ክፍል ሁለት
የ Joshua
Breakthrough Renewal Teaching and
Preaching Ministry
የአገልግሎት አነሳስና ጽንሰ ሃሳቡ ምን እንደሚመስል በመጀመርያው የክፍል አንድ ማብራርያዬ ላይ በሚገባ ገልጨዋለሁ አሁን ደግሞ የአገልግሎቱን ተልዕኮና መሠረታዊ ዓላማው ምን እንደሚመስል ተልዕኮውን አውቀው ዓላማውን ሊደግፉ ለሚፈልጉ ሁሉ ግልጽ በማድረግ ላብራራው እወዳለሁ
1ኛ)ጽንሰ ሃሳቡ ወይንም ሚኒስትሪው ይዞት የተነሳው መነሻ ሃሳብ ምን እንደሚመስል ተመልክተናል
2ኛ)ተልዕኮውና መሠረታዊው ዓላማ ምን እንደሚመስል እንመለከታለን
ሀ _ የ Joshua Breakthrough Renewal
Teaching and
Preaching
Ministry
የተነሳው የወጣውና አገልግሎቱንም የጀመረው እናት በሆነችው
በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሥር ሆኖ ኦርቶዶክስ ወደ ጥንተ መሠረቷ ቀድሞ ይዛው ወደ ነበረችው ወደ መጀመርያው ወንጌል እንድትመለስ ማድረግ ነው እናት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አሁን ላይ ተመሥርተው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን የማዳኑን ወንጌል ለሚሰብኩ አብያተክርስቲያናት ሁሉ እናት የሆነች ቤተክርስቲያን ናት ብል ማጋነን አይሆንብኝም ምክንያቱም በአብዛኛው በወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ያሉ አማኞች ወይ አባታቸው አለበለዚያም እናታቸው እንደገናም አያት ቅድመ አያቶቻቸው እህት ወንድምንም ጨምሮ ኦሮዶክሶች ናቸው ከአማኙም መካከል የኋላ ታሪኩ ወይም ባግ ግራውንዱ ኦርቶዶክስ ያልሆነና ከኦርቶዶክስ ያልመጣ የኦርቶዶክስ ጠረን ያልሸተተውና
ኦሮዶክስንም ያላሸተተ ማንም የለም ከሞላ ጎደል በአብዛኛው እንደዚህ ነው አንዳንዱም መሀል ገብቶ የወጣ በቆሎ ትምህርት ቤት ቅኔ ድጓውንና ጸዋትወ ዜማውን ሳይቀር ለመማር ሄዶ ውሻ የጮኸበት ነው አንዳንዱም የቅዳሴ መምሕር ተብሎ ሊመረቅ 14ቱን ቅዳሴ ሰለልኩላውንና ደብረ አባዩን እያገላበጠ የጮኸና የቀጸለ ነው ጸበል ጸዲቅም የቀመሰ ማነህ ባለ ሳምንት ያስጠምድህ በአስራ ስምንት…………… የተባለም አይጠፋም አይታጣም ሌላውም ድጓው ሰለልኩላውና ጸዋትወ ዜማውን እንዲያውቅ ባይጠበቅበትም ሌላ ቢቀር የሰንበት ተማሪ ተብሎ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በገረገራው አካባቢ ሆኖ የሰንበት ትምህርት ያልተማረ መዝሙር ያልዘመረና ታቦትም ሲወጣ ያላሸበሸበ ከበሮ ያልቆረቆረ የለም ብቻ ሁሉም በየፊናው ወደ ጌታ እስኪመጣና ይሄ ጌታ እስኪያገኘው ድረስ ይብዛም ይነስም ሁሉም የየበኩሉን ነገር አድርጓል በነዚህና በመሣሠሉት ነገሮች ውስጥ ያላለፈ አለ ብዬ አላስብም ከኦርቶዶክስ እምነት የመጣና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ባጝራውንድ ያለው ሁሉ በነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ አልፎአል ስለዚህ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በእንዲህ ሁኔታ ላለፍን ቅዱሳን ወገኖች ሁሉ ጀማሪና ቀዳሚ የሆነች እናት ናት ከዚህም ሌላ ይህቺ ቤተክርስቲያን የፕሮቴስታን እምነት ጀማሪ የነበረው ሉተር የተነሳው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነውና እርሱ ከመነሳቱ በፊት ወንጌልን የተቀበለች ቤተክርስቲያን ለመሆኗ ታሪክ ይመሠክራል የተጻፉት የቃሉ እውነቶችም ይናገራሉ ይኸውም በ14ኛው ክፍለ ዘመን አባ እስጢፋኖስ የሚባል የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ብቸኛ አዳኝነት በመስበክ በደብረብርሃንና በይፋት አካባቢ የተነሳ መሆኑ ከእርሱም ጋር ከ500 በላይ የሚሆኑ መነኮሳት መነሳታቸውን ታሪክ ይጠቁማል ከዚህም ጋራ ይህንኑ ትምህርታቸውን በመቃወም በዘመኑ አጼ ዘርአያዕቆብ የሚባል ንጉሥ ተነስቶ ለሥዕል ለማርያምና ለመስቀል ያልሰገደ ሰው እንዲሞት እንዲጠፋ ወስኖ እነዚህን ቅዱሳን በብርቱ ያሳድዳቸው እንደነበር ያልሰገዱትንም ሰዎች አፍንጫቸውን እየፎነነ ምላሳቸውን እየቆረጠ ይገድላቸው ስለነበረ ደብረ ብርሃን የተባለው ከተማ ብርሃን ከመውረዱ በፊት ደብረ ኤባ ይባል ነበርና በነዚህ ቅዱሳን መሰዋት ምክንያት ብርሃን ስለወረደ ደብረ ኤባ ለተባለው የደብረ ብርሃን ከተማ ደብረ ብርሃን የሚል ስያሜ መሰጠቱን ታሪክ በሰፊው ይናገራል የደቀ እስጢፋን ትምህርት ለመቃወም አጼ ዘርአያዕቆብ ካጻፋቸው የጸሎት ድርሰቶች አንዱ መስተብቊዕ ዘመስቀል ነው እንዲህ ይላል በእንተ ዝንቱ አዘዙ መምሕራነ ቅዱስ ወንጌል አምሳለ ፈጣሪ ልዑል ንስግድ ለመስቀል ወለማርያም ድንግል ትርጉም ልዑል ለሆነው ለፈጣሪ ምሳሌ ለሆኑት ለመስቀልና ለድንግል ለማርያም የቅዱስ ወንጌል መምሕራን ስላዘዙ እንስገድ የሚል ነው ነገር ግን መጽሐፍቅዱሳችን
ልዑል የሆነው ፈጣርያችን ምሳሌ የሌለውና ከማንም ጋር ልናመሳስለው እንደማንችል ይናገራል እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ ? የተቀረጸውንስ ምስል ሠራተኛ ሠርቶታል፥ አንጥረኛም በወርቅ ለብጦታል፥ የብሩንም ሰንሰለት አፍስሶለታል ይለናል ትንቢተ ኢሳይያስ 40 ፥ 18 እና 19 እግዚአብሔርን ያየው ስለሌለ ማንም እንዲህ ነው ሊለው በሌላውም ሰው ሊመስለው አይችልም እግዚአብሔርን ያየው በአባቱ እቅፍ ያለው የተረከውም
ልጁ ኢየሱስ ብቻ ነው ከዚህም ሌላ እርሱ የባሕርዩ ምሳሌ የክብሩም መንጸባረቅ ስለሆነ እርሱ ብቻ ይመስለዋል ከእርሱም በቀር እርሱን ብቻ ሊመስል የሚችል ማንም የለም እርሱም አብን አሳየንና ይበቃናል ብለው ለጠየቁት ደቀመዛሙርት እኔን ያየ አብን አይቶአል በማለት ነበር መልስ የሰጠው ዮሐንስ ወንጌል 1 ፥ 18 ፣ ዮሐንስ ወንጌል 14 ፥ 8 እና 9 ፣ ዕብራውያን 1 ፥ 1 _ 3 ስለዚህ መስቀልና ድንግል ማርያም ከልዑል እግዚአብሔር ጋር እኩልነት አግኝተውና እኩል ቦታ ተሰጥቶአቸው የእርሱ ምሳሌ ይሆናሉ
በምሳሌነትም ይጠቀሳሉ ብሎ ማሰብ ትልቅ የሆነ አላዋቂነት እና የድፍረት ኃጢአትም ነው አባ እስጢፋኖስና ተከታዮቹም ከዚህ እውነት የተነሣ ነው የፈጣሪ ምሥጋና ስግደትና አምልኮ አይገባቸውምና ለማርያም ለሥዕልና ለመስቀል መስገድ አይገባንም ያሉት መስዋዕትም ሆነው ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡት በትምህርተ ኅቡአት የጸሎት መጽሐፍም ላይ አኮ ከመ ይትረአይ አላ ከመ ይትሃለይ ውእቱ ዝንቱ መስቀል ይላል ትርጉም ይህ መስቀል የሚታይ አይደለም የሚታሰብ ነው ማለት ነው ስለዚህ ለእኛ የሚታሰብ እንጂ የሚታይ መስቀል የለንም ከዚህ የተነሳ መስቀልን በመስቀልነቱ እናስበዋለን እንጂ ይህ ነው መስቀል ብለን ቀርጸን ስለንና አይተን የምንሰግድለት የምንሳለመውና የምንስመው መስቀል ለእኛ የለንም መጽሐፍቅዱስ ጋር ሳንገባ ቃሉንም ሳንጠቅስ ለመስቀልም ሆነ ለሌሎች መስገድ እንደማይገባን የኦርቶዶክስ መጽሐፍ እርስ በእርሱ እየተጋጨ እየተቀራረነም ለእኛ ግን እንደ ቃሉ የሆነ መልስን ሰጥቶናል ስለዚህ እኛም የተጋጨውን ሳይሆን ተጋጭቶ እንደ ቃሉ እውነትን ያሳየንን ሃሳብ ይዘናል ለዚህም ነው እናት ቤተክርስቲያን ኦርቶዶክስ የወንጌል እውነት ያላት ናትና ወደ ወንጌሉ እውነት ወደ ጥንተ መሠረት ትመለስ ያልነው ለዚህች እናት ለሆነች
አንጋፋ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ወደ ወንጌል እውነት እና ወደ ጥንተ መሠረት መመለስ ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉት እነ አባ እስጢፋኖስ ብቻ ሳይሆኑ እነ አለቃ ታዬ በቅርቡም እኛ የደረስንባቸው መዳናችንንም ተመልክተው የደስታና የእንባ ሲቃ የተናነቃቸውን አንጋፋ የወንጌል አባት እነ አለቃ መሠረትንና ሌሎችንም ልናስታውስ እንችላለን ዛሬ እነዚህ አባቶች ከእኛ ጋር ሆነው በሕይወት ባይኖሩም ሥራዎቻቸውና ጽሑፎቻቸው ግን ትውልድን እየጠቀመና ወደ እውነተኛው ሕይወት እያሻገረ በመሆኑ እነዚህ አባቶች ዛሬም ሕያዋን ናቸው በነዚህ አባቶች ተጋድሎ የተካሄዱትን ተግባሮችና እንደ ቃሉ ተፈልፍለው የተጻፉትን የቃሉን እውነቶች እኛም በጥልቀት ብናጠና እርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ እኛ ራሳችን ከእነዚህ አባቶች በባሰ ሁኔታ ለዚህ ራዕይ መስዋዕት ልንሆን ተቀጣጥለን እንነሳለን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የወንጌል እውነትና ጥንተ መሠረት ያላት በመሆንዋ ወንጌልን እንደማያውቁ ወንጌል አታውቅም የእግዚአብሔር ቃል የላትም ስንል እንደ አሕዛብ ሀ ወይም አንድ ብለን ልንደርሳት አንነሳም ወንጌሉንና የወንጌሉን መሠረት የሸፈነውን የገድላ ገድላት አቡዋራና የስንክሳር ድሪንቶዎችን ከላይዋ ላይ ጥርግ አድርገን በቃሉ ስናወጣ ኢየሱስ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሞቶ የተነሳበትን የቃሉን እውነት ቁልጭ ብሎና ግልጽ ሆኖ በዚሁ ቤት እናየዋለ ያኔ ይሄ እውነት የተሸፈነባቸው ሰዎች ጌታን ለመቀበል የትም ሳይሄዱ እዚያው ባሉበት ጌታን ተቀብለው እዚያው እራሳቸው የሚወርሱ የመካኒቱ የሣራና የጨዋይቱ ልጆች ይሆናሉ ከዚህ የተነሣ እንግዲህ አሮጊቷ ሣራ ወለደች ማለት ይሄ ነው የጆሽዋ ሚኒስትሪ አንዱ የአገልግሎት ክፍል እንግዲህ ይህንን ይመስላል ስለዚህ በዚህ አገልግሎት ውስጥ ተካትቼ ራዕዩን አብሬ ማራመድ እፈልጋለሁ ለምትሉ ሰዎች በሩ ክፍት ነው ነገር ግን ወደዚህ ራዕይ አምኖና ቆርጦ ለመግባት የራዕዩን አላማ እውቀቱን ግቡንና ተልዕኮውን የሚያስከፍለውንም ዋጋ ከወዲሁ ተምኖና ገምቶ ጸልዮም መግባት ያስፈልጋል እንላለን ከዚህም ሌላ ይህንን ራዕይ በገንዘብ በአደረጃጀት በምክርና ገንቢ ሃሳቦችን በመስጠት በጸሎትና በመሣሠሉት ሁሉ አብሮ በመሆን ማገልገል ይቻላል እኛም ለዚህ በጣም ደስተኞች ነን ለዚህ ጉዳይ በፌስ በክ አድራሻዬ በኢሜሌ ብትጽፉልኝ ይደርሰኛል እንደገናም በዚሁ በፌስ ቡኬ ላይ የ Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry ላይ ያገልግሎቱ ግሩፕ ያዘጋጀሁ በመሆኔ እዚያ ግሩፕ ውስጥ መግባትና መሳተፍም ይቻላል በአካል የመገናኘትና የመቀራረብ ዘመን እስኪመጣም ድረስ በፌስ ቡኬ በብሎጎቼና በጎግል እንዲሁም በዩቲዩብ ላይ በቪዲዮ የተለቀቁና የሚለቀቁም ትምህርቶች መልዕክቶች ይኖራሉ በጽሑፍም ተዘጋጅተው የተለቀቁም እንደዚሁ አሉና እነርሱን መከታተል ነው ወደፊት እንደ ጌታ ፈቃድ ሌሎችም እቅዶች ይኖሩኛል እየጸለይኩበት እገኛለሁ እናንተም ጌታ ባሳሰባችሁ መጠን ጽልዩልኝ
ለ _ ሌላው ይሄ የጆሽዋ ሚኒስትሪ ኦርቶዶክስን ወደ ጥንተ መሠረት ወደ ወንጌል እውነት በመመለስ ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም አይሆንምም መጽሐፍቅዱሳችን ሲናገር እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ ስለሚል እኛም ክርስቶስ የሚፈልጋትን ቤተክርስቲያን ከእድፈት ከነውርና ከፊት መጨማደድ በመጠበቅ ይህቺኑ ቤተክርስቲያን ያለ እድፈት ሆና ለክርስቶስ ብቻ እንድትሆን በቃሉ እናዘጋጃለን ኤፌሶን 5 ፥ 27 ምክንያቱም መጽሐፍቅዱሳችን አሁንም የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሐሤትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጐናጸፍ ተሰጥቶአታል ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና እርሱም፦ ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው ብለህ ጻፍ አለኝ ደግሞም፦ ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው አለኝ ይለናል ራዕይ 19 ፥ 7 _9 እንግዲህ ይህቺ ሚስት ተብላና የሚስትነነት ቦታ ተሰጥቷት ወደ በጉ ሠርግ የምትቀርበዋ ቤተክርስቲያን የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጐናጸፍ ወደሚሰጣት ኃይልና ክብር የምትመጣው የእግዚአብሔርን ቃል በጥልቀት በመማርና በማጥናት ስለሆነ ለዚህ ጉዳይ ማንኛውንም የክርስቶስ ቤተክርስቲያንን ልናስተምር ልናስታጥቅና ልናገለግል ዝግጁ ነን በማስተማር በማገልገልና በማስታጠቅም ላይ እንገኛለን ሌላው ደግሞ በሐዋርያት ሥራ 14 ፥ 21 እና 22 ላይ በተጻፈው ቃል መሠረት በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው እጅግ ደቀ መዛሙርትን ካደረጉ በኋላ፥ የደቀ መዛሙርትን ልብ እያጸኑ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል እያሉ፥ ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ ይላልና እኛም ቃሉን ሰብከን ብቻ አንተውም እጅግ ደቀመዛሙርት እናደርጋለን ልብን እናጸናለን በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩም እንመክራለን ይህ እንግዲህ ለጆሽዋ ሚኒስትሪ ኦርቶዶክስን ወደ ጥንተ መሠረት ከመመለስ ባሻገር ይህም ዋነኛና ተቀዳሚ የሆነ ተግባሩ ነው በዚህ ሥራ ውስጥም በተከፈቱ በሮች ሁሉ ጌታን በማገልገል ላይ እገኛለሁ ወገኖች ከሞላ ጎደል እንግዲህ የ Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry ዓላማ እና ግብ ይህንን ይመስላል ጌታ በነገር ሁሉ ይባርካችሁ
ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ
No comments:
Post a Comment