Monday, 26 November 2018
በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ተሰግስገው የገቡ ፣ እግዚአብሔርን የተኩ ፣ የአማልክት አምልኮዎች ( ክፍል ሰባት ) ( ቊጥ...በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ተሰግስገው የገቡ ፣ እግዚአብሔርን የተኩ ፣ የአማልክት አምልኮዎች ( ክፍል ሰባት ) ( ቊጥር 8 ) እውነተኛዋ የኢየሱስ እናት ማርያምና ሐሰተኛ የተአምረ ማርያምዋ ማርያም ልዩነታቸው 1ኛ ) እውነተኛዋ የኢየሱስ እናት ማርያም ሀ ) ወሣህሉኒ ለትውልደ ትውልድ ለዕለ ይፈርህዎ የሉቃስ ወንጌል 1 : 50 ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል የሉቃስ ወንጌል 1 : 50 ብላለች ለ ) እስመ ገብረ ሊተ ኀይለ ዐቢያተ ወቅዱስ ስሙ የሉቃስ ወንጌል 1 : 49 ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው የሉቃስ ወንጌል 1 : 49 ብላለች ሐ ) ወትቤሎ ማርያም ለመልአክ ነየ አመተ እግዚአብሔር ይኲነኒ በከመ ትቤለኒ ወእምዝ ሖረ ወኀለፈ እምኀቤሃ መልአክ የሉቃስ ወንጌል 1 : 38 ማርያምም፦ እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ የሉቃስ ወንጌል 1 : 38 ብላለች 2ኛ ) ሐሰተኛ የተአምረ ማርያምዋ ማርያም ( የጠረፍዋ ንግሥት ) ሀ ) በተአምር 4 ላይ ማርያምን ለመገነዝ ሲሄዱ ታውፋንያ የተባለ አይሁድ አልጋዋን ስለያዘ እጁ በመልአክ ተቆርጦ አልጋው ላይ ቀረ። ይህ ሰው ሐዋርያትን ይቅርታ ጠየቀ፤ ክርስቶስንም ይቅር እንዲለው ለመነ። ሐዋርያት ግን ወደ እመቤታችን ለምን አሉት። ማርያም ቀድሞውኑ ከሞት ተነሥታ ነበርና ለመናት። ማርያምም ጴጥሮስን እንዲቀጥልለት ነገረችው። ጴጥሮስም በክርስቶስ ስምና በማርያም ስም እጁን መለሰለት ብላ ትናገራለች:: ለ ) እንደገናም በተአምር 33 ፥ 23 - 25 ላይ በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የፀናች ክብርት እመቤቴ ሆይ ከአንቺ ዘንድ ሽቶ የወደደውን ሁሉ ያላገኘ ማነው? በአንቺ አምኖ ያፈረ ማነው ? አንቺን ለምኖ ወደ ገሃነም ያወረድሽው ማነው ? ወደ ሠርግ ቤት ማለት ወደ መንግሥተ ሰማይ አገባሽው እንጂ ብላ ሰዎች ከእርስዋ እንዳይሄዱና እንዲያመልኩዋት ፣ እንዲሰግዱላትና እንዲገዙላትም ስለ ራሷ ታላቅነት ተናገረች :: 3ኛ ) በእነዚህ ጉዳዮች መጽሐፍቅዱስ የሚሰጠው ዳኝነት በተራ ቁጥር ሀ በተጠቀሰው ሃሳብ መሠረት ይህ ጴጥሮስ ትክክለኛውና እውነተኛው ሐዋርያው ጴጥሮስ ቢሆን ኖሮ ይደንቀን ነበር :: ነገር ግን በማርያም በኩል የታውፋንያን እጅ እንዲቀጥልለት የተነገረው ጴጥሮስ ፣ እንደገናም በክርስቶስ ስምና በማርያም ስም እጁን መለሰለት የተባለው ጴጥሮስ በመጽሐፍቅዱሳችን የምናውቀው እውነተኛውና ሐዋርያም የሆነው ጴጥሮስ አይደለም :: እውነተኛውና የመጽሐፍቅዱሱ ጴጥሮስማ በሐዋ 3 ፥ 6 ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ በማለት ነው በኢየሱስና በኢየሱስ ስም ብቻ በሽተኞችን የፈወሰው :: ይህ ብቻ አይደለም በሐዋ 4 ፥ 12 መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና ነው ያለው :: ከማርያም ትእዛዝ ተቀብሎ በማርያም ስም ፈወሰ ተብሎ የተጻፈበት ሥፍራ በመጽሐፍቅዱሳችን አንድም ቦታ ላይ የለም :: በማርያም ስም መፈወስም ሆነ አጋንንትን ማስወጣት የጌታም ሆነ የሐዋርያቱ ትምህርት አይደለም:: መጽሐፍቅዱሳችንም አይደግፈውም :: የተአምረ ማርያም ትምህርት ነው :: ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ የሆነ የተአምረ ማርያም ትምህርት ደግሞ የእግዚአብሔር ሳይሆን የአጋንንት ትምህርት ነውና አንቀበለውም :: የመጽሐፍቅዱሱ ጴጥሮስም ሆነ እንደ ጴጥሮስ ያለ የእግዚአብሔር ቃል እምነት ያለን እኛ ሁላችን በሽተኞችን እንድንፈውስ አጋንንትንም እንድናወጣ የታዘዝነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንጂ በማርያም ስም አይደለም የማርቆስ ወንጌል 16 ፥ 15 - 18 ፣ የማቴዎስ ወንጌል 10 ፥ 5 - 15 :: የኢየሱስ እናት ማርያምም ከሞት አልተነሳችም ደግሞም አላረገችም 1ኛ ቆሮንቶስ 15 ፥ 50 :: ከሞት ተነስቶ ያረገውና ተመልሶም የሚመጣው ኢየሱስ ብቻ ነው ዮሐንስ ወንጌል 3 ፥ 13 ፤ የሐዋርያት ሥራ 1 ፥ 11::እንደገናም የኢየሱስ እናት ማርያም ጴጥሮስን ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ያለንን የጌታ አማኞችን የሚላችሁን አድርጉ አለችን እንጂ የዮሐንስ ወንጌል 2 ፥ 5 ከሞት የተነሳች ሆናና በእግዚአብሔርም ቦታ ራስዋን ተክታ የሰዎችን ጸሎት አልሰማችም :: ደግሞም ፍጡር እንጂ አምላክ አይደለችምና የተቆረጡ እጆችን በስሜ በመለመን ቀጥልላቸው ስትል የነገረችውም ሆነ ትዕዛዝ የሰጠችው ሐዋርያ የለም :: በእግዚአብሔር ቦታ ራሷን ተክታም እንዲህ ዓይነቱን ትዕዛዝ አትሠጥም ፣ ልትሠጥም አትችልም :: ከዚህ የተነሳ እኛ የቃሉ አማኞች ፍጡር የሆነችዋን የኢየሱስን እናት ማርያም ከፈጣሪ ለይተን የምናውቅና ማርያምም የተፈጠረች እንጂ ፈጣሪ አለመሆንዋን የተረዳን ስለሆንን ፣ ነይ ነይ እምዬ ማርያም ፣ ንዒ ኃቤየ ኦ ድንግል ፣ ድንግል ሆይ ወደ እኔ ነይ ስንል በዓል አዘጋጅተንና አጽዋማትን ቀምረን የምንጠራት ማርያም የለችንም :: ከዚህም ሌላ ሐዋርያቱም ወደ ማርያም ለምኑ አላሉንም :: ትምህርታቸው አይደለችምና እነርሱ ክርስቶስን ነው የሰበኩልን:: በስሙም ብናምን የኃጢአታችንን ሥርየት እንደምናገኝ ነው የነገሩን 1ኛ ቆሮንቶስ 1 ፥ 23 ፤ የሐዋርያት ሥራ 10 ፥ 42 እና 43 የምናነበውን ቃል አስተውለን እንድንታዘዘውና በዚህም በሰማነው ቃል ወደ እውነቱ እንድንመጣ ቸሩ መድኃኔዓለም ያግዘን ይርዳን:: ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን አባ ዮናስ ጌታነህ ከጸአተ ግብጽ ኦርቶዶክሳዊና ሐዋርያዊ የተሃድሶ አገልግሎት
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment