Saturday 14 February 2015

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ከፍል አስራ ሁለት ከሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች ለመጠበቅ የምንወስደው መፍትሔ


የቤተክርስቲያን ተልዕኮ

 

 

ከፍል አስራ ሁለት

 

 

ከሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች ለመጠበቅ የምንወስደው መፍትሔ

 

 

የተወደዳችሁ ወገኖች የቤተክርስቲያን ተልዕኮ የሚለውን አርዕስት የምንጠቀልለው በዚህ የክፍል አስራ ሁለት የመጨረሻ ትምህርት ነው በዚህ ትምህርት ከሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች ለመጠበቅ የምንወስደው መፍትሔ ምን እንደሆነ እንመለከታለን በክፍል ሁለት ትምህርታችን ላይ የሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች መነሻ ሃሳብ በሚል የአንድ ትንቢት እውነተኛነት የሚታወቀው ትንቢቱ እንደተነገረው ሲፈጸም ነውና ዘዳግም 18 21 _ 22 ሆኖም በልዩ ችሎታ መጪውን ዘመን ከወዲሁ ከሚተነብዩ በአጋጣሚ ከሚፈጸም የሐሰተኛ ነቢያት ትንቢት እንድንጠበቅ ክፍሉ ያሳስበናል ዘዳግም 13 1 _ 5 ለምን ? ስንል እነዚህ ሰዎች የተፈጸመውን ትንቢት ተንተርሰው ወደማንፈልገው የስሕተት አሠራር ይወስዱናል የእግዚአብሔርንም ቃል እንድንተላለፍ ያደርጉናል ለዚህ ነው ነቢይ ወይም ሕልም ዐላሚ ከመካከልህ ተነስቶ ምልክት ወይም ድንቅ አደርጋለሁ ቢልህ የተናገረው ምልክት ወይም ድንቅ ቢፈጸም አንተ የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እናምልካቸው ቢልህ አምላካችሁ እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ ትወዱት እንደሆነ ያውቅ ዘንድ ሊፈትናችሁ ነውና የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ሕልም ዓላሚውን አትሥማ በሚል ሃሳብ ዙርያ የሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች መነሻ ሃሳብ ይህ በመሆኑ ይህንንም የተፈጸመውን ትንቢት ተንተርሰው ወደማንፈልገው የሥህተት አሠራር ይወስዱናል  እያልን ነበር ክፍል ሁለትን በስፋት የተማማርነው በክፍል አስራ ሁለት ላይ ግን እነዚሁ ሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች ከሚያስተላልፉት ቃልና ከትምህርቶቻቸው እንዲሁም በድንገት ከተፈጸሙ ትንቢቶቻቸው ለመጠበቅ የምንወስደውን መፍትሔ በዝርዝር እንመለከታለን ታድያ ከእነዚህ በዝርዝር ካቀረብኳቸው ነገሮች ለመጠበቅ

 

1ኛ)በፍጹም ልብ እርሱን መውደድ ስንወደው እንፈልገዋለን

 

 

2)ከእርሱ ጋር መጣበቅ ነው

የሚሉትን ዋና ሃሳቦች ተመርኩዘን በማብራራት ነው

 

 

1)በፍጹም ልብ እርሱን መውደድ ስንወደው እንፈልገዋለን

 

በዘዳግም 4 29  _ 31 ላይ ነገር ግን ከዚያ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትሻላችሁ በልብህም ሁሉ በነፍስህም ሁሉ የፈለግኸው እንደ ሆነ ታገኘዋለህ ይህም ሁሉ በደረሰብህ ጊዜ፥ ስትጨነቅ፥ በዘመኑ ፍጻሜ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ትመለሳለህ፥ ቃሉንም ትሰማለህ አምላክህ እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ነውና አይተውህም፥ አያጠፋህምም፥ ለአባቶችህም የማለላቸውን ቃል ኪዳኑን አይረሳም ይለናል እግዚአብሔርን በመፈለግ ውስጥ ቃሉን መስማት አለ አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር ተመለሰ የሚባለው ቃሉን ሲሰማ ነው ዘዳግም 4 31 በዚያን ጊዜ እስራኤል ያለ እውነተኛ አስተማሪና ካህን ያለ ሕግ ይኖሩ ስለነበር ለሚወጣ ለሚገባ ሰላም አልነበረም በሚኖሩት ሁሉ ላይ ታላቅ ድንጋጤ ነበር ወገን ከወገን ጋር ይዋጋ ነበር በማለት  ሳያበቃ በመከራቸውም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ አገኙት በማለት ቃሉ ይነግረናል 2 ዜና 15 1 _ 7 እግዚአብሔርን በመፈለግ ውስጥ ቃሉን ማግኘት ቃሉን መማር አለ ቃሉን የተማረና ቃሉን ያገኘ ሰው ደግሞ ሲወጣና ሲገባ ሰላሙ የተጠበቀ ነው ወገን ከወገን ጋር መዋጋትና ታላቅ ድንጋጤ አይኖርም ቃሉን አግኝቶ በመማር ውስጥ ትክክለኛ አቅጣጫ ነው ያለው እግዚአብሔርን ባለመፈለግ ውስጥ ሆነው ቃሉን ባላገኙ ሰዎች  ሕይወት ውስጥ ግን ሁልጊዜ ያለው ነገር በሐሰተኛ ነቢያት እና አስተማሪዎች አስተምሕሮት እንዲሁም  ትንቢት ተጠልፎ መወሰድና መሳት ሲሆን ከዚህም ሌላ በመግባት በመውጣት ሳይቀር ሰላም ማጣት ወገን ከወገን ጋር መዋጋትና ድንጋጤ በብዛት የሚታዩ ክስተቶች ናቸው የዛሬዋም ቤተክርስቲያን እግዚአብሔርን የመፈለግ መሻትዋ ደካማ ነውና  እንደሚገባ ቃሉን ያልሰማች ያላገኘችና ያልተማረች በመሆንዋ ለእነዚህ ነገሮች በብዙ የተጋለጠች ናት መንጋዎችዋ በሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች በቃላሉ ይጠመዳሉ በዚህም የተያዙ ይሆናሉ እንደገናም ሰዎች በቤቱ ውስጥ ነን እያሉ ሲወጡና ሲገቡ ሰላም የላቸውም ውጊያው ያለው ከደጅ ወይም ከሌላ ወገን ሳይሆን ወገን ከወገኑ ጋር ነው ይህ የሚያሳየን እንግዲህ ያለ እውነተኛ ካህንና አስተማሪ እንደኖሩት እንደ እስራኤል ቃሉን ባለመማር የመጣ ችግር ነው ዛሬም ታድያ ቃሉን ያለመማር ችግርና የእውነተኛ ካህን አስተማሪም መታጣት በሐሰተኛ ነቢያት እና አስተማሪዎች አስተምሕሮት እንዲሁም ትንቢት ተጠልፎ መወሰድን ፣ የእርስ በእርስ መበጣበጥና ድንጋጤንም ጭምር በይበልጥ አባብሶት ይገኛል እግዚአብሔር ከዚህ ያለማስተዋል ሕይወት በእውነተኛው የቃሉ ትምህርት ያውጣን መጽሐፍቅዱሳችን አሁንም ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይለናል ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ የአስቆሮቱ ያይደለ ይሁዳ ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ ልትገልጥ ያለህ እንዴት ነው ? አለው  ኢየሱስም መለሰ አለውም የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም  ዮሐንስ ወንጌል 14 21 _ 24 ጌታን ስንወድ ትዕዛዙ በእኛ ዘንድ ትሆናለች ትዕዛዙን የምንጠብቅም እንሆናለን እርሱም እራሱን ይገልጥልናል የማንወደው ከሆነ ግን ቃሉን አንጠብቅም ስለዚህ ትዕዛዙ በእኛ ዘንድ እንድትሆንና እንድንጠብቃትም  እርሱም ለእኛ ራሱን እንዲገልጥልን እርሱን  በፍጹም ልባችን በፍጹም ነፍሳችን እና በፍጹም ኃይላችን መውደድ ነው ዘዳግም 6 5 10 12 _ 13 ማርቆስ 12 30 ማቴዎስ 22 37 ሉቃስ 10 27

       ከሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች ለመጠበቅ የምንወስደው ሁለተኛውን መፍትሔ እንደሚከተለው እንመለከታለን

 

2ኛ)ከእርሱ ጋር መጣበቅ ነው

 

በዘዳግም 10 20 _ 22 ላይ አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፥ እርሱንም አምልክ ከእርሱም ተጣበቅ፥ በስሙም ማል ዓይኖችህ ያዩትን እነዚህን ታላላቆች የሚያስፈሩትንም ነገሮች ያደረገልህ እርሱ ክብርህ ነው፥ እርሱም አምላክህ ነው ይለናል ስለዚህ ሐሰትን ነግረውን ባልተፈጸመው ትንቢታቸው ምክንያት ከእነርሱ በመለየትም ሆነ እነርሱን በመገሰጽ እርምጃ የምንወስድባቸው ነቢያት 1) እግዚአብሔርን በመውደድና እርሱኑ በመፈለግ    2)ከእርሱ ጋር በመጣበቅ ነው በእነዚህ ሁለት ነጥቦች ውስጥ ሕይወታችን የተያዘ ሲሆን ሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎችን በቀላሉ ለማወቅና እነርሱንም ለመቋቋም መንፈሳዊ ጉልበት ስለሚኖረን  በውስጣችን ተሞልቶ ያለው ቃሉ ይጠብቀናልና በብዙ የተጠበቅን እንሆናለን ከዚያ ውጪ ግን አይሆንም በዘዳግም 13 5 ላይ አምላክህ እግዚአብሔር ትሄድባት ዘንድ ካዘዘህ መንገድ ሊያወጣህ፥ ከግብፅ ምድር ካወጣችሁ ከባርነትም ቤት ካዳናችሁ ከአምላካችሁ ከእግዚአብሔር ሊያስታችሁ ተናግሮአልና ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ይገደል እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ አርቅ ይለናል የቃሉ ሙላት ከሌለንና ካላወቅንበት በአብዛኛው የሐሰተኛ ነቢያት ቃል ከመሠረታዊው እውነት የሚያወጣን ይሆናል ከዚህ በመቀጠል እነዚህን ጥቅሶች እሰጣችኋለሁና አንብቧቸው ዘዳግም 18 20 ኤርምያስ 28 15 _ 17 ነብዩ ሐሰትን በመናገሩ ምክንያት የሚገደል መሆኑን ይናገራል ዘዳግም 17 7 ዘዳግም 19 19 ዘዳግም 21 21 ዘዳግም 22 21 24 ዘዳግም 24 7 ክፋቱን ከመካከል ማስወገድ እንደሚገባ ይናገራል ዘዳግም 18 22 ላይ ደግሞ ነቢዩን መፍራት እንደማይገባ ይናገራል ነገር ግን እነዚህን መሠረታዊ እውነቶች አምኖ ለመተግበር  ተገቢ የሆነውን የቃሉን መረዳት ማግኘት ወሳኝነት አለው ለዚህ ነው በፍጹም ልብ እርሱን መውደድና መፈለግ እንደገናም ከእርሱ ጋር መጣበቅ ያለብን በሐዲስ ኪዳን መጽሐፍም ይህንን እውነት  በ2ኛ ጴጥሮስ 3 16 _ 18 ላይ ሄደን ስንመለከት በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ እንግዲህ እናንተ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ፥ በዓመፀኞቹ ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ ለእርሱ አሁንም እስከ ዘላለምም ቀን ድረስ ክብር ይሁን አሜን የሚለን በመሆኑም በአመጸኞች ስሕተት ተስቦ ላለመጥፋት በጸጋውና በቃሉ እውቀት ማደግ በብሉይ ኪዳን ሕይወት ውስጥም ይሁን በሐዲስ ኪዳን ተፈላጊና ዋና ነገር እንደሆነ በተገቢው መንገድ ልናውቅ ልናሰምርበትም የሚገባ ነገር ነው ቅዱሳን ወገኖች የቤተክርስቲያን ተልዕኮ የሚለውን ትምህርት በጌታ ጸጋ እንዳጠናቅቅ የረዳኝን አምላክ አመሰግናለሁ በመቀጠል ለእናንተም ለአንባቢዎቼ የማሳስበው ይህንን ትምህርት በይበልጥ ለመረዳት ከክፍል አንድ ጀምሮ እስከ ክፍል አስራ ሁለት ድረስ ያለውን ሃሳብ እንደገና ከልሳችሁ ለማንበብ ብትነሱ ይበልጥ ግንዛቤን እንደምታገኙ ልጠቁም ነው በሌላ አዲስ ትምህርት እስከምንገናኝ ጌታ በነገር ሁሉ ይባርካችሁ የምላችሁ

 

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ

 

ለዘለዓለም ተባረኩልኝ

No comments:

Post a Comment