Tuesday 10 March 2015

ጥንተ አንቀጽ መካነ ሕይወት ፈውስነ ሲሳይነ ስቴነ መኮንንነ ትርጉም ፦ በር መሠማርያ የሕይወት መገኛ የሚያድን ምግባችን ሃይማኖተ አበው


ይህ _ Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry

 ሥር እየተዘጋጀ የሚቀርብላችሁ ትምህርት ነው

 

 

ጥንተ አንቀጽ መካነ ሕይወት ፈውስነ ሲሳይነ ስቴነ መኮንንነ

 

 

ትርጉም በር መሠማርያ የሕይወት መገኛ የሚያድን ምግባችን

            የሚፈርድልን መጠጣችን ነው

 

               ሃይማኖተ አበው

 

             

               እልመስጦግያ

 

               ምዕራፍ 3

 

 

ኢየሱስም ደግሞ አላቸው እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ

ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም

በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል

         

           

         የዮሐንስ ወንጌል 10 1 _ 15 7 _ 10

 

 

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ዛሬ የምንማማርበት ሃሳብ በሃይማኖተ አበው የተጠቀሰውን ቃል ከመጽሐፍቅዱሱ ቃል ጋር በማገናዘብና በማስተያየት ይሆናል ለምን ማስተያየት አስፈለገን ? ስንል የጥንቷ ኦርቶዶክሳዊት ሐዋርያዊትና ዓለማቀፋዊት ቤተክርስቲያናችን ትክክለኛውን የእግዚአብሔር ቃል እውነት እንደምትከተል የሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ጠቋሚ ሆኖ ስላየነው ነው ስለዚህ ይህንን በሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ላይ ያገኘነውን የእግዚአብሔር ቃል እውነት ከመጽሐፍቅዱሱ ቃል ጋራ በማገናዘብ ዛሬ ላይ ላለው፣ መንገድ ለለቀቀው ሕዝባችን ትክክለኛውን የእግዚአብሔር ቃል እውነት እናስተምራለን የዛሬዋን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንንም ወደ ጥንተ መሠረቷ ወደ እግዚአብሔር ቃል እውነት እንድትመለስና ይህንኑ የእግዚአብሔር ቃል እውነት ብቻ እንድታስተምር በብዙ እንጥራለን እንደክምላታለን እናበረታታታለን ደግሞም ቃሉን እናስታጥቃለን የሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ክርስቶስ ኢየሱስ በር መሠማርያ የሕይወት መገኛ የሚያድን ምግባችን የሚፈርድልን መጠጣችን ነው ይለናል ክርስቶስ ኢየሱስ ደግሞ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 10 1 _ 15  ጀምሮ ስንመለከት እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው በማለት ይጀምርና የእርሱ የሆኑ በጎቹ ድምጹን እንደሚሰሙ እርሱም በስማቸው ጠርቶ እንደሚወስዳቸው ይናገራል አያይዞም የራሱ በጎች ድምጹን ሰምተው እንደሚከተሉት ከሌላው ግን እንደሚሸሹ አበክሮ ይነግረናል በመቀጠልም እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል በማለት ይነግረናል የሚያሰማራ እረኛ ወደ በጎች በረት በበሩ ነው የሚገባው በሩ እያለ በሌላ በኩል ሊገባ አይወድም ደግሞም አይፈልግም ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ስለጉዳዩ ሲናገር በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው አለን ኢየሱስ ግን ወደ በጎች በረት በበሩ የሚገባ ስለሆነ የበጎች እረኛ ነው በጎቹም አውቀው ድምጹን ይሰሙታል የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል ካወጣቸውም በኋላ በፊታቸው ይሄዳል ለዚህ ነው በጎቹም ድምጹን ያውቃሉና ይከተሉታል የሚለን ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም የሌሎችን ድምጽ አያውቁምና በማለት ይዘግብልናል ታድያ ኢየሱስ ወደ በጎች በረት በበሩ የሚገባ ድምጹንም የሚያሰማ በጎቹንም በየስማቸው ጠርቶ የሚወስድ መልካም እረኛ ብቻ ሳይሆን እርሱ እውነተኛም የበጎች በር ነው ስለዚህ ወንበዴው ዲያብሎስ ኢየሱስ ወደ በጎች በረት በበሩ የሚገባ መልካም እረኛ ብቻ ሳይሆን እውነተኛም የበጎች በር መሆኑን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በበሩ በኩል ሊመጣ ቢወድ የሚያጋጥመውን የከፋ አደጋ መቋቋም አይችልምና በትክክለኛው የበጎች በር አይመጣም እንደገናም በበሩ ሳይሆን በሌላ ድንገት ሾልኮ ገብቶም እንኳ ከሆነ የሚወጣው አሁንም በሌላ መንገድ ነው ስለዚህ የማያወላውል አሳቻ መንገድም የማይሰጥ እውነተኛ የበጎች በር እርሱ ኢየሱስ ብቻ ስለሆነ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል አለን የሃይማኖተ አበውም መጽሐፍ እንግዲህ ያረጋገጠልን በመጽሐፍቅዱሱ ላይ የተጻፈልንን ይህንኑ እውነት ነው ጥንተ አንቀጽ መካነ ሕይወት ፈውስነ ሲሳይነ ስቴነ መኮንንነ ስንተረጉመው በር መሠማርያ የሕይወት መገኛ የሚያድን ምግባችን የሚፈርድልን መጠጣችን ነው የሚለውን ትርጉም ሲሰጠን እናገኛለን የሃይማኖተ አበው መጽሐፍ መሠማርያ የሕይወት መገኛ ማለቱ ጌታ ኢየሱስ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል ስላለን ነው ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ መዳኛ የሕይወት መገኛ መውጫ መግቢያችንና መሠማርያችን  ነው እግዚአብሔር አብ ለደኅንነታችን ልጁን ኢየሱስን እስኪልከው ድረስ  ይሄ ሁሉ አልነበረም ማለት ሕይወት ያላገኘን ደኅንነት የሚባል ነገር የማናውቅ መውጫ መግቢያችን የማይታወቅ መሠማርያም የሌለን ኮብላዮች ተንከራታቾችና ተቅበዝባዥ ሕዝቦች ነበርን እንደውም መጽሐፍቅዱሳችን ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች እንደነበርን ነው የሚነግረን በኤፌሶን 2 3 ላይ ወንሕነሂ ነበርነ ኲልነ ትካት በፍትወተ ሥጋነ ወገበርነ ፈቃደ ሥጋነ ወዘሐለይነ ወኮነ ውሉደ መንሱት ከመ ኲሉ ኃጥአን ትርጉም በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን ይለናል ከቁጣ ልጅ ደግሞ የሚጠበቀው መዳንና ዕረፍት መውጣትና መግባት መሠማርያም ማግኘት ሳይሆን መቅበዝበዝ ነው ስለዚህ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እስኪመጣልንና የእግዚአብሔርን ቁጣ በመስቀል ላይ ለብቻው በሞቱ ለእኛ ሲል እስኪቀበልልን ድረስ ዕረፍትና መዳን የሌለን መሠማርያም ያላገኘን ተቅበዝባዦች ነበርን ለዚህም ነው ጴጥሮስ በግልጽ ሳይደብቀን ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል ያለን 1 የጴጥሮስ መልእክት  2 24 እና 25 እግዚአብሔር የሁላችንንም በደል በእርሱ ላይ ስላኖረና የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ስለነበረ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን ስለዚህ አሁን ወደ ነፍሳችን እረኛ ተመልሰን የዳንና መሠማርያም ያገኘን ስለሆንን አሁን ተቅበዝባዦች አይደለንም በመሆኑም ይህንን እውነት የተቀበለና ያመነ ሁሉ አሁንም ከመቅበዝበዝ ወጥቶ በኢየሱስ ይድናል መሠማርያም ያገኛል ኢየሱስም ያድነዋል እውነተኛ የበጎች በር ኢየሱስ ነውና ስለዚህ  ይህንን መልዕክት ለምታነቡ ሁሉ አንድ መልዕክት አለኝ ከመቅበዝበዝ ወጥታችሁ በዚህ የበጎች በር በሆነው በኢየሱስ በኩል ግቡ እላችኋለሁ በዚህ በር በኩል ብቻ ለመግባት ስትወስኑና በበሩም ስትገቡ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ያድናችኋል ያወጣችኋል መሠማርያም ይሆናችኋል ከመቅበዝበዝም ትድናላች ጌታ እግዚአብሔር የምናነበውን ቃል ይባርክልን  ከዚህ በመቀጠልም የሃይማኖተ አበው ጸሐፊ እንደተናገረው ኢየሱስ እንዴት የሚያድን ምግባችን የሚፈርድልን፣ መጠጣችን እንደሆነ በሚቀጥለው የትምህርት ክፍለ ጊዜ እንመለከተዋለን እስከዚያው የጌታ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን የምላችሁ

 

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ

 

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

 

No comments:

Post a Comment