢሆን ያለው ሁኔታ ይሄ ነው ዛሬም  አገልጋዮቻችን አንዳንዶች መሪዎች ናቸው የምንላቸው ሳይቀሩ ምንም እንኳ እንዲህና እንዲያ እያደረግን ነው አለን በቦታው ብለው ቢናገሩም መንፈሳዊ አቅም ያጡበት ጉዳይ እንዳለ  ግን ከነገሮቻቸውና ከሁኔታዎቻቸው ማስተዋል ችለናል ለዚህ መፍትሔው ምንም ሳይሉ ምክንያት ሳያበዙና  ልብንም ሳያደነድኑ እንደሎዶቅያ ቤተክርስቲያንም እኔ ሙሉ ነኝ አንዳች አያስፈልገኝም ሳይሉ በጊዜ ወደ እግዚአብሔር በንስሐ መመለስ የተዉትንና ቸልም ያሉትን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ መፈጸም የናቁትን ሊሰሙትም ያልፈለጉትን የእግዚአብሔር ቃል ዳግመኛ ሊያከብሩት መመለስ አማራጭ የሌለው ነገር ነው ይህ ካልሆነ ግን ፍጻሜው መልካም አይሆንም ንጉሥ ሳኦል የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜያለሁ እያለ ከላይ ታች ቢልም እንደገናም የፍጻሜ ገመዱን ለማርዘም ፈልጎ ትግል ውስጥ ቢገባና የሚችለውን ሁሉ ቢያደርግም ውጤቱ ግን አሳዛኝና እጅግም የከፋ ነበር እግዚአብሔር ከንግሥናችን ከዘውዳችንና ከስማችን ጋር ሳይሆን ሁልጊዜም ከትዕዛዛቱ ጋር ነው ያለው ለዚህም ነው ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ ያለን ሕዝቅኤል 36 25 _ 27 ከርኩሰታችን ነጽተንና የድንጋዩ ልብ ወጥቶልን የሥጋ ልብ ሲሰጠን እግዚአብሔር መንፈሱን በውስጣችን ሊያኖርና በትዕዛዙ ሊያስኬደን አይቸገርም ነገር ግን ከዚህ ይልቅ ጌታ እግዚአብሔር የተቸገረው በደንዳናውና በድንጋዩ ልብ ነው ይህንን ሁኔታ በሐዲስ ኪዳኑም ስንመለከተው ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም አለ ዮሐንስ ወንጌል 14 21 24 ስንወደው ለዝና ለክብር ለዘውድና ለንግሥና  ስንል በትዕዛዙ ላይ አናምጽም የእግዚአብሔርንም ቃል አናቃልልም የእግዚአብሔር ትዕዛዛት ደግሞ እንድንፈጽመው የተጻፉልን የፍቅር ትእዛዞች ስለሆኑ ከባባዶች አይደሉም ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም ይለናል 1 ዮሐንስ መልዕክት 5 3 የምናነበውን አስተውለን እንድንጠቀምበት ጌታ ይርዳን

 

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

Wednesday, 4 February 2015

Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry: Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preachin...

Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry: Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preachin...: Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry: የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ምዕራፍ ሁለት ክፍል አስራ አንድ ... : የቤተክርስቲያን ተልዕኮ  ...

የመልዕክት ርዕስ ሳኦልን ያሳሰበውና ግድ ያለው ነገር

የመልዕክት ርዕስ ሳኦልን ያሳሰበውና ግድ ያለው ነገር
ለቅዱሳን የታዘዘ ወቅታዊ መልዕክት
ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ

የመልዕክት ርዕስ

ሳኦልን ያሳሰበውና ግድ ያለው ነገር

እርሱም በድያለሁ አሁን ግን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት እባክህ አክብረኝ
ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ አለው 
1ኛ ሳሙኤል  15 ፥ 30

የተወደዳችሁ ወገኖች ይህንን መልዕክት በማስተዋል ሆናችሁ የምትከታተሉ ሁሉ ሳኦልን በተቀዳሚነትና በዋናነት ያሳሰበው ግድ ያለውም ነገር በእግዚአብሔር ፊት የሠራው በደል ያጠፋቸው ጥፋቶች ሳይሆኑ የሕዝቤ ሽማግሌዎች እያለ በሚጠራቸው መሪዎች አስተዳዳሪዎች ፊት እና በእስራኤል ፊት የነበረው ክብር እንዳይቀንስ ዝቅም እንዳይል ከመፍራት የተነሳ እየመጣበት ያለ አስከፊ ገጽታ ነው ነው በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ሳሙኤልን በድያለሁ አሁን ግን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት እባክህ አክብረኝ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ እያለ ሲማጸነው ሲለማመጠውም እንመለከታለን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት እባክህ አክብረኝ ማለቱ ሳሙኤልም ሳኦልን የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል የእስራኤል ሃይል እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይዋሽም አይጸጸትም ብሎት ነበርና ይህንኑ የተናገርክበትን ሃሳብህን ለውጠህ መንግሥትሕ የጸና ለሌላም የማይሰጥ ንጉሥ ነህ በለኝ በእስራኤልም ሆነ በሽማግሌዎች ፊት እንዲሁ ስትል አክብረኝ ማለቱ ነበር ለዚሁ ጉዳዩ ሳኦል ሳሙኤልን አንተ ለእግዚአብሔር የተባረክህ ሁን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ፈጽሜያለሁ በማለት ፣ የፈጸመም በመምሰል በብዙ የውዳሴ ቃልና የማሞካሸት ቃል ቀርቦታል ሳሙኤል ግን የሳኦልን የፊት ለፊት ኩሸትና የለበጣ ቃል ሳይሆን ከሳኦል ጀርባ ያለውን የበጎች ጩኸት ፣ የበሬዎችም ግሣት በጆሮው የሰማ በመሆኑ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድርነው የሚል ጥያቄ ካቀረበለት ውጪ ሌላ ምንም ሊለው አልፈለገም መቼም ሳኦልን የሚያሳቅሉ የሚያሳጡትም ነገሮች ከፊት ለፊቱ ባይኖሩም ከጀርባው ተደበቀው ገበናውን የሚያወጡበት የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ወይንም በሌላ ቃል የእርም አቤቱታዎች  ለሳሙኤል ጆሮ በእርግጠኝነት መድረሳቸው አልቀረም ታድያ እነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ እያሉ  ሳኦል ሳሙኤልን አንተ ለእግዚአብሔር የተባረክህ ሁን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ፈጽሜያለሁ ስላለው ብቻ ሳሙኤልም እውነት ነው የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የፈጸምክ ታማኝ ንጉሥ ነህ ስለዚህ ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ንገሥ እንደማይለው ለሁላችንም ግልጽ ነው ስለሆነም ሳሙኤል በከንቱ ውዳሴና በሳኦል የለበጣ ቃል የሚገበዝ ፣ በዘመናችን እንዳሉ አስመስለውም እንደሚናገሩና እንደሚኖሩ እንደ አንዳንድ ነቢያት በበላበትም የሚጮህ ዓይነት ሰው አይደለም እርሱ ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ በመሆኑ እግዚአብሔር ያለውን ብቻ የሚናገር ነው ሳኦል በዚህ አላበቃም ይህ የለበጣ ቃሉ በሳሙኤል ፊት ተቀባይነት እንዳጣ ሲረዳ መልኩን ቀይሮ እባክህ ኃጢአቴን ይቅር በለኝ ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ የሚል ልመና ውስጥ ገባ ይህ የሳኦል ልመና አሁንም የኃጢአትን ይቅርታ አስገኝቶ ለእግዚአብሔር ለመስገድ ካለ ናፍቆትና ጉጉት የመጣ ሳይሆን ንግሥናን ዘውድንና በሰውም ፊት የሆነ ክብርን ላለማጣት ሲባል ተቀነባብሮ የቀረበ የይምሰል ይቅርታና ለእግዚአብሔር የመስገድ ፍላጎት ነው ታድያ ሳኦል ንግሥናውን ላለማጣት ሲል ኃጢአትን እንደታቀፈ ለእግዚአብሔር ቢሰግድም ሳሙኤል ግን እንዲህ ባለ ሁኔታ ከእርሱ ጋር ሊሰግድ  አልተመለሰም ዛሬ ታድያ ሳኦል ብቻ ሳይሆን ብዙ ሰዎች  ሳኦልን  በሚመስል ብልሃትና የክፋት አሠራር ውስጥ ተቀምጠው  ለእግዚአብሔር መስገድን  ብቸኛና አማራጭ የሌለው ዓላማቸው ያደረጉ ፣ የእነርሱም መስገድ ሳያንሳቸው ለሚያያቸው ሁሉ ጤናማ ክርስቲያንና ታማኝ አገልጋይ ለመምሰል ሳኦል  ሳሙኤልን እንዳለው ለራሱም ሄዶ እንዳደረገው  ኑ  ልትሰግዱ ከእኛ ጋር ተመለሱ በማለት ክብርንና ጥቅምን ጥልቅ የሆነ የግል ፍላጎታቸውንም ከማሳካት የመነጨ ተውኔት የሚፈጽሙ በዘመናችንም እንደ ሳኦል ያሉ መንፈሳውያን አርቲስቶች አልጠፉም  እነዚህ ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚሰግዱ መስለው ለእግዚአብሔር እንድንሰግድ ከእኛ ጋር ተመለሱ ይበሉ እንጂ እውነተኛው ስግደት ለእግዚአብሔር እንዲሰጥ ከመቅናት ተነስተው እያደረጉት ያለ ነገር አይደለም እንደውም እውነቱን ለመናገር እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔር ይልቅ ስግደቱም ይሁን ማንኛውም ነገር በቅድሚያ ለእነርሱ ቢሆን ለእነርሱም ሆኖ ቢቀርብ ደስታውን አይችሉትም ለእግዚአብሔር እንድንሰግድ ከእኛ ጋር ተመለሱ የሚለው ያላሰለሰ ድምጻቸው ግን መንፈሳዊ ሊያሰኛቸው የተዘጋጀ የማጥመጃ መሣርያቸው ነው ይህም የሚያሳየን  እነዚህ ሳኦልን የመሰሉ ሰዎች ወይም የሳኦል ወንድሞች ማለት ይቻላል ዓይን ያወጣውን የበሬዎቻቸውን እና የበጎቻቸውን ግሣት ከጀርባቸው እየሰማን እንዳልሰማንባቸው አድርገው በመቁጠር ብንሰማም እንኳን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለን ምንም ሳንናገርና ትንፍሽም ሳንል እነርሱ የሚፈልጉትን ስግደት ብቻ ለእግዚአብሔር እንድናመጣ አብረናቸውም እንድንሰግድ የሚሰብኩና የሚያስተምሩም ከሆነ ምንም ሳናቅማማ አሜንታችንን ከፍ ባለ ድምጽ እያሰማን አብረናቸው እንድንኖር  ሳያሰልሱ የሚወተውቱን ናቸው ይህንን የየዋህነት መንገዳችንን ተጠቅመውም እነርሱ ያጠፉት ሳያንሳቸው እነርሱ ጥፋት ውስጥ ዓይናችን እያየ ወስደው  ሊዘፍቁን ፣ ሊጎዘጉዙንና ሊነክሩን የጥፋታቸውም ተባባሪዎች ሊያደርጉን የሚሹ ናቸው ነገር ግን ይህ የጸጋ ዘመን ያልቃልና እግዚአብሔር የቀጠረላቸው ቀን እውነተኛ ንስሐ እንዲገቡ የተቀጠረ ቀን ነው እንጂ ይህን ክፉ ተግባራቸውን እየፈጸሙ በክፋታቸውም እየባሱ እየሳቱና እያሳቱ የሚጓዙበት የሕይወት መስመር አይደለም እነዚህን ሰዎች ተመለሱ አይበጃችሁም ማለት በመጽሐፉ ቃል መሠረት እውነት ቢሆንም በእነርሱ አስተሳሰብ ግን በራስ ላይ ገመድን እንደማሳጠር ተብሎ ስለሚታሰብ እንዲህ ዓይነቱ  ሰው በእነርሱ ራዳር ውስጥ የገባና ቀይ የትራፊክ መብራት ሳይቀር የጣሰ መኪና ዓይነት ነው እንዲህ  ላሉ ሰዎች ዛሬ ሳሙኤልና የሳሙኤል መልዕክቶች አስፈላጊ አይደሉም ቢኖሩም አፍራሽ ናቸው ከሚባሉ በስተቀር ተቀባይነት የላቸውም ስለዚህ ቅዱሳን እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ስናገኝ ስም ያላቸው አገልጋዮችም ይሁኑ በወንበር ላይ የተቀመጡ መሪዎች መንፈሳዊ የሚመስለውን የእናምልክ ግብዣቸውን ከምንቀበል ይልቅ በቅድሚያ ተቀበሉንም አልተቀበሉን ይህንን ነገር አይተን ቸል ማለት አንችልምና  ስደትና መገፍተር ቢበዛብንም ያለምንም ይሉኝታ ይህን የማስመሰል ተግባር እንደ ሳሙኤል ጴጥሮስንም ፊት ለፊት እንደተቃወመው እንደ ጳውሎስ  እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ጥላቻቸውንና ተቃውሞአቸውን ተንኮላቸውንም ጭምር ፈርተን ዝም ልንላቸው አይገባም ይልቁንም ያመጡትን ያምጡ  እኛ ግን አምላካችንን ታምነን ሳንፈራቸው አላበጃችሁም ስንል ልንቃወማቸው ሳናቋርጥም በአጽንኦት ልንገስጻቸው ይገባል እግዚአብሔር በዚህ ኃይል ያስነሳን አሜን

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ