Friday 22 November 2019

የመልዕክት ርዕስ ፦ ወደ ሥራችን እንመለስ ( መጽሐፈ ነህምያ 4 ፥ 15 ) . ___ የመልዕክት ርዕስ ፦ ወደ ሥራችን እንመለስ የተወደዳችሁ ቅዱሳን የእግዚአብሔር ሕዝቦች በሙሉ ሰላም ለእናንተ ይሁን :: ይህ የተለቀቀው የቪዲዮ መልዕክት ሐዋርያዊት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የወንጌላውያኑን ወይንም የፕሮቴስታንቱን ቤተክርስቲያንም ጭምር የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ ሁላችሁም በማስተዋል ሰምታችሁ እንድትጠቀሙ እጋብዛለሁ :: መልዕክቱ በቪዲዮው ላይ በግልጥ ስለተቀመጠ ብዙ ማብራራት አይጠበቅብኝም :: በአጭሩ ለማስቀመጥ ግን ይህንን ቃል የተጠቀመው ነህምያ ሲሆን በመጽሐፈ ነህምያ 4 ፥ 15 ላይ ጠላቶቻችንም ይህ ነገር እንደ ደረሰልን እግዚአብሔርም ምክራቸውን ከንቱ እንዳደረገው ሰሙ እኛም ሁላችን ወደ ቅጥሩ እያንዳንዳችንም ወደ ሥራችን ተመለስን በማለት ተናገረ :: በዚህ ውስጥ ታድያ ጌታ እግዚአብሔር የተስተጓጐለውን የራሱን ሥራ ለአስተጓጓዮች ነግሮ ሳይሆን የሚመልሰን የአስተጓጓዮችን ምክር አፍርሶና ከንቱ ምክራቸውም እንደፈረሰባቸው ለራሳቸው ሳይቀር ነግሮና አሳውቆ ነው የሚመልሰን :: እኛም ታድያ ይህን አውቀን እግዚአብሔር እስኪመልሰን መጠበቅ የለብንም :: እኛው ራሳችን ወደ ሥራው ተመለሰን መመለሳችንንም እንደ ነህምያ በሁሉም ፊት ማወጅ እና ማሳወቅ አለብን :: ነህምያ የነገረንም ሆነ ያሳየን ቁምነገር እንግዲህ ይህንን ይመስል ነበር :: ጠላት ሁልጊዜ የማይተኛ ሆኖ የእግዚአብሔርን ሥራ ለማስተጓጐል የመከረና እየመከረም ያለ ቢሆንም ምክሩ ግን ትላንት ፈርሶ የሚቀር አይሆንም ፣ ዛሬም እስከ ለዘላለምም እየፈረሰበት ይኖራል :: ይሁን እንጂ ታድያ ይሄ ጊዜ ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜው ስለሆነ እኛም የእግዚአብሔር አገልጋዮችና ቅዱሳን ሕዝቦች ይህን እውነት አውቀን ቶሎ ፈጠን በማለት እግዚአብሔር ወደ ሰጠን ሥራ መመለስ ይሁንልን እላለሁ :: ለበለጠ መረጃ ይህንን ቪዲዮ እንድትሠሙት እጋብዛለሁ :: መልዕክቱንም ሌሎች ሼር ማድረግ አትርሱ ተባረኩ :: ወንድማችሁ አባ ዮናስ ነኝ

Saturday 16 November 2019


የሥልጣን ሽኩቻ መንስዔዎች ምን ምን ናቸው 


የተወደዳችሁ ወገኖች ሰላም ለእናንተ ይሁን 

 ውድ ወገኖቼ ሆይ የሥልጣን ሽኩቻ መንስዔዎች ምን ምን ናቸው በሚል ርዕስ ጥቂት ቆይታ ከእናንተ ከአንባቢዎቼ ጋር አደርጋለሁና ተከታተሉኝ :: ሰዎች በቤተክርስቲያን በመሪነትና በአገልግሎት ሥልጣን ለምን ይሻኮታሉ ? ሀገርን ወደ መምራትና ወደ ማስተዳደር ጉዳይ አልፈንም ስንሄድ ይሄ የስልጣን ሽኩቻ ብሶና ተባብሶ ሰዎችን በብሔር በጎሳና በቋንቋ እስከመከፋፈል ያዳረሰና ያጨራረሰ    ደምንም ያቃባ ብርቱ መዘዝ ሆኖ አግኝተነዋል :: ታድያ ሰዎች በዚህ የሥልጣን ሽኩቻ እንዲጠመዱና እዚህ ደረጃም ላይ እንዲደርሱ የሚያደርጋቸው ምንድነው ስንል ከጦርነት መልስ የመጣ የተንበሸበሸ ዕረፍት ነው የሚል ሙሉ የሆነ መልስ እናገኛለን :: ሰዎች ዕረፍት ሲበዛላቸው ወይንም ወደ ዕረፍት ሲመለሱ የሚሠሩት ነገር ስለሌላቸው ሥራ ፈት ይሆናሉ :: አንድ ሰው ሲናገር እንዲህ አለ ሥራ የፈታ አዕምሮ የሰይጣን ወርክ ሾፕ ነው በማለት ተናገረ :: ታድያ ሰዎችም ሥራ በሚፈቱ ጊዜ እንዲሁ የሰይጣን ወርክ ሾፕ ይሆናሉ :: ጊዜያቸውንም እንዲሁ በሃሜትና በአሉባልታ የሚያሳልፉ ይሆኑና  አንዱን ሲያነሱ ሌላውን ሲጥሉ ፣ ሲቀዱና ሲሰፉ ይውላሉ :: ወደገዛ ወንድሞቻቸውም ተመልሰው በወንድሞቻቸው ላይ በአገልግሎት በሥራ በእውቀት በደሞዝ እርከንና በመሣሠሉት  ቀደመን ያሉትን ሁሉ ሰው ብቻ ከንቱ በሆነ ቅንዓት ይጠሉትና እንዲሁ ሲያሳድዱት ስሙንም ሲያጠፉት ይገኛሉ :: ለዚህም ነው መጽሐፍቅዱሳችን በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ እርስ በእርሳችን እየተነሳሳንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ ሲል የመከረን  ገላትያ 5 25 እና 26   እንመልከት ::

ወገኖቼ ሆይ የሥልጣን ሽኩቻን የወለደው እንዳልኳችሁ የተንበሸበሸ ዕረፍት ሲሆን ፣ ይሄ ከልክ በላይ የሆነ የተንበሸበሸው ዕረፍት ደግሞ ሰዎችን ሥራ ፈት ከማድረጉ ባሻገር  እያንዳንዱ በገዛ ወንድሙ ላይ ጠላት ሆኖና በጠላትነትም ተነስቶ ይህንኑ ወንድሙን እንዲገድል ሆኗል ፣ እግዚአብሔር ይቅር ይበለን :: የሚደንቀው ደግሞ ይሄ ሁኔታ በደጅ ወይም በውጪ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቤት መጀመሩ ነው :: እግዚአብሔር ቤት ያለው ግድያ የክላሽ ድምጽና የጠመንጃ ተኩስ የማይሰማበት ከባዱ ግድያ ሲሆን ፣ በሀገር ላይ እየተሰማ ያለው ግድያ ግን ጩቤውን ፣ ስለቱን ፣ ካራውንና ድንጋዩን ሁሉ ያስተባበረ ፣ በመሣርያም ጭምር የሆነ ነፍስ የማጥፋት ግድያ ነው:: ይሁን እንጂ ታድያ ሁለቱም ግድያዎች በእግዚአብሔር ዘንድ በእኩል ዓይን የሚታዩ በመሆናቸው  ልዩነት የላቸውም :: ገዳዮቹንም በእግዚአብሔር ዙፋን ፍርድ በነፍሰ ገዳይነት  የሚያስጠይቃቸው ይሆናል :: 

የተወደዳችሁ ወገኖች ለዚህ እውነታዬ ብርቱ ማስረጃ ለመስጠት ወደ ኢትዮጵያ ታሪክ ሄጄ አንድ ክፍል ለማንሳት እገደዳለሁ :: እርሱም ምንድነው ብትሉኝ ከ900 —- 1200 ( ከዘጠኝ መቶ እስከ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ) ዓመት ባለ ክፍለ ዘመን የተነሳች ዮዲት የተባለች አይሁዳዊት ሴት ኢትዮጵያን ለአርባ ዓመት ስትገዛ በትልቅ ጭካኔ ነበር የገዛችው :: የኦርቶዶክስን ገዳማትና አድባራትን አቃጥላለች የሀገርን ቅርስና ታሪክ አውድማለች ፣ ሰዎችን አርዳለች ፣ ገድላለች ፣ አጥፍታለች :: ጭካኔዋና የአገዛዝ ቀንበርዋም ከልክ ያለፈ ፣ አረመኔነትንም ጭምር የተላበሰ ነበር :: በዚህ ሁኔታ ውስጥ ታድያ  በሀገር ደረጃ ያሉ ሰዎችም ይሁኑ ከቤተክርስቲያን ሰዎች መካከል ከለቅሶ ፣ ከዋይታና እግዚአብሔርንም ከመማጸን ውጪ አንድም ትንፍሽ ያለ ሰው አልነበረም :: ዘማሪ ተስፋዬ ጫላ እንደማያልፍ የለም ሁሉ አለፈና የሰቆቃ ዘመን በደስታ ተተካ ብሎ እንደዘመረው ክፉው የ40 ዓመቱ የዮዲት ጉዲት የጭካኔ አገዛዝ ካከተመ ፣ በምትኩም ለሀገርም ሆነ ለቤተክርስቲያን የነጻነትና የጸጥታ  ዘመን ከመጣ በኋላ ቤተክርስቲያንም ሆነ ሀገር ይህንን እግዚአብሔር ያመጣውን ዕረፍት በጎ ለሆነው ሥራ  ሲጠቀሙበት አልተስተዋለም :: ይልቁንም  ሁለቱም ወደየግል ጉዳዮቻቸው ተመልሰው የእርስ በእርስ ግጭትና ጠብን ነው የጀመሩት  :: ሰላምን ሻ ተከተላትም እንደሚል ቃሉ የመጣውን ሰላም እንደ ትልቅ ዕድል ቆጥረው ይህንኑ ሰላም የፈለጉም ሆነ የሻቱም አልነበሩም ፣ አልተከተሉትምም 1ኛ ጴጥሮስ 3 ፥ 10 - 12  :: በዚያን ጊዜ የነበረ  ሥልጣን ከነገደ ሳባ ወደ ነገደ ዛጉዬ ስለተመለሰ ይሄ ሁኔታ ያስከፋቸው የሳባውያን ነገድ በዛጉዬ መንግሥት ላይ ትልቅ ሽኩቻ ፈጠሩ :: በወቅቱ ሆኖም ተደርጎም የማይታወቅ ሽኩቻ በእነዚህ ጎሳዎች መካከል ተካሄደ :: በዚህ ውስጥ ታድያ ቤተክርስቲያን የማስታረቅ ቃል በውስጥዋ ከመኖሩ የተነሳ ሥልጣንን አስመልክቶ በነገዶች መካከል በተደረገው ግጭት የአስታራቂነቱን ቅድሚያ በመውሰድና ሕዝቦችንም ማለትም የሳባንና የዛጉዬ ነገድ ወደ አንድነት በማምጣት እነዚሁኑ ሰዎች እንደ አንድ ሕዝብ አድርጋ ማስታረቅም ሆነ ማስማማት ሲገባት ከእነርሱ ይልቅ እርስዋ ብሳና ጎራም ለይታ  የጥቅሙም ሆነ የግጭቱ ተባባሪና ፊት መር በመሆንዋ  ምክንያት ፍቅር ጠፍቶ አምልኮተ እግዚአብሔር ተዘንግቶ ይህቺው እዚያ ዘመን ላይ የነበረች ቤተክርስቲያን የዘርና የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸምያ ወደ መሆን አዘመመች :: ከላይ ባየነው ተጽዕኖም አማካኝነት በ1300 ( በአንድ ሺህ ሦስት መቶ ዓመት ) በአቡነ ተክለ ሃይማኖት የፖለቲካና የሃይማኖት መሪ መሆን ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ድረስ ( 1966 ዓመተ ምሕረት ) ቤተ መንግሥት ከቤተ ክህነት ጋር ተጣመረ ፣ ነገሥታቱም ሁሉም ባይባሉም የራሳቸው ስምና ዝና እንዲጻፍላቸው እንዲመሰገኑ ምስላቸውም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲሰቀልና ማዕጠንት እንዲታጠን ለብቻቸው ማስቀደሻ ሥፍራ እንዲዘጋጅላቸው ፣ ሲሞቱም ቃልኪዳን ተቀብለዋል በሚል ጻድቃን ተብለው በዕለተ ሞታቸው እንዲዘከርላቸው በስማቸው ታቦት እንዲቀረጽላቸው አጥንታቸውም ሳይቀር ሕዝቡን እንዲገዛ አስምለውና አስገዝተው የሄዱ በመሆናቸው ቤተክርስቲያን ዛሬ ላለችበት ትልቅ ውድቀት ምክንያት ሆኖአል :: ሌላው ቀርቶ የእነርሱ ካባና መቋምያ ፣ መቀመጫ መንበሮቻቸው ሳይቀር ሻማ እየተለኮሰለትና እየታጠነ ፣ መልክአ ውዳሴ ተደርሶላቸው ማሕሌት የሚቆምላቸው ጊዜያት ነበረ :: ታድያ በዚህ ሁኔታ በ14ኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ ከምንኩስናው ዓለም  ወደ ቤተመንግሥት በማናለብኝነት ዘው ብሎ ገብቶ ራሱን በማንገሥ እና በትረ መንግሥቱንም በመጨበጥ  በወንጌል እውነት ተዋጅተው  እየሰበኩ ያሉትን ወገኖች ለንጉሥ አልሰገዱም በማለት የሞት ጭፍጨፋና ግድያን ያካሄደባቸው ከዚህ የተነሳ ነው :: እነርሱም ሲመልሱለት ራሳችንን ለሥሉስ ቅዱስ አስገዝተናልና በሥላሴ ላይ አራተኛ አካል አንጨምርም ፣ ለዛም ለአራተኛው አካል አንሰግድም በማለታቸው ምክንያት አስረውና አርባ ጅራፍ እያንዳንዳቸውን በመግረፍ በጉድጉዋድ ውስጥ አንገታቸውን ብቻ ብቅ በማድረግ የጋማ ከብት ነድተውባቸዋል :: ታድያ ከዚያን ጊዜ የጀመረው ክፋት ነው ዛሬ ድረስ ቀጥሎ ቤተ ክርስቲያንዋ ወደ ጥንተ መሠረትዋ ተመልሳ ወንጌልን ብቻ እንድትሠብክ በሚታገሉላት  አገልጋዮች ላይ አሁን ድረስ ትልቅ የሆነ ስደትና ሰልፍ ያለው :: በዚህ ውስጥ እንግዲህ ወንጌልን መመከቻ አድርገው ሥልጣን ለምኔ ጥቅም ለምኔ ያሉ አገልጋዮች ሲሰደዱ ሆዳቸው አምላካቸውና ክብራቸው በነውራቸው የሆኑ አገልጋዮች ደግሞ  በዚያው መጠን አሳዳጆች ሆነው ይኸው አሁን ያለንበት ደረጃ  ላይ ደርሰናል :: እነዚህ ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ አገልጋዮች ደግሞ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብቻ የሚገኙ ሳይሆኑ በወንጌላውያን ቤተክርስቲያንም ጭምር ሳይቀር የአገልግሎት ሥልጣንና ስም ለብሰው ከዚህ በከፋ ሁኔታ እያሳደዱ ያሉ ሰዎችም በብዛት ይገኙበታል :: 

በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ክፋቱ እየጨመረ ሄዶ የአባ እስጢፋኖስ ደቀመዛሙርት እጃቸውና እግራቸው እየተቆራረጠ ፣ አፍንጫቸውም እየተፎነነ ወይንም እየተቆረጠ እንዲሞቱ ቢደረግም እነርሱ ግን ይሄ ሁሉ ሳይበግራቸው ለእውነት ወንጌል ቆመውና መከራውንም ታግሰው ያስተማሩ ነበሩ ይሁን እንጂ በዚያ ዘመን እንደገናም ይባስ ተብሎ በአፄ በዕደ ማርያም በአፄ እስክንድር በአፄ ዘመደ ጽዮን ፣ በአፄ ናኦድ በአፄ ልብነ ድንግልና በመሳሰሉት እየታደኑ ተደበደቡ ተገደሉ ከቅጽረ ቤተክርስቲያንም ሳይቀር እንዲባረሩ ተደረጉ :: ዛሬም ታድያ ሥልጣንን መውደድ የሚያመጣው መዘዝ ከዚህ ሁለት እጥፍ የጨመረ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም :: ሥልጣናቸውን የሚወዱ ሰዎች አሁንም በዚህ ጉዳይ ምንም ከማድረግ ወደ ኋላ አይመለሱም :: ይህ ነው እንግዲህ ቤተክርስቲያንንም ሆነ ሀገርን ወደ ኋላ ያስቀረና ወደ ከፋ ነገርም የወሰደ  :: ራሳቸውን የወደዱ ሰዎች በሀገር ደረጃም ይሁን በቤተክርስቲያን ዕርቅን የማይሰሙ ጨካኞች ፣ ከዳተኞች ፣ ችኩሎች ፣ በትዕቢት የተነፉ ናቸው 2ኛ ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 3 ን በሙሉ  እንመልከት ::

መልዕክቴን ስጠቀልል በሀገር ጉዳይ መረጋጋትና ሰላም እንዲመጣ በቤተክርስቲያንም እንዲሁ እውነተኛው የጽድቅ ወንጌል ተሰብኮ ለሕዝብ መዳን እንዲሆንና ጌታም እንዲከብር ራስ ወዳድም ሆነ ራስ ተኮር የሆኑ ሰዎች ከነገሮቻቸውና ከየግል ጥቅሞቻቸው በፍጥነት ተመልሰው ሕዝባዊና ሀገራዊ አስተሳሰብ ሊይዙ ይገባል እላለሁ :: በቤተክርስቲያንም ደረጃ ያሉ ሰዎች ደግሞ በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ ራሳቸውን ደብቀው የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉ  እንደ አንድ ትንንሽ መንግሥት ራሳቸውን ሊቆጥሩና ሊያስቆጥሩ ቢወዱም ከዚህ  ይልቅ የሚመጣውን የክርስቶስን መንግሥት በጽድቅ ሊሰብኩ ራሳቸውን ቢሰጡ የምንፈልገው ዘላለማዊ የጌታ ሰላም ይመጣል :: እንደገናም ይህንን የጌታ ሰላም በማምጣትና   ወደ ሰዎችም ሁሉ በማድረስ  ቤተክርስቲያን የመጀመርያዋ ትሆናለች :: ጌታ እግዚአብሔር ከራሳችን ነገር አውጥቶ ለዚህ እውነት ያቁመን ተባረኩ !! 

አባ ዮናስ ጌታነህ 

ከስምዓ ጽድቅ ሐዋርያዊ ኦርቶዶክስ ተሃድሶ 

666 እና የኢሉሚናቲ መንፈስ...የመታወቅያ ካርዶችና ፓስፖርቶች እንዲሁም ምልክቱን በቀኝ ክንዳቸው በቀበሩ የሚሰ...

Friday 8 November 2019

ዘረኝነትና መዘዙ በሀገራችን ላይ እንዲሁም በቤተክርስቲያን

ጮራ: ፍካሬ መጻሕፍት

ጮራ: ፍካሬ መጻሕፍት: READ PDF “ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን ዐውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይኾን ዘንድ፥ የእግዚ...