Tuesday, 4 September 2018

በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ተሰግስገው የገቡ ፣ እግዚአብሔርን የተኩ ፣ የአማልክት አምልኮዎች ( ክፍል ስድስት ) ( ቊ...በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ተሰግስገው የገቡ ፣ እግዚአብሔርን የተኩ ፣ የአማልክት አምልኮዎች ( ክፍል ስድስት ) ( ቊጥር 2 ) በውኑ ድንግል ወደ እኛ በአሁኑ ሰዓት መምጣት ትችላለችን ? ሀ ) በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን መጽሐፈ ሰዓታት ( የሰዓታት መጽሐፍ ) በተባለው የጸሎት መጽሐፍ ካህናት በመንፈቀ ሌሊት ተነስተው ንዒ ኀቤየ ኦ ድንግል ፣ ድንግል ሆይ ወደ እኔ ነይ ሲሉ ረጅሙን ዜማ እያዜሙ ይጸልያሉ በፍልሰታ ጸምና በዓቢይ ጾም እንዲሁም በሌሎች አጽዋማት ሳይቀር ካህናት በመንፈቀ ሌሊት ተነስተው ይህንኑ ጸሎት በዚህ የሰዓታት መጽሐፍ መሠረት ያደርሳሉ ለ ) ህዝባዊ መዝሙርም ወጥቶለት ፣ ህዝባችንም ነይ ነይ እምዬ ማርያም እያለ በመዘመር ድንግልን ይማጸናል ይህ ለምን ይሆን ? 2ኛ ) እግዚአብሔር ልጆቹ አድርጎ ስለተቀበለን ድንግል ሆይ ወደኔ ነይ ወይንም ነይ ነይ እምዬ ማርያም ስንል የምንጠራት ድንግል የለችንም:: የተወደዳችሁ ወገኖቼ ሰላም ለእናንተ ይሁን የዛሬው ትምህርቴ በቁጥር ሁለት ላይ የተመሠረተ ነው :: በቁጥር ሁለት ትምህርታችን የምንመለከተው እግዚአብሔር እንዴት አድርጎ እንደተቀበለን የሚገልጹ ሃሳቦችን በማንሳት ነው :: ውድ ወገኖቼ ሆይ እግዚአብሔርን እኛ አልተቀበልነውም ፣ እንደገናም ጽድቃችን የመርገም ጨርቅ ስለሆነና ኃጢአተኞችም ከመሆናችን የተነሳ የኃጢአት ደሞዝ የሆነውን ሞት በላያችን ላይ ተሸክመን የምንዞር ሰዎች ስለሆንን እግዚአብሔርን የሚቀበል ማንነት የለንም :: እርሱ ግን ይሄ ሁሉ ነገር በላያችን ላይ እንዳለ አውቆ እኔም እቀበላችኋለሁ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ አለን( 2ኛ ቆሮንቶስ 6 ፥ 17 - ፍጻሜ ):: የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስንም በማመናችንና በመቀበላችን ምክንያት ልጆቹ አድርጎ ተቀበለን ( ዮሐንስ ወንጌል 1 ፥ 11 እና 12 ):: ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲቀበለን እግዚአብሔር የላከውን ኢየሱስን እንደ እናቱ ማርያም ፣ ከኃጢአተኞች ዋና ነኝ እንዳለውና የጌታውንም ምህረት እንደተቀበለው እንደ ጳውሎስ ፣ እኛም ኃጢአተኝነታችንን አምነን ጌታንና የጌታንም ምሕረት ለሕይወታችን ወስነን መቀበል አለብን የሉቃስ ወንጌል 1 ፥ 47 ፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1 ፥ 12 - 17 :: ይህንን ጌታ በተቀበልን ጊዜ ደግሞ አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነት መንፈስ እናገኛለን :: ይሄ መንፈስ ያለው እንደገና ለፍርሃት የባርነት መንፈስ የተቀበለ አይሆንም :: መንፈሱም ልጅ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ወራሽ መሆኑንም ይመሰክርለታል ( ሮሜ 8 ፥ 14 _ 17 ) :: ለዚህም ነው የገላትያ መጽሐፍ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባርያ አይደለህም ልጅም ከሆንክ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ ያለን ( ገላትያ 4 ፥ 4 - 7 ) :: ታድያ እግዚአብሔር እንደተቀበለው ያወቀና ልጁንም ኢየሱስን የተቀበለ ውስጡ ያለው የወራሽነት መንፈስ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የሆነ የባርነት መንፈስ ባለመሆኑ ነይ ነይ እምዬ ማርያም እና የመሣሠሉትን የሚልበት ማንነት የለውም :: ጌታን ያልተቀበለና ለፍርሃት በሆነ ማንነት ተውጦ የባርነት መንፈስ የሚሰማው ሰው ግን አይደለም ነይ ነይ እምዬ ማርያም ማለት ገና እንደ ንጉሥ ሳኦል መናፍሥት ጠሪ ቤት ሄዶና የክፉ መንፈስ መጫወቻ እስከ መሆን ደርሶ ሊሞት ይችላል :: ይህ እንዳይሆን ነው እንግዲህ የተቀበለንን እግዚአብሔር በማወቅ እስከ ሞት ድረስ ወዶ ሕይወቱን በመስጠት ያዳነንን ጌታ ተቀብለን የእግዚአብሔር ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንሁን የምንላችሁ :: ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይቀርም እንደሚባለው ሆኖ ይህንን እኛ ያልናችሁን የእግዚአብሔር እውነት ቸል በማለት የሞተችዋን ፣ ያልተነሳችዋንና ያላረገችዋን ፣ በመሞትዋም ምክንያት ልትሠማን የማትችለዋን ድንግል ፣ የለም ትሰማናለች በሚል ድርቅና ተይዘን በየበዓላቱና በየገዳማቱ ነይ ነይ እምዬ ማርያም ስንላት ብንውል ፣ አልፈን ሄደንም ሱባዔ ገብተንና በር ዘግተን ብንጠራት ፍጻሜያችን ክስረትና የጠረፍዋ ንግሥት መጫወቻም ሆኖ መቅረት ስለሆነ ከወዲሁ እናስብበት እላለሁ :: የበዓል ነቢያት በአንድ ወቅት ከነቢዩ ኤልያስ ጋር ፉክክር ገብተው አምላካቸውን ሊጠሩ በጣም ብዙ ደከሙ :: ወይፈኑንም ወስደው አዘጋጁ፥ ከጠዋትም እስከ ቀትር ድረስ፦ በኣል ሆይ፥ ስማን እያሉ የበኣልን ስም ጠሩ። ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስም አልነበረም፤ በሠሩትም መሠዊያ ዙሪያ እያነከሱ ያሸበሽቡ ነበር በቀትርም ጊዜ ኤልያስ፦ አምላክ ነውና በታላቅ ቃል ጩኹ፤ ምናልባት አሳብ ይዞታል፥ ወይም ፈቀቅ ብሎአል፥ ወይም ወደ መንገድ ሄዶአል፥ ወይም ተኝቶ እንደ ሆነ መቀስቀስ ያስፈልገዋል እያለ አላገጠባቸው :: በታላቅም ቃል ይጮኹ፥ እንደ ልማዳቸውም ደማቸው እስኪፈስስ ድረስ ገላቸውን በካራና በቀጭኔ ይብዋጭሩ ነበር :: ቀትርም ካለፈ በኋላ መሥዋዕተ ሠርክ እስኪደርስ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስና የሚያደምጥም አልነበረም ይለናል መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ  18 : 25 - 29 :: ይህን ከመሰለ ሁኔታ ለመውጣት ታድያ መጽሐፍቅዱሳችን የሚለንን መስማት አማራጭ የለውም ስለዚህ አሁንም መጽሐፍቅዱሳችን በአንተ ምክር መራኸኝ ከክብር ጋር ተቀበልከኝ ይለናል :: እንደገናም አንተ የመረጥከው በአደባባዮችህም ለማደር የተቀበልከው ምስጉን ነው ከቤትህ በረከት እንጠግባለን በማለትም ይነግረናል ( መዝሙር 73 ፥ 24 ፤ መዝሙር 65 ፥ 4 ) ተባረኩ :: ሕዝቡም አውቀው ተከተሉት ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር መፈወስም ያስፈለጋቸውንም ፈወሳቸው ( የሉቃስ ወንጌል 9 ፥ 11 ) ለተጨማሪ መረጃ ው የተለቀቀውን ቪዲዮ ይመልከቱ ከጸአተ ግብጽ ኦርቶዶክሳዊና ሐዋርያዊ የተሃድሶ አገልግሎት ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ አስፋው

No comments:

Post a Comment