Sunday, 21 February 2016
( ትምህርት ሦስት ) የትምህርቱ ርዕስ ፦ ለአብርሃምና ለዘሩ የተስፋው ቃል በእምነት ጽድቅ ነው እንጂ በሕግ አይደ...የትምህርቱ ዋና ዋና ነጥቦች የትምህርቱ ርዕስ ፦ ለአብርሃምና ለዘሩ የተስፋው ቃል በእምነት ጽድቅ ነው እንጂ በሕግ አይደለም ( ሮሜ 4 ፥ 13 _ 15 ) የክፍሉ ሃሳብ ለምን ይህንን ተናገረ ? ስንል በተጻፈው ቃል መሠረት ከሕግ የሆኑት ወራሾች ከሆኑ እምነት ከንቱ ሆኖአል የተስፋውም ቃል ተሽሮአል ወደ ማለት ሃሳብ ሰዎች ሊመጡ የሚችሉ በመሆናቸው ይህንኑ ከሕግ የሆነ ወራሽነትን ይዘው ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እንዳይሄዱ ለአብርሃምና ለዘሩ በተነገረው የተስፋ ቃል መሠረት የምንጸድቀው ከእምነት በሆነ ጽድቅ እንጂ በሕግ አለመሆኑን ለይቶ በማወቅ አንድና ብቸኛ በሆነው በዚህ እውነት ላይ ብቻ ጸንተው እና እርግጠኞችም ሆነው እንዲቆሙ ለማድረግ ነው ሕግን ከመጠበቅ በሆነ ጽድቅ ወራሽነት የለም ስለዚህ ጉዳይ አሁንም የገላትያ መጽሐፍ እንዲህ ይለናል 1ኛ ) ሕግ ምንድነው ? ስንል ፦ ሕግ ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ ይለናል እና ስለዚህ ሕግ የተስፋው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል የተጨመረና መቅሠፍትን የሚያደርግ መተላለፍንም የሚገልጽ ነው ገላትያ 3 ፥ 19 ፤ ሮሜ 3 ፥ 20 ፣ ሮሜ 4 ፥ 15 2ኛ )ሕጉ መቅሰፍትን ያደርጋልና ነገር ግን ሕግ በሌለበት መተላለፍ የለምና የሚል የእግዚአብሔር ቃል ተጽፎልናል እንደገናም ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ፥ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል፤ አታመንዝር ያለው ደግሞ፦ አትግደል ብሎአልና ተብሎም የተጻፈልን በመሆኑ ከዚህ እውነት አንጻር ሕግን ጠብቆ ያልተሰናከለ ማንም ሰው የለም አናገኝምም ስለዚህ የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ሆነ ሮሜ 4 ፥ 15 ፤ የያዕቆብ መልእክት 2 ፥ 10 ፤ ሮሜ 10 ፥ 4 3ኛ ) እንደገናም ይህንኑ ቃል አሁንም ሐዋርያው ይበልጥ ሊያጎለብተው አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና አለን ሮሜ 3 ፥ 19 እና 20 4ኛ ) በመሆኑም ሕግ የሰዎችን ከሕግ በታች መሆን እየተናገረ የዓለሙን አፍ በመዝጋት ዓለሙን በሙሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች እንዲቀመጡ ያደረገ ከላይ በገለጽኩት ሃሳብ መሠረትም ይህ ሕግ አሁንም የሰዎችን ኃጢአትና መተላለፍን ሁሉ ያለአንዳች ማቅማማት ሳይደብቅ እያጋለጠ ፣ በትክክለኛ ሁኔታም እየገለጸ የሚያኖርና የሚኖርም ነው ሮሜ 7 ፥ 7 _ 25 5ኛ ) ይህ ብቻ አይደለም ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎልናል ይሁን እንጂ ታድያ በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎም የተጻፈ በመሆኑ ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን ገላትያ 3 ፥ 10 ፣ 13 5ኛ )ሕያው ሊያደርግ የሚቻለው ሕግ ተሰጥቶ ቢሆንስ በእውነት ጽድቅ ከሕግ በሆነ ነበር ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ይሰጥ ዘንድ መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል ይለናል ገላትያ 3 ፥ 21 እና 22 6ኛ ) ከዚህም ሌላ ይሄው ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም አይደለም ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላም የተሰጠው ይህ ሕግ አሁንም አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳንና የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም ይለናል ለምን ስንል ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል በማለት አብርሃም በእግዚአብሔርም የተረጋገጠ ኪዳንና የተሰጠ የተስፋን ቃል በእርግጠኝነት መያዙን የክፍሉ ሃሳብ በተገቢው መንገድ ይጠቁመናል ገላትያ 3 ፥ 17 እና 18 ለዚህም ነው እንግዲህ በሐዋርያት ሥራ 13 ፥ 32 _ 39 ላይ እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ፦ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና እንደገናም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ ከሙታን እንደ አስነሣው፥ እንዲህ፦ የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ ብሎአል ደግሞ በሌላ ስፍራ፦ ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም ይላልና ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በእርሱ በኩል የኃጢአት ስርየት እንዲነገርላችሁ፥ በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን ያለን ስለዚህም የምኩራቡ አለቆች ወንድሞች ሆይ ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ ብለው በላኩባቸው ጊዜ ጳውሎስ ተነስቶና በእጁ ጠቅሶ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን በሚል ኃይለ ቃል ሊናገረው፣ በጽኑም ሊሰብከው የፈለገው ጥንት ለአባቶች የተሰጠ ተስፋና የምስራች ነው ተብሎ የተነገረለትን የናዝሬቱ ኢየሱስን ነው ታድያ ይህ የእግዚአብሔር ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ ዛሬ ዘመን ላይ ላለነው ለእኛ ብቻ የተሰጠ ተስፋና የምስራች ሳይሆን ለእነዚሁ ለእምነት አባቶች ለነአብርሃምም ጭምር አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠ ኪዳንና የማይሻር የተስፋ ቃል ሆኖ የተሰጠ ተስፋና የምሥራች ነው ታድያ ይህንን የተሰጠ ተስፋና የምስራች ነው የእምነት አባቶች እነ አብርሃም የጠበቁትና የተቀበሉት በመሆኑም ዛሬ ላይ እኛ ተፈጥረን ፣ ወይም ተገኝተን ማለት ይቻላል በዚህ የአባቶቻችን ተስፋና የምስራች በሆነው በናዝሬቱ ኢየሱስ ፍጹም ልናፍርበት አይገባም ያለዚያ ጌታ የሚሰጠን ለሁላችን የሚሆን ዕረፍትና መዳን የለም ከአባቶች ከነ አብርሃም ጀምሮ ጌታ ኢየሱስ ተስፋና የምስራች ሆኖ ለሁላችን ሲሰጥ እንዲሁም ሲሰበክ ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሠጠውምና ተብሎ በቃሉ የተጻፈልን በመሆኑ መበስበስ በሌለበት በአዲስ ትንሣኤ የተነሣ ነውና መበስበስን አላየም ዳዊት ግን በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን ሃሳብ ካገለገለ በኋላ በአንቀላፋ ጊዜ መበስበስን አይቶአል ይህ እግዚአብሔር ያስነሳው ግን መበስበስን አላየም ይለናል ይህ እግዚአብሔር ያስነሣውና መበስበስንም ያላየው ደግሞ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው ጌታ እግዚአብሔር አስነስቶ ለእኛ ለልጆቹ የምስራችና ተስፋ ነው ብሎ የፈጸመልን የናዝሬቱ ኢየሱስ ሲነሣ ከዳዊት ዘር የተወለደና እንደ ቅድስና መንፈስ ከሙታን መነሣት የተነሳ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ የተገለጠ እንዲሁም የተነሣም ነው ይህንን ነው እንግዲህ ጳውሎስ ወንጌል የሚለን ወንጌል ማለት የልጁ ወንጌል ነውና ሮሜ 1 ፥ 1 _ 5 ፤ ሮሜ 16 ፥ 25 እና 26 የተወደዳችሁ ወገኖች በትምህርቴም ማጠቃለያ ልናገር የምወደው አንድ እውነት እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በእርሱ በኩል የኃጢአት ስርየት እንዲነገርላችሁ፥ በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን ተብሎ በእርግጠኝነት የተጻፈልን በመሆኑ እንግዲህ በሙሴ ሕግ ልንጸድቅበት ከማይቻለን ሁሉ ወጥተን በእርሱ በክርስቶስ በኩል የኃጢአትን ሥርየት በማግኘት ያልጸደቅንም ሰዎች መጽደቅ ፣ ያልዳንም ሰዎች እንዲሁ መዳን ይሁንልን ስል በዚህ ጉዳይ ላይ ደግሞ መጽሐፉ እንዳንጠራጠር አስረግጦ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን ብሎናልና እኔም የመጽሐፉን ቃል ተከትዬ ይህ በክርስቶስ እና በክርስቶስ ብቻ የተገኘ የኃጢአት ሥርየት እንዲሁም መጽደቅ ለሁላችን የታወቀ ይሁን በማለት ይህንኑ የመጽሐፉን ቃል ለእናንተ ለወገኖቼ በእምነትና በሥልጣን አውጃለሁ በመቀጠልም ከእነዚህ ማብራርያዎች ባሻገር ይህ ትምህርት ጽድቅን ያልተከተሉት አሕዛብ ጽድቅን አገኙ፥ እርሱ ግን ከእምነት የሆነ ጽድቅ ነው በማለት በሮሜ 9 ፥ 30 የተጠቀሰውን ሃሳብ አንስቶ ጽድቅ በእምነት እንጂ በሕግ አለመሆኑን ሊጠቁመን ወደ ሦስት የሚደርሱ ዓበይት ነጥቦችን በዝርዝር ያስቀምጣል ፦ 1ኛ ) ጽድቅ የሚገኘው በእምነት ነው ዕብራውያን 11 ፥ 7 ፤ ዘፍጥረት 15 ፥ 6 ፤ ፊልጵስዩስ 3 ፥ 2 _ 10 ፣ 8 እና 9 2ኛ ) እኛም የምንጸድቀው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት ነው ሮሜ 3 ፥ 27 እና 28 ፤ ገላትያ 2 ፥ 16 ፣ 21 ፤ ገላትያ 5 ፥ 4 3ኛ ) እግዚአብሔርም የሚያጸድቀን በእምነት ነው ሮሜ 3 ፥ 28 _ 30 ፤ ሮሜ 3 ፥ 25 እና 26 ፤ ሮሜ 4 ፥ 16 እና 17 ፤ ገላትያ 3 ፥ 8 የተወደዳችሁ ቅዱሳን በቪዲዮ የተለቀቀው ትምህርት ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንላችሁ እነዚህን ዋና ዋና ሃሳቦች ለተጨማሪ በማብራርያነት አክዬበታለሁ በመሆኑም በዚሁ በቪዲዮ የተለቀቀውን ትምህርት ሳያመልጣችሁ በመስማት ለሌሎችም ሼር እንድታደርጉ በማክበር ላሳስባችሁ እወዳለሁ በነገር ሁሉ ተባረኩ ሰላም ሁኑ የJoshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልጋይና ባለ ራዕይ ቀሲስ ዮናስ ጌታነህ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment